ሰኔ 27 ቀን 2014 ዓ/ም
ዳኞች፡- ተፈሪ ገብሩ (ዶ/ር)
ቀነአ ቂጣታ
ፈይሳ ወርቁ
ደጀኔ አያንሳ
ብርቅነሽ እሱባለው
አመልካች፡- አቶ ግርማቸው ወርቅነህ - አልቀረቡም
ተጠሪ፡- ድል በትግል አክስዮን ማህበር - ጠበቃ አለዊ ከድር ቀረቡ
መዝገቡ ተመርምሮ ተከታዩ ፍርድ ተሰጥቷል።
ፍ ር ድ
በዚህ መዝገብ የተያዘው ጉዳይ የጠቅላላ ጉባኤ ውሳኔ እንዲሻር የቀረበ የዳኝነት ጥያቄን የሚመለከት ሲሆን የሰበር አቤቱታው የቀረበው የፌደራል መጀመሪያ ደረጃ ፍ/ቤት በመ/ቁ 200878 በቀን 13/12/2013 ዓ.ም የሰጠው ውሳኔ እና የፌደራል ከፍተኛ ፍ/ቤት በመ/ቁ 280639 በቀን 21/04/2014 ያሳለፈው ትእዛዝ መሰረታዊ የህግ ስህተት የተፈጸመበት በመሆኑ ይታረምልኝ በማለት አመልካች ስለጠየቁ ነው።
ከመዝገቡ መረዳት እንደሚቻለው በመጀመሪያ ደረጃ ፍ/ቤት የአሁን አመልካች በቀን 05/11/2013 ዓ.ም ባቀረቡት አቤቱታ በተጠሪ ማህበር ውስጥ ባለአክስዮንና የማህበሩ ቦርድ ሰብሳቢ ነኝ፤ ተጠሪ 50 አባላት ያሉት ሲሆን የማህበሩ ጠቅላላ ጉባኤ ሊጠራ የሚችለው በማህበሩ መመስረቻ ጽሁፍና በንግድ ህጉ አዋጅ ቁጥር 1243/2013 መሰረት በቦርድ ወይም በኦዲተር አማካኝነት ነው፤ የማህበሩ ቦርድ ሰብሳቢ የሆንኩት ከሳሽ ከአቅም በላይ በሆነ ምክንያት ልገኝ የማልችል ካልሆነ በቀርም የጠቅላላ ጉባኤው ስብሰባ የሚመራውም በከሳሽ አማካኝነት ነው፤ ጠቅላላ ጉባኤው ከመደረጉ 15 ቀናት በፊት ስለስብሰባው መኖር በጽሁፍ ወይም በማስታወቂያ ለባለአክስዬኖች ሁሉ መገለጽ ይገባዋል፤ የጠቅላላ ጉባኤው በምን ጉዳይ ላይ እንደሚነጋገርም አጀንዳው አስቀድሞ ለአባላት መገለጽ የሚገባው ስለመሆኑ ሁሉ ተደንግጓል፡፡ ሰኔ 19/2013 ዓ.ም በደንቡና ህጉ መሰረት ከሳሽ በቦርድ ሰብሳቢነት የተገኘሁበትን ስብሰባ በጥቂት አባላት በተፈጠረ ረብሻ ምክንያት የጠቅላላ ጉባኤው ስብሰባው ሳይደረግ ቀርቷል፡፡ ይሁን እንጂ ህጋዊ የነበረውን ስብሰባ በሀይል የበተኑ የማህበሩ አባላት በሳምንቱ ሰኔ 26/2013 ዓ.ም ህግን ባልተከተለ ሁኔታ በሚስጥር ጠቅላላ ጉባኤ በማድረግ ሀምሌ 3/2013 ዓ.