የኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዲሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ

የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት

ሰበር ሰሚ ችሎት

 የሠ//ቁጥር 201652

                                                                                                                                         ጥቅምት 05ቀን 2014 /

ዳኞች፡- ብርሃኑ አመነዉ

      ተሾመ ሽፈራዉ

          ሀብታሙ እርቅይሁን

        ብርሃኑ መንግሥቱ

   ነጻነት ተገኝ

አመልካቾች -1.  አቶ አባስ ሙሀመድ - ቀረቡ

 2. አቶ ሹሚ ቁንቢ - ቀረቡ

ተጠሪ - የኢትዮጵያ መድን ድርጅት - ጠበቃ የኋላወርቅ ፍሬው - ቀረቡ

መዝገቡ ተመርምሮ ከዚህ የሚከተለዉ የፍርድ ዉሳኔ ተሰጥቷል፡፡

ጉዳዩ የኢንሹራንስ ዳረጎት የሚመለከት ነዉ፡፡ ተጠሪ በአመልካቾች ላይ በፌዴራል መጀመሪያ ደረጃ ፍርድ በመሰረተዉ ክስ ንብረትነቱ 1 አመልካች የሆነ በሰሌዳ ቁጥር 0487 የሚታወቀዉ ተሽከርካሪ 2 ተጠሪ በፈጸሙት ጥፋት ተጠሪ የመድን ሽፋን የሰጠዉን የሰሌዳ ቁጥር 3-62699አአ የሆነ ተሽከርካሪ በቀን 01/11/2008/ በመግጨት ጉዳት አድርሷል፡፡ተጠሪ ለደንበኛዉ ባለበት የዉል ግዴታ መሰረት ጉዳት የደረሰበት ተሽከርካሪ አስጠግኖ ከጉዳት በፊት ወደ ነበረበት ይዘት ለመመለስ ብር 343,172.80 ወጪ አድርጓል፡፡በመሆኑም 1 አመልካች የጉዳት አድራሹ ተሽከርካረ ባለንብረት በመሆናቸዉና 2 ተጠሪ ጉዳቱን ያደረሰዉ ተሽከርካሪ አሽከርካሪ በመሆናቸዉ ተጠሪ ለጥገና ያወጣዉን ወጪ ከሕጋዊ ወለድ ጋር እንዲከፍሉ ይወሰንልኝ በማለት ዳኝነት ጠይቀዋል፡፡

አመልካቾች ለክሱ በሰጡት መልስ ፍርድ ቤቱ ጉዳዩን የመዳኘት ሥልጣን የለዉም የሚል እና ክሱ የቀረበዉ በሕግ የተደነገገዉ የይርጋ ጊዜ ካለፈ በኋላ ነዉ የሚሉ የመጀመሪያ ደረጃ መቃወሚያዎችን በማስቀደም ፍሬ ነገሩን በተመለከተ በሰጡት ዉሳኔ በተጠሪ ደንበኛ ተሽከርካሪ ላይ ለደረሰዉ ጉዳት አመልካቾች ጥፋት የለብንም፡፡የካሳዉም መጠን በባለሙያ ወይም በድርጅቱ ኮሚቴ ያልተረጋገጠ ስለሆነ አመልካቾች ባለንበት የጉዳቱ መጠን እና ወጪዉ ሊመረመር ይገባል በማለት መልሳቸዉን በመስጠት ተከራክረዋል፡፡

ፍርድ ቤቱም በመ/ቁጥር 271193 ላይ አስቀድሞ በመጀመሪያ ደረጃ መቃወሚያዎች ላይ በቀን 10/11/2011/ በሰጠዉ ብይን ዉድቅ ካደረገ በኋላ ፍሬ ነገሩን በተመለከተ የግራ ቀኙን ክርክርና ምስክሮች ሰምቶና ማስረጃዎችን መርምሮ በቀን 24/04/2012 / በሰጠው ውሳኔ በተጠሪ ደንበኛ ተሽከርካሪ ላይ ጉዳት ያደረሰዉ ንብረትነቱ 1 አመልካች የሆነና 2 ተጠሪ ሲሽከረከር የነበረ ተሽከርካሪ እንደሆነ በማስረጃ በመረጋገጡ ለደረሰዉ ጉዳት 1 ተጠሪ በፍ//ሕግ ቁጥር 2081 መሰረት ጥፋት ላይ ያልተመሰረተ ኃላፊነት አለበት፡፡እንዲሁም 2 ተጠሪ ደግሞ በፍ//ሕግ ቁጥር 2028 እና 2082/2 በጥፋት ላይ የተመሰረተ ኃላፊነት አለባቸዉ በማለት ወስኗል፡፡ተጠሪ የደንበኛዉን ተሽከርካሪ ለማስጠገን የሚያስፈልገዉን ወጪና የጉዳቱን መጠን በባለሙያ እና በገለልተኛ ተጫራቾች አጣርቶ ክስ የተመሰረተበትን ወጪ ማዉጣቱ በማስረጃ ስለተረጋገጠ ተጠሪ በደንበኛዉ ተሽከርካሪ ላይ የደረሰዉን ጉዳት ለማስጠገን ያወጣዉን ወጪ ብር 343,172.80 9% ሕጋዊ ወለድ ጋር በክሱ ምክንያት ተጠሪ ላወጣዉ ወጪ ብር 23,104.84 አመልካቾች በአንድነትና በነጠላ ኃላፊነት ለጠሪ እንዲከፍሉ ወስኗል፡፡አመልካቾች በዚህ ዉሳኔ ቅር በመሰኘት ይግባኝ ለፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ቢያቀርቡም ፍርድ ቤቱ በመ/ቁጥር 254343 ላይ በቀን 24/02/2013/ በሰጠዉ ትእዛዝ በፍ////ሕግ ቁጥር 337 መሰረት ሰርዞባቸዋል፡፡

