የኢትዮጵያ ፌደራላዊ ዲሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ
የፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት
ሰበር ሰሚ ችሎት
የሰ/መ/ቁ. 188483
ጥር 25 ቀን 2013 ዓ/ም
ዳኞች፡- ብርሃኑ አመነው
ተሾመ ሽፈራው
ሀብታሙ እርቅይሁን
ብርሃኑ መንግስቱ
ነፃነት ተገኝ
አመልካች ፡- አንበሳ ኢንሹራንስ ኩባንያ - ጠበቃ አበራ ታደሰ - ቀረቡ
ተጠሪ ፡- 1. አቶ ጌትሽ ፈንታሁን ጠበቃ ኤልያስ መሀመድ - ቀረቡ
2. አቶ ሐሰን አህመድ
መዝገቡ ተምርምሮ ተከታዩ ፍርድ ተሠጠ፡፡
ፍ ር ድ
የሰበር አቤቱታው የቀረበው የፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ይግባኝ ሰሚ ችሎት በሠጠው ውሳኔ መሠረታዊ የሆነ የሕግ ስህተት ተፈጽሞበታል በሚል ነው፡፡ የክርክሩን አመጣጥ ከስር ፍርድ ቤት የመዝገብ ግልባጭ እንደተረዳነው አመልካች ከሳሽ ሲሆን ተጠሪዎች ተከሳሾች ነበሩ፡፡ አመልካች ያቀረበው ክስ የሠሌዳ ቁጥር 3-09593 አማ. የሆነ የ1ኛ ተጠሪ ተሽከርካሪ ሰኔ 25 ቀን 2006 ዓ/ም ከሶሮቃ ወደ ጎንደር ከተማ በ2ኛ አመልካች እየተሽከረከረ አመልካች የመድን ዋስትና የሠጠው የሠሌዳ ቁጥር 3-82048 አ.አ. ሆነ ቶዮታ ፒክአፕ መኪና ገጭቶ ጉዳት በማድረሱ አመልካች ለደንበኛው የከፈለውን ብር 766,226.96 በአንድነትና በነጠላ ኃላፊነት ተጠሪዎች እንዲከፍሉኝ የሚል ነው፡፡ ተጠሪዎች የፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት የግዛት ክልል ሥልጣን የለውም በማለት የተቃወሙ ሲሆን በአማራጭ ክርክር የደረሰው የተሽከርካሪዎች ግጭት ነው፡፡ ሙሉ ጉዳት አልደረሰም፡፡ 2ኛ ተጠሪ ለግጭቱ ጥፋተኛ አይደለም በማለት የጉዳት ካሣ መጠኑ ላይ ክርክር አቅርበዋል፡፡ ለ1ኛ ተጠሪ ተሽከርካሪ የሦስተኛ ወገን ኃላፊነት የመድን ዋስትና የሠጠው ናይል ኢንሹራንስ በክርክሩ ጣልቃ ገብቶ ተከራክሯል፡፡
የፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ተጠሪዎች ያቀረቡትን የመጀመሪያ ደረጃ መቃወሚያ ውድቅ በማድረግ ግራቀኙን አከራክሮ ጉዳቱ የደረሰው ሁለቱ ተሽከርካሪዎች ግጭት ስለሆነ ጉዳቱን እኩል ይቻሉ በማለት ተጠሪዎች ብር 232,691.42 እንዲከፍሉ እና ጣልቃ ገብ የነበረው ናይል ኢንሹራንስ ብር 100,000.00 እንዲከፍል ወስኗል፡፡ አመልካች እና ተጠሪዎች ያቀረቡትን ይግባኝ አጣምሮ የመረመረው የፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ይግባኝ ሰሚ ችሎት ተጠሪዎች ያቀረቡትን ይግባኝ ውደቅ ሲያደርግ አመልካች ካቀረበው ክርክር