ም ቃለ ጉባኤው ጸድቆ እንዲመዘገብ መጠየቃቸውን አሁን የተረዳሁ በመሆኑ ይህ ጠቅላላ ጉባኤ የተጠራው ስብሰባውን መጥራት በማይችሉ አባላት በመሆኑ፣ ከሳሽ ሳላውቅና በሰብሳቢነት ሳልገኝ የተደረገ በመሆኑ፣ ለሁሉም አባላት ጥሪ ሳይደረግ የተወሰኑ አባላት ብቻ ከደንቡ ውጭ ከ1 ቀን በፊት ጥሪ ተደርጎላቸው በመሆኑ፣ ጠቅላላ ጉባኤውም በምን ጉዳይ ላይ እንደሚነጋገር በጥሪው ወረቀት ላይ ያልተገለጸ በመሆኑ ስብሰባው ህገወጥ ነው፡፡ በመሆኑም በቀን 26/10/2013 ዓ.ም የተደረገው ጠቅላላ ጉባኤ ከማህበሩ መመስረቻ ጽሁፍ፣ መተዳደሪያ ደንብ፣ ከንግድ ህጉ አዋጅ ቁጥር 1243/2013 በሚቃረን መልኩ የተደረገ በመሆኑ ስብሰባው ላይ የተሰጡ ውሳኔዎች እንዲሻሩ ይወሰንልኝ በማለት ዳኝነት ጠይቀዋል፡፡
ተጠሪ በቀን 03/12/2013 ዓ.ም በሰጠው መልስ በመጀመሪያ ደረጃ መቃወሚያነት ከሳሽ በተሰጣቸው የስራ ሀላፊነት ልክ ለመምራት ባለመቻላቸው፣ አብረው ያሉትን አመራሮች ሀሳብ ካለመቀበልም በላይ በመሳደብና የስነ ምግባር ብልሹነት በማሳየት በተደጋጋሚ እንዲያስተካክሉ በጠቅላላ ጉባኤ ቢገለጽላቸውም ሊያስተካክሉ ባለመቻላቸው፣ አባላቶቹን በዘርና በሀይማኖት በመከፋፈልና በማሳመጽ እንዲሁም የቦርድ አባላትን ከህግ ውጭ የሚያግዱ በመሆናቸው፣ ከማህበሩ ስራ አመራር ቦርድ እውቅና ውጭ ተጋባዦችን በመጥራት ግርታን በመፍጠር ከሳሽ ራሳቸው ባደራጇቸው ግለሰቦች ብጥብጥ ተነስቶ የነበረ በመሆኑ የማህበሩ አባላቶች ሳይበተኑ በቀሪ የቦርድ አባላቶች ፊርማ ተሰብስቦ በአስቸኳይ ስብሰባ ከ8 ቀን በፊት በመጥራት ጠቅላላ ጉባኤ በማካሄድ ሰኔ 26/2013 ዓ.ም 2/3ኛ በሆነ ድምጽ ከሳሽ ከቦርድ አባልነት እንዲነሱ የተወሰነ እና ከቀረበው አጀንዳና ሌሎች በአክስዬኑ ህልውና ላይ በመወያየት ቃለ ጉባኤውን በቀን 02/11/2013 ዓ.ም ያጸደቀ ሲሆን ይህ ደግሞ አክስዮን ማህበሩ ላይ የሚደርሰውን ጉዳት ለመታደግና ለማበልጸግ የተደረገ በመሆኑ የሚነቀፍበት የህግ ምክንያት የለም፡፡ በመሆኑም በማህበሩ መመስረቻና መተዳደሪያ ደንብ መሰረት ከሳሽ ከአቅም ማነስ ምክንያት በተገቢው ሊሰሩ ባለመቻላቸው የተነሱ በመሆኑ ልነሳ አይገባም የሚል ክስ ሊያቀርቡ አይችሉም፡፡ በንግድ ህጉ አዋጅ ቁጥር 1243/2013 አንቀጽ 305(1) መሰረት ተቃራኒ የሆነ ድንጋጌ በማህበሩ መመስረቻ ጽሁፍ ውስጥ ቢኖርም ጠቅላላ ጉባኤው የቦርድ አባላትን በማናቸውም ጊዜ መሻር እንደሚችል የተደነገገ በመሆኑ ከሳሽን ከቦርድ አባልነት መሻራቸው በህጉ አግባብ በመሆኑ ማህበሩን የሚያስጠይቀው ባለመሆኑ ክሳቸው ውድቅ ሊደረግ ይገባል፡፡ በተጨማሪም በንግድ ህጉ አንቀጽ 305(2) መሰረት ማህበሩ ከሳሽን ያነሳው በህግና በስነ ምግባር ብልሹነት የማህበሩ ህልውና አደጋ ላይ በመውደቁ ሲሆን ይህ እንኳን ሳይሆን ያለበቂ ምክንያት እንኳን የተሻረ የቦርድ አባል ወደ ሀላፊነት የመመለስ መብት የለውም፤ ሆኖም ማህበሩን የጉዳት ካሳ መጠየቅ እንደሚችል የተደነገገ በመሆኑ ከሳሽ ያቀረቡት የጉዳት ካሳ ክስ ባለመሆኑ ክሱ ውድቅ እንዲደረግ በማለት ተከራክሯል፡፡
የስር ፍርድ ቤት ክርክሩንና የተጠሪን የፍሬ ነገር ማስረጃዎች ከመረመረ በኋላ ከሳሽ ያቀረቡት ክስ የማህበሩ ጠቅላላ ጉባኤ በቀን 26/10/2013 ዓ.ም ያስተላለፈው ውሳኔ ይሻርልኝ የሚል በመሆኑና ጠቅላላ ጉባኤው ደግሞ ያስተላለፈው ውሳኔ ከሳሽን ከማህበሩ የቦርድ ሰብሳቢነት የሻረ ስለሆነ፤ የጠቅላላ ጉባኤውን ውሳኔ መሻር ደግሞ ከሳሽን ወደ ማህበሩ የቦርድ ሰብሳቢነት ተመለስ ብሎ መወሰን በመሆኑና ከቦርድ አባልነት የተሻረ የማህበር ቦርድ አባልን ወደ ስልጣኑ የሚመለስበት የህግ አግባብ የሌለ በመሆኑ የከሳሽ ክስ የንግድ ህጉን ድንጋጌ ተከትሎ የቀረበ ባለመሆኑና የንግድ ህግን ድንጋጌ የሚቃረን በመሆኑ የከሳሽ ክስ የክስ ምክንያት የለውም በማለት ክሱን በመጀመሪያ ደረጃ መቃወሚያ ውድቅ በማድረግ ውሳኔ ሰጥቷል፡፡
በዚህ ውሳኔ ቅር በመሰኘት ከሳሽ ለከፍተኛ ፍ/ቤት ይግባኝ ቢያቀርቡም ተቀባይነት አላገኙም፡፡ የሰበር አቤቱታው የቀረበው በዚህ ነው።
አመልካች በቀን 25/04/2013 ዓ/ም ባቀረቡት ማመልከቻ ተፈፀመ የሚሉትን የህግ ስህተት ዘርዝረው የስር ፍ/ቤቶች ውሳኔ ተሽሮ ጉዳዩ እንደገና ታይቶ ተገቢው ውሳኔ እንዲሰጥልኝ በማለት ቅሬታቸውን አቅርበዋል፡፡
ቅሬታው በሰበር አጣሪ ችሎት ተመርምሮ ጉዳዩ ለሰበር ችሎቱ እንዲቀርብና ተጠሪ መልስ እንዲሰጥበት ተደርጓል፡፡ ተጠሪ በቀን 24/05/2014 ዓ.ም ባቀረበው መልስ በስር ፍርድ ቤት ያቀረበውን ክርክር በማጠናከር የስር ፍ/ቤቶች ውሳኔ የህግ ስህተት የለበትም ተብሎ እንዲጸና ጠይቋል፡፡ አመልካችም የመልስ መልስ አቅርቧል፡፡
