የሰ/መ/ቁጥር 190729
የካቲት 24 ቀን 2013 ዓ/ም
ዳኞች ፡- ብርሀኑ አመነው
ተሾመ ሽፈራው
ሀብታሙ እርቅይሁን
ብርሀኑ መንግስቱ
ነፃነት ተገኝ
አመልካች ፡ አቶ አያልነህ ገ/ማርያም ጠ. መንግስተአብ ይልማ - ቀረቡ
ተጠሪዎች ፡ 1ኛ. ወ/ሮ ክብነሽ ጎሹ ጠ. ዳንኤል ብርዬ ቀረቡ
2ኛ. ወ/ሮ ሮዳ ሁሴን አልቀረቡም
መዝገቡ ተመርምሮ ተከታዩ ፍርድ ተሰጥቷል፡፡
ፍ ር ድ
ክርክሩ የቤት ሽያጭ ውል እንዲፈርስ የቀረበ ክስን መሰረት ያደረገ ሲሆን ጉዳዩ በተመጀረበት የፌደራል የመጀመሪያ ደረጃ ፍ/ቤት 1ኛ ተጠሪ ከሳሽ፣ አመልካች 1ኛ ተከሳሽ እንዲሁም 2ኛ ተጠሪ 2ኛ ተከሳሽ በመሆን ተከራክረዋል፡፡
1ኛ ተጠሪ ግንቦት 21 ቀን 2007 ዓ.ም ፅፈው ባቀረቡት ክስ በየካ ክፍለ ከተማ ወረዳ 12 የሚገኝ ስፋቱ 700 ካሬ ሜትር የሆነ የመኖሪያ ቤት ከአመልካች ጋር አብረን ስንኖር በጋራ ያፈራን ሲሆን በመካከላችን በተፈጠረ አለመግባባት በ2004 ዓ.ም ተለያይተናል፡፡ ይህ የጋራ ንብረት ተሽጦ አመልካች እና 1ኛ ተጠሪ እንድንከፋፈል በዚሁ ፍ/ቤት በመ/ቁጥር 90477 ክስ መስርቼ ክርክር ላይ እያለን 2ኛ ተጠሪ ቤቱን ሰኔ 5 ቀን 2003 ዓ.ም በተደረገ ያልጸደቀ የሽያጭ ውል በብር 400,000 ከ1ኛ ተጠሪ መግዛታቸውን በመግለፅ ወደ ክርክሩ ጣልቃ ገብ በመሆን ህዳር 23 ቀን 2007 ዓ.ም ካቀረቡት አቤቱታ ቤቱ መሸጡን ያወቅኩ ስለሆነ የሽያጭ ውሉ እንዲፈርስ ይወሰንልኝ በማለት ዳኝነት ጠይቀዋል፡፡
አመልካች ለክሱ በሰጡት መልስ 1ኛ ተጠሪ የሽያጭ ውሉ ይፍረስልኝ የሚል ክሳቸውን ያቀረቡት ውሉ ከተደረገ ከ3 ዓመት 11 ወር በኋላ ስለሆነ ክሱ በይርጋ ይታገዳል፤ ሰኔ 12 ቀን 2002 ዓ.ም በአመልካች እና በ1ኛ ተጠሪ መካከል በተደረገ የንብረት ክፍፍል ስምምነት 1ኛ ተጠሪ በቤቱ ላይ ያላቸው የባለቤትነት መብት ቀሪ ስለሆነ ክስ ለማቅረብ የሚያስችል መብትና ጥቅም የላቸውም፤ በዚህ ስምምነት ቤቱ ለአመልካች የደረሰኝ እና ጉዳዩ በሽምግልና ያለቀ ስለሆነ ክሱ ተገቢነት የለውም በማለት የመጀመሪያ ደረጃ መቃወሚያቸውን አቅርበዋል፡፡ በአማራጭ ባቀረቡት መልስ አመልካች እና 1ኛ ተጠሪ እንደ ባልና ሚስት አብረን ስንኖር የተጠቀሰውን ንብረት በጋራ ያፈራን ቢሆንም ሰኔ 12 ቀን 2002 ዓ.ም የንብረት ክፍፍል አድርገን ግንኙነታችን በመቋረጡ እና በየግል የያዝነውን ንብረት ለ3ኛ ወገን ያስተላለፍኩ ስለሆነ የሽያጭ ውሉ ሊፈርስ አይገባም በማለት ተከራክረዋል፡፡