አመልካቾች በቀን 24/05/2013 / የተጻፈ የሰበር አቤቱታ ያቀረቡት ተጠሪ አወጣሁኝ ያለዉ ወጪ በባለሙያ ወይም በመንግስት ድርጅት ያልተጣራ ስለሆነ ዉድቅ ይደረግልን በማለት ላቀረብነዉ ተቃዉሞ ብይን ሳይሰጥ ከትራንስፖርት ባለስልጣን ማስረጃ ሳይቀርብ ከግል ጋራዥ የተሰበሰበዉን የዋጋ መጠን መሰረት አድርጎ ዉሳኔ መስጠቱ ሊታረም የሚገባዉ ስህተት ነዉ፡፡ ድርጊቱ የተፈጸመዉ በቀን 01/11/2008/ ሆኖ ክሱ በቀን 01/08/2011/ ስለቀረበ ክስ የማቅረብ መብቱ በይርጋ የታገደ ነዉ በማለት ያቀረብነዉን መቃወሚያ የሥር ፍርድ ቤት አለአግባብ ዉድቅ በማድረግ ወስኗል፡፡በፍ////ሕግ ቁጥር 19 እና 27 መሰረት ከዉል ዉጪ የሚከሰቱ ጉዳዮች ሁሉ መታየት ያለባቸዉ ድርጊቱ በተፈጸመበት ቦታ በሚያስችለዉ ፍርድ ቤት እንደሆነ ተደንግጎ እያለ በአርሲ ዞን ሄጦሳ ወረዳ ደያአ ቀበሌ ገበሬ ማኅበር ዉስጥ የተፈጸመዉን ድርጊት መነሻ ያደረገዉን ክስ የፌዴራል መጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት የመዳኘት ሥልጣን የለዉም በማለት ያቀረብነዉን መቃወሚያ አለግባብ ዉድቅ ማድረጉ መሰረታዊ የሕግ ስህተት ነዉ፡፡እንዲሁም የተጠሪ ደንበኛ ተሽከርካሪ ጉዳት የደረሰበት በፍጥነት ምክንያት መሆኑን የቴክኒክ ዉጤት የሚያሳይ ቢሆንም የትኛዉ ተሽከርካሪ ፍጥነት ላይ እንደሆነ ዉጤቱ የማይገልጽና የአመልካቾች ትራክተር በባህሪዉ በዝግታ የሚጓዝ መሆኑን ፍርድ ቤቱ ግንዛቤ ዉስጥ ሳያስገባና ማስረጃ በአግባቡ ሳይመዝን የሰጠዉ ዉሳኔ መሰረታዊ የሕግ ስህተት የተፈጸመበት ስለሆነ ይታረምልን በማለት አቤቱታቸዉን አቅርበዋል፡፡

የሰበር አጣሪ ችሎት አቤቱታውን መርምሮ በስር የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት ተጠሪ ለአመልካቾች ብር 47,078.00 ቢቀነስላቸዉ ተቃዉሞ የለኝም በሚል አስመዝግቦ እያለ ቤቱ ይሕንን ገንዘብ ሳይቀንስ የወሰነበትን አግባብ ተጠሪ ባለበት እንዲመረመር ትዕዛዝ በመስጠቱ ተጠሪ በቀን 22/07/2013 / የተፃፈ መልስ በማቅረብ ተጠሪ የጉዳት መጠን በተመለከተ በራሱ ሰርቪየር ከማስገመቱም በላይ በጨረታ አስወስኖ በዝቅተኛ ዋጋ ስላስጠገነ አሰራሩ ሕግን መሰረት ያደረገ ነዉ፡፡2 ተጠሪ በፈጸሙት ጥፋት በደንብ መተላለፍ በመቀጣታቸዉ ተረጋገጥ የይርጋ መቃወሚያ ዉድቅ መደረጉ በአግባቡ ነዉ፡፡ተጠሪ በፌዴራል መንግስት የተመዘገበና የፌዴራል መንግስት መስሪያ ቤት ስለሆነ ጉዳዩ በፌዴራል ፍርድ ቤት ታይቶ በመወሰኑ የተፈጸመ ስህተት የለም፡፡እንዲሁም የሥር ፍርድ ቤቶች ጉዳዩን በማስረጃ አጣርተዉና መዝነዉ ስለወሰኑ የማስረጃ ምዘና ጉዳይ እንደመሰረታዊ የሕግ ስህተት ሊቆጠር የሚገባ ባለመሆኑ የተፈጸመ ስህተት የለም ተብሎ የአመልካቾች የሰበር አቤቱታ ዉድቅ ይደረግልኝ በማለት ተከራክሯል፡፡አመልካቾችም በቀን 29/07/2013/ የተጻፈ የመልስ መልስ በማቅረብ ተከራክረዋል፡፡

