የኢትዮጵያ ፌደራላዊ ዲሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ
የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት
ሰበር ሰሚ ችሎት
የሰ/መ/ቁ. 214557
ቀን ፡- ጥቅምት 28 ቀን 2016 ዓ/ም
ዳኞች- እትመት አሰፋ
ደጀኔ አያንሳ
ኑረዲን ከድር
መላኩ ካሳዬ
ሀብታሙ እርቅይሁን
አመልካቾች ፡- 1. ወ/ሪት ናዲያ በሽር
2. ወ/ሪት ሶፊያ በሽር
3. አቶ ቶማስ በሽር
ተጠሪዎች ፡- 1. ወ/ሮ ማርዬማ አብዱ - ቀረቡ
2. ወ/ሪት ዚነት አብዱ
መዝገቡ ተመርምሮ ተከታዩ ፍርድ ተሠጠ፡፡
ፍርድ
የሰበር አቤቱታው የቀረበው የፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ያጸናው እና የፌዴራል መጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት የሰጠው ውሳኔ መሠረታዊ የሕግ ስህተት ተፈጽሞበታል በሚል ነው፡፡ የክርክሩን አመጣጥ ከስር ፍርድ ቤት የመዝገብ ግልባጭ እንደተረዳነው አመልካቾች በስር ፍርድ ቤት ከሳሾች፤ 1ኛ ተጠሪ ተከሳሽ እና 2ኛ ተጠሪ ጣልቃ ገብ ሆነው ተከራክረዋል፡፡ ጉዳዩ የተጀመረው በፌዴራል መጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት ሲሆን አመልካቾች መጋቢት 03 ቀን 2010 ዓ/ም አሻሽለው ባቀረቡት ክስ ህዳር 18 ቀን 2010 ዓ/ም በውርስ ሀብትነት እንዲጣሩ ከተጠየቁት ንብረቶች በተጨማሪ
በቦሌ ክፍለ ከተማ ወረዳ 9 የቤት ቁጥር አዲስ በካርታ ቁጥር ቦሌ 5/317/7/1049/19/08/01 መኖሪያ ቤት 1ኛ ተጠሪ የሚጠቀሙበት ቤቱ እስካሁን ያስገኘው እና ለወደፊቱ ሊያስገኘው የሚችለው ገቢ፤
በንፋስ ስልክ ላፍቶ ክፍለ ከተማ ወረዳ 01 የሚገኙ ሁለት ቤቶች የቤት ቁጥራቸው አዲስ 144 ካሬ ሜትር ላይ የሰፈሩ ባለ 3 ፎቅ እየተከራዩ ያሉ የኪራይ ገቢያቸው በሟች ወይም በ1ኛ ተጠሪ ስም የሚገኝ፤
ብራ አክሲዮን ማህበር፣ ጀት ኮንስትራክሽን፣ ዲ ፎር ዲ ሃይላክስ ደብል ጋቢና የታርጋ ቁጥር ኮድ 3 አ.አ A31846 በወ/ሮ የሺመቤት ጥላሁን ስም ከቀረጥ ነጻ የገባ አሁን በ1ኛ ተጠሪ እጅ የሚገኝ፤
በቆጠራ ወቅት የተገኙ የቤት ቁሳቁሶች፤
በኢትዮጲያ ንግድ፣ በአዋሽ፣ በኦሮሚያ ኢንተርናሽናል፣ በወጋገን፣ በዘመን፣ በአቢሲኒያ፣ በኦሮሚያ ህብረት ሥራ፣ በአንበሳ ኢንተርናሽናል፣ በህብረት፣ በዳሽን፣ በንብ፣ በቡና ኢንተርናሽናል፣ በደቡብ ግሎባል ባንክ በሟች ወይም በተጠሪ ስም ያለ ገንዘብ፤
አክሲዮን በሟች ወይም በተጠሪ ስም ወይም በአንድንት ያለ ዋስትና (የመድን ዋስትና)፤
የአክስዮን ድርሻ በኦሮሚያ፣ ናይል፣ ብሔራዊ ኢንሹራንስ፤ ናይስ (ህብረት)፣ አፍሪካ፣ ንብ፣ ሉሲ፣ ፀሐይ፣ ኢትዮ ላይፈ፣ አዋሽ፣ ወጋገን ኢንሹራንስ ያለ፤ የመድን ዋስትና ኢንሹራንስ እና አክሲዮን ድርሻ፤
በፌዴራል መጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት በ1ኛ ተጠሪ እና በወ/ሮ የሺመቤት ጥላሁን መካከል በኮ/መ/ቁጥር 246414 የብር 400,000 የቼክ ገንዘብ ክርክር እና በኮ/መ/ቁ 246415 የብር 240,000 የቼክ ገንዘብ ክርክር ላይ የተሰጡ ውሳኔዎች፤ በፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት በ1ኛ ተጠሪ እና በወ/ሮ የሺመቤት ጥላሁን መካከል በኮ/መ/ቁጥር 179663 የብር 600,000 ክርክር፣ በኮ/መ/ቁ 179797 የብር 5,000,000 የቼክ ክርክር እና በኮ/መ/ቁ 190514 የፍትሐ ብሔር ክርክር በቀጠሮ ላይ ያለ እንዲጣራልን በማለት ዳኝነት ጥቀዋል፡፡
1ኛ ተጠሪ መጋቢት 10 ቀን 2010 ዓ/ም በተጻፈ የመከላከያ መልስ