አኳያ ተጨማሪ ብር 50,422.00 ተጠሪዎች እንዲከፍሉ የሥር ፍርድ ቤት ውሳኔን በማሻሻል ወስኗል፡፡ ይህ የሰበር አቤቱታ የቀረበው በዚህ ውሳኔ ነው፡፡ የአመልካች የሰበር አቤቱታ ይዘትም ለደረሰው ጉዳት ግራቀኙ ኃላፊነት አለባቸው መባሉ ተገቢ አይደለም፤ ለጉዳቱ ጥፋተኛው 2ኛ ተጠሪ ነው የሚል ሲሆን የሰበር አጣሪ ችሎት በዚሁ ነጥብ ላይ ለሰበር ችሎት ያስቀርባል በማለት ተጠሪዎች ክርክር እንዲያቀርቡ የተደረገ ሲሆን መስቀለኛ የሠበር አቤቱታም አቅርበዋል፡፡
የክርክሩ ሂደት በአጭሩ ከላይ የተገለጸው ሲሆን እኛም ጉዳዩ በፌደራል ፍርድ ቤቶች መታየቱ ሕጋዊ መሆን አለመሆኑን? በጭብጥነት በመያዝ መዝገቡን መርምረናል፡፡
እንደመረመርነው ለክሱ መሠረት የሆነው ጉዳት የተከሠተው በአማራ ክልል ውስጥ ስለሆነና አመልካች በፌደራል መንግሥት የተመዘገበ የንግድ ድርጅት ከመሆኑ አኳያ፤ ሊመረመር የሚገባው ጭብጥ ክሱ የክልል ፍርድ ቤት በውክልና ሊመለከተው የሚችል የፌደራል ጉዳይ ነው ወይስ በፌደራል ፍርድ ቤት የሚታይ ክርክር ነው የሚለውን የሚመለከት ነው፡፡ በኢፌዲሪ ሕገ-መንግሥት አንቀጽ 78(2) መሠረት የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በ2/3ኛ ድምጽ የፌደራል ከፍተኛ ሆነ የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት እንዲደራጅ እስካልወሰነ ድረስ የፌደራል ከፍተኛና የፌደራል የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤቶች ሥልጣን በውክልና ለክልል ፍርድ ቤቶች ተሰጥቷል፡፡ ምላሽ የሚያስፈልገው ጉዳይ በውክልና በተሠጠ ሥልጣን ላይ የፌደራል ፍርድ ቤቶች ጉዳዩን የማየት ሥልጣን አላቸው ወይስ የላቸውም? የሚለው ጉዳይ ነው፡፡ ክርክሩን በፍትሐ ብሔር ሥነ-ሥርዓት ሕጉ መሰረት መምራት እና መቆጣጠር የፍርድ ቤቱ ኃላፊነት ሲሆን በዚህ ሂደት ከሚመረምራቸው ጉዳዮች መካከል ጉዳዩ ላይ ለመወሰን ሥልጣን ያለው መሆን አለመሆኑ ዋነኛው ነው፡፡ የፍርድ ቤት ሥልጣን ብሔራዊ የመዳኘት ሥልጣን (judicial jurisdiction)፣ የሥረ-ነገር ሥልጣን (material jurisdiction) እና የግዛት ወይም ከበባዊ ሥልጣን (local or territorial jurisdiction) በሚል የተከፋፈለ ነው፡፡ ብሔራዊ የመዳኘት ሥልጣን ከሀገሮች ሉዓላዊነት፣ የሚሠጠው ፍርድ በሌሎች ሀገሮች ዕውቅና ሊሠጠውና ሊፈጸም የሚችል መሆን አለመሆኑ እና ከተከሳሽ መብት ጋር የተያያዘ መሠረቱ ዓለምአቀፍ ሕግና የታወቁ የሕግ መርሆዎች ሆኖ የአንድ ሀገር ፍርድ ቤት ጉዳዩን ለመመልከት ከተከሳሹ ወይም የክርክሩ ምክንያት የሆነው ተግባር ከተፈጸመበት ወይም አከራካሪ የሆነው ንብረት ከሚገኝበት ቦታ ጋር በቂ የሆነ ግንኙነት ያለው ሆኖ ሲገኝ ወይም ተከሳሽ የሆነው ወገን በሀገሪቱ ፍርድ ቤቶች ለመዳኘት ያለው ፈቃድ ላይ መሠረት በማድረግ የሚወሰን ነው፡፡ የሥረ-ነገር ሥልጣን በአንድ ሀገር ጉዳዩን ለመዳኘት ሥልጣን ባላቸው ፍርድ ቤቶች መካከል በዋነኛነት ታሳቢ የሚያደርገው የፍርድ ቤቱን አቅም ወይም ችሎታ (competence of the court)፣ ፍትሐዊነትን፣ ኢኮኖሚንና የሥራና ሀብት ክፍፍልን መሠረት አድርጎ በገንዘብ ግምት (pecuniary jurisdiction) ወይም በጉዳዩ ዓይነት (subject matter jurisdiction) ወይም ጉዳዩን በመጀመሪያ ሆነ በይግባኝ ደረጃ (original and appellate jurisdiction) የሚያዩት ሥለመሆኑ በፍርድ ቤቶች መካከል የሚመለከቱት ጉዳዩችን የሥልጣን ድልድል የሚደረግበት ነው፡፡ የግዛት ክልል ሥልጣን ደግሞ አንድን ጉዳይ ተቀብሎ ለመስማት እና ለመወሰን ዐቅም ካላቸው ፍርድ ቤቶች መካከል በየትኛው ፍርድ ቤት ቀርቦ መታየት እንዳለበት የሚያመለክት ነው፡፡ ያስፈለገበትም ዓላማም ተመሳሳይ የሥረ-ነገር ሥልጣን ያላቸው ግን በተለያዩ ማስቻያ ቦታ ላይ በሚያስችሉ ፍርድ ቤቶች መካከል ለዜጎች ፍትሕ የማግኘት መብትን በቅርብ ለማረጋገጥና ለተከራካሪ ወገኖች ይልቁንም ለተከሳሹና ለምስክሮቹ ምቹ ሁኔታ ለመፍጠር ሲባል ነው፡፡ ሥልጣኑም በተከራካሪዎች አድራሻ፣ ንብረቱ በሚገኝበት ቦታ፣ ውሉ በተመሠረተበት ወይም በሚፈፀምበት ወይም ጉዳቱ በደረሠበት ቦታ ወይም ተመሳሳይ ምክንያቶችን በመያዝ የሚመለከቷቸውን ጉዳዮች የሚለዩበት ነው፡፡ ይሕ ኢትዮጵያ የፌደራል ሥርዓትን ሳትከተል በፍትሐ ብሔር ሥነ-ሥርዓት ሕጉ የተቀረጸ የፍርድ ቤቶች የግዛት ክልል የሥልጣን ክፍፍል ሥርዓትን በመሆኑ ተግባራዊ ሲደረግ የፌደራል ሥርዓቱን ባገናዘበ መልኩ ሊሆን ይገባል፡፡
ኢትዮጵያ የፌደራል የመንግሥት አወቃቀር ሥርዓትን በ1987 ዓ/ም በወጣው የኢፌዲሪ ሕገ-መንግሥት መከተሏን ተከትሎ ሥልጣን በክልሎችና በፌደራል መንግሥት የተከፋፈለ ስለመሆኑ በሕገ-መንግሥቱ ከአንቀጽ 50-52 ላይ ተመልክቷል፡፡ በዚህም ክልሎች በሥልጣናቸው ሥር ባሉ ጉዳዮች ሉዓላዊ ሥልጣን አላቸው፡፡ ክልሎች እንደ ፌደራል መንግሥት ሕግ-አውጪ፣ ሕግ አስፈጻሚና የዳኝነት አካል ያደራጃሉ፡፡ በኢፌዲሪ ሕገ-መንግሥት አንቀጽ 78 መሠረት የዳኝነት አካሉ በፌደራል እና በክልል መንግሥት ደረጃ መቋቋሙ እና በአንቀጽ 80(1)(2) ላይ በፌደራል ጉዳዮች የፌደራል ፍርድ ቤት፤ በክልላዊ ጉዳዮች የክልል ፍርድ ቤት የመጨረሻ ሥልጣን ያለው መሆኑ መመልከቱ በፌደራልና በክልል መንግሥታት መካከል የፍርድ ቤት የሥልጣን ክፍፍል እንዳለ ያሳያል፡፡ የፌደራል ወይም የክልል