FEDERAL SUPREME COURT
የሰበር መ/ቁ 210376
ጥቅምት 07 ቀን 2016 ዓ.ም
ዳኞች፡ ብርሃኑ አመነው
ረታ ቶሎሳ
በእውቀት በላይ
ቀነዓ ቂጣታ
ኑረዲን ከድር
አመልካች፡- ገምሹ በየነ ኮንስትራክሽን ኃ/የተ/የግ/ማህበር
ተጠሪ፡- የኢትዮጵያ መንገዶች ባለስልጣን
መዝገቡ ተመርምሮ የሚከተለው ፍርድ ተሰጥቷል፡፡
ፍርድ
መዝገቡ ለዚህ ሰበር ችሎት የቀረበው የአዲስ አበባ ንግድና የዘርፍ ማህበራት ምክር ቤት የተቋቋመ ግልግል ጉባዔ በ5/8/2013ዓ.ም በሰጠው ውሳኔ አመልካች ቅር በመሰኘት ባቀረበው የሰበር አቤቱታ መነሻነት ነው፡፡
የጉዳዩ አመጣጥ በአጭሩ ሲታይ በአዲስ አበባ ንግድና የዘርፍ ማህበራት ምክር ቤት ግልግል ጉባዔ በነበረዉ ክርክር አመልካች በተጠሪነት ተጠሪ ደግሞ በአመልካችነት የተሰየሙ ቢሆንም ሁለቱም ወገኖች የየራሳቸዉን ክስ ወይም ዳኝነት ለጉባዔዉ አቅርበዉ ስለነበረ ከሳሽም ተከሳሽም የነበሩ ሲሆን ተጠሪ በ13/1/2020(እ.አ.አ) የተሸሻለ ክስ እንዲሁም አመልካች በ27/06/2018(እ.አ.አ) የተፃፈ ክስ ለአዲስ አበባ ንግድና የዘርፍ ማህበራት ምክር ቤት የግልግል ጉባዔ አቅርበዋል፡፡
ሁለቱም ክሶች የመነጩት ከመሐል ሜዳ ተነስቶ ዓለም ከተማ የሚልቀው ከኪ.ሜ 72 እስከ አለም ከተማ ያለውን ክፍል -2 የ48 ኪ.ሜ መንገድ ተጠሪ ለማስገንባት አመልካች ለመገንባት እ.ኤ.አ ዲሴምበር 28 ቀን 2012 በተፈረመ ውል የግንባተው ዋጋ ብር 915,292,775.75 (ዘጠኝ መቶ አስራ አምስት ሚሊዮን ሁለት መቶ ዘጠና ሁለት ሺ ሰባት መቶ ሰባ አምስት ከ75/100) የማጠናቀቂያው ጊዜ 1095 የቀን መቁጠሪያ ቀናት ነበር፡፡ አመልካች በግንባታው ሂደት በውል ሰነዱ ውስጥ ከተቀመጠው ተጨማሪ የስራ ጊዜና ገየንዘብ ካሳ የሚያሰጡ ችግሮች ያጋጠሙት መሆኑን በመግለጽ የ875 ቀናት የጊዜ ማራዘሚያ እና የብር 117,689,868.00 (አንድ መቶ አስራ ሰባት ሚሊዮን ስድስት መቶ ሰማኒያ ዘጠኝ ሺህ ስምንት መቶ ስልሳ ስምንት) ካሳ ጥያቄ ግንባታውን ለሚቆጣጠረውና ውሉን ለሚያስተዳድረው አማካሪ መሐንዲስ አቅርቦ አማካሪ መሐንዲሱ ወሳኝ ናቸው ያላቸውን ስትራክቸራልና ኤርዝዎርክ ጊዜ ስራዎች መዘግየት ምክንያት የ153 ቀናት ማራዘሚያ እና የዜሮ ብር ካሳ ወስኗል፡፡
አመልካች ቅር በተሰኘባቸው የአማካሪ መሐንዲሱ ውሳኔ ክፍሎች ላይ ለአለመግባባት ገምጋሚ ባለሙያ Dispute Review Expert(DRE) ቅሬታ አቅርቦ በመታየት ላይ እያለ መሀንዲሱ የራሱን ውሳኔ በማሻሻል ተጨማሪ የ100 ቀናት የጊዜ ማራዘሚያ እና የብር 6,564,689.34 (ስድስት ሚሊዮን አምስት መቶ ስልሳ አራት ሺህ ስድስት መቶ ሰማኒያ ዘጠኝ ከ34/100) ካሳ ለአመልካች እንዲከፈለው በአሰሪው ጭምር በማስፀደቅ ወሰነ፡፡ DRE ባለሙያዉም ቀርቦለት የነበረውን ቅሬታ መሰረት በማድረግ ጉደዩን መርምሮ እ.ኤ.አ ኖቬምበር 30 ቀን 2017 የ418 ቀናት ጊዜ ማራዘሚያና የገንዘብ ካሳ ብር 28,532,689.11( በመሐንዲሱ ተወስኖ የነበረዉን 253 ቀናት የጊዜ ማራዘሚያ እና ብር 6,564,698.34 ካሳ ገንዘብን በውስጡ ባካተተ መልኩ) ለአመልካች እንዲከፈል ወሰነ፡፡
በDREዉ ውሳኔ ሃሳብ/Recommendation አመልካችና ተጠሪ ቅር በመሰኘት ሁለታቸዉም ለአዲስ አበባ ንግድና የዘርፍ ማህበራት ምክር ቤት የግልግል ተቋም የየግል ክሳቸውን ያቀረቡ ሲሆን ተጠሪ እ.አ.አ በ13/01/2020 ባቀረበው የተሸሻለ ክስ DRE አማካሪ መሐንዲስ ከዲዛይን መዘግየት ጋር በተያያዘ የሰጠውን የ418 ቀናት የጊዜ ማራዘሚያ እና ብር 28,532,689.11 (ሃያ ስምንት ሚሊዮን አምስት መቶ ሰላሳ ሁለት ሺህ ስድስት መቶ ሰማኒያ ዘጠኝ ከ11/100) ገንዘብ ካሳ ክፍያና እንዲሁም ከዚህ በተጨማሪነትም በቂ የዲዛይን መረጃ ባለመኖሩ ምክንያት ተከስቶ ለነበረዉ ምርታማነት መቀነስ እና ቀጥሎም ሥራዉ ሙሉ በሙሉ በመቆሙ (idle resource) ምክንያት ለደረሰ ወጪ/ኪሳራ ማካካሻ የማግኘት መብት አለው በማለት እ.አ.አ ዲሴምበር 27 ቀን 2017 የሰጠው ውሳኔ ሙሉ በሙሉ ውድቅ እንዲደረግ በማለት አቤቱታ አቅርቧል፡፡
አመልካች ባቀረበው የመጀመሪያ ደረጃ መቃወሚያ በውሉ መሰረት ክርክሩ በመጀመሪያ በአማካሪ መሀንዲስ ቀጥሎ በDRE በመጨረሻም በግልግል ማካሄድ ሲገባው ተጠሪ ሁሉንም ደረጃ አሟጦ ሳይጠቀም DRE የሰጠውን የብር 28,532,689.11 (ሃያ ስምንት ሚሊዮን አምስት መቶ ሰላሳ ሁለት ሺህ ስድስት መቶ ሰማኒያ ዘጠኝ ከ11/100) ውሳኔ ሙሉ በሙሉ ለማስሻር ዳኝነት ማቅረቡ ተገቢነት የለውም፡፡ይህ የDRE ውሳኔ አማካሪ መሐንዲሱ የወሰነውን ብር 6,564,689.34 (ስድስት ሚሊዮን አምስት መቶ ስልሳ አራት ሺህ ስድስት መቶ ሰማኒያ ዘጠኝ ከ34/100) የማያካትት ሲሆን ተጠሪ በዚህ ውሳኔ አለመስማማቱን በመግለጽ ለ DRE ቅሬታ ባለማቅረቡ ውሳኔው ከዚህ አኳያ የፀና ብቻ ሳይሆን ከፀና ብዙ ጊዜ የሆነውን ጉዳይ ጭምር የግልግል ጉባዔው ተቀብሎ ሊመለከተው ስልጣን የለውም በማለት የተቃወመ ሲሆን በመከላከያ መልሱ የመሬት ስራን (earth work) የቁፋሮ ስራ ሊከናወን የሚገባ ብቸኛ ስራ አድርጎ ተጠሪ ማቅረቡ ስህተት ነው፤ አመልካች ሀብቶቹን በሙሉ ወደ ስራ ማስገባቱን፣ የስትራክቸር ስራን በሚመለከት የተጠሪ ክርክሮች ስህተትና እርስ በእርስ የሚጋጩ መሆኑን፣ ጊዜ ማራዘሚያን አስመልክቶ የ DRE ባለሙያዉ የሰጠዉ ውሳኔ ሃሳብ ትክክል እና የሚነቀፍ አለመሆኑን፣ ተጠሪ የማያሰራ ያልተሟላና ያልተጠበቀ ዲዛይን መስጠቱንና በዚህ ምክንያትም የስራ መስተጓጎል እና ቀጥሎም ለተወሰነ ጊዜ ስራዉ ሙሉ በሙሉ የመቆም ችግር ማስከተሉንና የመሳሰሉትን በመግለጽ ተከሯክሯል፡፡
በሌላ በኩል አመልካች(ተቋራጩ) ለግልግል ተቋሙ እ.አ.አ ሰኔ 27 ቀን 2018 ባቀረበው ክስ መንገዱን ተጠሪው (አሰሪው) በሚሰጠው ዲዛይንና ቴክኒክ መዘርዝር (specification) መሰረት ለመገንባት በጨረታ አሸንፎ ውል መፈራረሙን እና የግንባታ ቁጥጥር ሥራው ከውሉ መጀመሪያ ጊዜ እስከ ሰኔ 2014 እ.አ.አ. ድረስ ክላሲክ ኮንሰልታንት፣ እ.አ.አ. ከጥር 2015 ጀምሮ ደግሞ ዲዛይኑን በሰራው ኮር ኮንሰልታንት ኢንጂነሪንግ አማካሪ ድርጅት መሰራቱን ጠቅሶ ይህ በመካከላቸዉ ለተፈጠረው አለመግባባት ዋነኛ ምክንያት ከአሰሪው የተሰጠው የዲዛይን ጉድለት ስለመሆኑ፣ ያልተጠናቀቀና ተግባራዊ ሊደረግ የሚችል ዲዛይን አለመኖር፣ በዲዛይን ክለሳ/ለዉጥ ምክንያት የስራ መጠን በመጨመር እና በዚህ ምክንያት ተጨማሪ ጊዜን እና ወጪ ማካካሻን የሚያሰጡ ሁኔታዎች በመፈጠራቸዉ ሲሆን በአንፃሩ ግን ተጠሪ ይሄንኑን ግዴታውን ባለመወጣ ጉዳት አድርሶብኛል፡፡
በመሆኑም በዲዛይን መሻሻል ምክንያት ለተከሰተ የስራ መጠን መጨመር 450 ቀናት፣ ዲዛይን ዘግይቶ በመሰጠቱ 425 ቀናት፣ ከነአካተዉ የሚያሰራ ዲዛይን ባለመኖሩ ምክንያት ለ92 ቀናት ስራ በመቆሙና በመሳሰሉት ምክንያት የወጪ ማካካሻ ጥያቄ ለመሐንዲሱ የቀረበ ቢሆንም መሐንዲሱ ከፍሉን ጥያቄ የፕሮጀክቱ ስራ ሲያልቅ በሚኖረው ትክክለኛ ወጪ መሰረት በማድረግ ታይቶ ተገቢዉ ምላሽ ያነ የሚሰጥበት ነዉ በሚልና እንዲሁም ሥራው ከዲዛይን ችግር ጋር በተያያዘ ቆሞ ነበር በተባለበት ወቅትም በሌሎች ቦታዎች ላይ ስራ ስለነበር መሳሪያዎቹ ጥቅም ላይ መዋል ይችሉ ነበር በሚልና በመሳሰሉት ምክንያት መሐንዲሱ ለቀረበለት ተጨማሪ ጊዜ ማራዘሚያ እና ካሳ ጥያቄ በቂ ምላሽ ባለመስጠቱ ቅር በመሰኘት ለDRE የጊዜና የወጪ ማካካሻ ይገባኛል ጥያቄ ቢያቀርብም ጉዳዩ በዚህ ደረጃም ባግባቡ አለመታየቱን በመግለጽ የግልግል ጉባዔው ብር 87,157,179.42 (ሰማኒያ ሰባት ሚሊዮን አንድ መቶ ሃምሳ ሰባት ሺህ አንድ መቶ ሰባ ዘጠኝ ከ42/100) እንዲወሰንለት ጠይቋል፡፡
ተጠሪ (አሰሪው) ባቀረበው የመጀመሪያ ደረጃ መቃወሚያ ከምርታማነት መቀነስና ያለ ስራ የቆሙ መሳሪዎች ጋር በተያያዘ የቀረቡ ጥያቄዎች አስቀድሞ ለDRE ያልቀረቡ በመሆናቸው ለግልግል ጉባዔ በቀጥታ ሊቀርቡ እንደማይገባ መቃወሚያ አቅርበዋል፡፡ለክሱ ባቀረበው የመከላከያ መልስም ለስራዉ መጓተትና መዘግየት ምክንያት የሆኑ ክስተቶችን መንስዔ እና ውጤቱን ተቋራጩ አላስረዳም፤በጥቅት ቦታዎች ላይ የጂኦቴክኒካል ምርመራ ችግር ነበር፣ይህ ችግር ደግሞ ሊፈጠር የቻለው ተቋራጩ ለመሬት ስራ ተገቢውን ጥበቃ ባለማድረጉ ያልተገባ የማቴሪያል አወጋገድ በመፈፀሙና በአመልካች መፈፀም ያለበት የጂኦቴክኒካል ምርመራ ባግባቡ ሳይፈፀም በመዘግየቱ ምክንያት መሆኑንና የመሳሰሉትን በማንሳት ተከራክሯል፡፡የአፈር መንሸራተት የተከሰተው በዲዛይን ችግር ምክንያት ሳይሆን በከፊል ተቋራጩ በውሉ መሰረት ባለመስራቱ ቢሆንም መሳሪያዎች ከቦታ ወደ ቦታ በመንቀሳቀሳቸው ለደረሰ ጉዳት ሂሳቡን በማስላት የማካካሻ ክፍያ ተፈጽሞለታል፡፡የአፈር መናድ ያጋጠመው በ860 ሜትር ላይ ብቻ ነው፣ ለዚህ መፍትሔ አልተሰጠም ማለት ደግሞ የተሟላ ዲዛይን እንዳልተሰጠ የሚያስቆጥር አይደለም፡፡ተቋራጩ በ25/10/2014 በተፃፈ ደብዳቤ መሰረት ሥራ አቆምኩ የሚለው ትክክል አይደለም፤ስራ ለማቆም የውል መብት የለውም፣ ደረሰብኝ ላለው ጉዳት ማስረጃ አላቀረበም፡፡አሰሪው የ153 ቀናት የውል ጊዜ ማራዘሚያ ቢወስንም ተቋራጩ ለ DRE ቅሬታ በማቅረቡ አማካሪ መሀንዲሱ የሰጠውን የ100 ቀናት የውል ጊዜ ማራዘሚያ እና የብር 6,564,689.34 (ስድስት ሚሊዮን አምስት መቶ ስልሳ አራት ሺህ ስድስት መቶ ሰማኒያ ዘጠኝ ከ34/100) ውሳኔ ጉዳዩ ለ DRE ከተመራ በኋላ ስለሆነ ቅሬታው ተቀባይነት የለውም፡፡ በስራ መጠን መጨመር ምክንያት ከሚራዘም ጊዜ ጋር የተያያዘ ክፍያን በሚመለከት ከውል ጊዜ መራዘም ጋር የሚያያዝ የወጪ ማካካሻን ለማስላት ትክክለኛው መንገድ በውሉ ንዑስ አንቀጽ 52.3 መሰረት መቀመጡንና ይህም የጠቅላላ ቀጥተኛ ያልሆነ ወጪ አካል የሆነና ከጊዜ ጋር የሚደረግ ከስራ መጠን መጨመር ጋር ግንኙነት የሌለው ነው፡፡በምርታማነት መቀነስ ምክንያት ተቋራጩ የጠየቀውንና DREው በመርህ ደረጃ ተቀብሎ በማስረጃ አልተደገፈም ብሎ ያለፈውን የግልግል ጉባዔው ተቀብሎ ማየት የለበትም፡፡አመልካች ስራውን ለመስራት ተጨማሪ ወጪ አስከትሎብኛል በማለት ያለማስረጃ 34% የምርታማነት መቀነስ ጉዳት አጋጥሞኝ ነበር ሲል ያቀረበው ማካካሻ ጥያቄ በውሉ አንቀጽ 3.6 መሰረት ተቀባይነት የለውም፤ ተቋራጩ ይሄንኑን ጥያቄ በፍ/ብ/ህ/ቁ 2017 እና በውሉ መሰረት በወቅቱ ከማስረጃ ጋር አላቀረበም በማለት ተከራክሯል፡፡