ከዚህ በላይ አጠር ባለ መልኩ የተመለከተዉ የግራ ቀኝ ክርክርና በስር ፍርድ ቤቶች የተሰጡ ዉሳኔዎች ይዘት ሲሆን እኛም ሰበር አጣሪ ችሎት ጉዳዩ ለሰበር ችሎት ያስቀርባል ሲል የያዘዉን ጭብጥ በመለወጥ የሥር ፍርድ ቤት ጉዳዩን የመዳኘት ሥልጣን የለዉም ተብሎ የቀረበዉን መቃወሚያ ዉድቅ በማድረግ በመወሰኑ የተፈጸመ መሰረታዊ የሕግ ስህተት መኖር አለመኖሩን አግባብነት ካለዉ ሕግ ጋር በማገናዘብ እንደሚከተለዉ መርምረናል፡፡

እንደመረመርነው በተጠሪ የቀረበው ክስ ንብረትነቱ 1 አመልካች የሆነ ተሽከርካሪ 2 አመልካች ሲሽከረከር በነበረበት ጊዜ በኦሮሚያክል አርሲ ዞን ሄጦሳ ወረዳ ደያአ ቀበሌ ገበሬ ማኅበር ዉስጥ በተጠሪ የመድን ሽፋን የሰጠዉን የሰሌዳ ቁጥር 3-62699አአ የሆነ ተሽከርካሪ ገጭቶ ጉዳት በማድረሱ ተጠሪ የደንበኛዉን ተሽከርካሪ ለማስጠገን ያወጣዉን ወጪ ብር 343,172.80 ለማስከፈል ዳኝነት የተጠየቀበት ነዉ፡፡ ጉዳቱ የተከሠተው በኦሮሚያ ክልል ውስጥ ስለሆነና ተጠሪ በፌዴራል መንግሥት የተመዘገበ የንግድ ድርጅት ከመሆኑ አኳያ፤ ሊመረመር የሚገባው ጭብጥ ክሱ የክልል ፍርድ ቤት በውክልና ሊመለከተው የሚችል የፌዴራል ጉዳይ ነው ወይስ በፌዴራል ፍርድ ቤት የሚታይ ክርክር ነው የሚለውን የሚመለከት ነው፡፡

በኢፌዲሪ ሕገ-መንግሥት አንቀጽ 78/2 መሠረት የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት 2/3 ድምጽ የፌዴራል  ከፍተኛ ፍርድ ቤት ሆነ የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት እንዲደራጅ እስካልወሰነ ድረስ የፌዴራል  ከፍተኛና የፌዴራል  የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤቶች ሥልጣን በውክልና ለክልል ፍርድ ቤቶች ተሰጥቷል፡፡ ምላሽ የሚያስፈልገው ጉዳይ በውክልና በተሠጠ ሥልጣን ላይ የፌዴራል  ፍርድ ቤቶች ጉዳዩን የማየት ሥልጣን አላቸው ወይስ የላቸውም? የሚለው ጉዳይ ነው፡፡ ክርክሩን በፍትሐ ብሔር ሥነ-ሥርዓት ሕጉ መሰረት መምራት እና መቆጣጠር የፍርድ ቤቱ ኃላፊነት ሲሆን በዚህ ሂደት ከሚመረምራቸው ጉዳዮች መካከል ጉዳዩ ላይ ለመወሰን ሥልጣን ያለው መሆን አለመሆኑ ዋነኛው ነው፡፡ የፍርድ ቤት ሥልጣን ብሔራዊ የመዳኘት ሥልጣን (judicial jurisdiction) የሥረ-ነገር ሥልጣን (material jurisdiction) እና የግዛት ወይም አካባቢያዊ ሥልጣን (local or territorial jurisdiction) በሚል የተከፋፈለ ነው፡፡ ብሔራዊ የመዳኘት ሥልጣን ከሀገሮች ሉዓላዊነት፣ የሚሠጠው ፍርድ በሌሎች ሀገሮች ዕውቅና ሊሠጠውና ሊፈጸም የሚችል መሆን አለመሆኑ እና ከተከሳሽ መብት ጋር የተያያዘ መሠረቱ ዓለምአቀፍ ሕግና የታወቁ የሕግ መርሆዎች ሆኖ የአንድ ሀገር ፍርድ ቤት ጉዳዩን ለመመልከት ከተከሳሹ ወይም የክርክሩ ምክንያት የሆነው ተግባር ከተፈጸመበት ወይም አከራካሪ የሆነው ንብረት ከሚገኝበት ቦታ ጋር በቂ የሆነ ግንኙነት ያለው ሆኖ ሲገኝ  ወይም ተከሳሽ የሆነው ወገን በሀገሪቱ ፍርድ ቤቶች ለመዳኘት ያለው ፈቃድ ላይ መሠረት በማድረግ የሚወሰን ነው፡፡ የሥረ-ነገር ሥልጣን በአንድ ሀገር ጉዳዩን ለመዳኘት ሥልጣን ባላቸው ፍርድ ቤቶች መካከል በዋነኛነት ታሳቢ የሚያደርገው የፍርድ ቤቱን አቅም ወይም ችሎታ (competence of the court) ፍትሐዊነትን፣ ኢኮኖሚንና የሥራና ሀብት ክፍፍልን መሠረት አድርጎ በገንዘብ ግምት (pecuniary jurisdiction) ወይም በጉዳዩ ዓይነት (subject matter jurisdiction) ወይም ጉዳዩን በመጀመሪያ ሆነ በይግባኝ ደረጃ (original and appellate jurisdiction) የሚያዩት ሥለመሆኑ በፍርድ ቤቶች መካከል የሚመለከቱት ጉዳዩችን የሥልጣን ድልድል የሚደረግበት ነው፡፡ የግዛት ክልል ሥልጣን ደግሞ አንድን  ጉዳይ ተቀብሎ ለመስማት እና ለመወሰን ዐቅም ካላቸው ፍርድ ቤቶች መካከል በየትኛው ፍርድ ቤት ቀርቦ መታየት እንዳለበት የሚያመለክት ነው፡፡ ያስፈለገበትም ዓላማም ተመሳሳይ የሥረ-ነገር ሥልጣን ያላቸው ግን በተለያዩ ማስቻያ ቦታ ላይ በሚያስችሉ ፍርድ ቤቶች መካከል ለዜጎች ፍትሕ የማግኘት መብትን በቅርብ ለማረጋገጥና ለተከራካሪ ወገኖች ይልቁንም ለተከሳሹና ለምስክሮቹ ምቹ ሁኔታ ለመፍጠር ሲባል ነው፡፡ ሥልጣኑም በተከራካሪዎች አድራሻ፣ ንብረቱ በሚገኝበት ቦታ፣ ውሉ በተመሠረተበት ወይም በሚፈፀምበት ወይም ጉዳቱ በደረሠበት ቦታ ወይም ተመሳሳይ ምክንያቶችን በመያዝ የሚመለከቷቸውን ጉዳዮች የሚለዩበት ነው፡፡ ይህ ይሄኛዉ አይነት የዳኝነት ሥልጣን በፍትሐ ብሔር ሥነ ሥርዓት ሕጉ የተደነገገበት አግባብ በወቅቱ የነበረዉን ሥርዓትና የፍርድ ቤቶች የሥልጣን ክፍፍል መሰረት ተደርጎ አገራችን በሕገ መንግስቱ የተዘረጋዉን የፌዴራል ሥርዓት ከመከተሏ በፊት ተግባራዊ ሲሆን የነበረ በመሆኑ አሁን ከምንከተለዉ የፌዴራል ሥርዓት ጋር ተገናዝቦ መታየት ያለበት ነዉ፡፡ ፌዴራል