2ኛ ተጠሪ በኩላቸው አመልካች ካቀረቡት የመጀመሪያ ደረጃ መቃወሚያ ጋር ተመሳሳይነት ያለው መቃወሚያ ያቀረቡ ሲሆን በተጨማሪነትም ግራ ቀኝ በመ/ቁጥር 90477 ላይ ክርክር እያደረግን ስለሆነ እና በሁለቱ መዝገቦች ላይ የሚያዘው ጭብጥ ተመሳሳይ ስለሆነ ክሱ በፍ/ሥ/ሥ/ሕ/ቁጥር 244(2)(ሐ) መሰረት ውድቅ ሊደረግ ይገባል በማለት ተከራክረዋል፡፡ በአማራጭ ባቀረቡት መከራከሪያ አመልካች እና 1ኛ ተጠሪ መስማማት ባለመቻላቸው ሰኔ 12 ቀን 2002 ባደረጉት የመለያየት ውል ቤቱን አመልካች እንዲወስዱ ተስማምተዋል፡፡ በዚህ መነሻነት 2ኛ ተጠሪ ቤቱን ሰኔ 5 ቀን 2003 ዓ.ም በብር 400,000 ገዝቼ ተጨማሪ ግንባታ ያከናወንኩበት ስለሆነ ወደ ነበረበት ሊመለስ አይችልም፡፡ ውሉም በአዋዋይ ፊት ያልተፈፀመው አመልካች እና ተጠሪ በ1993 ዓ.ም ቤቱን ሲገዙ ባልፀደቀ ውል ስለሆነ ነው በማለት ተከራክረዋል፡፡
ፍርድ ቤቱ በመቃወሚያው ላይ በሰጠው ብይን በመ/ቁጥር 90477 1ኛ ተጠሪ የጋራ ንብረት እንዲካፈሉ እንዲወስንላቸው ሲሆን በተያዘው ጉዳይ የተጠየቀው ዳኝነት የሽያጭ ውል ይፍረስልኝ የሚል የተለያየ ጭብጥ ስለሆነ በፍ/ሥ/ስ/ሕ/ቁጥር 244(2)(ሐ) መሰረት የቀረበው መቃወሚያ ተገቢነት የለውም፡፡ ውሉን ለማፍረስ የሚያስችል የክስ ምክንያት አለ ወይስ የለም የሚለውም በፍሬ ነገር ክርክር የሚጣራ ነው፡፡ 1ኛ ተጠሪ የውሉን መኖር ያወኩት ህዳር 23 ቀን 2007 ዓ.ም ነው በማለት ያቀረቡትን መከራከሪያ አመልካች እና 2ኛ ተጠሪ ስላልተቃወሙ ከዚህ ጊዜ ጀምሮ ውሉ እንዲፈርስ ዳኝነት እስከተጠየቀበት ግንቦት 21 ቀን 2007 ዓ.ም ያለው ግዜ 6 ወር ያልሞላው በመሆኑ በተሻሻው የፌደራል የቤተሰብ ሕግ አዋጅ ቁጥር 213/92 አንቀፅ 69(2) መሰረት ክሱ በይርጋ አይታገድም በማለት መቃወሚያውን አልፎታል፡፡ በፍሬ ጉዳይ ላይ በሰጠው ውሳኔ አመልካች እና 1ኛ ተጠሪ ሰኔ 12 ቀን 2002 ዓ.