2ቱ ቤቶች፣ ብራ አክሲዮን እና ጄት ኮንስትራክሽን የግል ሀብቶቼ ናቸው ይህንን አስመልክቶ የፌዴራል መጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት በመዝገብ ቁጥር 243134 ውሳኔ ሰጥቷል፤
ዲ ፎር ዲ ሃይላክስ ደብል ገቢና ተሽከርካሪ ንብረትነቱ የወ/ሮ የሺመቤት ጥላሁን ርስቄ የሆነው የየሺ ኮንስትራክሽን የጠጠር ማምረቻ ድርጅት ነው፤
በፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት በኮ/መ/ቁ 179664 ላይ ተይዞ የሚገኘው ገንዘብ ንብረትነቱ የሟች እና የ1ኛ ተጠሪ የጋራ ንብረት መሆኑ አይካድም ነገር ግን ከሳሽ ሟች አቶ በሽር አብደላ ሲሆኑ ክስ የቀረበበት የገንዘብ መጠን 100,000 የአሜሪካን ዶላር በአሁኑ ወቅት የምንዛሪ ዋጋው ብር 2.7 ሚሊየን እንጂ አመልካቾች እንደሚሉት አይደለም፤
በቦሌ ክፍለ ከተማ ወረዳ 9 ክልል ውስጥ የሚገኘው ቤት የ1ኛ ተጠሪ የግል ቤት ሲሆን በቤቱ ውስጥ ይገኛሉ ከተባሉት የቤት ቁሳቁሶች ውስጥ 10 ትራሶች ከእነ ትራስ ጨርቃቸው እና ሳምሰንግ ፍሪጅ ውጪ ያሉት ንብረቶች የእህቴ የስር ፍርድ ቤት 1ኛ ጣልቃ ገብ (ወ/ሮ ዘኒት አብዱ) ንብረቶች ናቸው፤
በአዋሽ፣ በወጋገን፣ በዘመን እና በአቢሲኒያ ባንክ ውስጥ በሟች፣ በ1ኛ ተጠሪ ወይም በጋራ ስማችን የተቀመጠ ገንዘብ የለም፤
በኢትዮጲያ ንግድ ባንክ በ1ኛ ተጠሪ ስም በተከፈተ ሒሳብ ቁጥር 30131453756 ሟች እስካረፉ ድረስ ብር 1,710.67 ብቻ፣ በሟች ስም በተከፈተ ሒሳብ ቁጥር 1000151189532 ሟች እስካረፉበት ጊዜ ድረስ ብር 204.00 ብቻ፣ በኦሮሚያ ኢንተርናሽናል ባንክ በሟች ስም በተከፈተ የሒሳብ ቁጥር 504787 ሟች እስካረፉበት ጊዜ ድረስ ብር 100 ብቻ፣ በዳሽን ባንክ አክሲዮን ማህበር ባንክ በሟች ስም በተከፈተ የሒሳብ ቁጥር 5001903403152 ሟች እስካረፉበት ጊዜ ድረስ ብር 72,213.79 ብቻ፣ በኦሮሚያ ህብረት ሥራ ባንክ በሟች ስም በተከፈተ የሒሳብ ቁጥር 102044 ሟች እስካረፉበት ጊዜ ድረስ ብር 1,000 ብቻ፣ በአንበሳ ኢንተርናሽናል ባንክ ብር 114.42 ብቻ ተቀማጭ ገንዘብ አለ፤
በኢንሹራንስ ኩባኒያዎች በሟች፣ በተጠሪ ወይም በጋራ ስማቸው የተገባ የመድህን ዋስትና የለም፤ በሟች፣ በተጠሪ ወይም በጋራ ስማችን የተገዛ አክሲዮን የለም፤
በከፊል የተወሰኑ እና በከፊል ክርክር ላይ ያሉ የኮ/መ/ቁ 246414፣ 246415፣ 176963 እና 179797 ከወ/ሮ የሺመቤት ጥላሁን ርስቄ ጋር በጋራ ባቋቋመንው ጀት ኮንስትራክሽን የጠጠር ማምረቻ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማህበር በጋራ አቋቁመን ከዚሁ ጋር በተያያዘ ባለን የንግድ ሥራ ግንኙነት መነሻ በግል ድርጅታቸው ስም ለ1ኛ ተጠሪ በቼክ የያዟዋቸው ክፍያዎችን የሚመለከቱ ናቸው፡፡ ሰኔ 20 ቀን 2008 ዓ/ም ከወ/ሮ የሺመቤት ጥላሁን ጋር በተፈራረምነው ተጨማሪ የሽርክና ውል የሺ ኮንስትራክሽን የጠጠር ማምረቻ ኃላ/የተወሰነ የግል ማህበር ከእነ ሙሉ መብት እና ጥቅሙ ወደ ጀት ኮንስትራክሽን የጠጠር ማምረቻ ኃላ/የተወሰነ ተላልፎ በዚሁ ስም የተሰጡት እና በኮ/መ/ቁ 246414፣ 246415፣ 176963 እና 179797 የተያዘው ገንዘብ የ1ኛ ተጠሪ የግል ንብረቶቼ ናቸው፡፡
በመዝገብ ቁጥር 190514 እየተደረገ ያለው የገንዘብ ክርክር አይደለም፤ የጀት ኮንስትራክሽን የጠጠር ማምረቻ ኃላ/የተወሰነ ማህበር አስተዳደር እና ማህበሩ እንዲፈርስ በወ/ሮ የሺመቤት ጥላሁን በአማራጭ የቀረበውን ዳኝነት የሚመለከት ነው፡፡ ቼክን የሚመለከቱ ክርክሮችን በተመለከተ በባንክ የሚገኘው ገንዘብ በአጠቃላይ የ1ኛ ተጠሪ የግል ሀብት መሆኑ ተረጋግጦ ውሳኔ ስለተሰጠ የግሌ ነው በማለት ክርክራቸውን አቅርበዋል፡፡ 2ኛ ተጠሪ ግንቦት 15 ቀን 2010 ዓ/ም በተጻፈ ባቀረቡት የጣልቃ ገብነት አቤቱታ ነሐሴ 04 ቀን 2007 ዓ/ም በተደረገ የብድር ውል ለ1ኛ ተጠሪ ብር 500000፤ እንዲሁም ነሐሴ 10 ቀን 2008 ዓ/ም በተደረገ የብድር ውል የተበደሩት ብር 1600000 የ1ኛ ተጠሪ እና የሟች የጋራ ዕዳ ስለሆነ የውርስ ሀብቱ ከመከፋፈሉ በፊት እንዲከፈለኝ በማለት ዳኝነት ጠይቀዋል፡፡