ኢትዮጵያ የፌዴራል  የመንግሥት አወቃቀር ሥርዓትን 1987 / በወጣው የኢፌዲሪ ሕገ-መንግሥት መከተሏን ተከትሎ ሥልጣን በክልሎችና በፌዴራል መንግሥት የተከፋፈለ ስለመሆኑ በሕገ-መንግሥቱ ከአንቀጽ 50-52 ላይ ተመልክቷል፡፡ በዚህም ክልሎች በሥልጣናቸው ሥር ባሉ ጉዳዮች ሉዓላዊ ሥልጣን አላቸው፡፡ ክልሎች እንደ ፌዴራል መንግሥት ሕግ-አውጪ፣ ሕግ አስፈጻሚና የዳኝነት አካል ያደራጃሉ፡፡ በኢፌዲሪ ሕገ-መንግሥት አንቀጽ 78 መሠረት የዳኝነት አካሉ በፌዴራል እና በክልል መንግሥት ደረጃ መቋቋሙ እና በአንቀጽ 80(1)(2) ላይ በፌዴራል ጉዳዮች የፌዴራል  ፍርድ ቤት፤ በክልላዊ ጉዳዮች የክልል ፍርድ ቤት የመጨረሻ ሥልጣን ያለው መሆኑ መመልከቱ በፌዴራልና በክልል መንግሥታት መካከል የፍርድ ቤት የሥልጣን ክፍፍል እንዳለ ያሳያል፡፡ የፌዴራል  ወይም የክልል ጉዳዮች የሚለው በጉዳይ ዓይነት የተከፋፈለ ሥልጣን ስለሆነ የፍርድ ቤቶች ሥልጣን የተለየው የሥረ-ነገር ሥልጣንን መሠረት ያደረገ ቢመስልም ጉዳዩ ከሉዓላዊ ሥልጣን እና ክልላዊ ጉዳይ በፌዴራል ፍርድ ቤት ቢታይ ከጣልቃገብነት ጋር የተያያዘ በመሆኑ ጉዳዩ የብሔራዊ ዳኝነት ሥልጣንን የሚያስነሳ ነው፡፡ በፌዴራል  መዋቅር የብሔራዊ የዳኝነት ሥልጣን መሠረቱ ዓለምአቀፍ ሕግ ሳይሆን ሕገ-መንግሥት ነው፡፡ ሕገ-መንግሥቱ የፌዴራልና የክልል ፍርድ ቤቶች ያቋቋመና አንዱ የሌላዉን ሥልጣን አክብረው ለማስከበርም ግዴታ የጣለ ነው፡፡ይህንን ጉዳይ ከአለም አቀፍ አጠቃላይ መርሆዎች አንጻር ሳይሆን በፌዴራልና በክልል መንግሥታት መካከል ከሚኖረዉ ግንኙነት አንጻር አጥበን ያየን እንደሆነ በአንድ ሀገር ያሉና በሕገ-መንግሥቱ የሕግ የበላይነትን በማረጋገጥ አንድ የኢኮኖሚና የፖለቲካ ማሕብረሰብ ለመፍጠር በሚሠሩ ተቋማትና ዜጎች ላይ፣ የተለያየ ሥልጣን ቢሆንም የጋራ የሆኑ ጉዳዮች ደግሞ ባላቸው ተቋማት መካከል የሚነሳ ስለሆነ የተለየ ያደርገዋል፡፡ ይኸዉም በፌዴራል መዋቅር የፌዴራል መንግሥት ሉዓላዊነቱ በመላው የኢትዮጵያ ግዛት ነው፡፡ ነገር ግን በግዛቱ ሥር ሁሉንም በፈቃዱ መወሰንና መፈጸም የሚችል ሳይሆን በግልጽ በሕግ በተዘረጋው ሥርዓት ሥልጣኑን የሚጠቀም መሆኑን የሚመለከት ነው፡፡ ለክልል ፍርድ ቤት ሥልጣን መሠረቱ ግን በግዛት ክልል ሥር ያለ ሠውና ንብረት መሆን አለመሆኑን መሠረት ያደረገ (limited sovereignty) ነው፡፡