ም በስምምነት ክፍፍል ስለማድረጋቸው የቀረበው ውልና በዚህ ውል መሰረት ቤቱን በሽያጭ ስለማስተላለፉቸው አመልካች ያቀረቡት ውል በሀሰት የተዘጋጀ ሰነድ መሆኑ በፌደራል ከፍተኛ ፍ/ቤት በወ/መ/ቁጥር 161234 ተረጋግጦ አመልካች በወንጀል ተቀጥቷል፡፡ ይህ ውሳኔም በፌደራል ጠቅላይ ፍ/ቤት በይ/መ/ቁጥር 164836 ጸንቷል፡፡ በመሆኑም በክፍፍል በተገኘ ንብረት ላይ የተደረገ ሽያጭ ነው በማለት የቀረበው መከራከሪያ ተቀባይት የለውም፡፡ 2ኛ ተጠሪ የመጀመሪያው ውል ያልጸደቀ መሆኑን ጠቅሰው የሚከራከሩ ቢሆንም የውሉ መፅደቅ ክርክር ያልተነሳበት እና በነበረ ውል ግንኙነት የተገኘው መብት አሁን ላይ ክርክር የተነሳበትና ያልፀደ ስለሆነ እንዲሁም 1ኛ ተጠሪ በውሉ ፈቃዳቸውን ያልሰጡ እና በሀሰት የተዘጋጀ ሰነድን መሰረት አድርጎ የተፈጸመ ስለሆነ ውሉ ሊፈርስ ይገባል፡፡ 2ኛ ተጠሪ በቦታው ላይ ላደረጉት ተጨማሪ ግንባታ 1ኛ ተጠሪን ከሰው ከማስከፈል በስተቀር ወደ ነበርንበት ልንመለስ አይገባም በማለት የቀረበው መከራከሪያ ተገቢነት የለውም በማለት ወስኗል፡፡
አመልካች ውሳኔውን በመቃወም ይግባኛቸውን ለፌደራል ከፍተኛ ፍ/ቤት ያቀረቡ ቢሆንም በፍ/ሥ/ሥ/ሕ/ቁጥር 337 መሰረት ተሰርዟል፡፡
አመልካች የካቲት 10 ቀን 2012 ዓ.ም የተፃፈ የሰበር አቤቱታቸውን ያቀረቡት ይህን የስር ፍ/ቤቶች ውሳኔ በመቃወም ነው፡፡ የአቤቱታው ይዘት ባጭሩ ለክርክሩ መነሻ የሆነው የቤት ሽያጭ ውል የተፈፀመው ሰኔ 5 ቀን 2003 ዓ.ም ሲሆን 1ኛ ተጠሪ ውሉ እንዲፈርስ በፍ/ቤት ክስ ያቀረቡት ሐምሌ 17 ቀን 2007 ዓ.ም በመሆኑ በተሻሻለው የቤተሰብ ሕግ አንቀፅ 69(2) መሰረት አንደኛው ተጋቢ ውሉ መደረጉን ካወቀ በ6 ወር ጊዜ ውስጥ ክሱን ማቅረብ ያለበት እና በማንኛውም ሁኔታ ከ2 ዓመት በኋላ ውሉ እንዲፈርስ መጠየቅ የማይችል ስለመሆኑ የተቀመጠውን ፍፁም ይርጋ ያለአግባብ በመተርጎም 1ኛ ተጠሪ ውሉ መኖሩን ያወቁት ህዳር 23 ቀን 2007 ዓ.ም በመሆኑ የ6 ወር ጊዜው አላለፈም በማለት መወሰኑ መሰረታዊ የሕግ ስህተት የተፈፀመበት ነው፡፡ 1ኛ ተጠሪ ሰኔ 12 ቀን 2002 ዓ.ም በተደረገው የንብረት ክፍፍል ስምምነት ላይ ያለውን ፊርማ በመካዳቸው ፍ/ቤቱ ፊርማው እንዲመረመር ትዕዛዝ ከሰጠ በኋላ መዝገቡ የተዘጋ ቢሆንም እንደገና እንዲንቀሳቀስ ሲደረግ ፊርማው በፎረንሲክ እንዲመረመር አለመደረጉ ወይም ትዕዛዙ ቀሪ ስለመደረጉና ቀሪ የተደረገበት ምክንያት ሳይገለፅ መታለፉ አግባብ አይደለም፡፡ ውሉ እንዲፈርስ ሲወስንም ተዋዋዮች ወደ ነበሩበት እንዲመለሱ የሚያስችል ምክንያት አለ ወይስ የለም፤ በውሉ መፍረስ አንደኛው ወገን የሚበለፅግ እና ሌላው ወገን የሚጎዳ መሆኑን ከግምት ውስጥ ሳያስገባ የሰጠው ውሳኔ መሰረታዊ ሕግ ስህተት ተፈፅሞበታል የሚል ነው፡፡