2ኛ ተጠሪም በውርስ ማጣራት ሂደቱ ማመልከቻ በማቅረብ የንብረት ቁሳቁሶች የግል ንብረታቸው መሆናቸውን እና ብር 700,000.00 ውርሱ ዕዳ ያለበት ስለመሆኑ ክርክር አቅርበዋል፡፡
የፌዴራል መጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤቱ ውርሱ እንዲጣራ በማድረግና ማስረጃ በመስማት መዝገቡን መርምሮ በቦሌ ክፍለ ከተማ ወረዳ 9 እና በንፋስ ስልክ ላፍቶ ክፍለ ከተማ ወረዳ (ቀበሌ) 01 ክልል ውስጥ ያሉ ቤቶች፣ ጀት ኮንስትራክሽን እና በተጠሪ ስም በተለያዩ ባንኮች የሚገኘው ገንዘብ የ1ኛ ተጠሪ የግል ሀብት ነው፤ ምክንያቱም ሟች በሕይወት ሳሉ ነሐሴ 24 ቀን 2008 ዓ/ም በመዝገብ ቁጥር 243134 በተደረገ የንብረት ማግለል ስምምነት ውሳኔ ያገኘ ጉዳይ ስለሆነ በውርስ ሀብትነት የሚጣራበት አግባብ የለም፡፡ ብራ ኮንስትራክሽንን አስመልክቶ አመልካቾች በስህተት ያቀረቡት መሆኑን ስላመኑ ታልፏል፡፡ የሰሌዳ ቁጥር አ.አ 03-A31846 ተሽከርካሪ በየሺ ኮንስትራክሽን የጠጠር ማምረቻ ስም መመዝገቡ እና ወ/ሮ የሺመቤት ጥላሁን 1ኛ ተጠሪ እንዲያስረክቧቸው በፌዴራል መጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት በኮ/መ/ቁ 72234 ክስ ማቅረባቸው ስለተረጋገጠ፤ እንዲሁም የሺ ኮንስትራክሽን ጠጠር ማምረቻ ከነሙሉ መብት እና ጥቅሙ ወደ ጀት ኮንስትራክሽን ስለተቀላቀለ እና ጀት ደግሞ በንብረት ማግለል ስምምነት የ1ኛ ተጠሪ የግል ሀብት ሆኖ የተመዘገበ በመሆኑ ተሽከርካሪው የውርስ ሀብት አይደለም፡፡ በሟች ወይም በተጠሪ የተመዘገበ የአክሲዮን ድርሻ ወይም የመድን ዋስትና ያለመኖሩ ተረጋግጧል፡፡
በሟች ስም በዳሽን ባንክ በሒሳብ ቁጥር 5001903403152 ብር 230.39፣ በሒሳብ ቁጥር 00065187740221996 ብር 964.78፣ በሒሳብ ቁጥር 006518768222 የአሜሪካን ዶላር 1996፣ በየውጪ ገንዘብ ቁጥጥር እና ግብይት ቅርንጫፍ በሒሳብ ቁጥር 5074100321002 የአሜሪካን ዶላር 1117.79፣ በአንበሳ ኢንተርናሽናል ባንክ በሒሳብ ቁጥር 0010025612569 ብር 123.10፣ በኦሮሚያ ኢንተርናሽናል ባንክ በሒሳብ ቁጥር 504787120105011 ብር 105.83፣ ሟች ከወ/ሮ የሺመቤት ጥላሁን ጋር በኮ/መ/ቁ 179664 በነበራቸው የ100000 አሜሪካን ዶላር ክርክር ለሟች የተወሰነ ብር 2233280 የውርስ ሀብት ነው፡፡ ከወ/ሮ የሺመቤት ጥላሁን ጋር በመዝገብ ቁጥር 246414 የብር 400000፣ በመዝገብ ቁጥር 246415 የብር 240000፣ በመዝገብ ቁጥር 176963 የብር 600000 የቼክ ክርክርን በተመለከተ ቼኩ ለተጣሪ የተጻፈ ከመሆኑ ውጪ በምን ምክንያት ቼኩ ሊከፈላቸው እንደቻለ የሚገልጽ ማስረጃ ስለሌለ በሶስቱ መዝገቦች ላይ ብር 1240000 በአጠቃላይ በሟች ስም በባንክ የሚገኝ ገንዘብ ሟች ለወ/ሮ የሺመቤት ጥላሁን አበድረዋቸው የነበረ እና ውሳኔ ያረፈበት ስለሆነ ግማሹ የ1ኛ ተጠሪ ግማሹ የውርስ ሀብት ነው፤ አመልካቾች ብር 600000 ሟች በሕይወት እያሉ የሰጧቸው መሆኑን በምስክሮች የተገለጸና በክርክሩ ስላመኑ ወደ ውርስ ሀብት ተቀላቅሎ ክፍፍል ሊፈጸም ይገባል፡፡ በተጨማሪም ዕዳን አስመልክቶ ሟች በሕይወት እያሉ 1ኛ ተጠሪ ብር 700,000.00 ከ2ኛ ተጠሪ መበደራቸው የተረጋገጠ ሲሆን ይህ የብድር ውል ለትዳር ጥቅም መዋሉ በተጠሪ ምስክሮች እና በሰነድ ማስረጃ ተረጋግጧል፡፡ በመሆኑም ብር 700,000.00 የሟች እና የ1ኛ ተጠሪ የጋራ ዕዳ ስለሆነ ከሥር 2ኛ ጣልቃ ገብ ከነበሩ ሰው ብድር ጋር ብር 1,150,000.00 ከውርስ ሀብቱ ላይ በዕዳነት የሚፈለግ ነው በማለት ወስኗል፡፡