በሕገ-መንግሥቱ የሥልጣን ክፍፍሉም የክልል ከፍተኛና ጠቅላይ ፍርድ ቤቶች የፌዴራል ጉዳዮችን በውክልና ማየት የሚችሉ ሲሆን ክልላዊ ጉዳዮች በክልሎች ሉዓላዊ ሥልጣን ክልል ውስጥ (exclusive jurisdiction of state courts) ያለ በመሆኑ፤ በሕገ-መንግሥቱ አንቀጽ 80(3/) ለፌዴራል  ጠቅላይ ፍርድ ቤት ሠበር ሰሚ ችሎት የተሠጠው ሥልጣን እንደተጠበቀ ሆኖ፤ የፌዴራል  ፍርድ ቤቶች ማየት አይችሉም፡፡ ይሕም ክልላዊ ጉዳዮች ላይ የፌዴራል ፍርድ ቤቶች የመዳኘት ሥልጣን (judicial jurisdiction) የሌላቸው መሆኑን ሲያሳይ በውክልና እና በጣምራ ሥልጣናቸው ከሚመለከቱት በሥተቀር የክልል ፍርድ ቤቶች የፌዴራል  ጉዳዮችን ማየት አይችሉም፡፡ ከዚህ ጋር ተያይዞ መመርመር ያለበት በሕገ-መንግሥቱ የተመለከተው የፍርድ ቤቶች የጣምራነት ሥልጣን (concurrent jurisdiction) እና የፌዴራል ጉዳዮች የሚወሰኑበት ሥርዓት ነው፡፡ የፌዴራል ጉዳዩች ምን እንደሆኑ በሕገ-መንግሥቱ ያልተወሰነ ቢሆንም በፌዴራል ፍርድ ቤቶች አዋጅ ቁጥር 25/1988 አንቀጽ 3 መሠረት የፌዴራል  ጉዳዮች ሕገ-መንግሥቱን፣ የፌዴራል  መንግሥት ሕጎችንና ዓለም አቀፍ ሥምምነቶችን መሠረት ያደረጉ ጉዳዮች (based on laws) በፌዴራል  ሕግ ተገልጸው በተወሰኑ ባለጉዳዮች (parties) እና በሕግ በተገለጹ ቦታዎች (places) ላይ የሚነሱ ጉዳዮች ናቸው፡፡ በፌዴራል  ፍርድ ቤቶች አዋጅ ቁጥር 25/1988 አንቀጽ 4 እና 5 መሠረት የተዘረዘሩት የፌዴራል ፍርድ ቤት በብቸኝነት ሥልጣኑ የሚመለከታቸው ሕግንና ባለጉዳዮችን መሠረት አድርጎ የተለዩ የፌዴራል ጉዳዮች ሲሆን በሌሎች ሕጎች በግልፅ ለፌዴራል ፍርድ ቤት የተሠጡ ጉዳዮችን ይጨምራል፡፡ የአዋጁን አንቀጽ 11 እና ተከታዮችን ሥንመለከት ደግሞ ቦታን መሠረት በማድረግ አዲስ አበባና ድሬዳዋ ከተሞች ላይ የሚነሡ ጉዳዮች የፌዴራል ፍርድ ቤት የሚመለከታቸው የፌዴራል ጉዳዮች እንደሆኑ ተደንግጓል፡፡

በፌዴራል ፍርድ ቤቶች አዋጅ ቁጥር 25/1988 አንቀጽ 3 መሠረት ሕግን መሠረት አድርጎ የተለዩት የፌዴራል ጉዳዮች ውስጥ የፌዴራል መንግሥት ሕጎችን መሠረት ያደረጉ ጉዳዮች ያሉበት በመሆኑና በአዋጁ የትርጉም ክፍል አንቀጽ 2/3 ላይ የፌዴራል  መንግሥት ሕጎች ማለት በሕግ በተሠጠው ሥልጣኑ ክልል ሥር ያሉ ነባር ሕጎችን የሚጨመር መሆኑ ሲታይ በሕግ በግልጽ የፌዴራል ፍርድ ቤት ሥልጣን ሥር ከተመለከቱት ሕግን መሠረት ያደረጉ ጉዳዮች እና በፌዴራል ሥልጣን ሥር እንዲታዩ ከተወሰኑት ባለጉዳዮች ውጭ ያሉ የፌዴራል ሕግን መሠረት ያደረጉ ጉዳዮች የፌዴራልና የክልል ፍርድ ቤቶች በጣምራ ሥልጣናቸው የሚመለከቷቸው ናቸው፡፡ ሥለሆነም የፌዴራል ሕግን መሠረት ያደረጉ ሌሎች ጉዳዮች እንደተነሱበት ቦታ የፌዴራል ፍርድ ቤት ወይም የክልል ፍርድ ቤት በክልላዊ ሥልጣኑ ሊመለከተው ይችላል፡፡