ጉዳዩ በሰበር አጣሪ ችሎቱ ተመርምሮ አመልካች ያቀረቡት የይርጋ መቃወሚያ ሊታይ የሚገባው ሚስት የንብረቱን መሸጥ ካወቁበት ጊዜ ጀምሮ ነው? ወይስ ውሉ ከተደረገበት ሰኔ 5 ቀን 2003 ዓ.ም? ጀምሮ የሚለውን ከቤተሰብ ሕጉ ድንጋጌ አንፃር ለመመርምር ያስቀርባል በመባሉ ተጠሪዎች መልሳቸውን እንዲያቀርቡ ትዕዛዝ ተሰጥቷል፡፡
2ኛ ተጠሪ መጥሪያው ደርሷቸው ስላልቀረቡ መልስ የማቅረብ መብታቸው የታለፈ ሲሆን 1ኛ ተጠሪ ጥቅምት 13 ቀን 2013 ዓ.ም የተፃፈ መልሳቸውን አቅርበዋል፡፡ የመልሱ ይዘት ባጭሩ 2ኛ ተጠሪ እና አመልካች አባት እና ልጅ ሲሆኑ አመልካች ክፍፍል ያልተደረገበትን ሰነድ አልባ ቤት ከ1ኛ ተጠሪ ጋር የንብረት ክፍፍል አድርጌበታለው በማለት በሀሰት ባዘጋጀው የክፍፍል ስምምነት መነሻነት የተደረገውን የመንደር የሽያጭ ውል መኖሩን ካወኩበት ሕዳር 23 ቀን 2007 ዓ.ም ጀምሮ በቤተሰብ ሕጉ አንቀፅ 69 መሰረት በ6 ወር ጊዜ ውስጥ የሽያጭ ውሉ እንዲፈርስ ዳኝነት የጠየኩ ስለሆነ የይርጋ መቃወሚያው መታለፉ ተገቢ ነው፡፡ ለሽያጭ ውሉ መነሻ የሆነው የስምምነት ክፍፍል በሀሰት የተዘጋጀ መሆኑ ተረጋግጦ አመልካች በወንጀል የተቀጣ በመሆኑ በወንጀል ድርጊት መነሻ የተፈፀመን ከመነሻው የሌለ ውልን ሊፈርስ አይገባም በማለት አመልካች ያቀረበው ቅሬታ ተገቢ አይደለም፡፡ የክፍፍል ውሉ ላይ 1ኛ ተጠሪ ያልፈረምኩ እና የማላውቀው መሆኑ በፎረንሲክ ተረጋግጦ አመልካች በወንጀል የተቀጡ በመሆኑ ሰነዱ በፎረንሲክ አልተመረመረም በማለት የሚያነሱት ክርክር ተገቢነት የለውም፡፡ ውሉን አመልካች ንብረቱን ከ1ኛ ተጠሪ ለማሸሽ ከ2ኛ ተጠሪ ጋር በመመሳጠር የፈፀሙት እና ያልተመዘገ ሕገ ወጥ ውል በመሆኑ የደረሰባቸው ጉዳት የለም፡፡ በተጨማሪም ወደ ነበሩበት ላለመመለስ በስር ፍ/ቤት ያቀረቡት ዳኝነት የለም በማለት ተከራክረዋል፡፡
አመልካች የተፃፈ የመልስ መልሳቸውን ያቀረቡ ሲሆን የሰበር አቤቱታቸውን በማጠናከር ተከራክረዋል፡፡