ጉዳዩ የቀረበለት የአዲስ አበባ ንግድና የማህበራት ዘርፍ የግልግል ተቋም በሁለቱም ወገን የቀረበዉን ክስ እና የመከላከያ መልስ ከመረመረ በኃላ የመጀመሪያ ደረጃ መቃወሚያዎችን በመመርመር ከምርታማነት ማጣትና ያለስራ የቆሙ ግብዓቶች ጋር የተያያዘውን የካሳ ይገባኛል ጥያቄ አስቀድሞ ለ DRE ቀርቦ የነበረ መሆኑን፤ አሰሪው ለተቋራጩ ብር 28,532,689.11 (ሃያ ስምንት ሚሊዮን አምስት መቶ ሰላሳ ሁለት ሺህ ስድስት መቶ ሰማኒያ ዘጠኝ ከ11/100) እንዲከፍል DRE ባለሙያዉ በሰጠው ውሳኔ ውስጥ ብር 6,564,689.34 (ስድስት ሚሊዮን አምስት መቶ ስልሳ አራት ሺህ ስድስት መቶ ሰማኒያ ዘጠኝ ከ34/100) መካተቱን፤ አሰሪው የመሀንዲሱን ውሳኔ ማጽደቁንና ይሄንኑን የመሐንዲሱን ዉሳኔ ለማስሻርም ለ DREዉ ያቀረበው ቅሬታ አለመኖሩን፤ ከምርታማነት መቀነስና ያለስራ የቆሙ መሳሪያዎችና ሰዉ ኃይል ጋር በተያያዘ የቀረበው ገንዘብ ካሳ ጥያቄ ወደ DRE ይመለስ በሚል የቀረበዉን መቃወሚያ አለመቀበሉን፣በሌላ በኩል ፍሬ-ጉዳዩን በሚመለከት ከመነሻው መሐንዲሱ በቂና ተገቢ የዲዘይን ዝርዝር መረጃ ለተቋራጩ አለመስጠቱን፤ ተቋራጩ የዲዛይን ችግር መኖሩን ጠቅሶ ጥያቄ ሲያቀርብለት መሀንዲሱ ተጨማሪ ድሮዊንግ መስጠቱን፤ ሆኖም በዲዛይን ጉድለት ምክንያት ስራው ዘግይቷል፤ አሰሪውም ራሱ ይሄንኑን በማመን እና በመቀበል የጊዜ ማራዘሚያ በመስጠት ተቋራጩን ክሷል፤የውሉ ዓይነት Design Bid Build በመሆኑ በውሉ አንቀጽ 11.1 መሰረት ተቋረጩ መሬቱን ፈትሾ ሊገጥሙት የሚችሉትን ችግሮች ማጣራቱ ስለመሬቱ ሁኔታ ከመሀንዲስ ሪፖርት ማግኘቱ የአሰሪውን የዲዛይን ኃላፊነት አይቀንስም፤ የገንዘብ ካሳ መጠንን በሚመለከት ተቋራጩ ሂሳቡን የሰራበት መንገድ ጥቅል ዘዴ (global approach) በመሆኑና ይህ ደግሞ ከዉሉ አኳያ ተገቢነት ያለዉ ባለመሆኑ ጉባዔው አልተቀበለውም፤በዲዛይን መሻሻል ምክንያት የጨመረውን የስራ መጠን ለማከናወን ጊዜ በመራዘሙ አሰሪው ለተቋራጩ የከፈለው ብር 223,678,323.25 (ሁለት መቶ ሃያ ሶስት ሚሊዮን ስድስት መቶ ሰባ ስምንት ሺህ ሶስት መቶ ሃያ ሶስት ከ25/100) በቂ ነው? አይደለም? የሚለው የሚወሰነው ስራዉ ተጠናቆ በውሉ አንቀጽ 52.3 መሰረት የርክክብ ምስክር ወረቀት ወጪ ሲደረግ ነው፤ ባጠቃላይ ተቋራጩ የጠየቀው ብር 89,157,179.42 (ሰማኒያ ዘጠኝ ሚሊዮን አንድ መቶ ሃምሳ ሰባት ሺህ አንድ መቶ ሰባ ዘጠኝ ከ42/100) ከሚገባው በላይ ስለሆነ ሊከፈለው አይገባም፤ ይልቁንም ሊከፈለዉ የሚገባው ብር 15,257,360.49 (አስራ አምስት ሚሊዮን ሁለት መቶ ሃምሳ ሰባት ሺ ሶስት መቶ ስልሳ ከ49/100) ሆኖ ይህም በአማካሪ መሀንዲሱ ተወስኖ እና በአሰሪዉ ጭምር ተቀባይነት ያገኘዉን ገንዘብ ካሳ ብር 6,564,689.34 (ስድስት ሚሊዮን አምስት መቶ ስልሳ አራት ሺህ ስድስት መቶ ሰማኒያ ዘጠኝ ከ34/100) የያዘ/ያካተተ በመሆኑ ቀሪው ተከፋይ ብር 8,692,662.15 (ስምንት ሚሊዮን ስድስት መቶ ዘጠና ሁለት ሺህ ስድስት መቶ ስልሳ ሁለት ከ15/100) ብቻ ነው፤ የተሸሻለዉ ዲዛይን እስከሚሰጥ ድረስ ተራቋጩ ስራ ያቆመው የውሉን አንቀጽ 40.2 ድንጋጌን በመጣስ ስለሆነ በዚህ ረገድ ስራተቋራጩ የጠየቀው የጊዜ ማራዘሚያ እና የካሳ ጥያቄ ተቀባይነት የለውም፤እንዲሁም ከምርታማነት መቀነስ ጋር በተያየዘ የተጠየቀዉን ካሳም ተቋራጩ በተገቢ ማስረጃ አላስረዳም በማለትና እንዲሁም አማካሪ መሀንዲሱ ከወሰነው 253 ቀናት የዉል ጊዜ ማራዘሚያ ላይ 18 ቀን በመጨመር ባጠቃላይ 271 ቀናት የውል ጊዜ ማራዘሚያ ከፍ በማድረግ ወስኗል፡፡ የሰበር አቤቱታ የቀረበው ይህን ውሳኔ በመቃወም ለማስለወጥ ነው፡፡
የአመልካች ሰበር አቤቱታ በአጭሩ፡-ተጠሪ የDRE (ኤክስፐርት) ምክረ-ሃሳብ እንዲሻርለት ለግልግል ጉባዔ ክሱን ሲያቀርብ በመሃንዲሱ የተወሰኑትን የካሳ ክፍያ ብር 6,564,689.34 (ስድስት ሚሊዮን አምስት መቶ ስልሳ አራት ሺህ ስድስት መቶ ሰማኒያ ዘጠኝ ከ34/100) እና 253 ቀናት ጊዜ ማራዘሚያ ጨምሮ በማቅረቡ ግልግል ጉባዔው የማየት ስልጣን የለውም በማለት ያቀረበውን መቃወሚያ አልተቀበለንም፤በመካከላችን ያለው ውል የፕሮጀክት ማስፈጸሚያው መንገድ ውል "Design Bid Build" መሆኑ የግልግል ጉባዔው በውሳኔው የገለፀ ሲሆን ሆኖም ግን ከዚህ በተቃራኒ ከዲዛይን ጋር በተያያዙ ሁኔታዎችን በተመለከተ ለሚፈጠር ችግር ተቋራጩ ኃላፊነቱን ይጋራል በማለት ውሉን በመቀየሩ የፍ/ብ/ህ/ቁ 1733 የተመለከተውን ድንጋጌ በመጣስ አመልካች ሊያገኝ የሚገባውን ካሳና ተጨማሪ ጊዜ ማራዘሚያ ላይ ጉዳት ደርሷል፤አመልካች በፍ/ብ/ህ/ቁ 3177 መሰረት ያቀረበውን አቤቱታ የግልግል ጉባዔው የተረዳውና የተረጎመው በፍ/ብ/ህ/ቁ 1792 ስለ ከአቅም በላይ የሆነ ኃይል በተደነገገው ባሉት መስፈርቶች በመሆኑ መሰረታዊ የህግ ስህተት ፈጽሟል፤ በአመልችና በተጠሪ መካከል ባለው ውል የተጨማሪ ጊዜ ይሰጠኝ እና የተጨማሪ ገንዘብ ይከፈለኝ ጥያቄዎች ምን አይነት ማስረጃዎችን በማቅረብ መረጋገጥ እንዳለበት ባልተዋዋልንበት የግልግል ጉባዔው ወቅታዊ የሆኑ ሰነዶች (contemporary records) አመልካች አላቀረበም፣ የቀረበው ክርክር ጥቅል (globalized claims) እንጂ በዝርዝር በየራሳቸውም ሆነ በኢንዱስትሪ ደረጃ የተመዘገበ በሚል በማስረጃነት የቀረበ የለም በማለት የማሰረጃ ህግ ማውጣቱ መሰረታዊ የህግ ስህተት ነው፤ ጉባዔው ያለበቂ ትንታኔ እና ምክንያት የቀን ኪሳራውን አማካሪ መሀንዲሱ እና DRE (ኤክስፐርት) ካሰሉት ውጪ በቀን ብር 60,786.30 (ስልሳ ሺህ ሰባት መቶ ሰማኒያ ስድስት ከ30/100) ዝቅ አድርጎ ማስላቱ ስህተት ሲሆን የኢንዱስትሪው ልምድ የሚያስረዳው ማስረጃ አልቀረበም ማለቱ ስህተት ነው፤ አመልካች በምርታማነት መቀነስ (loss of productivity) እና በስራ መጠን መጨመር ምክንያት ከጊዜ ጋር በተያያዘ የጠየቅነውን ጉባዔው ያለምንም ምክንያት ውድቅ ማድረጉ ስህተት ነው፤ በስራ መጠን መጨመር ምክንያት ከጊዜ ጋር በተያያዘ የጠየቅነውን ዳኝነት ጥያቄው ሊስተናገድ የሚገባው ፕሮጀክቱ ተጠናቆ ርክብክብ ሲደረግ ነው ብሎ ከወሰነ በኋላ የተጠየቀው ዳኝነት እጅግ የተጋነነ ነው በማለት እርስ በእርሱ የሚቃረን ውሳኔ ጉባዔው መስጠቱ መሰረታዊ የህግ ስህተት ነው፤ የግልግል ጉባዔው ስለመዘግየት ኃላፊነት መደራረብ (concurrency of delay risks) የሰጠው ትንታኔ ስህተት የተፈፀመበት ነው፡፡በመሆኑም በመሀንዲሱ ተወስኖ በአሰሪው የፀደቀው ብር 6,564,689.34 (ስድስት ሚሊዮን አምስት መቶ ስልሳ አራት ሺህ ስድስት መቶ ሰማኒያ ዘጠኝ ከ34/100) እና 253 ቀናት ጊዜ ማራዘሚያ የግልግል ጉባዔው የማየት ስልጣን የለውም እንዲባል፣ በኤክስፐርቱ የተወሰነው ተጨማሪ 418 ቀናት የጊዜ ማራዘሚያ እንዲወሰኑልን፣ በምርታማነት መቀነስ ምክንያት የደረሰብን ጉዳት ብር 26,991,468.60 (ሃያ ስድስት ሚሊዮን ዘጠኝ መቶ ዘጠና አንድ ሺህ አራት መቶ ስልሳ ስምንት ከ60/100) ከነወለዱ እንዲወሰንልን፣ በአሰሪው ጥፋት ስራ በማቆማችን መሳሪዎችና የሰው ኃይል ምክንያት ለደረሰብን ጉዳት ብር 19,025,373.68 (አስራ ዘጠኝ ሚሊዮን ሃያ አምስት ሺ ሶስት መቶ ሰባ ሶስት ከ68/100) እንዲወሰንልን፣ በስራ መጨመር ምክንየት 450 ቀናቶች ከውሉ በላይ በመቆየታችን ለደረሰብን ጉዳት ብር 36,860,413.50 (ሰላሳ ስድስት ሚሊዮን ስምንት መቶ ስልሳ ሺ አራት መቶ አስራ ሶስት ከ50/100) ከነወለዱ እንዲወሰንልን እንዲሁም በዲዛይን መሻሻል ለደረሰብን ጉዳት ብር 19,555,252.26 (አስራ ዘጠኝ ሚሊዮን አምስት መቶ ሃምሳ አምስት ሺህ ሁለት መቶ ሃምሳ ሁለት ከ26/100) ይወሰንልን በማለት የሰበር አቤቱታቸውን አቅርበዋል፡፡
አመልካች አቤቱታ በሰበር አጣሪ ችሎት ተመርምሮ በአመልካች የቀረበው የብር 6,564,689.34 (ስድስት ሚሊዮን አምስት መቶ ስልሳ አራት ሺህ ስድስት መቶ ሰማኒያ ዘጠኝ ከ34/100) ክፍያ እና የ253 ተጨማሪ የስራ ቀናት በመሀንዲሱ ተወስኖና በተጠሪም ጭምር ፀድቆ እያለ ለገምጋሚ ባለሙያ ቀርቦ ምክረ ሀሳብ ሳይሰጥበት የግልግል ጉባዔው ክርክሩን ተቀብሎ ለማየት ስልጣን ያለው ስለመሆን አለመሆን እንደዚሁም የውሉ አይነት (Design Bid Build) በተዘጋጀ ዲዛይን ግንባታውን የሚሰራ ሥራ ተቋራጭ ጨረታ የመስጠት ሂደትን የተከተለ ሆኖ የዲዛይን ኃላፊነት የአሰሪው ስለመሆኑ በውሉ ተጠቅሶ ባለበት ሁኔታ አመልካች ከዲዛይን ጋር ተያይዘዉ ለሚፈጠሩ ችግሮች "ከተጠሪ ጋር ይጋራል" በሚል ያቀረቡት የካሳ ክፍያ እና ተጨማሪ የስራ ቀናት አስመልክቶ የተወሰነበት አግባብነት ከተከራካሪ ወገኖች ውል አንፃር ለመመርመር ሲባል መዝገቡ ያስቀርባል ተብሎ ተጠሪ መልስ እንዲሰጡበት ታዟል፡፡
ተጠሪ ባቀረቡት መልስ ጉባዔው ጉዳዩን የተመለከተው በተጠሪ በኩል በቀረበው ክርክር መነሻነትና በተጨማሪነት በኤክስፐርቱ የተወሰነውን ብር 28,532,689.00 (ሃያ ስምንት ሚሊዮን አምስት መቶ ሰላሳ ሁለት ሺ ስድስት መቶ ሰማኒያ ዘጠኝ) ውስጥ መሀንዲሱ የወሰነው ብር 6,564,689.34 (ስድስት ሚሊዮን አምስት መቶ ስልሳ አራት ሺህ ስድስት መቶ ሰማኒያ ዘጠኝ ከ34/100) ይካተታል ወይስ አይካተትም የሚለውን ጭብጥ ለመለየት የነበረ ሲሆን ጉባዔው ማየቱ የህግ ስህተት የለውም፤ በውሉ አንቀጽ 67.3.1.1 እና 67.3.1.2 መሰረት ጉዳዩን አይቶ ከማስተናገዱ ውጪ የመሀንዲሱን ውሳኔ አልወጠም፣ በዚህም በአመልካች ላይ የደረሰ ጉዳት የለም፤ ጉባዔው የዲዛይን ኃላፊነት የማነው የሚለውን መርምሮ የአሰሪው ነው በማለት ውሉን በትክክል የተረጎመ በመሆኑ በመካከላችን ያለው ውል የቀየረ ውሳኔ አልሰጠም፤ ጉባዔው የውሉን ጠቅላላ ድንጋጌ አንቀጽ 11.1 በመንተራስ ምንም እንኳ የዲዛይን ኃላፊነት የተጠሪ ቢሆንም የመሬቱን ሁኔታ ከመፈተሸ ጋር በተያያዘ ግን ተቋራጩ ከአሰሪው ጋር ኃላፊነት ይጋራል በማለት ከመጥቀስ ውጪ የግልግል ጉባዔው በውሳኔው ሃተታ አመልካች ከዲዛይን ጋር በተያያዙ ለሚፈጠሩ ችግሮች ከአሰሪው ጋር ኃላፊነት ይጋራል የሚል ሃሳብ ያላሰፈረ በመሆኑ የአመልካች አቤቱታ ሀሰት ነው፡፡ጉባዔው ይሄንን ቢልም እንኳን ለአመልካች በኤክስፐርቱ ከተወሰነለት የካሳ መጠንና ተጨማሪ ጊዜ የተቀነሰበት ዳኝነት የለም፡፡ጉባዔው ኤክስፐርቱ የወሰነውን ካሳ እና የተጨማሪ የውል ማከናወኛ ጊዜ ላይ ማሻሻያ ያደረገው አመልካች ዲዛይን የማዘጋጀት ኃላፊነት ከአሰሪው ጋር ይጋራል በሚል እሳቤ አይደለም፤ አመልካች ከመስከረም 5 ቀን 2007 ዓ.