ጉዳዮች የሚለው በጉዳይ ዓይነት የተከፋፈለ ሥልጣን ስለሆነ የፍርድ ቤቶች ሥልጣን የተለየው የሥረ-ነገር ሥልጣንን መሠረት ያደረገ ቢመስልም ጉዳዩ ከሉዓላዊ ሥልጣን እና ክልላዊ ጉዳይ በፌደራል ፍርድ ቤት ቢታይ ከጣልቃገብነት ጋር የተያያዘ በመሆኑ ጉዳዩ የብሔራዊ ዳኝነት ሥልጣንን የሚያስነሳ ነው፡፡ በፌደራል መዋቅር የብሔራዊ የዳኝነት ሥልጣን መሠረቱ ዓለምአቀፍ ሕግ ሳይሆን ሕገ-መንግሥት ነው፡፡ ሕገ-መንግሥቱ የፌደራልን ሆነ የክልልን ፍርድ ቤቶች ያቋቋመና አክብረው ለማስከበርም ግዴታ የጣለ ነው፡፡ ውጤቱም እንደ ሀገር የሚመረመረው የብሔራዊ የዳኝነት ሥልጣን ከሌላ ሀገር ዜጋ ጋር በተያያዘ እና ሌሎች ሀገሮች ጋር የዲፕሎማቲክ ቅራኔንም ሊፈጥር የሚችል ሲሆን በፌደራልና በክልል መንግሥታት መካከል ያለው ግን በአንድ ሀገር ያሉና በሕገ-መንግሥቱ የሕግ የበላይነትን በማረጋገጥ አንድ የኢኮኖሚና የፖለቲካ ማሕብረሰብ ለመፍጠር በሚሠሩ ተቋማትና ዜጎች ላይ፣ የተለያየ ሥልጣን ቢሆንም የጋራ የሆኑ ጉዳዮች ደግሞ ባላቸው ተቋማት መካከል የሚነሳ ስለሆነ የተለየ ያደርገዋል፡፡ በፌደራል መዋቅር የፌደራል መንግሥት ሉዓላዊነቱ በመላው የኢትዮጵያ ግዛት ነው፡፡ ነገር ግን በግዛቱ ሥር ሁሉንም በፈቃዱ መወሰንና መፈጸም የሚችል ሳይሆን በግልጽ በሕግ በተዘረጋው ሥርዓት ሥልጣኑን የሚጠቀም መሆኑን የሚመለከት ነው፡፡ ለክልል ፍርድ ቤት ሥልጣን መሠረቱ ግን በግዛት ክልል ሥር ያለ ሠውና ንብረት መሆን አለመሆኑን መሠረት ያደረገ (limited sovereignty) ነው፡፡
በሕገ-መንግሥቱ የሥልጣን ክፍፍሉም የክልል ከፍተኛና ጠቅላይ ፍርድ ቤቶች የፌደራል ጉዳዮችን በውክልና ማየት የሚችሉ ሲሆን ክልላዊ ጉዳዮች በክልሎች ሉዓላዊ ሥልጣን ክልል ውስጥ (exclusive jurisdiction of state courts) ያለ በመሆኑ፤ በሕገ-መንግሥቱ አንቀጽ 80(3)(ሀ) ለፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ሠበር ሰሚ ችሎት የተሠጠው ሥልጣን እንደተጠበቀ ሆኖ፤ የፌደራል ፍርድ ቤቶች ማየት አይችሉም፡፡ ይሕም ክልላዊ ጉዳዮች ላይ የፌደራል ፍርድ ቤቶች የመዳኘት ሥልጣን (judicial jurisdiction) የሌላቸው መሆኑን ሲያሳይ በውክልና እና በጣምራ ሥልጣናቸው ከሚመለከቱት በሥተቀር የክልል ፍርድ ቤቶች የፌደራል ጉዳዮችን ማየት አይችሉም፡፡ ከዚህ ጋር ተያይዞ መመርመር ያለበት በሕገ-መንግሥቱ የተመለከተው የፍርድ ቤቶች የጣምራነት ሥልጣን (concurrent jurisdiction) እና የፌደራል ጉዳዮች የሚወሰኑበት ሥርዓት ነው፡፡ የፌደራል ጉዳዩች ምን እንደሆኑ በሕገ-መንግሥቱ ያልተወሰነ ቢሆንም በፌደራል ፍርድ ቤቶች አዋጅ ቁጥር 25/1988 