አመልካቾች በዚህ ውሳኔ ቅር በመሰኘት የይግባኝ አቤቱታቸውን ለፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት አቅርበው ፍርድ ቤቱም ዳሽን ባንክ ሂሳብ የተገኘው ገንዘብ፣ ለአመልካቾች በሟች የተሰጠ የስጦታ ገንዘብ፣ በንብረት ማግለል ውል የ1ኛ ተጠሪ የግል ንብረት የተባሉ ቤቶች፣ ጀት ኮንስትራክሽን፣ በተጠሪ ስም በባንክ ያለ ገንዘብ እና 2ኛ ተጠሪ በጠየቁት መሠረት የተረጋገጠው በር 700,000.00 የውርስ ዕዳን በተመለከተ በሥር ፍርድ ቤት የተሰጠው ውሳኔ የሚቀፍበት ምክንያት የለም በማለት ይግባኙን ውድቅ አድርጓል፡፡ በሌሎች ጉዳች ላይ መልስ ሰጨዎችን ያስቀርባል በማለት ክርክር ቀጥሏል፡፡
ይሕ የሠበር አቤቱታ የቀረበው ከፍተኛ ፍርድ ቤቱ ተጠሪዎችን አያስቀርብም በማለት የአመልካቾችን ይግባኝ በመሰረዝ በሰጠው ከፊል ውሳኔ ላይ ነው፡፡ አመልካቾች መስከረም 21 ቀን 2014 ዓ/ም በጻፉት የሰበር አቤቱታ 1ኛ ተጠሪ በዳሽን ባንክ አለ በማለት ያመኑት እና የስር ፍርድ ቤቶች አለ በማለት ከወሰኑት ውሳኔ ጋር የሚቃረን ነው፡፡ የዳሽን ባንክ ሒሳብ ቁጥር 5001903403152 ግልባጩ ከመከላከያ መልስ ጋር ተያይዞ የቀረበው ደብተር ሟች እስካረፉበት ጊዜ ድረስ ቀሪ ተቀማጭ ብር 72,213.59 ያለው መሆኑ ተረጋግጦ ባለበት፤ 1ኛ ተጠሪ 72,213.59 እንዳለ ባመኑበት የስር ፍርድ ቤቶች በዚህ ሒሳብ ቁጥሩ ያለው ቀሪ ሒሳብ ብር 230.39 ብቻ የውርስ ሀብት መሆኑን ባንኩ አረጋግጧል በማለት ውሳኔ መስጠታቸው መስረታዊ የህግ ስህተት የተፈጸመበት ነው፡፡ 2ኛ ተጠሪ በክሱ የተካተቱት የቤት ቁሳቁሶች የግሌ ስለሆኑ ከክሱ ውስጥ እንዲወጡልኝ በማለት አቤቱታ ሲያቀርቡ አመልካቾች የቤት ቁሳቁሶቹ የሟች ስለሆኑ አቤቱታው ውድቅ እንዲደረግልን ጠይቀን ፍርድ ቤቱ አቤቱታውን ውድቅ በማድረግ የውርስ ማጣራቱ በውርስ አጣሪው እንዲጣራ የውርስ አጣሪ ሾሞ ነበር፡፡ ነገር ግን 2ኛ ተጠሪ በተሰጠው ትዕዛዝ ላይ ይግባኝ ሳይሉ፣ የጣልቃ ገብነት አቤቱታ በድጋሚ የቀረበ ነው ብለን እየተከራከርን ሳለ የፌዴራል መጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤቱ ከዚህ በፊት የሰጠውን ትዕዛዝ በሚቃረን መልኩ፣ የጣልቃ ገብነት አቤቱታውን በሚቃረን መልኩ አቤቱታውን በማስተናገድ፣ የተለያዩ የቤት ቁሳቁሶች የ2ኛ ተጠሪ ንብረቶች ናቸው በማለት ውሳኔ መስጠቱም ሆነ የፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ይህ ውሳኔው የሚነቀፍበት አግባብ የለም በማለት ትዕዛዝ መስጠቱ መሰረታዊ የህግ ስህተት ነው፡፡ 2ኛ ተጠሪ ጉዳዩ በሂደት ላይ እንዳለ እያወቁ እና ሲከታተሉት ከቆዩ በኋላ ጉዳዩ በክርክር ላይ ለ5 ወራት ከቆየ በኋላ ግንቦት 14 ቀን 2010 ዓ/ም ሟች በሕይወት እያሉ ለ1ኛ ተጠሪ እና ለሟች በ2 የብድር ውሎች በአጠቃላይ ብር 700,000 ያበደርኳቸው በመሆኑ የውርስ ዕዳ በመሆኑ እንዲከፈለኝ በማለት አመልክተዋል፡፡ አመልካቾች የብድር ውሉ ሟች በሕይወት እያሉ ያልተደረገ መሆኑን፣ አቤቱታቸውን በወቅቱ ያላቀረቡ መሆኑን እና በሀሰት የተዘጋጀ ማስረጃ ነው እያልን፤ 2ኛ ተጠሪ የቤት ቁሳቁሶችን ብቻ በተመለከተ ክርክር ባቀረቡበት እና የብድር ውል አለ በማለት አቤቱታ እንኳን ሳያቀርቡ ክስ የመስማት እና የክርክር ሂደቱ ከተጠናቀቀ በኋላ የብድር ውል በዕዳነት በአቤቱታ ማቅረባቸው፣ አግባብነት ያለው አይደለም፡፡ 2ኛ ተጠሪ ያቀረቡት ማስረጃ ስርዝ ድልዝ ያለበት ነው፤ እውነተኛ ብድር ቢሆን ኖሮ ሟችም በብድር ውል ላይ ተበዳሪ ይደረግ ነበር፤ ነገር ግን ሟች ተበዳሪ እንኳን ተደርገው በውሉ አልሰፈሩም በማለት ተከራክረን ሳለ የስር ፍርድ ቤቶች ያቀረብናቸውን ክርክሮች ውድቅ ያደረገበትን ምክንያት ሳይገልጽ፤ የብድር ውሎቹን ዋና አስቀርቦ ሳያይ የሟች የውርስ ሀብት ዕዳ ነው በማለት እንዲከፈል መወሰናቸው መሰረታዊ የህግ ስህተት የተፈጸመበት ነው፡፡
