የኢትዮጵያ ፌደራላዊ ዲሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ
የፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት
ሰበር ሰሚ ችሎት
የሰ/መ/ቁ. 191968
ቀን ፡- ሚያዚያ 28 ቀን 2013 ዓ/ም
ዳኞች፡- ብርሃኑ አመነው
ተሾመ ሽፈራው
ሀብታሙ እርቅይሁን
ብርሃኑ መንግስቱ
ነፃነት ተገኝ
አመልካች ፡- አቶ ዋኬኔ ዲንቃ
ተጠሪዎች ፡- 1. አቶ ኤብሳ እጅጉ ቀረቡ
2. አቶ ታሪኩ ዱጋሳ
3. ወ/ሮ ደሜ ሞቲ
4. አቶ ደበላ እጅጉ
መዝገቡ ተምርምሮ ተከታዩ ፍርድ ተሠጠ- አልቀረቡም
ፍርድ
የሰበር አቤቱታው የቀረበው የኦሮሚያ ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ሠበር ሰሚ ችሎት በሠጠው ውሳኔ መሠረታዊ የሕግ ስህተት ተፈጽሞበታል በሚል ነው፡፡ የክርክሩን አመጣጥ ከስር ፍርድ ቤት የመዝገብ ግልባጭ እንደተረዳነው አመልካች በሥር ፍርድ ቤት ከሳሽ ሲሆኑ ተጠሪዎች ተከሳሾች ሆነው ተከራክረዋል፡፡ አመልካች ጥቅምት 01 ቀን 2011 ዓ/ም በተጻፈ የክስ ማመልከቻ በጉዱሩ ወረዳ ጉደኔ ጫላ ሲበሬ ቀበሌ የሚገኝ 15.5 ሄክታር መሬት ወላጅ እናቴ ንጉሴ ኦብሴ ግንቦት 17 ቀን 2002 ዓ/ም ሕይወቷ ከማለፉ በፊት ስትጠቀምበት የነበረውን መሬት ስለያዙ እንዲለቁልኝ እና መሬቱን በማረስ የተጠቀሙበት የዓላባ ግምት በድምሩ ብር 3,607,212.00 እንዲከፍሉኝ በማለት ዳኝነት ጠይቀዋል፡፡ ተጠሪዎች ባቀረቡት መልስ ይዞታውን ከ1971 ዓ/ም ጀምሮ የምንጠቀምበት ስለሆነ ክሱ በይርጋ የታገደ ነው በማለት የመጀመሪያ ደረጃ መቃወሚያ አቅርበዋል፡፡
ጉዳዩን በመጀመሪያ ደረጃ የተመለከተው የሆሮ ጉዱሩ ወለጋ ዞን ከፍተኛ ፍርድ ቤት ግራቀኙን አከራክሮ በኦሮሚያ ክልል የገጠር መሬት አስተዳርና አጠቃቀቀም አዋጅ ቁጥር 130/1999 አንቀጽ 16 መሠረት የገጠር መሬት ይዞታ ጋር የሚፈጠር አለመግባባት በሽምግልና ለመፍታት ጥረት መደረግ እንዳለበትና አለመግባባቱ ካልተፈታም ክሱ ለወረዳ ፍርድ ቤት እንደሚቀርብ የተመለከተ ስለሆነ አመልካች የገጠር መሬት ይዞታ ክርክሩን የሰብል ምርትና ዓላባን ምክንያት በማድረግ ለከፍተኛ ፍርድ ቤት ክስ መመስረት የለበትም ብለናል፡፡ ክሱ ለከፍተኛ ፍርድ ቤት የሚቀርብ አይደለም እንጂ የሕግ ድጋፍ አለው ቢባል እንኳን ተጠሪዎች ይዞታውን ለ19 ዓመት የያዙት በመሆኑ ክሱ በይርጋ ቀሪ ነው በማለት ወስኗል፡፡ የኦሮሚያ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ይግባኝ ሰሚ ችሎት የአመልካችን ይግባኝ በፍብ/ሥ/ሥ/ሕ/ቁ. 337 መሠረት ባለመቀበል ሠርዟል፡፡ የኦሮሚያ ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ሠበር ሰሚ ችሎት ግራቀኙን አከራክሮ ክሱ የገጠር መሬት ይዞታ ክርክር ሳይሆን የውርስ ሀብት ጥያቄ በመሆኑ በሀብቱ ግምት መሠረት ለከፍተኛ ፍርድ ቤት መቅረቡ ተገቢ ነው፡፡ ክስ የቀረበበትን ይዞታ ተጠሪዎች ለ18 ዓመት የያዙ ስለመሆኑ አመልካችም ያመኑ በመሆኑ ክሱ በፍ/ሕ/ቁ. 1845 መሠረት በ10 ዓመት ይርጋ ቀሪ ነው ተብሎ መወሰኑ ላይ የተፈጸመ መሠረታዊ የሕግ ስህተት የለም በማለት ወስኗል፡፡