በሕገ መንግስቱ በአገራችን የተዘረጋዉን የፌዴራል ሥርዓት መሠረት ተደርጎ የተዋቀረው የዳኝነት ሥልጣን የፌዴራል እና የክልል ፍርድ ቤቶች ካላቸው የጣምራነት ሥልጣን ባለፈ በሕገ-መንግሥቱ አንቀጽ 78/2 እና 80(4-6) የፌዴራል ፍርድ ቤት በብቸኝነት ሥልጣኑ የሚመለከታቸውን ጉዳዮች የክልል ጠቅላይና ከፍተኛ ፍርድ ቤቶች በውክልና እንዲመለከቱ ሥልጣን ሰጥቷል፡፡ ይህም ሕገ-መንግሥቱ የክልል ፍርድ ቤቶችን ማብቃትን (empowerment)፣ተደራሽነትን፣ የክልሎችን ተሳትፎ ማሳደግ ላይ ዓላማ ያለውና ተቋሞቻቸው ላይ አመኔታ ያለው መሆኑን ያረጋግጣል፡፡ በሕገ-መንግሥቱ የዳኝነት አካል በፌዴራልና በክልል ደረጃ በየእርከኑ መዋቀሩ ሲታይ አደረጃጀቱ በተዋረድ ያለ የትይዩ አቀራረጽ (dual system) ያለው ቢሆንም የፌዴራልና የክልል ጉዳይን የክልል ፍርድ ቤቶች መመልከታቸው የተደባለቀ (integrated system) እንደሚከተልም ያሳያል፡፡

የክልል ፍርድ ቤቶች በጣምራ ሥልጣናቸው በክልል ግዛታቸው የተነሱ ጉዳዮች የመመልከት ሥልጣን ያላቸው በመሆኑ የፌዴራል ፍርድ ቤት ጉዳዩን የማየት ሥልጣን አይኖረውም፡፡ ጉዳዩ በክልል ፍርድ ቤት የሚታየው ጉዳዩ የተነሳበትን ቦታና ተከራካሪውን መሠረት በማድረግ ነው፡፡ የጣምራነት ሥልጣን መሠረቱ የፌዴራል መንግሥት ሕግን መሠረት ያደረገ የፌዴራል ጉዳይ በመሆኑ የፌዴራል ፍርድ ቤት በፌዴራል  ጉዳይ ላይ ብሔራዊ የመዳኘት ሥልጣን የለውም ሊባል አይችልም፡፡ ነገር ግን በፌዴራል ፍርድ ቤት አዋጅ ቁጥር 25/1988 አቀራረጽ መሠረት ከተለዩት ውስን የፌዴራል  ፍርድ ቤት ሥልጣኖች ውጭ ያሉ በክልል ግዛት የሚነሱ ጉዳዮችን የክልል ፍርድ ቤቶች እንዲመለከቷቸው የተተወ በመሆኑ ጉዳዩ የሥረ-ነገር ሥልጣን ጥያቄ የሚያስነሳ ይሆናል፡፡

በተመሳሳይ የክልል ፍርድ ቤቶች በፌዴራል  ፍርድ ቤት በብቸኝነት እንዲታዩ የተለዩ ጉዳዮችን (exclusive jurisdiction) በግዛታቸው በተከሠቱ ጉዳዮች፣ ባሉ ሠዎቸ ወይም ንብረቶች ጋር የሚነሱ ሲሆን በውክልና (delegation) እንዲመለከቱ በሕገ-መንግሥት ሥልጣን ተሰጥቷቸዋል፡፡ በክልል የሚነሱ የፌዴራል ጉዳዮች ላይ ጉዳዩ የፌዴራል  በመሆኑ የፌዴራል ፍርድ ቤቶች ብሔራዊ የመዳኘት ሥልጣን አላቸው፡፡ በፌዴራል  ፍርድ ቤት አዋጅ ቁጥር 25/1988 አንቀጽ 4 እና 5 የተመለከቱት የፌዴራል ጉዳዮችን በተከታዮቹ ድንጋጌዎች ለፌዴራል ፍርድ ቤቶች የሥረ-ነገር ሥልጣናቸውን ያከፋፈለ በመሆኑ ይህ ሕግ መሠረት ተደርጎ ሲታይ የፌዴራል ፍርድ ቤት ጉዳዩን ለመዳኘት የሥረ-ነገር ሥልጣን እንዳለው ያሳያል፡፡ የአፋር፣ የቤንሻንጉል/ጉሙዝ፣ ጋምቤላ፣ ሶማሌና የደቡብ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ክልሎች በሕገ-መንግሥቱ ያላቸው የፌዴራል  ከፍተኛ ፍርድ ቤትን ሥልጣን በውክልና በክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት የማየት ሥልጣን በፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ማደራጃ አዋጅ ቁጥር 322/1995 ሲነሳ በእነዚህ ክልሎች የፌዴራል  ክፍተኛ ፍርድ ቤት መደራጀቱ ታወጀ እንጂ በአምስቱ ክልሎች ግዛቶች የሚነሱ ጉዳዮችን የመመልከት የሥረ-ሥልጣን እንደ አዲስ ለፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት አለመሠጠቱ ቀድሞውንም በፌዴራል ፍርድ ቤቶች አዋጅ ቁጥር 25/1988 መሠረት የሥረ-ነገር ሥልጣን ተወስኖ ያደረ መሆኑን ያረጋግጣል፡፡ የፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ከአዲስ አበባና ድሬዳዋ ከተሞች ውጭ በእነዚህ ክልሎች ሲደራጅ የማስቻያ ቦታው የተወሰነ በመሆኑ ጉዳዮችን ለማየት የግዛት ክልል ሥልጣን ያገኛል፡፡ ይሕም የክልል ፍርድ ቤቶች በግዛታቸው ባሉ ሰዎቸ ወይም ንብረቶች ጋር የሚነሳ በውክልና የሚመለከቱትን የፌዴራል ጉዳይ ውክልናቸው ሳይነሳ ጉዳዩ ለፌዴራል ፍርድ ቤት ቀርቦ ከታየ የግዛት ክልል ሥልጣን ክርክር የሚያስነሳ መሆኑን ያስገነዝባል፡፡

