የሰ/መ/ቁጥር - 220567
ጥቅምት 06 ቀን 2016 ዓ.ም
`ዳኞች፡-
ተፈሪ ገብሩ (ዶ/ር)
እንዳሻዉ አዳነ
ተሾመ ሽፈራዉ
መላኩ ካሳዬ
ነፃነት ተገኝ
አመልካቾች፡-1.ወ/ሪት ናዲያ በሽር
2.ወ/ሪት ሶፊያ በሽር
3.አቶ ቶማስ በሽር
ተጠሪዎች፡- 1. ወ/ሮ ማርዬማ አብዱ
2. አቶ መሐመድ ሁሴን
መዝገቡ ተመርምሮ ተከታዩ ፍርድ ተሰጥቷል
ፍርድ
ይህ ጉዳይ የውርስ ክርክርን የሚመለከት ሲሆን፣ ክርክሩ በተጀመረበት በፌዴራል የመጀመሪያ ደረጃ ፍ/ቤት አመልካቾች ባቀረቡት አቤቱታ የውርስ አጣሪ ተሹሞ የሟች አባታችን አቶ በሽር አብደላ ሃሚድ የውርስ ሀብት እንዲጣራ በማለት የጠየቁትን ዳኝነት መነሻ ያደረገ ነዉ፡፡ 1ኛ ተጠሪም በቀረበባቸዉ አቤቱታ ላይ አለኝ የሚሉትን ክርክር አቅርበዉ ተከራክረዋል፡፡ ይህ በእንዲህ እንዳለ 2ኛ ተጠሪ በክርክሩ ጣልቃ በመግባት ነሐሴ 04 ቀን 2007 ዓ.ም በተደረገ የብድር ውል ብር 500,000.00 እንዲሁም ነሐሴ 10 ቀን 2008 ዓ.ም በተደረገ ሌላ የብድር ዉል ብር 1,100,000.00 በድምሩ ለ1ኛ ተጠሪ ብር 1,600,000.00 ያበደርኳቸው በመሆኑ የውርስ ሀብት ከመከፈሉ በፊት ዕዳዉ እንዲከፈለኝ በማለት ዳኝነት ጠይቀዋል፡፡
ጉዳዩን በመጀመሪያ የተመለከተዉ የስር የፌዴራል መጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤትም ግራ ቀኝ በየበኩላቸዉ ያቀረቡትን ክርክር ከሰማ በኋላ አመልካቾች በዉርስ ሀብትነት እንዲጣር ከዘረዘሯቸዉ ንብረቶች መካከል በቦሌ ክ/ከተማ ወረዳ 9 እንዲሁም በንፋስ ስልክ ላፍቶ ክ/ከተማ ወረዳ 01 ክልል ዉስጥ ያሉ ቤቶች፣ ጄት ኮንስትራክሽን፣ በ1ኛ ተጠሪ ስም በተለያዩ ባንኮች የሚገኝ ገንዘብ የተጠሪ የግል ንብረት ስለመሆኑ ሟች በህይወት እያሉ ነሐሴ 24 ቀን 2008 ዓ.ም በኮ/መ/ቁጥር 243134 ላይ በተደረገ የንብረት ማግለል ስምምነት ዉሳኔ ያገኘ በመሆኑ በድጋሚ በዉርስ ሀብትነት ሊጣራ አይገባም፡፡ የሰሌዳ ቁጥሩ አ.አ. 03-ኤ31846 የሆነዉ መኪና በንብረት ማግለል ስምምነት የ1ኛ ተጠሪ በሆነዉ የጄት ኮንስትራክሽን የተቀላቀለ በመሆኑ የዉርስ ንብረት አይደለም፡፡ በ1ኛ ተጠሪ የተመዘገበ የአክስዮን ድርሻ ወይም የመድን ዋስትና ስለመኖሩ አልተረጋገጠም፡፡ በተለያዩ ባንኮች መኖሩ የተረጋገጠዉ ገንዘብ የዉርስ ሀብት ነዉ፡፡ ሟች አቶ በሽር አብደላ ከወ/ሮ የሺመቤት ጥላሁን ጋር በኮ/መ/ቁጥር 179664 በነበራቸዉ የ100,000.00 የአሜሪካን ዶላር ክርክር ለሟች የተወሰነዉ ብር 2,233,280.00፤ 1ኛ ተጠሪ ከወ/ሮ የሺመቤት ጥላሁን ጋር በመ/ቁጥር 