የጉዳዩ አመጣጥ ባጭሩ ከላይ የተመለከተው ሲሆን በበኩላችን የአመልካች ክስ የክስ ምክንያት የለውም በማለት ክሱን በመጀመሪያ ደረጃ መቃወሚያ ውድቅ በማድረግ የተሰጠው ውሳኔ ከአመልካች የዳኝነት ጥያቄ ይዘትና ለጉዳዩ ተፈፃሚነት ካላቸው የህጉ ድንጋጌዎች አንፃር ተገቢ መሆን አለመሆኑን እንደሚከተለው መርምረናል፡፡
እንደሚታወቀው የፍ/ብ/ሥ/ሥ/ሕግ በዋናው ህግ የተቀመጡትን መብትና ግዴታዎች ወደ ተግባር ለመለወጥ እንዲያስችል ታስቦ የተዘረጋ ስርዓት ነው፡፡ ከሳሽ የሆነው ወገንም በከሳሽነት ተሰይሞ ክርክሩ እንዲቀጥል ለማድረግ አንደ ክርክሩ በማስረጃ አስደግፎ ቢያስረዳ ከህግ ወይም ከውል የመነጨ መብትና ግደታ ያለ መሆኑን ለማመልከት በሚያስችል ደረጃ ክሱ ተዘጋጅቶ መቅረብ እንዳለበት ከፍ/ብ/ሥ/ሥ/ሕ/ቁ 33/2/ እና 33/3/ ድንጋጌዎች ይዘት መገንዘብ ይቻላል፡፡ የእነዚህ ድንጋጌዎችን መስፈርት ያላሟላ ክስ ሲቀርብ ተከሳሾቹን እንኳ መጥራት እንደማያስፈልግ እና ክርክሩም በጅምር ደረጃ ሊቋረጥ እንደሚገባ ተገልፆ በፍ/ብ/ሥ/ሥ/ህ/ቁ 231/1/ሀ/ መደንገጉ ክርክሩ ውጤት ኖሮት በመሰረታዊ ህግ የተቀመጠውን መብትና ግዴታ ሊያስከብር መቻሉን ለማረጋገጥ ነው፡፡
በተያዘው ጉዳይ አመልካች ክስ ያቀረቡት በቀን 26/10/2013 ዓ.ም ተደረገ የተባለው ጠቅላላ ጉባኤ የተጠራው ስብሰባውን መጥራት በማይችሉ አባላት በመሆኑ፣ አመልካች ሳላውቅና በሰብሳቢነት ሳልገኝ የተደረገ በመሆኑ፣ ለሁሉም አባላት ጥሪ ሳይደረግ የተወሰኑ አባላት ብቻ ከደንቡ ውጭ ከ1 ቀን በፊት ጥሪ ተደርጎላቸው የተደረገ በመሆኑ፣ ጠቅላላ ጉባኤውም በምን ጉዳይ ላይ እንደሚነጋገር በጥሪው ወረቀት ላይ ያልተገለጸ በመሆኑ ጠቅላላ ጉባኤው ከማህበሩ መመስረቻ ጽሁፍ፣ መተዳደሪያ ደንብ፣ ከንግድ ህጉ አዋጅ ቁጥር 1243/2013 በሚቃረን መልኩ የተደረገ በመሆኑ ስብሰባው ላይ የተሰጡ ውሳኔዎች ሊሻሩ ይገባል በማለት ነው፡፡ ይህ የአመልካች አቤቱታ በፍ/ብ/ሥ/ሥ/ህ/ቁ 33/2/ እና 33/3/ እንደተደነገገው ከማህበሩ ስምምነትና ከንግድ ህጉ የመነጨ መብትና ግዴታ ያለ መሆኑን ለማመልከት የሚያበቃ ክርክር እንዳቀረቡ አስረጂ ሲሆን የአመልካች ክስ የክስ ምክንያት የሌለው ነው ተብሎ በመጀመሪያ ደረጃ መቃወሚያ ውድቅ የሚሆን አይደለም፡፡