ም እስከ ታህሳስ 22 ቀን 2007 ዓ.ም ድረስ ስራ ማቆሙን በተመለከተ በግልግል ጉባዔው ክርክር ሲደረግ የነበረው የውሉን አንቀጽ 40.1 በመጥቀስ እንጂ የፍ/ብ/ህ/ቁ 3177 የተደነገገውን በመጥቀስ አልነበረም፣ ይሄንን ድንጋጌ ጠቅሼ የተከራከርኩት ተጠሪ ነኝ፣ ተከሰተ የተባለው የዲዛይን ችግርም ስራውን ሙሉ በሙሉ የማያስቆም መሆኑ በተረጋገጠበት ሁኔታ አመልካች በፍ/ብ/ህ/ቁ 3177 ድንጋጌ ተጠቃሚ ሊሆን አይችልም፤የግልግል ጉባዔው በአመልካች በኩል የቀረቡትን የሰነድ እና የሰው ማስረጃዎችን ከቀረበዉ ዳኝነት ጥያቄ ይዘት አንፃር በመመርመር ማስረጃዎቹ በጥቅል የቀረቡ እንጂ በዝርዝር ያልቀረቡ በመሆናቸው እንደ ክሱ አቀራረብ አያስረዱም በማለት ውድቅ ማድረጉ የማስረጃ ምዘና እንጂ ሌላ የማሰስረጃ ህግ መደንገግ አይደለም፤ተጠሪ ተጠያቂ በሆነባቸው ምክንያቶች አመልካች በግንባታ ሳይቱ ለቆየባቸው ተጨማሪ እያንዳንዱ ቀናት ሊከፈለው የሚገባው የካሳ ልክ ስንት ነው የሚለው ነጥብ የፍሬ ነገርና የማሰስረጃ ክርክር በመሆኑ መሰረታዊ የህግ ስህተት አይደለም፤አሰሪው፣ አማካሪ መሀንዲሱ፣ ኤክስፐርቱ እና የግልግል ጉባዔው የቀረበውን ምርታማነት መቀነስ (loss of productivity) የካሳ ይገባኛል ጥያቄ ስሌትን በጉዳቱ ላይ ተመርኩዞ ያልቀረበ ነው በሚል ውድቅ ማድረጋቸው እየታወቀ ሰበርን በሚያሳስት ሁኔታ ሶስቱ የተቀበሉት በማስመሰል አመልካች ያቀረበው መከራከሪያ ተቀባይነት የለውም፤ የግልግል ጉባዔው የአመልካችና የተጠሪን ክርክር ተመልከቶና መርምሮ የሰጠው ውሳኔ እርስ በእርሱ የሚቃረን አይደለም፤ የፍ/ብ/ህ/ቁ 1757 ድንጋጌ ተከትሎ የዲዛይን መጓደል በተከሰተ ጊዜ አመልካች የውል ግዴታውን ለመወጣት የሚያስችል ቁመና ላይ ባለመሆኑ የዲዛይን መጓደሉ ባይኖርም ዝግጅቱ በአመልካች በኩል ስለሌለ ዞሮ ዞሮ በራሱ ጥፋት ወጪ ማውጣቱ አይቀርም በማለት የሰጠው ውሳኔ ስህተት የለውም፤ በመሆኑም አመልካች ለግልግል ጉባዔው ዳኝነት የጠየቀው ብር 89,157,179.42 እንጂ ብር 108,997,206.38 ባለመሆኑ ይከፈለው ከተባለ እንኳን ሊከፈለው የሚገባው ይሄንኑ በግልግል ጉባዔዉ የጠየቀው ያህል ካሳ ገንዘብ ሊሆን ይገባል እንጂ ከዚያ ውጭ ሊሆን አይገባም በማለት የተከራከረ ሲሆን አመልካችም የመልስ መልሱን በመስጠት የሰበር አቤቱታውን በማጠናከር ተከራክሯል፡፡
አጠቃላይ የጉዳዩ አመጣጥና ይዘት ከዚህ በላይ የተገለፀዉን ሲመስል ችሎቱም ይሄንኑ ለዚህ ሰበር አቤቱታ መነሻ የሆነዉን ግልግል ጉባዔ ዉሳኔ አግባብነት ከግራ ቀኙ ክርክር እና ለጉዳዩ አግበብነት ካላቸዉ ህጉ ድንጋጌዎች አንፃር በሚከተለዉ መልኩ መርመረናል፡፡
እንደመረመርነውም በመሰረቱ ለከርክሩ ምክንያት ከሆነው ግንባታ ስራ ዉል አፈፃፀም ጋር በተያያዘ የሚነሳ ማንኛዉም አለመግባባትን በተመለከተ ተዋዋይ ወገኖቹ አንዳቸው በሌላኛው ላይ የሚያቀርቡት የመብት ጥያቄ ካለ በመጀመሪያ ጥያቄው በውሉ መሰረት በተጠሪው ( አሰሪው) ለተመደበ አማካሪ መሃንዲስ ቀርቦ ሊስተናገድ እና በውሉ በተመለከተዉ ጊዜ ውስጥ ተገቢው ምላሽ ወይም ውሳኔ ሊሰጥበት የሚገባ መሆኑንና እንዲሁም በዚህ በመሀንዲሱ ውሳኔ ቅር የተሰኘ ወይም ያልረካ ወገን ካለ ደግሞ ጉዳዩን በቀጥታ ለግልግል ጉባኤዉ ከማቅረቡ በፊት አስቀድሞ ጉዳዩን ለአለመግባባት ገምጋሚ ኤክስፐርት (Dispute Review expert/DRE)አቅርቦ እንዲታይና በጉዳዩ ላይ አስቀድሞ በኤክፐርቱ የውሳኔ ሀሳብ/ምክረ-ሀሳብ (recommendation) እንዲሰጥበት በማድረግና ይሄንኑን በዚህ ረገድ በዉላቸዉ የተዘረጋዉን አለመግባባት መፍቻ መንገድ ወይም ስርዓት መከተል እንዳለባቸዉ ከግራ ቀኙ ውል ልዩ ሁኔታ አንቀፅ 67(1) ድንጋጌ ይዘትና አላማ መገንዘብ ይቻላል ፡፡
በዚሁ መሰረት ወደተያዘው ጉዳይ ስንመለስም አመልካች ከግንባታ ዉሉ ስራ አፈፃፀም ጋር በተያያዘ ተጠሪ የተሟላ እና ሊያሰራ የሚያስችል የዲዛይን ሰነዶችን በወቅቱ ማቅረብ ሲገባ ይሄንኑን ባለማቅረቡ ምክንያት ለባከነ ዉሉ ጊዜ ማካካሻ 425 ቀናቶች ተጨማሪ ጊዜ እና በዚሁ ዲዛይን ጉድለት እና መዘግየት ምክንያትና እንዲሁም የግንባታ ስራው ዲዛይን በመለወጡና ይሄንኑን ተከትሎም የስራ መጠኑ በከፍተኛ ሁኔታ በመጨመሩ ምክንያት 450 ቀናት በተጨማሪነት አመልካች በሳይት እንዲቆይ በመገደዱ በአጠቃላይ ከዲዛይን ጋር በተያያዘ ችግር በተፈጠረ መዘግየት እና ስራ መጠን መጨመር ምክንያት ከጊዜ ጋር በተያያዘ ለደረሰ ጉዳት የካሳ ገንዘብ ይገባኛል ጥያቄና እንዲሁም አመልካች ለአማካሪ መሀንዲሱ አቅርቦ ባፀደቀው ስራ ፕሮግራም መሰረት አመልካች ሙሉ በሙሉ በአቅሙ ተጠቅሞ መስራት ሲችል ተጠሪ ሊያሰራ የሚያስችል የተሟላ ዲዛይን ባለመስጠቱ ምክንያት ለተከሰተ ደካማ ስራ ክንውን/ምርታማነት መቀነስ (loss of productivity) ምክንያት ለደረሰ ጉዳት(cost of loss of productivity) ማካካሻ ገንዘብ ጥያቄና እንዲሁም ከዚህ በተጨማሪነትም የቀረበዉ ዲዛይንም ቢሆን ሙሉ በሙሉ ሊያሰራ ባለመቻሉና ዉሉን የሚቆጣጠርና የሚያስተዳድር መሀንዲስም ከነ-አካተዉ ከሰኔ ወር 2006 ዓ.ም ጀምሮ አስከ ጥር 4 ቀን 2007ዓ.