246424 ላይ የብር 400,000.00 ክርክር፣ በመ/ቁጥር 246415 ላይ የብር 240,000.00 ክርክር እንዲሁም በመ/ቁጥር 176963 ላይ የብር 600,000.00 የቼክ ክርክር መሠረት በአጠቃላይ የተወሰነዉ ብር 1,240,000.00 ግማሹ የዉርስ ሀብት ነዉ፡፡ በ1ኛ ተጠሪ እና በወ/ሮ የሺመቤት ጥላሁን መካከል የተደረገዉን የብር 5,000,000.00 የብድር ዉል እና የብድር ዉሉን ተከትሎ ለወ/ሮ የሺመቤት ጥላሁን የተሰጠዉን የብር 930,000.00 ቼክ አስመልክቶ በቤተሰብ ህጉ ላይ በተመለከተዉ አግባብ የአመልካቾች አባት በህይወት በነበሩበት ወቅት ያልተቃወሙ በመሆኑ በዉርስ ሀብትነት የሚጣራበት አግባብ የለም፡፡ ሟች በህይወት እያሉ ለአመልካቾች ለእያንዳንዳቸዉ የሰጡት ብር 600,000.00 በዉርስ ሀብት እንዲቀላቀል በማለት 1ኛ ተጠሪ ያቀረቡትን አስመልክቶ ሟች ስጦታዉን ማድረጋቸዉን ሲያወሩ መስማታቸዉን ምስክሮች የገለጹ ከመሆኑም በላይ አመልካቾችም ያመኑ በመሆኑ ወደ ዉርስ ተመልሶ ክፍፍሉ የሚፈጸም ይሆናል፡፡ ሟች በህይወት እያሉ 1ኛ ተጠሪ ከወ/ሪት ዘኒት አብዱ ብር 700,000.00 እንዲሁም ከአቶ መሀመድ ሁሴን (የአሁን 2ኛ ተጠሪ) ብር 1,600,000.00፣ በድምሩ ብር 2,300,000.00 ተበድረዋል፤ ሟች በብድር ዉሉ ላይ ያልፈረሙ ቢሆንም በጋብቻ ዉስጥ ለትዳር ጥቅም የዋለ መሆኑ በምስክሮች በመረጋገጡ ከዉርስ ሀብቱ የሚቀነስ በማለት ወስኗል፡፡
አመልካቾች በዚህ ዉሳኔ ባለመስማማት ያቀረቡትን ይግባኝ የተመለከተዉ የፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት በበኩሉ አመልካቾች ለይግባኝ ቅሬታቸዉ መሠረት ካደረጓቸዉ ነጥቦች ዉስጥ ከፊሎቹን አያስቀርብም በማለት ሰርዞ፣ በመ/ቁጥር 179797 እና በመ/ቁጥር 220557 ላይ በተደረጉት ክርክሮች በየቅደም ተከተላቸዉ ፍርድ ያረፈበት ብር 5,000,000.00 እና ብር 930,000.00 የ1ኛ ተጠሪ የግል ሀብት ነዉ ሲል የሰጠዉን ዉሳኔ አግባብነት፣ 1ኛ ተጠሪ ከስር 1ኛ ጣ/ገብ (ወ/ሪት ዘኒት አብዱ) ጋር ለሁለተኛ ጊዜ ያደረጉት ነዉ የተባለዉ የብድር ዉል የዉርስ ዕዳ ነዉ በሚል የተሰጠዉን ዉሳኔ ተገቢነት ላይ ብቻ አስቀርቦ የግራ ቀኝን ክርክር ሰምቷል፡፡ የግራ ቀኝ ክርክር ሰምቶም በ1ኛ ተጠሪ እና በወ/ሮ የሺመቤት ጥላሁን መካከል በመ/ቁጥር 179797 እና በመ/ቁጥር 220657 ላይ በነበረዉ የብድር ገንዘብ ክርክር በየቅደም ተከተላቸዉ ፍርድ ያረፈበት ብር 5,000,000.00 እና ብር 930,000.00 በድምሩ ብር 5,930,000.00 1ኛ ተጠሪ ያበደሩት ከሟች የአመልካቾች አባት ጋር በጋብቻ ዉስጥ እያሉ መሆኑ ባልተካደበት እና 1ኛ ተጠሪ ያበደሩት የግል ገንዘባቸዉ ስለመሆኑ የቀረበ ማስረጃ በሌለበት እንዲሁም የንብረት ማግለል ስምምነቱም ይህን የብድር ገንዘብ የማይመለከት ሆኖ እያለ የስር ፍርድ ቤት የዉርስ ሀብት አይደለም በማለት የሰጠዉ ዉሳኔ ስህተት ነዉ፡፡ 1ኛ ተጠሪ ከስር 1ኛ ጣ/ገብ (ወ/ሪት ዘኒት አብዱ) ጋር በድጋሚ አድርገዋል የተባለዉ የብር 300,000.00 የብድር ዉል ሰነድ ድልዝ ስርዝ ያለበት እና እርስ በርሱ የሚጋጭ አገላለጽ ያለበት በመሆኑ ሊታረም ይገባዋል፡፡ ሟች የአመልካቾች አባት ከ1ኛ ተጠሪ ጋር በጋብቻ ሲኖሩ 1ኛ ተጠሪ ከስር 2ኛ ጣልቃ ገብ (አቶ መሐመድ ሁሴን) ጋር ባደረጉት የብድር ዉል ከወሰዱት ብር 1,600,000.00 ዉስጥ ብር 1,100,000.00 ዕዳ መልሰናል በማለት አመልካቾች ያቀረቡት ክርክር በማስረጃ ያልተረጋገጠ በመሆኑ በዚህ ረገድ የስር ፍርድ ቤት የሰጠዉ ዉሳኔ ተገቢ ነዉ፡፡ 1ኛ ተጠሪ እና ሟች የአመልካቾች አባት በጋብቻ ሲኖሩ ለትዳራቸዉ ጥቅም ከ2ኛ ተጠሪ እና ከስር 1ኛ ጣ/ገብ (ወ/ሪት ዘኒት አብዱ) በብድር የወሰዱት ብር 2,000,000.00 መኖሩ የተረጋገጠ በመሆኑ የጋራ ዕዳ ነዉ በማለት የተሰጠ ዉሳኔ ተገቢ ነዉ በማለት የፌዴራል የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት ዉሳኔን በማሻሻል ወስኗል፡፡
ይህ የሰበር አቤቱታ የቀረበዉም በዚህ ዉሳኔ ቅር በመሰኘት ለማስለወጥ ሲሆን፣ አመልካቾች ጥር 30 ቀን 2014 ዓ.ም አዘጋጅተዉ ባቀረቡት የሰበር አቤቱታ የስር ከፍተኛ ፍርድ ቤት የሰጠዉ ዉሳኔ መሠረታዊ የህግ ስህተት የተፈጸመበት ነዉ የሚሉባቸዉን ምክንያቶች በመዘርዘር ታርሞ እንዲወሰንላቸዉ ዳኝነት ጠይቀዋል፡፡ የአቤቱታዉ ይዘትም በአጭሩ ከፍተኛ ፍርድ ቤቱ በመ/ቁጥር 179797 ላይ በነበረዉ ክርክር መሠረት የተሰጠዉ የብር 5,000,000.00 ዉሳኔ ግማሹ ለአመልካቾች ይገባል በማለት የሰጠዉ ዉሳኔ ተገቢ ቢሆንም በተጠቃሹ መዝገብ ላይ የተሰጠዉ ዉሳኔ የብር 5,000,000.00 ክፍያ ወለድና የተለያዩ ወጪዎችን የሚያጠቃልል መሆኑን ተከትሎ ዉሳኔዉ ከተሰጠበት ጥቅምት 02 ቀን 2009 ዓ.ም ጀምሮ ገንዘቡ በአፈፃፀም እስካለቀበት ጥር 18 ቀን 2014 ዓ.