የክርክሩ አመጣጥ ባጭሩ ከላይ የተመለከተው ሲሆን ጉዳዩ ለሰበር ሰሚ ችሎቱ ያስቀርባል ሲባል የተያዘውን ጭብጥ ከግራ ቀኙ ክርክር፣ በስር ፍ/ቤት በማስረጃ ከተረጋገጡ ፍሬ ጉዳዮች እንዲሁም ለጉዳዩ አግባብነት ካለው የሕግ ድንጋጌ ጋር በማገናዘብ እንደሚከተለው መርምረነዋል፡፡
እንደመረመርነውም አመልካች በዋናነት የሚከራከሩት ከ1ኛ ተጠሪ ጋር ሰኔ 12 ቀን 2002 ዓ.ም በተደረገ የስምምነት ውል መሰረት ክርክር የተነሳበት ቤት የአመልካች ድርሻ እንዲሆን ተስማምተን፤ ቤቱን ለ2ኛ ተጠሪ ሰኔ 5 ቀን 2003 ዓ.ም በተደረገ የሽያጭ ውል ያስተላለፍኩ በመሆኑና እንዲሁም በ1ኛ ተጠሪ የሽያጭ ውሉ እንዲፈርስ ክስ የቀረበው ሐምሌ 17 ቀን 2007 ዓ.ም ስለሆነ በፌደራል የቤተሰብ ሕግ አንቀፅ 69(2) መሰረት ክሱ በይርጋ ቀሪ ነው በማለት የቀረበው መቃወሚያ መታለፉ ተገቢ አይደለም በማለት ነው፡፡ በአንፃሩ 1ኛ ተጠሪ ከአመልካች ጋር ሰኔ 12 ቀነ 2002 ዓ.ም የንብረት ክፍፍል ስምምነት አለመፈራረማቸውን፤ አመልካች ከ2ኛ ተጠሪ ጋር ሰኔ 5 ቀን 2003 ዓ.ም የሽያጭ ውል ማድረጋቸውንም ያወቁትም ህዳር 23 ቀን 2007 ዓ.ም መሆኑን፤ ከዚህም ግዜ ጀምሮ የስድስት ወር ግዜ ሳያልፈው ግንቦት 21 ቀን 2007 ዓ.ም ውሉ እንዲፈርስ ክስ የመሰረትኩ እና የሽያጭ ውሉም ያልተመዘገበ መሆኑ ተረጋግጦ ውሉ እንዲፈርስ መወሰኑ ተገቢ ነው በማለት ተከራክረዋል፡፡
የጋራ የሆነን የማይንቀሳቀስ ንብረት ለመሸጥ ለመለወጥ፣ ለማከራየት፣ በመያዣነት ለመስጠት ወይም በሌላ በማንኛውም ሁኔታ ሌሎች ሰዎች በንብረቱ ላይ መብት እንዲያገኙ ለማድረግ የተጋቢዎቹ የጋራ ስምምነት እንደሚያስፈልግ፤ ከዚህ በተቃራኒ አንደኛው ተጋቢ የውል ግዴታ የገባ እንደሆነ ፍቃዱን ያልሰጠው ተጋቢ ግዴታው መገባቱን ካወቀበት ግዜ ጀምሮ በ6 ወር ውሰጥ ወይም በማንኛውም ሁኔታ ግዴታው በተገባ በ2 ዓመት ውስጥ ግዴታው እንዲፈርስ ሊጠይቅ እንደሚችል በፌደራል የቤተሰብ ሕግ አንቀፅ 68(1) እና 69 ላይ ተመላክቷል፡፡
ከክርክሩ ሒደት መገንዘብ እንደቻልነው አከራካሪ የሆነውን ቤት አመልካች እና 1ኛ ተጠሪ እንደ ባልና ሚስት አብረው ሲኖሩ በ1993 ዓ.ም በጋራ የገዙት ሲሆን አመልካችም ይህ ንብረት ከመነሻውም የጋራ ንብረት አይደለም በማለት የሚያቀርቡት መከራከሪያ የለም፡፡ አመልካች አጥብቀው የሚከራከሩት ሰኔ 12 ቀን 2002 ዓ.