ም ድረስ ባለመኖሩ ምክንያት ስራዉ ሙሉ በሙሉ ለቆመ ጊዜ የመሳሪያዎች እና ሰው ኃይል ስራ ፈተው በመቆማቸው ምክንያት ለደረሰ ኪሳራ(cost of idle resources) የካሳ ገንዘብ ይገባኛል ጥያቄ ለመሀንዲሱ ማቅረቡንና አማካሪ መሀንዲሱም በበኩሉ ይሄንኑን በዚህ መልኩ ተጨማሪ የዉሉ ስራ ማስፈፀሚያ ጊዜ ይሰጠኝ በሚልና እንዲሁም በሶስት ክፍያ ርዕሶች (heads of claim) ተከፋፍሎ የእያንዳንዳቸዉ ካሳ አሰላል ዘዴ እና መጠኑ ጭምር ተጠቅሶ በአመልካች ከቀረበለት የተጨማሪ ጊዜ እና የካሳ ገንዘብ ይገባኛል ጥያቄዎች መካከል ተጨማሪ ጊዜ ጥያቄን በተመለከተ በአመልካች ከተጠየቀው 425 ቀናት ውስጥ 153 ቀናቶችን፣ የካሳ ገንዘብ ጥያቄን በተመለከተ ደገሞ ዜሮ ብር የካሳ ገንዘብ መወሰኑን፤ይሄንኑን ተከትሎም ያሁን አመልካች በውሳኔዉ ቅር በመሰኘት ቅሬታውን ለገምጋሚ ኤክስፖርት አቅርቦ ጉዳይ በዚህ ደረጃ በመታየት ሂደት ላይ እያለ መሀንዲሱ አስቀድሞ በጉዳዩ ላይ የሰጠውን ውሳኔ መልሶ በማሻሻል ተጨማሪ ጊዜ ጥያቄን በተመለከተ አስቀድሞ በወሰነው 153 ቀናት ላይ 100 ቀናትን በመጨመር በጠቅላላው 253 ቀናትን እንዲሁም በዲዛይን ጉድለት እና መዘግየት ምክንያት ከጊዜ ጋር በተያያዘ ለደረሰ ጉዳት የማካካሻ ካሳ ገንዘብ ብር 6,547,698.34 ለአመልካች እንዲከፈለው ወስኖ የተቀሩት ሁለት የካሳ ክፍያ ርዕሶችን (heads of claim) ማለትም ከዲዛይን ጉድለት እና መዘግየት በተነሳ የስራ አፈፃፀም በመስተጓጎሉ ምክንያት ለተከሰተ ምርታማነት መቀነስ/ ደካማ ክንውን እና ቀጥሎም በተጠቀሰዉ ተመሳሳይ ዲዛይን አቅርቦት ችግር ምክንያት ስራው ሊቀጥል ባለመቻሉ ሙሉ በሙሉ ከመስከረም ወር እስከ ታህሳስ ወር 2007ዓ.ም ድረስ በቆመ ጊዜ ያለ ስራ ለባከነ ሀብት (idle resources) ማካካሻ የካሳ ገንዘብ ይገባኛል ጥያቄን በተመለከተ ደግሞ አመልካች ከውሉ አኳያ ይሄንኑን ሊያስረዱ የሚችሉ ተገቢነት እና ተቀባይነት ያላቸዉ ዝርዝር ማስረጃዎችን በአስቸኳይ እንዲያቀርብ በማሳሰብ ጭምር ጠቅሶ መወሰኑን፤ይህ በእንዲህ እንዳለ በአሁን አመልካች ቅሬታዉ አስቀድሞ ቀርቦለት የነበረዉ አለመግባባት ገምጋሚ ኤክስፐርትም በጉዳዩ ላይ የግራ ቀኙ ክርክርና አስተያያት ከተቀበለ በኃላ ጉዳዩን መርምሮ በዲዛይን ጉድለት እና መዘግየት ምክንያት የስራ አፈፃፀም በመስተጓጎሉ ምክንያት ለባከነ ዉሉ ጊዜን በተመለከተ 311 ተጨማሪ ቀናትን ሲወስን በዚሁ ዲዛይን አቅርቦት ችግር ምክንያት ስራዉ ሙሉ በሙሉ በመቆሙ ምክንያት ለባከነ ዉሉ ጊዜን በተመለከተ ደግሞ 107 ቀናትን በድምሩ 418 ቀናት ሲወስን ከካሳ ይገባኛል መብት ጥያቄዎች መካከል ደግሞ በዲዛይን ጉድለት እና መዘግየት ምክንያት የዉሉ ስራ ማስፈፀሚያ ጊዜ በመራዘሙ ከጊዜ ጋር በተያያዘ ደረሰ የተባለዉን ወጪ/ኪሳራን በተመለከተ የቀረበዉን የካሳ ገንዘብ ይገባኛል ጥያቄን ብቻ በመቀበልና ይሄንኑን በተመለከተ አማካሪ መሀንዲሱ አስቀድሞ ወስኖ የነበረዉን ካሳ ገንዘብ ባካተተ መልኩ በድምሩ ብር 28,532,689.11 ለአመልካች መወሰኑን፤ሆኖም ግን በዲዛይን አቅርቦት ችግር ምክንያት ተከሰተ በተባለዉ ደካማ ስራ ክንውን/ምርታማነት መቀነስና እንዲሁም ስራዉ ሙሉ በሙሉ በመቆሙ የተነሳ አጋጥሟል በተባለው ሀብት ብክነት(መሳሪያዎች እና የሰው ኃይል ስራ ፈተው በመቆማቸዉ) ምክንያት ደረሰ የተባለዉን ጉዳት/ወጪን ለመተካት የቀረቡ ካሳ ክፍያ ጥያቄዎችን ኤክስፐርቱ በመርህ ደረጃ ተቀብሎ ነገር ግን ካሳ መጠኑን በተመለከተ አመልካች ተገቢነት ባለዉ ዝርዝር ማስረጃ አለማስረዳቱን ጠቅሶ ይሄንኑን በተገቢ ማስረጃ እንዲያስገድፍ በሚል በጉዳዩ ላይ የመጨረሻ ዉሳኔ ሳይሰጥ በዚህ መልኩ አንጠልጥሎ ማለፉን፤ ይሁንና ጉዳዩን ቀጥሎ የተመለከተው የስር ግልግል ጉባኤ እነዚህን ሁለቱን ጉዳዮች (ማለትም ምርታማነት በመቀነሱ እና የግንባታ ስራዉ ሙሉ በሙሉ በቆመ ጊዜ በባከነ ሀብት ምክንያት አጋጥሟል የተባሉት ኪሳራዎችን በሚመለከት) በቀረበዉ የካሳ ይጋባኛል ጥያቄዎች ላይ ኤክስፐርቱ ባስተላለፈው ውሳኔ ላይ ግራ ቀኙ ያቀረቡትን ክስ/ቅሬታ ተቀብሎ ከተመለከተ በኃላ ስራዉ ሙሉ በሙሉ በቆመ ጊዜ መሳሪያዎችና የሰው ሀይል ስራ ፈተው በመቆማቸዉ ምክንያት ለባከነ ዉሉ ጊዜ ተጨማሪ ጊዜ ይሰጠኝ እና ካሳ ገንዘብ ይጋባኛል ጥያቄን በተመለከተ ሲጀመር አመልካች ስራውን ያቆመው የውሉ ጠቅላላ ሁኔታ አንቀፅ 40 ከሚያዘዉ ውጭ በሆነ ሁኔታ በመሆኑ ተጠሪ በዚህ ምክንያት ለባከነ ጊዜም ሆነ ለደረሰ ጉዳት ተጨማሪ ጊዜ ለመስጠትና ካሳ ክፍያ ለመፈፀም ኃላፊነት የለበትም በሚል ተጠሪን ሙሉ በሙሉ በዚህ ረገድ ከቀረበዉ ዳኝነት ጥያቄ ነፃ በማድረግ መወሰኑንና እንዲሁም በዲዛይን ጉድለት እና መዘግየት በተነሳ የግንባታ ስራዉ አፈፃፀም በመስተጓጎሉ የምርታማነት መቀነስ አጋጥሟል በሚል ደረሰ ለተባለዉ ጉዳት የካሳ ይጋባኛል ዳኝነት ጥያቄን በተመለከተ ደግሞ አመልከች ይሄዉ በዚህ ረገድ ደረሰብኝ ያለዉ ኪሳራ በእርግጥም የደረሰበት መሆኑን በተገቢ ማስረጃ ይሄንኑን በማስደገፍ አላስረዳም በሚል ከማስረጃ አቀባበል እና ምዘና አንፃር ውድቅ በማድረግ መወሰኑን የዉሳኔ ግልባጭ ያስረዳል፡፡