የ1ኛ ተጠሪ ምስክሮች ናቸው የተባሉት የሰጡት ምስክርነት ሟች ለአመልካቾች ለእያንዳንዳቸው ብር 600,000 በአጠቃላይ ብር 1,800,000 እንደሰጡዋቸው መስማታቸውን የሚገልጽ ነው፡፡ አመልካቾች ሟች በስጦታ መልክ ሰጡን ብለው አምነዋል የተባለው ብር 600,000 ብቻ ነው፡፡ የ1ኛ ተጠሪ ምስክሮች ቃል እና አመልካቾች አመኑት የተባለው የሚፋለስ ነው፡፡ 1ኛ ተጠሪ ሟች ለአመልካቾች ብር 600000 ሰጥተዋቸዋል በማለት ያቀረቡት የባንክ ደረሰኝ 1ኛ ተጠሪ ለ2ኛ አመልካች በባንክ የላኩላቸውን ገንዘብ እንጂ ሟች ለአመልካች የሰጡዋቸው ስጦታ መሆኑን የሚያረጋግጥ አይደለም፡፡ ሟች በሕይወት እያሉ ለአመልካቾች የሰጡዋቸው ስጦታ የለም፡፡ በመሆኑም በማስረጃ የተረጋገጠው እና በአመልካቾች የታመነው ወደ ውርስ ሀብት ተቀላቅሎ ክፍፍል ይፈጸም በማለት በስር ፍርድ ቤቶች የተሰጠው ውሳኔ መሰረታዊ የህግ ስህተት የተፈጸመበት ነው፡፡ 1ኛ ተጠሪ ከሟች ጋር ጋብቻ መፈጸማቸው የሚያረጋግጥ የጽሑፍ ማስረጃ ስላላቀረቡ በምስክሮች እንዲረጋገጥ ፍርድ ቤቱ ትዕዛዝ ሰጥቷል፡፡ በዚሁ መሰረት የተሰሙት ምስክሮቹ ሟች በሌሉበት ስለሆነ እና ፍርድ ቤት ሟች በሌሉበት ምስክሮች እንዲሰሙ ትዕዛዝ ባልሰጠበት ስለሆነ ሟች ንብረቱ የተጠሪ የግል ንብረት ቢባል አልቃወምም ብለዋል በማለት የተጻፈው እውነተኛ አይደለም፡፡ ይህንን እውነታ ማረጋገጥ የሚቻለው 1ኛ ተጠሪ ጋብቻው የመን ሀገር ተፈጸመ ሲሉ ምስክሮቻቸው ሀገር ውስጥ ጊምቢ ነው ማለታቸው እና ጋብቻው ተፈጸመ የሚሉበት ጊዜ የተለያየ መሆኑ ነው፡፡ በመሆኑም በቦሌ ክፍለ ከተማ ወረዳ 09 እና በንፋስ ስልክ ላፍቶ ክፍለ ከተማ ወዳ 01 ያሉ ቤቶች፣ የተከራዩ ቤቶችን ገቢ 1ኛ ተጠሪ በግላቸው እየወሰዱት ያለውን፣ የጄት ኮንስትራክሽን እና በተለያዩ ባንኮች በ1ኛ ተጠሪ ስም የሚገኝ ገንዘብ 1ኛ ተጠሪ የግል ንብረታቸው ስለመሆናቸው በመዝገብ ቁጥር 243134 በተሰጠ የንብረት ማግለል ውሳኔ ስላረጋገጡ በውርስ የሚጣራበት ምክንያት የለም፤ የውርስ ንብረት አይደለም በማለት የስር ፍርድ ቤቶ የሰጡት ውሳኔ መሰረታዊ የህግ ስህተት የተፈጸመበት ነው በማለት የስር ፍርድ ቤቶቹን ውሳኔ በመሻር ይህ ችሎት ንብረቶቹ የሟች እና የ1ኛ ተጠሪ የጋራ ሀብት ስለሆኑ የውርስ ንብረቶች ናቸው በማለት እንዲወሰንልን፡፡ የጀት ኮንስትራክሽን ድርጅት የሟች እና የ1ኛ ተጠሪ የጋራ ንብረት እንጂ የ1ኛ ተጠሪ የግል ንብረት ስላልሆነ የሰሌዳ ቁጥር አ.አ 03-A31846 የጄት ኮንስትራክሽን ንበረት ስለሆነ፤ በወ/ሮ የሺመቤት ጥላሁን ስም ቢመዘገብም በሟች ገንዘብ የተገዛ ስለሆነ የ1ኛ ተጠሪ የግል ንብረት ነው መባሉ መሰረታዊ የህግ ስህተት የተፈጸመበት ነው፡፡ በመሆኑም በአጠቃላይ በዳሽን ባንክ ያለው ገንዘብ ብር 72213.59፣ በቦሌ እና በንፋስ ስልክ ላፍቶ የሚገኙት ቤቶች፣ ጀት ኮንስትራክሽን፣ በባንክ በተጠሪ ስም የሚገኘው ገንዘብ፣ የሰሌዳ ቁጥር አ.አ 03-A31846 የውርስ ንብረቶች ናቸው እንዲባሉ እና ክርክር የተነሳባቸው የቤት ቁሳቁሶች እና የብድር ውሎችን በተመለከተ ፍርድ ቤቱ የቀረበውን አቤቱታ መሰረት በማድረግ የሰጠውን ውሳኔ በመሻር ቁሳቁሶቹ የውርስ ሀብት ናቸው እንዲባሉ እና በብድር ምክንያት ከሟች የውርስ ንብረት ላይ እንዲከፈል የተባለው ተሸሮ ሙሉ ለሙሉ የውርስ ሀብት ነው ተብሎ እንዲወሰንልን በማለት ዳኝነት ጠይቀዋል፡፡