ይህ የሰበር አቤቱታ የቀረበው በዚህ ውሳኔ ነው፡፡ የአመልካች የሰበር አቤቱታ ይዘትም የሥር ከፍተኛ ፍርድ ቤት ሥልጣን የለኝም ካለ ክሱን ተቀብሎ ማስተናገድ አልነበረበትም፡፡ ክርክሩ የውርስ ሀብትን የሚመለከት በመሆኑና ይርጋው መቆጠር ያለበት አውራሼ ከሞቱበት ጊዜ ጀምሮ ስለሆነ ክሱ በይርጋ ሊታገድ አይገባም፡፡ ተጠሪዎች ይዞታውን ለ19 ዓመት መያዛቸው በማስረጃ አልተረጋገጠም የሚል ሲሆን የሰበር አጣሪ ችሎት ጉዳዩን ተመልክቶ ከገጠር መሬት ጋር የተያያዘ የውርስ ክርክርም ቢሆን የወረዳ ፍርድ ቤት ሥልጣን ሆኖ እያለ ከፍተኛ ፍርድ ቤቱ ክሱን ተቀብሎ በማስተናገድ ውሳኔ መስጠቱ ሕጋዊነቱን ለመመርመር ለሰበር ሰሚ ችሎቱ ያስቀርባል በማለት ተጠሪዎች መልስ እንዲያቀርቡ ያዘዘ ሲሆን ከ1ኛ - 3ኛ ያሉት ተጠሪዎች ያቀረቡት መልስ የእርሻ መሬት ላይ የሚገኝ ሰብል ገምቶ በብር 3,607,212.00 ገንዘብ ላይ የቀረበው ክስ የከፍተኛ ፍርድ ቤት ሥልጣን ነው፡፡ ይዞታውም ከ39 ዓመት በላይ በእጃችን የቆየ ስለሆነ ውሳኔው ላይ የተፈጸመ መሠረታዊ የሕግ ስህተት የለም ብለዋል፡፡ አመልካች የመልስ መልስ በማቅረብ የሠበር አቤቱታቸውን በማጠናከር ተከራክረዋል፡፡ 4ኛ ተጠሪ መጥሪያ ደርሷቸው ባለመቅረባቸው ጉዳዩ በሌሉበት ታይቷል፡፡
የክርክሩ ሂደት በአጭሩ ከላይ የተገለጸው ሲሆን እኛም የሥር ከፍተኛ ፍርድ ቤት የቀረበውን ክስ ለመመልከት የሥረ-ነገር ሥልጣን አለው ወይስ የለውም? ክሱ በይርጋ ቀሪ ነው መባሉ ሕጋዊ መሆን አለመሆኑን? የሚለውን በጭብጥነት በመያዝ መዝገቡን እንደሚከተለው መርምረናል፡፡
የመጀመሪያውን ጭብጥ እንደመረመርነው አመልካች ጥቅምት 01 ቀን 2011 ዓ/ም በተጻፈ የክስ ማመልከቻ በጉዱሩ ወረዳ ጉደኔ ጫላ ሲበሬ ቀበሌ የሚገኝ 15.5 ሄክታር መሬት ወላጅ እናቴ ንጉሴ ኦብሴ ግንቦት 17 ቀን 2002 ዓ/ም ሕይወቷ ከማለፉ በፊት ስትጠቀምበት የነበረውን መሬት ስለያዙ እንዲለቁልኝ እና መሬቱን በማረስ የተጠቀሙበት የዓላባ ግምት በድምሩ ብር 3,607,212.00 እንዲከፍሉኝ በማለት ዳኝነት ጠይቀዋል፡፡ ክርክሩን በፍትሐ ብሔር ሥነ-ሥርዓት ሕጉ መሰረት መምራት እና መቆጣጠር የፍርድ ቤቱ ኃላፊነት ሲሆን በዚህ ሂደት ከሚመረምራቸው ጉዳዮች መካከል ጉዳዩ ላይ ለመወሰን ሥልጣን ያለው መሆን አለመሆኑ ዋነኛው ነው፡፡ የፍርድ ቤት ሥልጣን ብሔራዊ የመዳኘት ሥልጣን (judicial jurisdiction)፣ የሥረ-ነገር ሥልጣን (material jurisdiction) እና የግዛት ወይም ከበባዊ ሥልጣን (local or territorial jurisdiction) በሚል የተከፋፈለ ነው፡፡ በያዝነው ጉዳይ አከራካሪ ሆኖ የሚመረመረው የሥር ከፍተኛ ፍርድ ቤት የሥረነ-ገር ሥልጣን ያለው መሆን አለመሆኑ ነው፡፡ የሥረ-ነገር ሥልጣን በአንድ ሀገር ጉዳዩን ለመዳኘት ሥልጣን ባላቸው ፍርድ ቤቶች መካከል በዋነኛነት ታሳቢ የሚያደርገው የፍርድ ቤቱን አቅም ወይም ችሎታ (competence of the court)፣ ፍትሐዊነትን፣ ኢኮኖሚንና የሥራና ሀብት ክፍፍልን መሠረት አድርጎ በገንዘብ ግምት (pecuniary jurisdiction) ወይም በጉዳዩ ዓይነት (subject matter jurisdiction) ወይም ጉዳዩን በመጀመሪያ ሆነ በይግባኝ ደረጃ (original and appellate jurisdiction) የሚያዩት ሥለመሆኑ በፍርድ ቤቶች መካከል የሚመለከቱት ጉዳዩችን የሥልጣን ድልድል የሚደረግበት ነው፡፡
አመልካች ለሥር ከፍተኛ ፍርድ ቤት ያቀረቡት ክስ ሁለት ዳኝነቶች በአንድ ላይ ተጣምረው የቀረበቡት ነው፡፡ የመጀመሪያ የገጠር መሬት ይዞታ እንዲለቀቅላቸው ሲሆን ይሕም በኦሮሚያ ክልል የገጠር መሬት አስተዳደርና አጠቃቀም አዋጅ ቁጥር 130/1999 አንቀጽ 16(1)(ረ) ላይ በወረዳ ፍርድ ቤት ሥልጣን ሥር የሚወድቅ ጉዳይ ስለመሆኑ ተመልክቷል፡፡ ሁለተኛው ዳኝነት የዓላባ ግምትና በይዞታው ላይ ያለ ንብረት ግምት በድምሩ ብር 3,607,212.00 እንዲከፈላቸው ያቀረቡት የገንዘብ ግምትን መሠረት ያደረገው ነው፡፡ ክሱ ጥቅምት 01 ቀን 2011 ዓ/ም ሲቀርብ የሥረ-ነገር ሥልጣን እንደገና ያደላደለው የኦሮሚያ ክልል ፍርድ ቤቶች አዋጅ ቁጥር 216/2011 ዓ/ም በክልሉ ምክር ቤት ጸድቆ ሥራ ላይ የዋለና ስድስት ወር የመሸጋገሪያ ጊዜ ያለው ሲሆን በአዋጁ አንቀጽ 30(3) ሆነ በቀድሞው አዋጅ ቁጥር 141/2000 አንቀጽ 27(3) መሠረት ብር 3,607,212.00 የከፍተኛ ፍርድ ቤት ሥልጣን ነው፡፡
የገጠር መሬት አስተዳደርና አጠቃቀም አዋጅ ቁጥር 130/1999 በዋነኛነት ስለገጠር መሬት ባለይዞታዎች ስላላቸው መብትና አስተዳደር ጋር የተያያዙ መሠረታዊ መብቶችን የሚመለከት ቢሆንም ስለፍርድ ቤት ሥልጣን የተመለከተው ድንጋጌ የሥነ-ሥርዓት ሕግ ይዘት ያለው ነው፡፡ በአዋጁ ላይ የተመለከተው ከመሬት ይዞታ ጋር የተያያዘ ክርክር የወረዳ ፍርድ ቤት ሥልጣን ስለመሆኑ ያመለከተው ክፍል ከሥነ-ሥርዓት ሕጉ ሆነ ከፍርድ ቤቶች አዋጅ ላይ የተመለከቱ ጉዳዮች ቢኖሩም ከገጠር መሬት ጋር ለተያያዘ ጉዳይ አዋጅ ቁጥር 130/1999 ልዩ ሕግ ስለሆነ በሕግ አተረጓጎም መርሕ መሠረት ልዩ ሕጉ በቀዳሚነት መተግበር አለበት፡፡ ስለሆነም ከገጠር መሬት ጋር የተያያዘ ክርክር፤ ክርክሩ ይዞታ መብትን ለማስከበርም ሆነ የውርስ መብትን ወይንም ከገጠር መሬት ጋር የተያያዘ ሌላ መብትን ለማስከበር፤ ክሱ መቅረብ ያለበት ለወረዳ ፍርድ ቤት ነው፡፡ በዚህ ረገድ የክልሉ ሰበር ሰሚ ችሎት ከገጠር መሬት ውርስ መብት ጋር በተያያዘ ለሚቀርብ ክስ በአዋጅ ቁጥር 130/1999 የተመለከተው የወረዳ ፍርድ ቤት ሥልጣን ተፈጻሚነት የለውም ማለቱ ሥህተት ያለበትና ሊታረም የሚገባው ነው፡፡