ከዚህ ከክርክሩ ሂደትም በግልፅ መገንዘብ እንደሚቻለዉ ከምርታማነት መቀነስ እና ስራዉ ሙሉ በሙሉ በመቆሙ ምክንያት አመልካች ጉዳት ደረሰብኝ በሚል አቅርቧቸዉ በነበረዉ የካሳ ገንዘብ ይጋባኛል ዳኝነት ጥያቄዎችን በሚመለከት አማካሪ መሀንዲሱም ሆነ ኤክስፐርቱ የመጨረሻ ማጠቃለያ ውሳኔ(ዉሳኔ ሀሳብ) ያልሰጡበት መሆኑን ነዉ፡፡ከዚህ ጋር በተያያዘ በተለይ አማካሪ መሀንዲሱ አስቀድሞ የሰጠዉን ውሳኔ በኃላ ላይ በማሻሻል ባስተላለፈዉ ውሳኔ አመልካች ይሄንኑን ከምርታማነት መቀነስ እና ስራዉ ሙሉ በሙሉ በቆመ ጊዜ በባከነ ሀብት ምክንያት ኪሳራ የደረሰበት መሆኑን ጠቅሶ በተለያየ ሁለት ክፍያ ርዕሶች በማደራጀት ያቀረበውን የካሳ ይገባኛል ጥያቄዎችን በተመለከተ አመልካች ይሄንኑን ጥያቄዎች (claims) የሚያስረዱለትን ተገቢነት ያላቸዉ ማስረጃዎችን በአስቸኳይ በማቅረብ ጉዳዩ ባጠረ ጊዜ እንዲቋጭ እና እንዲጠናቀቅ የበኩሉን ጥረት እንዲያደርግ በማሳሰብ እና መብቱን በመጠበቅ ጭምር ማለፉን እንጂ በጉዳዩ ላይ የመጨረሻ ውሳኔ ባልተሰጠበትና እንዲሁም አመልካችም ቢሆን ይሄንን ጉዳይ በተመለከተ አስቀድሞ ከቀረበዉ ማስረጃ በተጨማሪ ሌላ የማቀርበዉ ማስረጃ ስለሌለኝ ጉዳዩ አስቀድሞ በቀረበዉ ማስረጃ መሰረት በማድረግ ተገቢዉ ዉሳኔ ይሰጠኝ በሚል አቋሙን ግልፅ በማድረግም መከራከሩን የክርክሩ ሂደት በማያሳይበት ሁኔታና እንዲሁም ይህ የአማካሪ መሀንዲሱ ውሳኔም በአሰሪ/በተጠሪ ጭምር ተቀባይነት አግኝቶ በፀደቀበትና እንዲሁም ከመሀንዲሱ በመቀጠል ጉዳዩን ተቀብሎ በተመለከተው አለመግባባት ገምጋሚ ኤክስፐርቱም ጭምር ጉዳዩ ታይቶ የመጨረሻ ውሳኔ ሀሳብ ባልተላለፈበት ሁኔታ የግልግል ጉባዔዉ ይህ በአማካሪ መሀንዲሱም ሆነ ኤክስፐርቱ የመጨረሻ ዉሳኔ/ዉሳኔ ሀሳብ ያልተሰጠበትን ጉዳይ ተቀብሎ እና አይቶ በቀጥታ በራሱ መወሰኑ ከግራ ቀኙ ውል ልዩ ሁኔታ አንቀፅ 67(1) እና ፍ/ብ/ስ/ስ/ህ/ቁ- 317(2) ድንጋጌዎች ይዘት እና ዓላማ አንፃር ተዋዋይ ወገኖቹ በመካከላቸዉ የሚነሳን አለመግባባት ከመቋጨት አኳያ በዉል ስምምነታቸዉ እና ህጉ የተዘረጋዉን ስርዓት በጠበቀ መልኩ በየደረጃዉ ታይቶ እንዳይወሰን ከማድረጉም በላይ የመሰማት መብታቸውን በእጅጉ ያጣበበ ሆኖ በመገኘቱ የግልግል ጉባዔዉ ከምርታማነት መቀነስ እና ስራዉ በመቆሙ ምክንያት ጉዳት ደረሰብኝ በሚል አመልካች ባቀረበዉ የካሳ ይገባኛል ጥያቄዎች ላይ በቀጥታ በራሱ ያስተላለፈዉ ዉሳኔ ከአዋጅ ቁ.1234/2013 አንቀፅ 2(4)(ረ) እና 10 ድንጋጌዎች አንፃር መሰረታዊ የህግ ስህተት የተፈፀመበትና ሊታረም የሚገባ ሆኖ አግኝተነዋል፡፡
እንዲሁም የተጠሪ በሆነ ምክንያት ዲዛይን በመሻሻሉና በዚህ የተነሳም የስራ መጠን በመጨመሩ ምክንያት አመልካች ለተጨማሪ 450 ቀናት በሳይት እንዲቆይ መደረጉን ተከትሎ ከጊዜ ጋር በተያያዘ ጉዳት ወይም ተጨማሪ ወጪ እንደሚደርስበት ጠቅሶ ይሄዉ በዚህ ረገድ የደረሰበት ወጪ ጭምር ሊከፈለኝ ይገባል በሚል ያቀረበውን የገንዘብ ካሳ ጥያቄን አስመልክቶ ኤክስፐርቱም ሆነ ግልግል ጉባዔዉ ይህን ተጨማሪ ስራ መጠን ለማሰራት ተጠሪ በከፈለው ስራ ዋጋ ብር 223,679,323.72 ውሥጥ ይህ ቀጥተኛ ያልሆነ ወጪ (over head cost) ጭምር ስላለ አመልካች ከዚህ አንፃር የሰበሰበዉ ቀጥተኛ ያልሆነ ወጪ በዚህ 450 ቀናት ተጨማሪ ቆይታ ወቅት በተጨባጭ ከሚያወጣዉ ወጪ ያነሰ ከሆነ ይሄዉ ልዩነቱ ተሰልቶ በዉሉ አንቀፅ 52(3) መሰረት ሊከፈለዉ የሚገባ መሆኑን፣ ሆኖም ግን ይህንን ወጪ መጠን በትክክል ለይቶ ማወቅ የሚቻለዉ ስራዉ ተጠናቆ ሪክክብ ሲፈፀም መሆኑን የዉሉ አንቀፅ 52(3) ድንጋጌ ይዘት የሚያስገነዝብ በመሆኑ ስራዉ አሁን ባለበት ደረጃ ይሄንኑን መወሰን አይቻልም በሚል ጉዳዩን በእንጥልጥል ትተዉ ማለፋቸዉን እንጂ ይህ የዉሉ ስራ መጠን በመጨመሩ ምክንያት ከጊዜ ጋር በተያያዘ የሚደርሰዉ ቀጥተኛ ያልሆነ ወጪ ለአመልካች ሊከፈለዉ አይገባም በሚል በጉዳዩ ላይ የተሰጠ መጨረሻ ዉሳኔ በሌለበትና ይህ ከሆነ ደግሞ ጉዳዩን በተመለከተ በኤክስፐርቱም ሆነ ግልግል ጉባዔዉ ተጠቃሎ በየደረጃዉ የተሰጠ የመጨረሻ ዉሳኔ ሀሳብ እና ዉሳኔ ከሌለ ደግሞ በጉዳዩ ላይ በአዋጁ ቁ.1234/2013 አንቀፅ 10 ስር እንደተመለከተዉ ከጅምሩ የሰበር አቤቱታ ሊቀርብበት የሚችል ባለመሆኑ ይህ በዚህ ረገድ በአመልካች የቀረበዉ ሰበር አቤቱታ በዚህ ስነ-ስርዓታዊ ምክንያት ባለመቀበል ውድቅ ተደርጎ ታልፏል፡፡
እንዲሁም በዲዛይን ጉድለት እና መዘግየት በተነሳ በተፈጠረ ስራ መስተጓገል ምክንያት ለባከነ ጊዜ ማካካሻ ተጨማሪ ጊዜ ይሰጠኝ የሚለው የአመልካች ጥያቄን በተመለከተ የግልግል ጉባኤው በዚህ ረገድ በስር አለመግባባት ገምጋሚ ኤክስፖርት የተሰጠውን የ311 ቀናት ተጨማሪ ጊዜ በመቀነስ 271 ቀናት ተጨማሪ ጊዜን ለአመልካች የወሰነ ሲሆን ከዚሁ ከዲዛይን ጉድለትና መዘግየት ምክንያት ለባከነ ጊዜ ተጨማሪ ጊዜ መሰጠቱን ተከትሎ የውሉ ጊዜ በመራዘሙ ምክንያት የደረሰ ኪሳራን አስመልክቶ የግልግል ጉባዔው በዚሁ ረገድ ለአመልካች ከወሰነዉ 271 ቀናት ውስጥ 20 ቀናት በአመልካች ጭምር በተስተዋለ መዘግየት ምክንያት የባከነ መሆኑን ጠቅሶ ይህ በዚህ አግባብ በሁለቱም ወገኖች በኩል ባለ ምክንያት የባከነዉ ጊዜ ተጨማሪ ጊዜን የሚያሰጥ እንጂ የካሳ ክፍያን የሚያሰጥ አይደለም በሚል ይሄንኑን 20 ቀናት በመቀነስ የ251 ቀናት ተጨማሪ የውሉ ጊዜ የካሳ ክፍያ (በአማካሪ መሀንዲሱ ተወስኖ በኤክስፖርቱ ጭምር ተቀባይነት ያገኘው ብር 6,564,689 ጨምሮ ) በድምሩ ብር 15,257,360 ለአመልካች መወሰኑን ተከትሎ አመልካች ከዚህ ጋር በተያያዘ የግልግል ጉባኤው የካሳ መጠኑን ስያሰላ የአመልካች እለታዊ ወጪ ብር 60,786.30 እንደሆነ ይዞ እና ይሄንኑን መሰረት በማድረግ (የ20 ቀኑን ኃላፊነት ከውስጡ ቀንሶ በማዉጣት) የ251 ቀናት ካሳ ክፍያን የወሰነበትና ከመሳሰሉት ጋር በተያያዘ አመልካች ለዚህ ሰበር ችሎት ያቀረበው ሰበር ቅሬታም ሆነ ተጨማሪ ጊዜን በሚመለከትም ጉባኤው ኤክስፖርቱ የሰጠውን ውሳኔ ሀሳብ በማሻሻል በሰጠው ውሳኔ ክፍል ላይ ያቀረበው ቅሬታ በዋናነት በግልግል ጉባዔዉ ላይ መሰረታዊ የሆነ ህግ ስህተት መፈፀሙን የሚያሳይ ሳይሆን ይልቁንም በፍሬ ነገር ክርክር እና ማስረጃ ምዘና ላይ ያተኮረ በመሆኑና ይህ ደግሞ ከህገ-መንግስቱ አንቀፅ 83(3)(ሀ) እና አዋጅ ቁ .234/2013 አንቀፅ - 2(4) እና 10 ድንጋጌዎች መሰረት ለዚህ ሰበር ሰሚ ችሎት ከተሰጠዉ ስልጣን አንፃር ሲታይ ለዚህ ሰበር ችሎት ቀርቦ ሊታይ እና ሊስተናገድ የሚችል ባለመሆኑ የይሄንኑ በዚህ ምክንያት አልተቀበልነውም፡፡
ከዲዛይን ኃላፊነት ጋር በተያያዘ አመልካች ያቀረበዉን ሰበር ቅሬታ በተመለከተ በመሰረቱ ዉሉ‹‹Design-Bid-Build›› በመባል የሚታወቀዉ ከመሆኑ አኳያ በዚህ ረገድ የሚመጣ ኃላፊነት ሙሉ በሙሉ የአሰሪዉ መሆኑን የሚያሳይ ሲሆን የስር ግልግል ጉባኤዉም አመልካች በሰበር አቤቱታዉ እንደጠቀሰዉ ይሄንኑን ኃላፊነት አመልካች ጭምር እንዲጋራ የወሰነ ሳይሆን ይህ የዲዛይን ኃላፊነት በማያሻማ መልኩ ሙሉ በሙሉ በተጠሪ ተከሻ ላይ የሚወደቅ መሆኑን የወሰነዉ(የግልግል ጉባኤዉ ገፅ 33-34 ይመለከታል)፡፡በውሳኔ ማጠቃለያ ተ.ቁ.5 ላይ የግልግል ጉባኤዉ ያሰፈረዉ ሀሳብ ተቋራጩ ወደ ግንባታ ስራዉ ከመግባቱ በፊት አስቀድሞ በራሱ መሬቱን/ሳይቱን ከመፈተሹ ጋር በተያያዘ እንጂ ከዲዛይን ዝግጅት ጉድለት እና ባጠቃላይ ከዲዛይን ጋር በተያያዘ የሚመጣን ኃላፊነት የሚመለከት አይደለም፡፡ስለሆነም የስር ግልግል ጉባኤዉ የዲዛይን ኃላፊነት የአመልካች ጭምር መሆኑን ሳይሆን ሙሉ በሙሉ የተጠሪ ኃላፊነት መሆኑን የወሰነ ከመሆኑም በላይ በዚህ ምክንያትም ከአመልካች የተቀነሰ አንዳችም የተጨማሪ ጊዜም ሆነ ካሳ ገንዘብ መኖሩን ዉሳኔዉ ሰለማያሳይ አመልካች በዚህ ረገድ ከዲዘይን ኃላፊነት ጋር በተያያዘ ያቀረበዉ ሰበር ቅሬታ በግልፅ ከሚታየዉ ግልግል ጉባዔ ፍርድ እና ዉሳኔ ይዘት ወጭ በመሆኑ አልተቀበልነዉም፡፡
ከዚህም በተጨማሪነትም በአማካሪ መሀንዲሱ ተወስኖ ራሱ በአሰሪው ጭምር በፀደቀዉ ብር 6,564,698 ካሳ ገንዘብ እና 253 ተጨማሪ ቀናት ጉዳይን በተመለከተ አስቀድሞ በዚህ ረገድ ለኤክስፐርቱ በአሰሪዉ የቀረበ ቅሬታም በሌለበት የግልግል ጉባኤው ይሄን ጭምር ተቀብሎ እና ተመልክቶ መወሰኑ ያላግባብ ነው በሚል አመልካች ያቀረበው መከራከሪያም ቢሆን የግልግል ጉባኤው ይሄንኑን ተቀብሎ ሊመለከት የቻለው በኤክስፖርቱ የተወሰነው ብር 28,532,689 ካሳ ገንዘብ ውስጥ አስቀድሞ በመሐንዲሱ የተወሰነዉ(አሰሪዉ ጭምር የፀደቀዉ) ብር 6,564,689.34 ይካተታል? ወይስ አይካተትም? የሚል ክርክር በተጠሪ በኩል በመቅረቡ ምክንያት በመሆኑና እንዲህ ከሆነ ደግሞ የግልግል ጉባዔዉ በአማካሪ መሀንዲሱ ተወስኖ በአሰሪዉ ጭምር የፀደቀዉን ዉሳኔ በዉጤት ደረጃ ሳይለወጥ ከፍ ሲል እንደተጠቀሰዉ በዚህ ረገድ በተጠሪ በኩል በተነሳዉ ክርክር ላይ እልባት ከመስጠት አኳያ ጉዳዩን ማየቱ እና ይሄንኑን የአማካሪ መሀንዲሱን ውሳኔ ጭምር ከግምት ባስገባ እና ታሳቢ ባደረገ መልኩ በሌሎች የክርክር ነጥቦች ላይ መወሰኑ በአግባቡ ሊባል ከሚችል በስተቀር በጉዳዩ ላይ ከአዋጅቁ. 1234/2013 አንቀፅ 2(4) እና 10 ድንጋጌዎች አንፃር መሰረታዊ የሆነ የህግ ስህተት መፈፀሙን የሚያሳይ ባለመሆኑ ይሄንኑን በዚህ ረገድ በአመልካች የቀረበውን ቅሬታ እና መከራከሪያም አልቀበልነውም፡፡በመሆኑም ተከታዩ ተወስኗል፡፡
ዉሳኔ
1.ይሄንን ጉዳይ በተመለከተ የአ/አበባ ንግድ እና የዘርፍ ማህበራት ምክር ቤት በተቋቋመዉ ግልግል ጉባዔ በ5/8/2013ዓ.ም የተሰጠዉ ፍርድ በፍ/ብ/ስ/ስ/ህ/ቁ.348(1) መሰረት ተሻሽሏል፡፡
2.አመልካች በዲዛይን ጉድለት እና መዘግየት ምክንያት ከምርታማነት መቀነስ እና ስራዉ ሙሉ በሙሉ በቆመበት ወቅት ጉደት ደርሶብኛል በማለት አቅርቦ በነበረዉ የካሳ ይገባኛልና እንዲሁም ስራዉ ሙሉ በሙሉ ቆሟል በተባለበት ጊዜ ለባከነዉ ተጨማሪ ጊዜ ይሰጠኝ ሲል አቅርቦ በነበረዉ ዳኝነት ጥያቄ ላይ የሰጠዉ ዉሳኔ ክፍል በፍ/ብ/ስ/ስ/ህ/ቁ.348(1) መሰረት ተሽሯል፡፡አመልካች ይሄንኑን በተመለከተ አማካሪ መሐንዲሱም ሆነ ኤክስፐርቱ በዉሳኔዉ (ዉሳኔ ሀሳብ) በገለፁት መሰረት አቅርቦ በዉላቸዉ መሰረት ተገቢዉን የማስወሰን መብቱ የተጠበቀ ነዉ፡፡
3.ሌላዉ የግልግል ጉባኤዉ ዉሳኔ ክፍል በዚህ ዉሳኔ አልተነካም/አልተለወጠም፡፡
4.የዚህ ሰበር ችሎት ክርክሩ ያስከተለባቸዉን ወጪና ኪሳራ ግራ ቀኙ የየራሳቸዉን ይቻሉ ብለናል፡፡
መዝገቡ ተዘግቷል፣ወደ መ/ቤት ይመለስ፡፡
የማይነበብ የአምስት ዳኞች ፊርማ አለበት
ፍ/ደ