የሰበር አጣሪው ችሎት ጉዳዩን ተመልክቶ በግራቀኙ መካከል ባለው ክርክር የአሁን 1ኛ ተጠሪ የሆኑት ለአመልካቾች ለእያንዳንዳው ከውርስ ሀብቲ ብር 600,000.00 ተሰጥቷል በማለት ላቀረቡት ክርክር አመልካቾች ገንዘቡን መቀበላቸውን አምነዋል በማለት ገንዘቡ ከውርስ ሀብቱ ታሳቢ ይደረግ ተብሎ የተሰጠው ውሳኔ ተገቢ መሆን አለመሆኑን ለማጣራት ተጠሪዎች መልስ እንዲያቀርቡ አዟል፡፡
1ኛ ተጠሪ የካቲት 16 ቀን 2014 ዓ/ም በሰጡት የመከላከያ መልስ የስር ፍርድ ቤቶች ውሳኔ በአዋጅ ቁጥር 1234/2013 አንቀጽ 2(4) ስር የተዘረዘሩትን መሰረታዊ የህግ ስህተት ተፈጽሟል የሚያሰኙትን አንዳቸውንም ነጥብ ያላስረዱ በመሆኑ የተፈጸመ መሰረታዊ የህግ ስህተት የለም፡፡ አመልካቾች ጉዳዩ ለሰበር ያስቀርባል በተባለው ነጥብ ላይ ያቀረቡት ቅሬታ መሰረታዊ የህግ ስህተትን መሰረት ያደረገ ሳይሆን ማስረጃን የሚመለከት በስጦታ የወሰዱትን ገንዘብ ይመልሱ ተብሎ ምስክሮች የሰጡትን ቃል መሰረት አድርጎ የተሰጠን ውሳኔ መሰረት ያደረገ እና የማስረጃ ክርክርን መሰረት ያደረገ ስለሆነ ቅሬታቸው መሰረታዊ የህግ ስህተት መፈጸሙን አያስረዳም ተብሎ ውድቅ እንዲደረግልን፡፡ ለሰበር ያስቀርባል ከተባለው ጭብጥ አኳያ የሟች የውርስ ንብረት የሆነ ገንዘብ ለአመልካቾች የተከፈላቸው መሆኑን አልካዱም፤ 2ኛ አመልካች አምነዋል፡፡ አከራካሪው ገንዘብ የተከፈላቸው ለመሆኑ በአመልካቾች ያልተካደ እና በባንክ ቤት ደረሰኝ ማስረጃነት የተረጋገጠ ስለሆነ ገንዘቡ ወደ ሟች ውርስ ሀብት ይመለስ ተብሎ በስር ፍርድ ቤቶች የተሰጠው ውሳኔ የሚነቀፍበት ምክንያት የለም፡፡ ሟች በሕይወት እያሉ በእሳቸው ትዕዛዝ ከ1ኛ ተጠሪ ጋር በጋብቻ ውስጥ በነበሩበት ወቅት 1ኛ ተጠሪ ለ2ኛ አመልካች በባንክ በኩል የተላለፈለቸው ብር 600,000 በጋራ ካፈሩት ንብረት ላይ ለዛውም ከሟች ድርሻ ላይ በመሆኑ በ1ኛ ተጠሪ በኩል በባንክ በኩል መላኩ የሚያስከትለው ህጋዊ ውጤት የለም፡፡ በመሆኑን የስር ፍርድ ቤቶች ውሳኔ መሰረታዊ የህግ ስህተት የተፈጸመበት አይደለም ተብሎ እንዲጸናልን በማለት ዳኝነት ጠይቀዋል፡፡ 2ኛ ተጠሪ የካቲት 16 ቀን 2014 ዓ/ም በተጻፈ የመከላከያ መልስ ያስቀርባል ከተባለው ጭብጥ አኳያ አከራካሪው ጭብጥ 2ኛ ተጠሪን የሚመለከት ጉዳይ አይደለም፤ በስር ፍርድ ቤቶች በዚህ ነጥብ ላይ በአመልካቾች እና በ2ኛ ተጠሪ መካከል ክርክር አልነበረም፡፡ በመሆኑም አመልካቾች ከ2ኛ ተጠሪ ጋር ካላቸው ክርክር አኳያ ያስቀርብላ ያልተባለ በመሆኑ አይመለከተኝም በማለት ወጪ እና ኪሳራ እንዲተካላቸው ታዞ ከአቤቱታው እንዲሰናበቱ ጠይቀዋል፡፡ አመልካቾች መጋቢት 08 ቀን 2014 ዓ/ም በተጻፈ የመልስ መልስ 1ኛ ተጠሪ የአመልካቾችን የሰበር ቅሬታዎች በሙሉ በሚመለከት መልስ ያልሰጡ ወይም በመሸሽ የተሰጠ መልስ በመሆኑ መልስ መስጠት እንዳልፈለጉ የሚቆጠር ወይም የሰበር ቅሬታዎቹን እንዳመኑ ተቆጥሮ ውሳኔ እንዲሰጥልን በማለት የሰበር አቤቱታቸውን በማጠናከር ተከራክረዋል፡፡
የክርክሩ ሂደት በአጭሩ ከላይ የተገለጸው ሲሆን እኛም የሥር ፍርድ ቤት ውሳኔ ላይ የተፈጸመ መሠረታዊ የሕግ ስህተት መኖር አለመኖሩን እንደሚከተለው መርምረናል፡፡
እንደመረመርነው አመልካቾች ያቀረቡት የክስ አቤቱታ የሟች አቶ በሽር አብደላ የውርስ ሀብት እንዲጣራ ሲሆን 1ኛ ተጠሪ ሟች ባለቤት ሲሆኑ የሥር ተከሳሽ በመሆን እና 2ኛ ተጠሪ ደግሞ ጣልቃ በመግባት የውርሱ ዕዳ እንዲጣራላቸው አመልክተዋል፡፡ አሁን በዚህ ችሎት አከራካሪ ሆነው የቀረቡት በዳሽን ባንክ የሚገኝ ገንዘብ፣ የ2ኛ ተጠሪ ናቸው በተባሉ ቁሳቁስ ንብረቶች፣ የ1ኛ ተጠሪ ያደረጉትና በፍርድ ቤት የጸደቀው የማግለል ውል የተመለከቱት ንብረቶች የግል መባላቸው፣ ለአመልካቾች ሟች በሕይወት ያሉት ሰጡት የተባለ ገንዘብ አለ ተብሎ መወሰኑ እና የ2ኛ ተጠሪ ባቀረቡት ክርክር መሠረት ውርሱ ብር 700,000.00 ዕዳ አለበት መባሉን የተመለከተ ነው፡፡
