የሰ/መ/ቁ. 123104
ታህሳስ 6 ቀን 2009 ዓ/ም
ዳኞች፡- ዓሊ መሐመድ
ተኽሊት ይመሰል
ቀነዓ ቂጣታ
ሰናይት አድነው
ጰውሎስ ኦርሺሶ
አመልካች፡- የኦርሚያ ደንና ዱር እንስሳት ድርጅት - ነ/ፈጅ አቶ ሞይስፈን ከበደ ቀረቡ
ተጠሪዎች፡- የሀጂ ኢብራሂም ወራሾች
መዝገቡ ተመርምሮ የሚከተለው ፍርድ ተሰጥቷል፡፡
ፍ ር ድ
የክርክሩ መነሻ የአፈጻጸም ክስ ሲሆን በመጀመሪያ የቀረበውም ለፌዴራል የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ ችሎት ነው፡፡ የአሁኑ ተጠሪዎች የፕራይቬታይዜሽን እና የመንግሥት ልማት ድርጅት ተቆጣጣሪ ኤጀንሲ በ1998 ዓ/ም የሰጠውን ውሳኔ የአሁኑ አመልካች እንዲፈጸምላቸው የአፈጻጸም ክስ አቅርበዋል፡፡ ጉዳዩ የቀረበለት የፌዴራል የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት የልደታ ምድብ ችሎት የቀረበውን የአፈጻጸም ክስ በተመለከተ በፍትሓብሔር ሥነ ሥርአት ህ/ቁ.19/1/ መሠረት የአፈጻጸም ተከሳሽ ሥራውን በሚያከናውንበት በኦረሚያ ክልል ላሉ ፍርድ ቤቶች ማቅረብ ይችላል እንጂ ጉዳዩን የማየት ሥልጣን የለኝም ሲል የከ.መ.ቁ.213728 በቀን 28/09/2006 ዓ/ም መዝገቡን ዘግቷል፡፡
ተጠሪዎች በትዕዛዙ ቅር በመሰኘት ይግባኝ ለፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት አቅርበዋል፡፡ ይግባኙ የቀረበለት የፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ይግባኙን ተቀብሎ የግራ ቀኙን ካከራከረ በኃላ በኮ/መ/154049 በቀን 17/12/2007 ዓ/ም የሥር ፍርድ ቤትን ትዕዛዝ በመሻር ጉዳዩን የማየት ሥልጣን አለው ባማለት በፍትሓብሔር ሥነ ሥርዓት ህግ ቁጥር 341 መሰረት መልሷል፡፡
የአሁኑ አመልካች የፌዴራል ክፍተኛ ፍርድ ቤት የሰጠውን ውሳኔ ለማስለወጥ ይግባኝ ለፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት የፍትሓብሔር ይግባኝ ሰሚ ችሎት ያቀረበ ሲሆን የጠቅላይ ፍርድ ቤቱ ይግባኝ ሰሚ ችሎት የግራ ቀኙን ካከራከረ በኃላ በፍ/መ/ቁ.117240 በቀን 22/04/2008 ዓ/ም በውሳኔው ማጠቃለያ ላይ ሁለቱም ፍርድ ቤቶች የአፈጻጸም ክሱ በመደበኛ ፍርድ ቤት መቅረብ የሚገባው ስለመሆኑ ወይም መደበኛ ፍርድ ቤቶች ጉዳዩን የማየት ሥልጣን ያላቸው ስለመሆኑ ተመሳሳይ ውሳኔ በመስጠታቸው አዋጅ በአዋጅ ቁጥር 25/88 አንቀጽ 9 (2) ድንጋጌ መሠረት በይግባኝ ደረጃ የሚታይ አይደለም በማለት ወስኗል፡፡
ይህ የሰበር አቤቱታ የቀረበውም የጠቅላይ ፍርድ ቤቱ የፍትሓብሔር ይግባኝ ሰሚ ችሎት የሰጠውን ውሳኔ በመቃወም ነው፡፡ የሰበር አቤቱታው ተመርምሮ የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤቱ በሰጠው ፍርድ የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት እና የፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት አንድ ዓይነት ውሳኔ ሠጥተዋልና ጉዳዩን በይግባኝ የማየት ሥልጣን የለኝም ያለው በእርግጥ የፌዴራል የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት እና የከፍተኛ ፍርድ ቤት አንድ ዓይነት ፍርድ ሰጥተዋል ወይ? የሚለውን ነጥብ ለመመርመር ሲባል ጉዳዩ ለሰበር ችሎት እንዲቀርብ ተደርጓል፡፡ የሰበር አቤቱታው ለተጠሪዎች ደርሶዋቸው ሚያዝያ 11 ቀን 2008 ዓ/ም የተጻፈ መልስ የሰጡ ሲሆን አመልካችም በቀን/15/09/2008 ዓ/ም የተጻፈ የመልስ መልስ አቅርቧል፡፡