በሌላ በኩል የገጠር መሬት አዋጁ ሙሉ የሥነ-ሥርዓት ሕግን የሚሸፍን ድንጋጌዎች የሌሉት በመሆኑ ሌሎች የሥነ-ሥርዓት ጉዳዮች ሲኖሩ የፍትሐ ብሔር ሥነ-ሥርዓት ሕጉ ሆነ የኦሮሚያ ፍርድ ቤቶች አዋጅ ተፈጻሚነት ይኖራቸዋል፡፡ በገጠር መሬት አዋጅ ቁጥር 130/1999 ላይ ከገጠር መሬት ጋር በተያያዘ ከሚቀርብ ክስ ጋር ተጣምረው በአንድ ላይ ሊቀርቡ ስለሚችሉ ጉዳዮች ሆነ በአንድ ላይ ተጣምረው የሚቀርቡ የተለያዩ ዳኝነቶች ሲኖሩ የፍርድ ቤቱ ሥልጣን እንዴት ይወሰናል በሚሉና በሌሎች ከክርክር አመራር ጋር በተያያዙ ጉዳዮች የሚመለከት ዝርዝር ድንጋጌ የለውም፡፡ ሕጉ በዋነኛት ስለገጠር መሬት ባለይዞታዎች መብትና መሬት አስተዳደር ጋር የተያየዙ ጉዳዮች ለመወሰን የወጣ በመሆኑ ዝርዝር የሥነ-ሥርዓት ሕጎችን እንዲሸፍንም አይጠበቅበትም፡፡ የፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ሰበር ሰሚ ችሎት በመዝገብ ቁጥር 120087 (በቅጽ 21 እንደታተመ) በፍብ/ሥ/ሥ/ሕ/ቁ. 218 እና 216 የተመለከተውን ከመሬት ሕጉ ጋር በማገናዘብ የይዞታ መብትን ለማስከበር የሚቀርብ ክስ እና ዓላባውን መሠረት ያደረገ ክስ ተነጣጥሎ በቀረበ ጊዜ ስለሚኖረው ወጤት ዋና ጭብጥ አድርጎ ክሶቹ ተነጣጥለው መቅረባቸው የሥነ-ሥርዓት ሕጉን ያልተከተለ ነው ተብሎ ውድቅ ሊደረግ አይገባም በማለት ትርጉም የሠጠበት ቢሆንም ሁለቱም ዳኝነቶች አብረው ሲቀርቡ እና የፍርድ ቤት ሥልጣን አከራካሪ ሲሆን የሚያስከትለው የሕግ ውጤት ምን እንደሚሆን በጭብጥነት ይዞ ያልመረመረ በመሆኑ ጉዳዩን መመልከቱ ተገቢ ሆኖ ተገኝቷል፡፡
በፍብ/ሥ/ሥ/ሕ/ቁ. 17(2) ላይ በአንድ ክስ ውስጥ የተለያዩ ዳኝነቶች ተጣምረው ሲቀርቡ የፍርድ ቤቱ ሥልጣን የሚወሰነው ከፍተኛ ግምት ያለውን አቤቱታ መሠረት በማድረግ ስለመሆኑ ተመልክቷል፡፡ አመልካች ሁለት ዳኝነቶች ያቀረቡ ሲሆን የመጀመሪያ ግምት የሌለው የገጠር መሬትን ለመረከብ የቀረበ ሲሆን ይሕም ወረዳ ፍርድ ቤት ሥልጣን ነው፡፡ ሁለተኛው የዓላባ ጥቅም መሠረት ያደረገ ብር 3,607,212.00 ለማስከፈል የቀረበ ክስ ሲሆን ጉዳዩም የከፍተኛ ፍርድ ቤት ሥልጣን ነው፡፡ ከቀረቡት ሁለት ዳኝነቶች ከፍተኛ ግምት ያለው ሁለተኛው ዳኝነት በመሆኑ ክሱ ተጠቃሎ መቅረብ ያለበት ለከፍተኛ ፍርድ ቤት ስለሆነ የሥረ-ነገር ሥልጣኑ የከፍተኛ ፍርድ ቤት ሊሆን ይገባል ብለናል፡፡ ስለሆነም አመልካች ክሱን ለሥር ከፍተኛ ፍርድ ቤት ማቅረባቸው ተገቢነት ያለው ሆኖ አግኝተነዋል፡፡
በፍብ/ሥ/ሥ/ሕ/ቁ. 231(1)(ለ) መሠረት ክሱ የቀረበለት ፍርድ ቤት ጉዳዩን ለመመልከት የሥረ-ነገር ሥልጣን ያለው መሆን አለመሆኑን ወደክርክር ሂደት ከመግባቱ በፊት አስቀድሞ የመመርመር ኃላፊነት
አለበት፡፡ የሥር ከፍተኛ ፍርድ ቤትም ክሱ እንደቀረበለት ሥልጣን ያለው መሆን አለመሆኑን ሳይመረምር ውሳኔ በሠጠ ጊዜ ክሱ የወረዳ ፍርድ ቤት ሥልጣን ነው ማለቱ ተገቢነት የለውም፡፡ ሥልጣን የለኝም ካለም ክሱን ለመመልከት ሥልጣን ላለው ፍርድ ቤት መመለስ ሲገባው በሥረ-ነገሩ ተመልክቶ ክሱ በይርጋ ቀሪ ነው ማለቱ የክርክር አመራር ግድፈት ያለበት ነው፡፡ ፍርድ ቤቱም ጉዳዩን ለማየት ሥልጣን ያለው ሆኖ እያለ ሥልጣን የለኝም ማለቱ መሠረታዊ የሆነ የሕግ ስህተት ነው፡፡ ነገር ግን ክሱን ለመመልከት ሥልጣን ያለው በመሆኑ ክሱን ተቀብሎ የይርጋ ክርክሩን መመርመሩ በውጤት ደረጃ ተቀብለነዋል፡፡