በሌላም በኩል የፍሬ ነገር ክርክርና ማስረጃ ታይቶ ውሳኔ ሊሰጥ የሚገባው መቃወሚያው ላይ ብይን ከተሰጠ በኃላ መሆኑ ይታወቃል፡፡ የመጀመሪያ ደረጃ መቃወሚያ አወሳሰንን በተመለከተም በፍ/ብ/ሥ/ሥ/ህ/ቁ 244 እንዲሁም 245(1) እና (2) እንደተደነገገው ተከሳሽ ለክሱ መቃወሚያ ባቀረበ ጊዜ ፍርድ ቤቱ መቃወሚያውን ተቀብሎ ሌላው ተከራካሪ ወገን በጉዳዩ ላይ የሚያቀርበውን ክርክር ከሰማ በኋላ ውሳኔ ለመስጠት ተገቢ መስሎ የሚገምተውን ማስረጃ በመመርምር የቀረበው መቃወሚያ በተገቢና በቂ በሆነ ማስረጃ የተደገፈ መሆን አለመሆኑን በማረጋገጥ ህጉን መሰረት በማድረግ ይወስናል፡፡ ይህ ማለት ግን ከሳሽ ወገን በፍሬ ነገር ደረጃ የሚያቀርበው ክርክር እና ማስረጃ እንኳ ሳይታይ መቃወሚያውን መሰረት በማድረግ የተከሳሽ የፍሬ ነገር ክርክርና ማስረጃ ታይቶ ክሱን በመጀመሪያ ደረጃ መቃወሚ ውድቅ ተደርጓል በማለት መወሰን ስለ ክርክሩ አመራር የተዘረጋውን ስርዓት የተከተለ ካለመሆኑም በላይ የከሳሹንም መብት የሚያጣብብ በመሆኑ ተቀባይነት የለውም፡፡
በአጠቃላይ አመልካች ያቀረቡት ክስ ሙሉ ይዘቱና መንፈሱ ሲታይ በቀን 26/10/2013 ዓ.ም ተደረገ የተባለው ጠቅላላ ጉባኤ ከማህበሩ መመስረቻ ጽሁፍ፣ መተዳደሪያ ደንብና ከንግድ ህጉ አዋጅ ቁጥር 1243/2013 በሚቃረን መልኩ የተደረገ መሆኑን በማረጋገጥ የቀረበ በመሆኑ፤ ክሱንም ለፍርድ ቤት ለማቅረብ ምክንያት ያለው በመሆኑ፤ እንዲሁም የአመልካች የፍሬ ነገር ክርክርና ማስረጃ ሳይታይ የአንድ ወገን የፍሬ ነገር ማስረጃ ታይቶ ክሱ በመቃወሚያ ውድቅ ተደርጓል የሚባልበት የህግ ምክንያት ባለመኖሩ፤ የስር ፍርድ ቤት የአንድ ወገን የፍሬ ነገር ማስረጃ መርምሮ የአመልካች ክስ የክስ ምክንያት የለውም በማለት ክሱን በመጀመሪያ ደረጃ መቃወሚያ ውድቅ አድርጌያለሁ በማለት የተሰጠው ውሳኔ የፍ/ብ/ሥ/ሥ/ህ/ቁ 33/2/፣33/3/፣ 231/1/ሀ/፣ 244 እና 245 ድንጋጌዎችን ይዘትና ትክክለኛ አፈፃፀም የተከተለ ባለመሆኑ የህግ ስህተት የተፈፀመበት ነው ብለናል፡፡ ይግባኝ ሰሚው ችሎትም ይህን ሳያርም ማለፉ የሚነቀፍ ነው፡፡ ስለሆነም ተከታዩን ወስነናል፡፡
ው ሣ ኔ
የማይነበብ የአምስት ዳኞች ፊርማ አለበት
ፋ/ዘ