አንቀጽ 3 መሠረት የፌደራል ጉዳዮች ሕገ-መንግሥቱን፣ የፌደራል መንግሥት ሕጎችንና ዓለም አቀፍ ሥምምነቶችን መሠረት ያደረጉ ጉዳዮች (based on laws)፤ በፌደራል ሕግ ተገልጸው በተወሰኑ ባለጉዳዮች (parties) እና በሕግ በተገለጹ ቦታዎች (places) ላይ የሚነሱ ጉዳዮች ናቸው፡፡ በፌደራል ፍርድ ቤቶች አዋጅ ቁጥር 25/1988 አንቀጽ 4 እና 5 መሠረት የተዘረዘሩት የፌደራል ፍርድ ቤት በብቸኝነት ሥልጣኑ የሚመለከታቸው ሕግንና ባለጉዳዮችን መሠረት አድርጎ የተለዩ የፌደራል ጉዳዮች ሲሆን በሌሎች ሕጎች በግልፅ ለፌደራል ፍርድ ቤት የተሠጡ ጉዳዮችን ይጨምራል፡፡ የአዋጁን አንቀጽ 11 እና ተከታዮችን ሥንመለከት ደግሞ ቦታን መሠረት በማድረግ አዲስ አበባና ድሬዳዋ ከተሞች ላይ የሚነሡ ጉዳዮች የፌደራል ፍርድ ቤት የሚመለከታቸው የፌደራል ጉዳዮች ስለመሆናቸው ተደንግጓል፡፡
በፌደራል ፍርድ ቤቶች አዋጅ ቁጥር 25/1988 አንቀጽ 3 መሠረት ሕግን መሠረት አድርጎ የተለዩት የፌደራል ጉዳዮች ውስጥ የፌደራል መንግሥት ሕጎችን መሠረት ያደረጉ ጉዳዮች ያሉበት በመሆኑና በአዋጁ የትርጉም ክፍል አንቀጽ 2(3) ላይ የፌደራል መንግሥት ሕጎች ማለት በሕግ በተሠጠው ሥልጣኑ ክልል ሥር ያሉ ነባር ሕጎችን የሚጨመር መሆኑ ሲታይ በሕግ በግልጽ የፌደራል ፍርድ ቤት ሥልጣን ሥር ከተመለከቱት ሕግን መሠረት ያደረጉ ጉዳዮች እና በፌደራል ሥልጣን ሥር እንዲታዩ ከተወሰኑት ባለጉዳዮች ውጭ ያሉ የፌደራል ሕግን መሠረት ያደረጉ ጉዳዮች የፌደራልና የክልል ፍርድ ቤቶች በጣምራ ሥልጣናቸው የሚመለከቷቸው ናቸው፡፡ ሥለሆነም የፌደራል ሕግን መሠረት ያደረጉ ሌሎች ጉዳዮች እንደተነሱበት ቦታ የፌደራል ፍርድ ቤት ወይም የክልል ፍርድ ቤት በክልላዊ ሥልጣኑ ሊመለከተው ይችላል፡፡
በኢትዮጵያ የፌደራል ሥርዓት መሠረት አድርጎ የተዋቀረው የዳኝነት ሥልጣን የፌደራል እና የክልል ፍርድ ቤቶች ካላቸው የጣምራነት ሥልጣን ባለፈ በሕገ-መንግሥቱ አንቀጽ 78(2) እና 80(4-6) የፌደራል ፍርድ ቤት በብቸኝነት ሥልጣኑ የሚመለከታቸውን ጉዳዮች የክልል ጠቅላይና ከፍተኛ ፍርድ ቤቶች በውክልና እንዲመለከቱ ሥልጣን ሰጥቷል፡፡ ይህም ሕገ-መንግሥቱ የክልል ፍርድ ቤቶችን ማብቃትን (empowerment)፣ የክልሎችን ተሳትፎ ማሳደግ ላይ ዓላማ ያለውና ተቋሞቻቸው ላይ አመኔታ ያለው መሆኑን ያረጋግጣል፡፡ በሕገ-መንግሥቱ የዳኝነት አካል በፌደራልና በክልል ደረጃ በየእርከኑ መዋቀሩ ሲታይ አደረጃጀቱ በተዋረድ ያለ የትይዩ አቀራረጽ (dual system) ያለው ቢሆንም የፌደራልና የክልል ጉዳይን የክልል ፍርድ ቤቶች መመልከታቸው የተደባለቀ (integrated system) እንደሚከተልም ያሳያል፡፡