ወደ ሁለተኛው ጭብጥ ስንመለስ አመልካች ላቀረቡት የውርስ ገጠር መሬት ይዞታና ገንዘብ ይከፈለኝ ክስ ተጠሪዎች ክሱ በይርጋ ቀሪ ነው በማለት የመጀመሪያ ደረጃ መቃወሚያ አቅርበዋል፡፡ የይርጋ ክርክሩ የቀረበው አመልካች ክሱን ለማቅረብ የክስ የማቅረቢያ ጊዜው (limitation of action) አልፏል በሚል ነው፡፡ ይርጋ መብትን (extinctive prescription) እና/ወይም መብትን ለማስከበር የሚቀርብ ክስን ቀሪ የሚያደርግ ነው፡፡ እንደክሱ መሠረት ዓይነት ተፈጻሚ የሚሆነው የይርጋ ደንብና ሕግ የተለያየ ነው፡፡ የቀረበዉ ክስ በይርጋ ቀሪ ሊሆን የሚገባ መሆን አለመሆኑን በመወሰን ረገድ ፍርድ ቤቶች መሰረት እንዲያደርጉ የሚጠበቅባቸዉ በከሳሽ ክስ ላይ የተመለከተዉን የክስ ምክንያት ነው፡፡ ሁሉም የገጠር የእርሻ መሬት ጋር የተያያዘ የክስ ዓይነት ላይ ተመሳሳይ የይርጋ ደንብ ተፈጻሚ ሊሆን አይችልም፡፡ ክሱ ይዞታ እንዲለቀቅ የሚቀርብ የይዞታ መብትን ለማስከበር የሚቀርብ ክስ ወይም የገጠር መሬት ውርስ ይገባናል በሚል የቀረበ ክስ ወይም ከገጠር መሬት ጋር የተያያዘ ውልን መሠረት ያደረገ ክስ መሆኑ እየታየ እንደክሱ የዳኝነት መሠረት ክሱ በይርጋ ቀሪ የሚሆንበት ጊዜና ለጉዳዩ ተፈጻሚ የሚሆነው የይርጋ ደንብ ወይም ድንጋጌ የተለያየ ነው፡፡ ስለሆነም የክሱን መሠረት መለየት የይርጋ ክርክሩንም ሆነ ቀጣይ ያሉ ሂደቶችን ለመመራት አስፈላጊ መሆኑን መገንዘብ ያስልጋል፡፡
የአመልካች የክስ መሠረት የሆነው የገጠር መሬት ውርስን መሠረት ያደረገ በመሆኑ ከገጠር መሬት ጋር በተያያዘ ተፈፃሚነት ያለዉ የይርጋ ድንጋጌ ስለመኖሩ የክልሉ ገጠር መሬት አስተዳደር እና አጠቃቀም አዋጅ ቁጥር 130/99 የተለየ ድንጋጌ የለዉም፡፡ ይህ ማለት ግን ከገጠር መሬት ውርስ መብት ጋር የተያያዘ በሚቀርብ ክስ ላይ የይርጋ ደንቦች ተፈፃሚ አይሆኑም ማለት አይደለም፡፡ ስለሆነም በዚህ ረገድ በሚቀርብ ክስ ላይ ተፈጻሚ የሚሆነው የይርጋ ደንብ በፍ/ሕ/ቁ. 1677(1) እና 1845 የተመለከተው የ10 ዓመት ጊዜ ነው፡፡ አመልካች በሥር ፍርድ ቤት በተደረገ የቃል ክርክር መሬቱ በተጠሪዎች ከተያዘ ከ18 ዓመት በላይ መሆኑን አምነው የተከራከሩ ስለመሆኑ ከውሳኔው ግልባጭ ተረድተናል፡፡ ስለሆነም ክስ የቀረበው ከ10 ዓመት በኋላ በመሆኑ ክሱን በ10 ዓመት ይርጋ ቀሪ መደረጉ ላይ የተፈጸመ መሠረታዊ የሕግ ስህተት አላገኘንበትም፡፡
ውሳኔ
1. የኦሮሚያ ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ሠበር ሰሚ ችሎት በመዝገብ ቁጥር 318367 ጥር 19 ቀን 2012 ዓ/ም፣ የኦሮሚያ ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ይግባኝ ሰሚ ችሎት በመዝገብ ቁጥር 220530 ሰኔ 12 ቀን 2011 ዓ/ም፣ የሆሮ ጉዱሩ ወለጋ ዞን ከፍተኛ ፍርድ ቤት በመዝገብ ቁጥር 23958 ታህሳስ 24 ቀን 2011 ዓ/ም የሠጡት ውሳኔ በፍብ/ሥ/ሥ/ሕ/ቁ. 348(1) መሰረት በውጤት ደረጃ ፀንቷል፡፡
2. በዚህ ችሎት ለወጣ ወጭና ኪሣራ ግራቀኙ የየራሳቸውን ይቻሉ ብለናል፡፡
ትዕዛዝ