ም ከተጠሪ ጋር የንብረት ክፍፍል ማድረጋቸውን በዚህም መነሻነት ቤቱ የአመልካች ድርሻ እንዲሆን ተስማምተው የሽያጭ ውሉ ሰኔ 5 ቀን 2003 ዓ.ም ከተደረገ በኋላ በ2007 ዓ.ም ውሉ እንዲፈርስ የቀረበው ክስ በይርጋ ቀሪ ይሆናል በማለት ነው፡፡ 1ኛ ተጠሪ የሽያጭ ውል መኖሩን ያወቁት ጉዳዩን በመጀመሪያ ደረጃ በተመለከተው የፌደራል የመጀመሪያ ደረጃ ፍ/ቤት በአመልካች ላይ የጋራ ንብረት ክፍፍል ክስ በኮ/መ/ቁ 90444 መስርተው ክርክር ላይ እያሉ ሕዳር 23 ቀን 2007 ዓ.ም 2ኛ ተጠሪ የሽያጭ ውሉን መሰረት አድርገው በክርክሩ ጣልቃ ለመግባት ካቀረቡት አቤቱታ መሆኑን ገልፀው የሚከራከሩ ሲሆን አመልካችም ሆነ 2ኛ ተጠሪ ይህን በመቃወም ያቀረቡት መከራከሪያ የለም፡፡ ከዚህም ሌላ 1ኛ ተጠሪ የሽያጭ ውሉ አለመመዝገቡን ጠቅሰው ክርክር አቅርበዋል፡፡ አመልካችም ሆነ 2ኛ ተጠሪ የሽያጭ ውሉ መመዝገቡን ገልጸው ያቀረቡት መከራከሪያ የለም፡፡ ይልቁኑም 2ኛ ተጠሪ የሽያጭ ውሉ ያልተመዘገበው አመልካች እና 1ኛ ተጠሪ ቤቱን በ1993 ዓ.ም የገዙት ባልተመዘገበ ውል በመሆኑ ከአመልካች ጋር ያደረጉት የሽያጭ ውልም ያለመመዝገቡን ገልፀው ተከራክረዋል፡፡ ይህም የሽያጭ ውሉ በማይንቀሳቀስ ንብረት ላይ የተፈፀመ እንደመሆኑ የፍ/ሕ/ቁጥር 1723 በሚደነግገው አግባብ ስልጣን ባለው ሰነዶች ማረጋገጫ እና ምዝገባ ፅ/ቤት አለመመዝገቡን የሚያረጋግጥ ነው፡፡ እንዲሁም በፍ/ሕ/ቁጥር 2878 መሰረት ውሉ ለክርክሩ መሰረት የሆነው ቤት በሚገኝበት አከባቢ በሚገኝ የማይንቀሳቀስ ንብረት መመዝገቢያ የባህር መዝገብ ላይ አለመመዝገቡን ያሳያል፡፡ የማይንቀሳቀስ ንብረትን የሚመለከቱ ውሎች ምዝገባ አላማም በተዋዋዮች መካከል ውሉን የተመለከቱ አከራካሪ ሁኔታዎች ቢነሱ ጉዳዩን በቀላሉ እልባት ለመስጠት ለማስቻል እንዲሁም በንብረቱ ሽያጭ ላይ መብት ጠያቂ ሶስተኛ ወገኖች ካሉ ውሉ ስለመደረጉ አውቀው ተገቢውን መፈጸም እንዲችሉ ለማስቻል ነው፡፡ አመልካች እና 2ኛ ተጠሪ ውሉን መዋዋላቸው ባይካካዱም ይሕ የሽያጭ ውል በፍ/ሕ/ቁጥር 1723 እና 2878 መሰረት ስልጣን ባለው አካል ያልተመዘገበ በመሆኑ 1ኛ ተጠሪ በቤቱ ላይ የተደረገውን የሽያጭ ውል አውቀው መቃወሚያ ሊያቀርቡበት የሚችሉበት አግባብ የለም፡፡ በአንፃሩ 1ኛ ተጠሪ ይህ የሽያጭ ውል መኖሩን ያወቁት ህዳር 23 ቀን 2007 ዓ.