ክርክሩን በፍትሐ ብሔር ሥነ-ሥርዓት ሕጉ መሰረት መምራት እና መቆጣጠር የፍርድ ቤቱ ኃላፊነት ሲሆን በተገቢው ሁኔታ ካልተመራ የሥነ-ሥርዓት ሕጉን ዓላማዎች የሆኑትን እንደ አንጻራዊ እውነትን የመፈለግ፣ ሥነ-ሥርዓታዊ ፍትህ፣ ክርክርን ውጤታማ፣ ወጭና ጊዜ ቆጣቢ በሆነ አግባብ መምራት የመሳሰሉትን ማሳካት ስለማይቻል የተከራካሪዎችን መብት ይነካል፡፡ ክርክር የሚወሰነው በተጠየቀው ዳኝነት አግባብ እንደሆነ የፍብ/ሥ/ሥ/ሕ/ቁ. 182(2) ላይ ተመልክቷል፡፡ ፍርድ ቤቱም ከቀረበው ዳኝነት አኳያ ከግራቀኙ ክርክር በመነሳት በፍብ/ሥ/ሥ/ሕ/ቁ. 246 እና ተከታዮቹ መሠረት በተነሱት ጉዳዮች ጭብጥ መስርቶ ውሳኔ የመስጠት ኃላፊነት አለበት፡፡ የፍሬ ነገር ጭብጦች ናቸው፡፡ በክርክር ሂደት ፍሬ ነገሮችን ማረጋገጥ የሚቻልባቸው ዘዴዎች ማስረጃ፣ በፍርድ ቤት በሚሠጥ የእምነት ቃል፣ ፍርድ ቤት በራሱ ግንዛቤ ሊወስድባቸው የሚችሉ ጉዳዮች፣ የሕግ ግምት እና የመሓላ ቃል ናቸው፡፡ በፍትሐ ብሔር ክርክር የምንከተለው የማስረዳት ደረጃ ከሁለቱ ወገን የተሻለ ያስረዳው ማን ነው (preponderance of evidence) የሚለውን በመመርመር ነው፡፡ የማስረጃ ተገቢነት (relevancy test)፣ የማስረጃው ተቀባይነትን (admissibility) ደንቦችን መከተል እና ለማስረጃው የሚሰጠውን ክብደት (weight of evidence) በመለየት የመወሰን ኃላፊነት ማስረጃ ለመስማትና ለመመዘን ኃላፊነት ያለባቸው ፍርድ ቤቶች ዋና ተግባር ነው፡፡ ፍርድ በሚሰጥበት ጊዜም ምክንያትን ማስፈር እንደሚገባ በፍትሐ ብሔር ሥነ-ሥርዓት ሕጉ አንቀጽ 182(1) የተመለከተ ግዴታ ነው፡፡ ፍርድ በሚጻፍበት ጊዜ ስለጉዳዩ መግቢያ፣ በክርክሩ የተነሱትን ፍሬ ነገሮች ማስፈር፣ ምላሽ የሚያስፈልገውን የፍሬ ነገር ወይም የሕግ ጭብጥ መለየት፣ በተለየው ጭብጥ ማስረጃውን በመመዘን እና ተፈጻሚነት ያለውን ሕግ በመተግበር ለውሳኔው ምክንያትን በማስፈር ዳኝነት የተጠቀበትን ጉዳይ እልባት መሥጠትን ይጠይቃል፡፡ በዚህም ተከራካሪ ወገን በአግባቡ የተሰማ፣ ማስረጃው በአግባቡ ግምት ውስጥ የገባና ዳኛው ሕጉን እና የቀረበውን ማስረጃ መሠረት አድርጎ የወሰነው ስለመሆኑ ሊያረጋግጥ ይገባል፡፡
በተያዘው ጉዳይ በሥር ፍርድ ቤት የሟች አቶ በሽር አብደላ ውርስ ውርስ አጣሪ የተሾመ ሲሆን የውርስ ሀብቱ፣ የውርሱ ዕዳ፣ ወራሾች እና ድርሻቸው የሚመለከት ሪፖርት ቀርቦ ግራቀኙ ክርክር አቅርበውበትና በማስረጃ ተጣርቶ ውሳኔ መሰጠቱን ተገንዘበናል፡፡ አመልካቾች በሰበር አቤቱታ ያቀረቡት የዳሽን ባንክ በሟች ስም የሚገኝ ሂሳብ በተመለከተ በሥር ፍርድ ቤት ዝርዝር ሂሳብ መግለጫ ቀርቦበት ሠነዱን መሠረት ተደርጎ ውሳኔ የተሰጠበት ነው፡፡ ለአመልካቾች ሟች በሕይወት እያሉ የሰጡት ገንዘብ ወደውርሱ እንዲመለሱ በቀረበው ክርክር መሠረት ማስረጃ ተሰምቶና አመልካቾች በዚህ ረገድ ያቀረቡትን ክርክር በመመልከት የተደረሰበት የፍሬ ነገር ድምዳሜ ነው፡፡ የ1ኛ ተጠሪ የግል ንብረት የተባሉ በቦሌና በንፋሰ ስልክ ላፍቶ ክፍለ ከተማ የሚገኙ ቤቶች፣ ጀት ኮንስትራክሽንና በዚህ ድርጅት የተመዘገበ ተሽከርካሪ፣ በ1ኛ ተጠሪ ስም ባንክ ሂሳብ ያለ ገንዘብ በተመለከተ 1ኛ ተጠሪ ከሟች ባለቤተቻው አቶ በሽር አብደላ ጋር በ24/12/2008 ዓ/ም ባደረጉት የንብረት ማግለል ውል የ1ኛ ተጠሪ የግል ንብረት መሆናቸው የተመላከተና የንብረት ማግለል ውሉም በፍርድ ቤት በመዝገብ ቁጥር 243134 የጸደቀ መሆኑን መሠረት በማድረግ የውርስ ሀብት አይደሉም መባሉ በፍርድ ቤት የጸደቀውን የንብረት ማግለል ውል መሠረት ያደረገ ነው፡፡ ይሕም የሥር ፍርድ ቤት የቀረበውን ክርክርና ማስረጃ በመስማት የደረሰበት የፍሬ ነገር ድምዳሜ መሆኑን ያሳያል፡፡ የፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ሰበር ሰሚ ችሎት በኢፌዲሪ ሕገ-መንግሥቱ አንቀጽ 80(3) ሆነ የፌደራል ፍርድ ቤቶች አዋጅ ቁጥር 1234/2013 አንቀጽ 10 ላይ በመጨረሻ ውሳኔ ላይ በተፈጸመ መሠረታዊ የሕግ ስህተት እንጂ የፍሬ ነገር ክርክር እንዲመለከት ሥልጣን ያልተሰጠው ስለሆነ በዚህ ረገድ የቀረበው የሰበር አቤቱታ ተቀባይነት የለውም ብለናል፡፡
በሌላ በኩል አመልካቾች ከ2ኛ ተጠሪ አንጻር ያቀረቡት ሰበር አቤቱታ ሁለት ጊዜ የጣልቃገብት አቤቱታ ማቅረባቸው ሆነ ብር 700,000.00 የውርስ ዕዳ ነው መባሉ ስህተት አለበት የሚል ነው፡፡ የውርስ ማጣራት ሥራ በፍ/ሕ/ቁ. 942 እና ተከታይ ድንጋጌዎች እንደተመለከተው የውርስ ሀብትና ዕዳ መለየት፣ ኑዛዜ መኖር አለመኖሩን ማጣራት፣ ወራሾችን እና ድርሻቸውን የመለየትና የማጣራት ተግባር የሚከናወንበት ሂደት በመሆኑ ውርሱ ዕዳ ያለበት መሆን አለመሆኑና ዕዳ ካለበትም የዕዳውን መጠን ማጣራት ዋና ተግባር ነው፡፡ ስለዚህ ውርስ ማጣራት ከሌሎች የክስ አቤቱታዎች ያለውን የተለየ ባሕሪ መገንዘብ ያሰፈልጋል፤ 2ኛ ተጠሪ በክርክሩ የጣልቃገብነት አቤቱታ ባያቀርቡም ውርሱ ዕዳ ያለበት መሆኑ ከተረጋገጠ ውርስ አጣሪው ዕዳውን በሪፖርቱ ማካተት ይኖርበታል፡፡ በክርክሩ ሂደት የውርስ ሀብቱ ብር 700,000.00 ዕዳ ያለበት ስለመሆኑ በቀረበው ማስረጃ መረጋገጡን የሥር ፍርድ ቤት በውሳኔው አስፍሮ የውርስ ዕዳ ነው ማለቱ የማስረጃ ምዘና የሚመለከት በመሆኑ በዚህ ችሎት የሚመረመር ጭብጥ አይደለም፡፡ 2ኛ ተጠሪም በሥር ፍርድ ቤት ከፊል ንብረቶች ላይ የተሰጠው እግድ እንዲነሳ ሲያመልክቱ በክርክሩ ጣልቃ ገብተው ካልጠየቁ በስተቀር የእግድ ይነሳልኝ አቤቱታው የማይመረመር ስለመሆኑ የሥር ፍርድ ቤት ትዕዛዝ መስጠቱን ተከትሎ እግድ የተሰጠባቸውና የእኔ ናቸው የሚሏቸውን ንብረቶች በተመለከተ የጣልቃገብነት አቤቱታ ያቀረቡ መሆኑን ከቀረበው የሥር መዝገብ የክርክር ሂደት ተገንዝበናል፡፡ ክርክር የቀረበባቸው ንብረቶች ላይ ማስረጃ መሠረት ተድርጎ ውሳኔ መሰጠቱ ተገቢ ነው፡፡ 2ኛ ተጠሪም በተጨማሪነት ውርሱ ላይ የሚጠይቁት ዕዳ መኖሩን ገልጸው ዕዳው እንዲጣራ መጠየቃቸው የውርስ ማጣራት ሂደትን መሠረት ያደረገ ነው ከሚባል በስተቀር በሂደቱ ሆነ በውጤቱ የተፈጸመ መሠረታዊ የሆነ የሕግ ስህተት አላገኘንበትም፡፡ ስለሆነም ተከታዩ ውሳኔ ተሰጥቷል፡፡
ውሳኔ
1. የፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት በመዝገብ ቁጥር 274531 ሐምሌ 07 ቀን 2013 ዓ/ም እና የፌዴራል መጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት በመዝገብ ቁጥር 64892 መጋቢት 29 ቀን 2013 ዓ/ም ዳሽን ባንክ ሂሳብ የተገኘው ገንዘብ፣ ለአመልካቾች በሟች የተሰጠ የስጦታ ገንዘብ፣ በንብረት ማግለል ውል የ1ኛ ተጠሪ የግል ንብረት የተባሉ ቤቶች፣ ጀት ኮንስትራክሽን፣ በተጠሪ ስም በባንክ ያለ ገንዘብ እና 2ኛ ተጠሪ በጠየቁት መሠረት የተረጋገጠው በር 700,000.00 የውርስ ዕዳን በተመለከተ የሠጡት ውሳኔ በሰበር ሥነ-ሥርዓት መመሪያ ቁጥር 17/2015 አንቀጽ 9(1)(ሀ) መሰረት ፀንቷል፡፡
2. በዚህ ችሎት ለወጣ ወጭና ኪሣራ ግራቀኙ የየራሳቸውን ይቻሉ ብለናል፡፡
ትዕዛዝ
የውሳኔው ግልባጭ ለስር ፍርድ ቤቶች ይተላለፍ፡፡
የሥር ፍርድ ቤት መዝገብ ይመለስ፡፡
መዝገቡ ተዘግቷል ወደ መዝገብ ቤት ይመለስ፡፡
የማይነበብ የአምስት ዳኞች ፊርማ አለበት
ፅ/ወ