የውሳኔው ግልባጭ ለስር ፍርድ ቤቶች ይተላለፍ፡፡
መዝገቡ ተዘግቷል ወደ መዝገብ ቤት ይመለስ፡፡
የማይነበብ የሶስት ዳኞች ፊርማ አለበት
ፋ/ዘ
የልዩነት ሃሳብ
እኛ ስማችን በ2ኛ እና 5ኛ ተራ ቁጥር ላይ የተሰየምነዉ ዳኞች የዞኑ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ጉዳዩን በቀጥታ ክስ ተቀብሎ የማየት ስልጣን የለዉም የሚል ሃሳብ ስላለን የልዩነት ሃሳባችንን እንደሚከተለዉ አስፍረናል፡፡
ለክርክሩ ምክንያት የሆነዉ ጉዳይ የገጠር መሬትን የሚመለከት ነዉ፡፡ ከእርሻ መሬት ይዞታ መብት ጋር በተያያዘ የሚነሳ ክርክር ጉዳዩ በሚመለከታቸዉ ተከራካሪዎች በዉይይትና በስምምነት እንዲፈታ ጥረት የሚደረግ ስለመሆኑ እና በስምምነት ሊፈታ ካልቻለ በተከራካሪ ወገኖች በተመረጠ ሽምግልና ወይንም በክልሉ የገጠር መሬት አስተዳደር በተደነገገዉ መሠረት የሚወሰን ስለመሆኑ በፌዴራል መንግስት በወጣዉ የገጠር መሬት አስተዳደር እና አጠቃቀም አዋጅ ቁጥር 456/97 አንቀጽ 12 ስር ተመላክቷል፡፡ ከገጠር መሬት ጋር በተያያዘ የሚነሳ የይዞታ ይገባኛል ክርክር እልባት የሚያገኝበትን አግባብ የኦሮሚያ የገጠር መሬት አስተዳደር እና አጠቃቀም አዋጅ ቁጥር 130/99 ይደነግጋል፡፡ በዚህም መሠረት ክርክሮቹ በወረዳዉ ፍርድ ቤት ቀርበዉ ከመታየታቸዉ በፊት በግራ ቀኝ ስምምነት እና ቀጥሎም በሽምግልና መታየት የሚገባቸዉ ስለመሆኑ ከአዋጁ አንቀጽ 16 እንዲሁም አዋጁን ለማስፈጸም በወጣዉ ደንብ ቁጥር 151/2005 አንቀጽ 18 ላይ ተመልክቷል፡፡ ከገጠር መሬት ይዞታ መብት ጋር በተያያዘ የሚነሱ ክርክሮች በተቻለ መጠን በአካባቢዉ ሽማግሌ ካልሆነ ደግሞ ለወረዳዉ ፍርድ ቤት ቀርበዉ በመጀመሪያ መታየት እንዳለባቸዉ ከላይ በተመለከቱት የፌዴራል እና የኦሮሚያ ክልል የገጠር መሬት አስተዳደር እና አጠቃቀም አዋጆች የተደነገገበት መሠረታዊ ዓላማም በአርሶ አደሮች መካከል በእርሻ መሬት ይዞታ ምክንያት የሚነሱ አለመግባባት ጉዳዮች በቅርብ ታይተዉ በተቻለ መጠን ወደ ሙግት ሳይገባ እልባት እንዲሰጠዉ በማድረግ ወደ ሙግት የሚገባ ከሆነም ሙግቱ ቅርብ በሆነዉ በወረዳ ፍርድ ቤት እንዲታይ በማድረግ አርሶ አደሮች ከመሬት ይዞታ አጠቃቀም ጋር በተያያዘ ለምርት ስራ የሚያዉሉት ጊዜ እንዲሁም ገንዘብ ያላግባብ እንዳይባክን ጥበቃ ለማድረግ ነዉ ተብሎ ይታመናል፡፡ ከገጠር መሬት ጋር በተያያዘ ከሚቀርብ ዳኝነት ጋር በተያያዘ የሚነሳን የስልጣን ጥያቄ በመወሰን ረገድም ይህንኑ የአዋጁን ዓላማ ከግምት ዉስጥ በማስገባት ትርጓሜ መስጠት ያስገልጋል የሚል እምነት አለን፡፡
አብላጫዉ ድምጽ የዞኑ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ጉዳዩን ለማየት ስልጣን አለዉ በሚል ለደረሰበት ድምዳሜ የሰጠዉ መሠረታዊ ምክንያት የይዞታ ክርክር እና የአላባ ግምት አብረዉ በመቅረባቸዉ የተነሳ የፍርድ ቤት ስልጣን አከራካሪ የሆነ እንደሆነ የዳኝነት ስልጣን መወሰን የሚቻለዉ ከፍተኛ ግምት ያለዉን አቤቱታ መሠረት በማድረግ ስለመሆኑ በፍ/ብ/ሥ/ሥርዓት ህጉ አንቀጽ 17(2) ላይ የተመለከተዉን ድንጋጌ መሠረት በማድረግ መሆኑን እና የኦሮሚያ ክልል የገጠር መሬት አስተዳደር እና አጠቃቀም አዋጅም ይህን አስመልክቶ የተለየ ድንጋጌ የሌለዉ መሆኑን በመጥቀስ ነዉ፡፡ በእርግጥ ሁለት የተለያዩ ዳኝነቶች ተጣምረዉ በአንድ ላይ ሲቀርቡ የፍርድ ቤቱን ስልጣን ለመወሰን ከፍተኛ ግምት ያለዉን ዳኝነት መሠረት በማድረግ ነዉ የሚለዉን እኛም የምንስማማበት ነዉ፡፡ ይሁንና የሥ/ሥርዓት ህጉ በወጣበት ወቅት በነበረዉ የመንግስት አወቃቀር እና የፍርድ ቤቶች የስልጣን ድልድል መሠረት የማይንቀሳቀስ ንብረት (የማይንቀሳቀስ ንብረት መሬትን እንደሚያካትት በፍትሐብሔር ህጉ አንቀጽ 1130 ላይ ከተመለከተዉ መገንዘብ ይቻላል) እንደየአግባብነቱ ለወረዳ ፍርድ ቤት፣ ለአዉራጃ ፍርድ ቤት እና ለከፍተኛ ፍርድ ቤት ሊቀርብ እንደሚችል በፍ/ብ/ሥ/ሥርዓት ህጉ አንቀጽ 13፣ 14 እና 15 ላይ ከተመለከቱት ድንጋጌዎች መገንዘብ ይቻላል፡፡ ስለሆነም በየደረጃዉ ካሉት ፍርድ ቤቶች ጉዳዩን የማየት ስልጣን ያለዉ የትኛዉ ፍርድ ቤት እንደሆነ የሚወሰነዉ የንብረቱን ግምት ወይም ከንብረት ማስመለስ ጥያቄዉ ጋር አብሮ ተያይዞ የሚቀርብ የገንዘብ ጥያቄ (ለምሳሌ የማይንቀሳቀስ ንብረትን ለማስመለስ ከሚቀርብ ክስ ጋር ከንብረቱ የሚገኝ ጥቅም ወይም ዉዝፍ ኪራይ ወይም ከንብረቱ የሚገኘዉን ገቢ አጠቃሎ ማቅረብ እንደሚቻል ሰለሚደነግገዉ የፍ/ብ/ሥ/ሥርዓት ህጉ አንቀጽ 218 /ሀ/ ማየት ይቻላል) መሠረት በማድረግ ነዉ፡፡ ከላይ የተመለከተዉ የፍ/ብ/ሥ/ሥርዓት ህጉ አንቀጽ 17 (2) ድንጋጌም ይህንኑ እዉነታ መሠረት በማድረግ የተቀረጸ እንደሆነ ይታመናል፡፡
በሌላ በኩል፣ ከፍ ሲል እንደተመለከተዉ፣ ከእርሻ መሬት ጋር በተያያዘ የሚፈጠር አለመግባባት ቢቻል ከሙግት ዉጪ በአማራጭ በአገር ሽማግሌዎች እንዲታይ ካልሆነም ለወረዳ ፍርድ ቤት በመጀመሪያ መቅረብ እንዳለበት የክልሉ የገጠር መሬት አስተዳደር እና አጠቃቀም አዋጅ አስገዳጅነት ባለዉ ኃይለ ቃል በግልጽ የሚደነግግ በመሆኑ ከዳኝነት ስልጣን ጋር በተያያዘ በጠቅላላዉ በፍ/ብ/ሥ/ሥርዓት ህጉ ላይ የተመለከቱት ድንጋጌዎች ለተያዘዉ ጉዳይ ተፈፃሚነት አይኖራቸዉም፡፡ ይህም ማለት የእርሻ መሬትን የሚመለከት የዳኝነት ጥያቄ ከመሬቱ ከሚገኘዉ የአላባ ግምት ጭምር መቅረቡ እና የአላባዉ ግምት ከወረዳዉ ፍርድ ቤት ስልጣን በላይ ሆኖ መገኘቱ ዳኝነቱ በከፍተኛ ፍርድ ቤት እንዲታይ ምክንያት ሊሆን አይገባም ማለት ነዉ፡፡ ከአላባ ግምት ጋር ተጣምሮ በመቅረቡ ምክንያት ከገጠር መሬት ጋር ተያይዞ የሚቀርብ ክርክር ለዚህ ዓላማ በአዋጁ የተዘረጋዉን ሥርዓት ሳይከተል የቀረበዉን የገንዘብ ግምት ለማየት ስልጣን ላለዉ ለዞን ከፍተኛ ፍርድ ቤት እንዲቀርብ ማድረግ ከላይ የተመለከተዉን የአዋጁን ዓላማ የሚያፋልስ ዉጤት ይኖረዋል፡፡ በአዋጁ በተዘረጋዉ ስርዓት መሠረት ጉዳዩ እንዲታይ ካለመፈለግ በአላባ እያሳበቡ ጉዳዩ በቀጥታ በተለይም ለከፍተኛ ፍርድ ቤት እንዲቀርብ ለሚፈልጉ ሰዎችም በር የሚከፍት ሲሆን ይህም አዋጁ በዚህ ረገድ የዘረጋዉ ስርዓት ወጥነት ባለዉ መልኩ ተግባራዊ እንዳይሆን ምክንያት ይሆናል፡፡ ስለሆነም ምንም እንኳ በፍ/ብ/ሥ/ሥርዓት ህጉ ላይ ከስልጣን ጋር በተያያዘ የተመለከቱት መርሆዎች እንደየአግባብነታቸዉ ተፈፃሚ ሊሆኑ የሚችሉበት ሁኔት ቢኖርም፣ ከገጠር መሬት ጋር በተያያዘ የሚፈጠር አለመግባባት ለማየት ስልጣን ያላቸዉን አካላት አስመልክቶ አዋጁ በልዩ ሁኔታ የደነገገ በመሆኑ በፍ/ብ/ሥ/ሥርዓት ህጉ አንቀጽ 17(2) ላይ የተመለከተዉ ድንጋጌ ተፈፃሚነት ሊኖረዉ አይገባም፡፡
ይህ የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ሰበር ሰሚ ችሎትም ይህን ሁሉ ከግምት ዉስጥ በማስገባት እንዲሁም አጠቃላይ ከገጠር መሬት ጋር ተያይዞ የሚቀርብ የዳኝነት ጥያቄ የሚስተናገድበትን ሥርዓት አስመልክቶ በክልሉ አዋጅ ቁጥር 130/99 አንቀጽ 16 ላይ ከተመለከተዉ ድንጋጌ አጠቃላይ ዓላማ አንፃር አገናዝቦ ከመረመረ በኋላ ያላግባብ የተያዘ ገጠር መሬት እንዲመለስለት ክስ የሚያቀርብ ወገን ከመሬቱ ከሚገኝ የአላባ ግምት ጋር አጣምሮ ማቅረብ እንደሌለበት እና ፍርድ ቤትም ሊቀበለዉ እንደማይገባ በሰ/መ/ቁጥር 120087 (ቅጽ 21 ላይ እንደታተመዉ) ላይ የህግ ትርጉም ሰጥቷል፡፡ በሰ/መ/ቁጥር 108060 ላይም ተመሳሳይ ይዘት ያለዉ ዉሳኔ ሰጥቷል፡፡ ይህም የሚያሳየዉ በአላባ ግምት ሰበብ ከገጠር መሬት ጋር በተያያዘ የሚቀርብ ክርክር ይህንኑ አስመልክቶ በአዋጁ አንቀጽ 16 ላይ ከተዘረጋዉ ሥርዓት ዉጪ ሊሆን የማይገባዉ መሆኑን ነዉ፡፡
በመሆኑም የአሁን አመልካች ለክርክሩ መነሻ ከሆነዉ መሬት ላይ መብት አለኝ የሚል ከሆነ በቅድሚያ ጥያቄዉን በክልሉ የገጠር መሬት አዋጅ መሠረት በየደረጃዉ ባሉት አካላት አቅርቦ መብቱን ካረጋገጠ በኋላ የአላባ ጥያቄዉን ማቅረብ ሲገባዉ ይህን ባለማድረግ ዳኝነቱን ከአላባ ግምት ጋር በማጣመር ለዞኑ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ክስ ማቅረቡ ስህተት ሲሆን፣ የሆሮ ጉዱሩ ወለጋ ዞን ከፍተኛ ፍርድ ቤትም ይህን የአመልካችን ክስ ዉድቅ ማድረግ ሲገባዉ በአንድ በኩል ፍርድ ቤቱ ስልጣን የለዉም እያለ በሌላ በኩል ስልጣን ሲኖረዉ ብቻ የሚመረምረዉን የይርጋ ጉዳይ መሠረት በማድረግ ክሱ በይርጋ ይታገዳል የሚል እርስ በእርሱ የሚጋጭ ዉሳኔ መስጠቱ፤ የክልሉ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ይግባኝ ሰሚ እና ሰበር ሰሚ ችሎቶችም ይህን ማረም ሲገባቸዉ ያላግባብ (ስልጣን ለሌለዉ) ለዞኑ ከፍተኛ ፍርድ ቤት የቀረበዉን ክስ መሠረት በማድረግ ጉዳዩን በመመርመር የሰጡት ዉሳኔ ከገጠር መሬት ዳኝነት ጋር በተያያዘ በክልሉ የገጠር መሬት አዋጅ ላይ የተመለከተዉን አጠቃላይ ዓላማ የሚያፋልስ ከመሆኑም በላይ ይህ ሰበር ሰሚ ችሎት ከላይ በተመለከቱት መዛግብት ላይ የሰጠዉን አስገዳጅ የህግ ትርጉም ያላገናዘበ ሆኖ አግኝተነዋል፡፡ በዚህም ምክንያት በስር በየደረጃዉ ያሉ የክልሉ ፍርድ ቤቶች ዉሳኔ ሙሉ በሙሉ ሊሻር ይገባዋል በሚል ሃሳብ ከአብላጫዉ ድምጽ በሃሳብ ተለይተናል፡፡
የማይነበብ የሁለት ዳኞች ፊርማ አለበት
ፋ/ዘ