ም መሆኑ እና ውሉ እንዲፈርስ በፍ/ቤት ክስ የመሰረቱት ግንቦት 21 ቀን 2007 ዓ.ም መሆኑ ተረጋግጧል፡፡ እንደሚታወቀው የይርጋ ድንጋጌዎች አላማ መብቱን የሚጎዳ ነገር መፈጸሙን እያወቀ በመብቱ ሳይሰራ የሚቆይን ከሳሽ ክስ የማቅረብ መብት መገደብ እንጂ መብቱ ስለመነካቱ የማያውቅ ወይም ማወቅ የሚችልበት እድል የሌለውን ከሳሽ ክስ የማቅረብ መብት መገደብ አይደለም፡፡ የሽያጭ ውሉ ባልተመዘገበበት እና በሌላ ሁኔታ 1ኛ ተጠሪ ስለሽያጭ ውሉ መደረግ አወኩ ካሉበት ጊዜ በፊት ስለማወቃቸው በአመልካች የቀረበ ክርክር የሌለ ከመሆኑም በላይ 1ኛ ተጠሪ ውሉ አውቀዋል ወይም ማወቅ ነበረባቸው ተብሎ የሚገመተው ውሉ የተመዘገበ ቢሆን ኖሮ ነበር፡፡ ይህ ባልሆነበት ውሉ በተደረገበት በ2 ዓመት ውስጥ ክስ ማቅረብ ነበረባቸው የሚለው የአመልካች ክርክር የቤተሰብ ህጉን አንቀጽ 69 አላማ እና መንፈስ ያላገናዘበ ከመሆኑም በተጨማሪ ከተጋቢዎች አንዱ የሌላኛውን ፍቃድ ሳያገኝ ውል እየተዋዋለ የ2 ዓመት የይርጋ ጊዜ እስኪያልፍ ደብቆ በማቆየት በውሉ ላይ ፍቃደኝነቱን ያልገለጸውን ተዋዋይ ወገን ውሉ እንዲፈርስ የመጠየቅ መብቱን አላግባብ እንዲያጣ የሚያደርግ ነው፡፡ በማይንቀሳቀስ ንብረት ላይ የሚደረጉ ውሎች በሚመለከተው አካል እስካልተመዘገቡ ድረስ የውል ይፍረስልኝ ክስ ማቅረቢያ የ2 ዓመት የይርጋ ጊዜ መቆጠር መጀመር ያለበት በውሉ ላይ ስምምነቱን ያልሰጠው ተጋቢ የውሉን መደረግ ካወቀበት ጊዜ ጀምሮ ሊሆን ይገባል፡፡ ይህም ማለት በቤተሰብ ህጉ አንቀጽ 69 በማንኛውም ሁኔታ ውሉ ከተደረገበት ጀምሮ በሁለት ዓመት ውስጥ የውል ይፍረስልኝ ክስ መቅረብ አለበት የሚለው ድንዳዴ ተፈጻሚ መሆን ያለበት እንዲፈርስ የሚጠየቀው ውል በሚመለከተው የመንግስት አካል የተመዘገበ ከሆነ ወይም ባይመዘገብ እንኳን በሌላ አግባብ ስለውሉ መደረግ በሚያውቅ ተጋቢ ላይ ሊሆን ይገባል፡፡ በመሆኑም በተያዘው ጉዳይ በቤተሰብ ሕጉ አንቀፅ 69 ላይ የተመለከተው የይርጋ ጊዜ መቆጠር መጀመር ያለበት 1ኛ ተጠሪ ውሉ መደረጉን ካወቁበት ህዳር 23 ቀን 2007 ዓ.ም ጀምሮ መሆን ስለሚገባው እና 1ኛ ተጠሪም የሽያጭ ውሉ መደረጉን ካወቁበት ጀምሮ ክስ እስከ መሰረቱበት ግንቦት 21 ቀን 2007 ዓ.ም 6 ወር ሳይሞላው ክስ የመሰረቱ በመሆኑ በአመልካች እና በ2ኛ ተጠሪ በኩል የተነሳው የይርጋ መከራከሪያ መታለፉ መሰረታዊ የሕግ ስህት የተፈፀመበት አይደለም፡፡
በመቀጠልም የሽያጭ ውሉ እንዲፈርስ የተሰጠውን ውሳኔ አግባብነት ስንመለከት አመልካች አከራካሪውን ቤት ከ1ኛ ተጠሪ ጋር በጋራ ያፈሩት መሆኑን ሳይክዱ ሰኔ 12 ቀን 2002 ዓ.ም በተደረገ የክፍፍል ስምምነት የአመልካች ንብረት እንዲሆን 1ኛ ተጠሪ የተስማሙ በመሆኑ የሽያጭ ውሉ እንዲፈርስ መወሰኑ አግባብ አይደለም በማለት ተከራክረዋል፡፡ ነግር ግን ሰኔ 12 ቀን 2012 ዓ.ም የንብረት ክፍፍል ተደርጎበታል በተባለው ሰነድ ላይ 1ኛ ተጠሪ አለመፈረማቸው እና አመልካች ሰነዱን በሐሰት ያዘጋጁት መሆኑ ተረጋግጦ አመልካች በፌደራል ከፍተኛ ፍ/ቤት በወ/መ/ቁ 161234 በወንጀል የተቀጡ ሲሆን ይህ የጥፋተኝነት ውሳኔም በፌደራል ጠቅላይ ፍ/ቤት ይግባኝ ሰሚ ችሎት በይ/መ/ቁ 164836 በተሰጠ ውሳኔ ፀንቷል፡፡ ይህ የወንጀል ውሳኔ በፍትሐብሔር ጉዳዮች ላይ እንዳለ ተቀባይነት ያለው ማስረጃ (Conclusive Evidence) በመሆኑ አመልካች በስር ፍ/በት ፊርማው በፎረንሲክ ሳይመረመር የተሰጠው ውሳኔ ተገቢ አይደለም በማለት የሚያነሱት መከራከሪያ ተቀባይነት የለውም፡፡ በመሆኑም ሰኔ 12 ቀን 2002 ዓ.ም ተደረገ የተባለው የንብረት ክፍፍል ስምምነት በሀሰት የተዘጋጀ በመሆኑ እንዲሁም በሽያጭ ውሉ 1ኛ ተጠሪ ፍቃዳቸውን ያልሰጡ መሆኑ በመረጋገጡ የሽያጭ ውሉ እንዲፈርስ በስር ፍ/ቤቶች የተሰጠው ውሳኔ ላይ የተፈፀመ የሕግ ስህተት የለም፡፡
አመልካች በይዞታው ላይ ከሽያጭ ውሉ በኋላ በ2ኛ ተጠሪ ተጨማሪ ግንባታ መደረጉን በመግለፅ ተዋዋዮችን ወደ ነበርንበት መመለስ አይቻልም፤ ውሉ እንዲፈርስ ሲወሰንም አንደኛው ወገን ያለአግባበብ የሚበለፀግ መሆን አለመሆኑ ከግምት ውስጥ ሳይገባ መወሰኑ ተገቢ አይደለም በማለት የሚከራከሩ ቢሆንም ይህ መከራከሪያ ሊቀርብ የሚገባው በ2ኛ ተጠሪ በመሆኑ እና 2ኛ ተጠሪ የመጀመሪያ ደረጃ ፍ/ቤቱ በሰጠው ውሳኔ ይግባኝ ስለማቅረባቸው ወይም በዚህ ሰበር ሰሚ ችሎት በተደረገው ክርክር መጥሪያ የደረሳቸው ቢሆንም ቀርበው ይህን ገልፀው ያቀረቡት መከራከሪያ እና የመስቀለኛ የሰበር አቤቱታ ስለሌለ የአመልካች ክርክር ተቀባይነት የለውም በማለት ተከታዩን ወስነናል፡፡
ው ሳ ኔ
መዝገቡ ተዘግቷል፤ ወደ መዝብ ቤት
የማይነበብ የአምስት ዳኞች ፊርማ አለበት
ማ/ተ