ነገር ግን በፍትሐ ብሔር ሥነ-ሥርዓት ሕጉ ከተመለከተው የግዛት ክልል የተለየ ውጤት ያለው ነው፡፡ ሥነ-ሥርዓት ሕጉ በሚቀረጽበት ጊዜ የፌዴራል ሥርዓት አወቃቀር ባለመኖሩ ተመሳሳይ የሥረ-ነገር ሥልጣን ያላቸው ፍርድ ቤቶች በተለያዩ የፌዴራልና የክልል መንግሥታት ሥልጣን ክልል ውስጥ በሚሆንበት ጊዜ የሚያስነሳውን ክርክር የሚመለስ አይደለም፡፡ የሥነ-ሥርዓት ሕጉ አቀራረጽም ከፌዴራል  ሥርዓቱ ጋር ተጣጥሞ መተርጎም ይኖርበታል፡፡ ጉዳዩ በሥነ-ሥርዓት ሕጉ እንደተቀረጸው የግዛት ክልል ሥልጣን በዋነኛነት አመቺነትን ብቻ መሠረት ያደረገ ነው፤ አመቺ እስከሆነ ድረስ በፌዴራል  ፍርድ ቤት ሊታይ ይችላል ከተባለ፤ በሕገ-መንግሥቱ የክልል ፍርድ ቤቶች ውክልና ሊነሳ የሚችለው በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት 2/3 ድምጽ ብቻ ስለመሆኑ በአንቀጽ 78/2 ላይ የተመለከተውን በመተላለፍ፤ የክልል ፍርድ ቤቶች በሕገ-መንግሥቱ የተሠጣቸውን የውክልና ሥልጣን በሕጉ በተገለጸው አግባብ ሳይነሳ በፍርድ ቤቶች ውክልናውን የማንሳት ውጤት ያስከትላል፡፡ ሕገ- መንግሥቱ የፌዴራል ጉዳይን በውክልና በክልል ፍርድ ቤቶች እንዲታይ የወሰነበትንና ሊያሳካው የፈለገውን ዓላማና ግብ ላይ እንዳይደርስ ያደርጋል፡፡

በተጨማሪም ጉዳዩን የሚመለከተው ፍርድ ቤት ሥልጣን የሚወሰነው በሕግ ሆኖ እያለ በክልል ፍርድ ቤት በውክልና ሊታይ የሚችል ሥልጣን በፌዴራል  ፍርድ ቤት የሚቀርብ ከሆነ ተከራካሪዎች ክሱን የሚያቀርቡበት ፍርድ ቤት፤ የፌዴራል ወይስ የክልል ፍርድ ቤት ስለመሆኑ በራሳቸው ምርጫ እንዲያቀርቡ (forum shopping) የሚያደርግ ተገቢ ያልሆነ የዳኝነት አሠጣጥ ሥርዓት እንዲፈጠር ዕድል ይሠጣል፡፡ ስለሆነም በእነዚህ ምክንያቶች የክልል ጠቅላይና ከፍተኛ ፍርድ ቤቶች በሕገ-መንግሥቱ የፌዴራል ጉዳዮችን በውክልና እንዲመለከቱ የተሠጣቸው ሥልጣን መሠረቱ የፌዴራል አወቃቀር በመሆኑ ውክልናቸው በሕግ እስካልተነሳ ድረስ ጉዳዮቹ ለፌዴራል ፍርድ ቤት ሊቀርቡ አይችሉም፡፡ ጉዳዮቹ ቀርበው በፌዴራል ፍርድ ቤቶች ከታዩ ውጤቱም አስገዳጅነት ያለውን የፍርድ ቤት ሥልጣን ክፍፍል የሚጥስ ስለሆነ ጉዳዩ በየትኛውም ደረጃ ፍርድ ቤት ሲደርስ በተከራካሪዎች ሆነ በፍርድ ቤቱ የሥልጣን ጥያቄው ተነስቶ ክሱ ውድቅ ሊደረግ የሚገባው ነው፡፡

ወደያዝነው ጉዳይ ስንመለስ ክሱ መሠረት ያደረገው ከውል ውጭ ኃላፊነትን ሲሆን ጉዳት የደረሠበት ቦታ ኦሮሚያ ክልል አርሲ ዞን ሄጦሳ ወረዳ ደያአ ቀበሌ ገበሬ ማኅበር ዉስጥ ነው፡፡ በሚንቀሳቀስ ንብረት ላይ ጉዳት በደረሰ ጊዜ ክሱ የሚቀርበው ጉዳቱ በደረሰበት ሥፍራ በሚገኝ ፍርድ ቤት መሆኑን ስለግዛት ክልል የሚደነግገው የፍ////ሕግ ቁጥር 27/1 ላይ ተመልክቷል፡፡ ይሕም ክሱ ኦሮሚያ ክልል ፍርድ ቤት እንደሚታይ ያስረዳል፡፡ በሌላ በኩል የተከራካሪዎችን ማንነት ስንመለከት ተጠሪ በፌዴራል መንግሥቱ የተመዘገበና የፌዴራል መንግስት የልማት ድርጅት መሆኑ በፌዴራል ፍርድ ቤቶች አዋጅ ቁጥር 25/1988 አንቀጽ 5/6 መሠረት ጉዳዩን የመዳኘት ሥልጣን ያለው የፌዴራል ፍርድ ቤት ስለመሆኑ ያስገነዝባል፡፡ ይህ ምክንያት ጉዳዩን የፌዴራል ጉዳይ የሚያደርገዉ ቢሆንም ከዉል ዉጭ ኃላፊነትን ያስከትላል የተባለዉ ድርጊት ተከስቶ ጉዳቱ የደረሰዉ በኦሮሚያ ክልል በመሆኑ በሕገ-መንግሥቱ በተሠጠው ውክልና እና በስረ ነገር ዳኝነት ሥልጣን ክፍፍል መሠረት ጉዳዩ መታየት ያለበት በክልሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ነው፡፡

ሲጠቃለል የስር ፍርድ ቤት ጉዳዩን የመዳኘት ሥልጣን እንደሌለዉ ተጠቅሶ በአመልካቾች የቀረበዉን መቃወሚያ ከላይ በዝርዝር ከተመለከተዉ አንጻር በማየት ጉዳዩን ተቀብሎ መዳኘት የክልል ፍርድ ቤቶች የፌዴራል ጉዳይ በዉክልና እንዲዳኙ በሕገ-መንግስቱ የተዘረጋዉን የፍርድ ቤት ሥልጣን ክፍፍል የሚጥስ ስለሆነ ጉዳዩን በዉክልና የመዳኘት ሥልጣን የክልሉ የሚመለከተዉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ነዉ በማለት መወሰን ሲገባዉ ጉዳዩን ተቀብሎ በስረ ነገሩ በማየት ዉሳኔ መስጠቱ ሊታረም የሚገባዉ መሰረታዊ የሕግ ስህተት ነዉ፡፡ጉዳዩን በይግባኝ የተመለከተዉ ከፍተኛ ፍርድ ቤትም የስር ፍርድ ቤትን ስህተት ማረም ሲገባዉ የአመልካቾችን ይግባኝ በመሰረዝ የሰጠዉ ትእዛዝ መሠረታዊ የሆነ የሕግ ስህተት ያለበት ሆኖ አግኝተነዋል፡፡ስለሆነም ተከታዩ ተወስኗል፡፡

  1. የፌዴራል መጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት በመ/ቁጥር 271193 ላይ በመጀመሪያ ደረጃ መቃወሚያዎች ላይ በቀን 10/11/2011/ የሰጠዉ ብይን እና በስረ ነገሩ ላይ በቀን 24/04/2012 / የሰጠዉ ዉሳኔ እንዲሁም የፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት በመ/ቁጥር 254343 ላይ በቀን 24/02/2013/ የሰጠዉ ትእዛዝ በፍ////ሕግ ቁጥር 348/1 መሰረት ተሽረዋል፡፡
  2. የፌዴራል ፍርድ ቤት በሕገ መንግስቱ በተዘረጋዉ የፍርድ ቤቶች ዉክልና ሥልጣን መሠረት ጉዳዩን የመዳኘት የግዛት ሥልጣን የለውም በማለት ወስነናል፡፡ ይህ ዉሳኔ ተጠሪ ሥልጣን ባለዉ ፍርድ ቤት ክስ ከማቅረብ አያግደዉም፡፡

3. በዚህ ችሎት ለወጣ ወጭና ኪሣራ ግራቀኙ የየራሳቸውን ይቻሉ ብለናል፡፡

  1. የዉሳኔዉ ግልባጭ ለስር ፍርድ ቤት ይተላለፍ፡፡ ለግራ ቀኙም ግልባጩ ይሰጣቸዉ፡፡
  2. በመዝገቡ ላይ የተሰጠ የዕግድ ትእዛዝ ካለ ተነስቷል፤ይጻፍ፡፡
  3. የስር ፍርድ ቤት መዝገብ ይመለስ፡፡
  4. መዝገቡ ተዘግቷል፤ ወደ መዝገብ ቤት ይመለስ፡፡

የማይነበብ የአምስት ዳኞች ፊርማ አለበት

/