የክልል ፍርድ ቤቶች በጣምራ ሥልጣናቸው በክልል ግዛታቸው የተነሱ ጉዳዮች የመመልከት ሥልጣን ያላቸው በመሆኑ የፌደራል ፍርድ ቤት ጉዳዩን የማየት ሥልጣን አይኖረውም፡፡ ጉዳዩ በክልል ፍርድ ቤት የሚታየው ጉዳዩ የተነሳበትን ቦታና ተከራካሪውን መሠረት በማድረግ ነው፡፡ የጣምራነት ሥልጣን መሠረቱ የፌደራል መንግሥት ሕግን መሠረት ያደረገ የፌደራል ጉዳይ በመሆኑ የፌደራል ፍርድ ቤት በፌደራል ጉዳይ ላይ ብሔራዊ የመዳኘት ሥልጣን የለውም ሊባል አይችልም፡፡ ነገር ግን በፌደራል ፍርድ ቤት አዋጅ ቁጥር 25/1988 አቀራረጽ መሠረት ከተለዩት ውስን የፌደራል ፍርድ ቤት ሥልጣኖች ውጭ ያሉ በክልል ግዛት የሚነሱ ጉዳዮችን የክልል ፍርድ ቤቶች እንዲመለከቷቸው የተተወ በመሆኑ ጉዳዩ የሥረ-ነገር ሥልጣን ጥያቄ የሚያስነሳ ይሆናል፡፡
በተመሳሳይ የክልል ፍርድ ቤቶች በፌደራል ፍርድ ቤት በብቸኝነት እንዲታዩ የተለዩ ጉዳዮችን (exclusive jurisdiction) በግዛታቸው በተከሠቱ ጉዳዮች፣ ባሉ ሠዎቸ ወይም ንብረቶች ጋር የሚነሱ ሲሆን በውክልና (delegation) እንዲመለከቱ በሕገ-መንግሥት ሥልጣን ተሰጥቷቸዋል፡፡ በክልል የሚነሱ የፌደራል ጉዳዮች ላይ ጉዳዩ የፌደራል በመሆኑ የፌደራል ፍርድ ቤቶች ብሔራዊ የመዳኘት ሥልጣን አላቸው፡፡ በፌደራል ፍርድ ቤት አዋጅ ቁጥር 25/1988 አንቀጽ 4 እና 5 የተመለከቱት የፌደራል ጉዳዮችን በተከታዮቹ ድንጋጌዎች ለፌደራል ፍርድ ቤቶች የሥረ-ነገር ሥልጣናቸውን ያከፋፈለ በመሆኑ ይህን ሕግ መሠረት ተደርጎ ሲታይ የፌደራል ፍርድ ቤት ጉዳዩን ለመዳኘት የሥረ-ነገር ሥልጣን እንዳለው ያሳያል፡፡ የአፋር፣ የቤንሻንጉል/ጉሙዝ፣ ጋምቤላ፣ ሶማሌና የደቡብ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ክልሎች በሕገ-መንግሥቱ ያላቸው የፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤትን ሥልጣን በውክልና በክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት የማየት ሥልጣን በፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ማደራጃ አዋጅ ቁጥር 322/1995 ሲነሳ በእነዚህ ክልሎች የፌደራል ክፍተኛ ፍርድ ቤት መደራጀቱ ታወጀ እንጂ በአምስቱ ክልሎች ግዛቶች የሚነሱ ጉዳዮችን የመመልከት የሥረ-ሥልጣን እንደ አዲስ ለፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት አለመሠጠቱ ቀድሞውንም በፌደራል ፍርድ ቤቶች አዋጅ ቁጥር 25/1988 መሠረት የሥረ-ነገር ሥልጣን ተወስኖ ያደረ መሆኑን ያረጋግጣል፡፡ የፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ከአዲስ አበባና ድሬዳዋ ከተሞች ውጭ በእነዚህ ክልሎች ሲደራጅ የማስቻያ ቦታው የተወሰነ በመሆኑ ጉዳዮችን ለማየት የግዛት ክልል ሥልጣን ያገኛል፡፡ ይሕም የክልል ፍርድ ቤቶች በግዛታቸው ባሉ ሠዎቸ ወይም ንብረቶች ጋር የሚነሳ በውክልና የሚመለከቱትን የፌደራል ጉዳይ ውክልናቸው ሳይነሳ ጉዳዩ ለፌደራል ፍርድ ቤት ቀርቦ ከታየ የግዛት ክልል ሥልጣን ክርክር የሚያስነሳ መሆኑን ያስገነዝባል፡፡
ነገር ግን በፍትሐ ብሔር ሥነ-ሥርዓት ሕጉ ከተመለከተው የግዛት ክልል የተለየ ውጤት ያለው ነው፡፡ ሥነ-ሥርዓት ሕጉ በሚቀረጽበት ጊዜ የፌደራል ሥርዓት አወቃቀር ባለመኖሩ ተመሳሳይ የሥረ-ነገር ሥልጣን ያላቸው ፍርድ ቤቶች በተለያዩ የፌደራልና የክልል መንግሥታት ሥልጣን ክልል ውስጥ በሚሆንበት ጊዜ የሚያስነሳውን ክርክር የሚመለስ አይደለም፡፡ የሥነ-ሥርዓት ሕጉ አቀራረጽም ከፌደራል ሥርዓቱ ጋር ተጣጥሞ መተርጎም ይኖርበታል፡፡ ጉዳዩ በሥነ-ሥርዓት ሕጉ እንደተቀረጸው የግዛት ክልል ሥልጣን በዋነኛነት አመቺነትን ብቻ መሠረት ያደረገ ነው፤ አመቺ እስከሆነ ድረስ በፌደራል ፍርድ ቤት ሊታይ ይችላል ከተባለ፤ በሕገ-መንግሥቱ የክልል ፍርድ ቤቶች ውክልና ሊነሳ የሚችለው በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት 2/3ኛ ድምጽ ብቻ ስለመሆኑ በአንቀጽ 78(2) ላይ የተመለከተውን በመተላለፍ፤ የክልል ፍርድ ቤቶች በሕገ-መንግሥቱ የተሠጣቸውን የውክልና ሥልጣን በሕጉ በተገለጸው አግባብ ሳይነሳ በፍርድ ቤቶች ውክልናውን የማንሳት ውጤት ያስከትላል፡፡ ሕገ- መንግሥቱ የፌደራል ጉዳይን በውክልና በክልል ፍርድ ቤቶች እንዲታይ የወሰነበትንና ሊያሳካው የፈለገውን ዓላማና ግብ ላይ እንዳይደርስ ያደርጋል፡፡ ጉዳዩን የሚመለከተው ፍርድ ቤት ሥልጣን የሚወሰነው በሕግ ሆኖ እያለ በክልል ፍርድ ቤት በውክልና ሊታይ የሚችል ሥልጣን በፌደራል ፍርድ ቤት የሚቀርብ ከሆነ ተከራካሪዎች ክሱን የሚያቀርቡበት ፍርድ ቤት፤ የፌደራል ወይስ የክልል ፍርድ ቤት ስለመሆኑ በራሳቸው ምርጫ እንዲያቀርቡ (forum shopping) የሚያደርግ ተገቢ ያልሆነ የዳኝነት አሠጣጥ ሥርዓት እንዲፈጠር ዕድል ይሠጣል፡፡ ሥለሆነም በእነዚህ ምክንያቶች የክልል ጠቅላይና ከፍተኛ ፍርድ ቤቶች በሕገ-መንግሥቱ የፌደራል ጉዳዮችን በውክልና እንዲመለከቱ የተሠጣቸውን ሥልጣን መሠረቱ የፌደራል አወቃቀር በመሆኑ ውክልናቸው በሕግ እስካልተነሳ ድረስ ጉዳዮቹ ለፌደራል ፍርድ ቤት ሊቀርቡ አይችሉም፡፡ ጉዳዮቹ ቀርበው በፌደራል ፍርድ ቤቶች ከታዩ ውጤቱም አስገዳጅነት ያለውን የፍርድ ቤት ሥልጣን ክፍፍል የሚጥስ ስለሆነ ጉዳዩ በየትኛውም ደረጃ ፍርድ ቤት ሲደርስ በተከራካሪዎች ሆነ በፍርድ ቤቱ የሥልጣን ጥያቄው ተነስቶ ክሱ ውድቅ ሊደረግ የሚገባው ነው፡፡