የክርክሩ አመጣጥ ከላይ እንደተገለጸው ሲሆን ጉዳዩን ከሥር ፍርድ ቤቶች ውሳኔ፣በዚህ ችሎት ከተደረገው ክርክር እንዲሁም ያስቀርባል ሲባል ከተያዘው ጭብጥ አንጻር መርምረነዋል፡፡ ጉዳዩን እንደመረመርነውም በመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት እና በፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት አንድ ዓይነት ውሳኔ ተሰጥቷል ወይ? የሚለው ምላሽ ሊያገኝ የሚገባው ነው፡፡ የፌዴራል የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት የልደታ ምድብ ችሎት የአፈጻጸም ተከሳሽ ሥራውን የሚያከናውነው በኦሮሚያ ክልል በመሆኑ የፍርድ ባለመብቶች አቤቱታቸውን በክልሉ ለሚገኝ ፍርድ ቤት በመደበኛ ወይም ጉዳዩ የፌዴራል ነው ካሉ በተሰጣቸው ህገ መንግሥታዊ ውክልና መሠረት ማቅረብ ሲገባቸው የአፈጻጸም ክስ ለቀረበበት ፍርድ ቤት ማቅረባቸው ተገቢ አይደለም በማለት መዝገቡን ዘግቷል፡፡ ይህ ትዕዛዝ መሠረት ያደረገው በፍትሓብሔር ሥነ ሥርዓት ህግ ስለ ግዛት ከልል ሥልጣን የተደነገገውን ነው፡፡ በዚህ መሠረት ፍርድ ቤቱ ጉዳዩን ለማየት የግዛት ሥልጣን እንደሌለው ደምድሟል፡፡
ጉዳዩን በይግባኝ የተመለከተው የፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ውሳኔ መሠረት ያደረገው ደግሞ አዋጅ ቁጥር 25/88 ‘ን’ ነው፡፡ በዚህ አዋጅ መሠረት የሥር ፍርድ ቤት ጉዳዩን አይቶ ለመወሰን ሥልጣን አለው ተብሎ የሥር ፍርድ ቤት ትዕዛዝ ተሸሯል፡፡የሥር ፍርድ ቤት የሰጠውን ትዕዛዝ ይግባኝ ሰሚው ከፍተኛ ፍርድ ቤት አላጸናውም፡፡ መሠረታዊ ነጥቡ የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት የግዛት ክልል ሥልጣን የለኝም ሲል ይግባኝ ሰሚው ፍርድ ቤት ደግሞ የፌዴራል ፍርድ ቤቶችን ሥልጣን በሚደነግገው አዋጅ ቁጥር 25/88 አንቀጽ 5/21/ መሠረት ለፌዴራል ፍርድ ቤቶች የተሰጠ ሥልጣን ነው በማለት መወሰኑ ስታይ አንድ ዓይነት ድምዳሜ ላይ የተደረሰ ነው ብሎ ለመደምደም የሚያስችል አይደለም፡፡ ይህ በሆነበት ሁኔታ በሁለቱም ፍርድ ቤቶች የአፈጻጸም ክሱ በመደበኛ ፍርድ ቤት መቅረብ የሚገባው ስለመሆኑ ወይም መደበኛ ፍርድ ቤቶች ጉዳዩን የማየት ሥልጣን ያላቸው ስለመሆኑ ተመሳሳይ ውሳኔ በመስጠታቸው በአዋጅ ቁጥር 25/88 አንቀጽ 9 (2) ድንጋጌ መሠረት በይግባኝ ደረጃ የሚታይ አይደለም በማለት የፈፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት የፍትሓብሔር ይግባኝ ሰሚ ችሎት የሰጠው ውሳኔ መሠረታዊ የህግ ስህተት የተፈጸመበት ሆኖ ተገኝቷል፡፡ በመሆኑም ተከታዩ ውሳኔ ተሰጥቷል፡፡
ው ሳ ኔ
መዝገቡ ወደ መዝገብ ቤት ይመለስ፡፡
የማይነበብ የአምስት ዳኞች ፊርማ አለበት
ፋ/ዘ