ወደያዝነው ጉዳይ ስንመለስ ክሱ መሠረት ያደረገው ከውል ውጭ ኃላፊነትን ሲሆን ጉዳት የደረሠበት ቦታ አማራ ክልል ከሶሮቃ ወደ ጎንደር ከተማ በሚወስደው መንገድ ነው፡፡ በሚንቀሳቀስ ንብረት ላይ ጉዳት በደረሰ ጊዜ ክሱ የሚቀርበው ጉዳቱ በደረሰበት ሥፍራ በሚገኝ ፍርድ ቤት መሆኑን ስለግዛት ክልል የሚደነግገው የፍብ/ሥ/ሥ/ሕ/ቁ. 27(1) ላይ ተመልክቷል፡፡ የሥር ተከሳሾች የሆኑት ተጠሪዎች መኖሪያ አድራሻቸው አማራ ክልል ነው፡፡ ይሕም ክሱ አማራ ክልል ፍርድ ቤት እንደሚታይ ያስረዳል፡፡ በሌላ በኩል የተከራካሪዎችን ማንነት ስንመለከት አመልካች በፌደራል መንግሥቱ የተመዘገበ የንግድ ድርጅት መሆኑ በፌደራል ፍርድ ቤቶች አዋጅ ቁጥር 25/1988 አንቀጽ 5(6) መሠረት ጉዳዩን የመዳኘት ሥልጣን ያለው የፌደራል ፍርድ ቤት ስለመሆኑ ያስገነዝባል፡፡ የፌደራል ጉዳይ ቢሆንም ጉዳዩ የተነሳው በአማራ ክልል በመሆኑ በሕገ-መንግሥቱ በተሠጠው ውክልና መሠረት መታየት ያለበት በክልሉ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ነው፡፡ የፌደራል ፍርድ ቤት ለክልል ፍርድ ቤት በውክልና የተሰጠን የፌደራል ጉዳይ ከተመለከተ በሕገ-መንግስቱ ያለውን የፍርድ ቤት ሥልጣን ክፍፍል የሚጥስ ስለሆነ ጉዳዩ በየትኛውም ደረጃ ፍርድ ቤት ሲደርስ በተከራካሪዎች ሆነ በፍርድ ቤቱ የሥልጣን ጥያቄው ተነስቶ ክሱ ውድቅ ሊደረግ የሚገባው ስለመሆኑ ሰበር ሰሚ ችሎቱ ቀደም ሲል በመዝገብ ቁጥር 181923 ትርጉም የሠጠበት ነው፡፡ ሥለሆነም የአማራ ክልል በሕገ-መንግሥቱ የተሠጠው የውክልና ሥልጣን ያልተነሳ ስለሆነ የፌደራል አወቃቀሩን መሠረት ያደረገው አስገዳጅነት ያለውን የፍርድ ቤት የግዛት ክልል ሥልጣን ክፍፍል በሚጥስ መልኩ በፌደራል ፍርድ ቤቶች ጉዳዩ ቀርቦ መታየቱ መሠረታዊ የሆነ የሕግ ስህተት ያለበት ሆኖ አግኝተነዋል፡፡
ው ሳ ኔ
1. የፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ይግባኝ ሰሚ ችሎት በመዝገብ ቁጥር 167520 መስከረም 30 ቀን 2012 ዓ/ም እና የፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት በመዝገብ ቁጥር 170005 ጥቅምት 02 ቀን 2011 ዓ/ም የሠጡት ውሳኔ በፍብ/ሥ/ሥ/ሕ/ቁ. 348(1) መሰረት ተሽሯል፡፡
2. የፌደራል ፍርድ ቤት ጉዳዩን የማየት የግዛት ሥልጣን የለውም በማለት ወስነናል፡፡
3. በዚህ ችሎት ለወጣ ወጭና ኪሣራ ግራቀኙ የየራሳቸውን ይቻሉ ብለናል፡፡
ት ዕ ዛ ዝ
የውሳኔው ግልባጭ ለሥር ፍርድ ቤቶች ይተላለፍ፡፡
መዝገቡ ተዘግቷል ወደ መዝገብ ቤት ይመለስ፡፡
የማይነበብ የአምስት ዳኞች ፊርማ አለበት
ፋ/ዘ