ም ድረስ ባለዉ አምስት ዓመት ከሦስት ወር ከ 17 ቀን በ 9% ወለድ ሲሰላ ብር 2,385,924.00 የሚመጣ በመሆኑ የዚህ ገንዘብ ግማሽ 1,192,962.00 1ኛ ተጠሪ ለአመልካቾች ድርሻቸዉን እንዲከፍሉ አለመወሰኑ፤ እንዲሁም በመ/ቁጥር 220657 ላይ በነበረዉ ክርክር ፍርድ ቤቱ የብድሩን ዋና ገንዘብ ብር 930,000.00 የአመልካቾች አባት እና የ1ኛ ተጠሪ የጋራ ነዉ በሚል የተሰጠ ዉሳኔ ተገቢ ቢሆንም ዉሳኔዉ 9% ወለድ ጭምር የሚያሳይ መሆኑን ግምት ዉስጥ አስገብቶ ዉሳኔዉ ክሱ ከቀረበበት ጥቅምት 07 ቀን 2011 ዓ.ም ጀምሮ የሰበር አቤቱታ እስከቀረበበት ጥር 30 ቀን 2014 ዓ.ም ድረስ የሦስት ዓመት ከሦስት ወር ወለድ ብር 277,528.00 የሚመጣ ሲሆን፣ የዚህ ግማሽ 138,764.00 የአመልካቾችን ድርሻ መወሰን ሲገባዉ ይህን አለመወሰኑ፤ በመዝገቡ ላይ የተወሰነዉን ወጪ እና ኪሳራ ሳይቀስን መቅረቱ መሠረታዊ የህግ ስህተት ነዉ፡፡ ከዚህም አልፎ 2ኛ ተጠሪ የባለቤቱ እህት የሆነችዉን 1ኛ ተጠሪ ለመርዳት ሐሰተኛ ዉል አዘጋጅቶ አቀረበ እንጂ በመካከላቸዉ የተደረገ የብድር ዉል የለም፤ አለ ቢባል እንኳ 1ኛ ተጠሪ የብድር ገንዘቡን ብር 1,100,000.00 ለ2ኛ ተጠሪ መክፈሏን የሚያሳይ ማስረጃ አመልካቾች አቅርበዉ እያለ ማስረጃዉ 1ኛ ተጠሪ የብድር ዕዳዉን ለመመለስ የላኩ መሆኑን አያሳይም በማለት ዉድቅ መደረጉ መሠረታዊ የህግ ስህተት በመሆኑ ታርሞ ይወሰንልን የሚል ነዉ፡፡
የሰበር አቤቱታዉ በአጣሪ ችሎት ተመርምሮ ያስቀርባል በመባሉም ተጠሪዎች መልስ እንዲሰጡበት ተደርጓል፡፡ በዚህም መሠረት 1ኛ ተጠሪ ግንቦት 17 ቀን 2014 ዓ.ም ጽፈዉ ባቀረቡት መልስ አመልካቾች የውርስ ሀብት እንዲጣራላቸው ለፌዴራል የመጀመሪያ ደረጃ ፍ/ቤት ባቀረቡት የውርስ ይጣራልን ክስም ሆነ የመጀመሪያ ደረጃ ፍ/ቤት የሰጠውን ውሳኔ በከፊል በመቃወም ለፌደራል ከፍተኛ ፍ/ቤት ባቀረቡት የይግባኝ ቅሬታ በመ.ቁ 179797 እና 220657 የተወሰነውን ገንዘብ በሚመለከት ወለዱ የውርስ ሀብት ነው ተብሎ ይወሰንልን የሚል አቤቱታ አላቀረቡም፡፡ አመልካቾች የውርስ ሀብት እንዲጣራ አቤቱታ ባቀረቡበት ወቅት ያልጠየቁትን የወለድ ጥያቄ አሁን በሰበር ደረጃ ማቅረብ የህግ ድጋፍ የለውም፡፡ በመ.ቁ 179797 ከተወሰነው የወጪ ገንዘብ ውስጥ 125,000 እና በመ.ቁ 220657 ከተወሰነው የወጪ ገንዘብ ውስጥ 93,000 ለጠበቃ አበል እንዲከፈል የተወሰነ ወጪ ነው፡፡ ገንዘቡን ለጠበቃዮ አልከፈልኩም፡፡ በብድር የተሰጠን 1,100,000 ብር ለአበዳሪያችን ለ2ኛ ተጠሪ አልተከፈለም፡፡ በአጠቃላይ የስር ፍርድ ቤት ወሳኔ መሠረታዊ የህግ ስህተት ያልተፈፀመበት በመሆኑ አመልካቾች ያቀረቡት አቤቱታ ውድቅ እንዲሆን በማለት ተከራክረዋል፡፡ 2ኛ ተጠሪ ግንቦት 17 ቀን 2014 ዓ.ም ጽፈው ባቀረቡት መልስ የብድር ገንዘብ አልተከፈለኝም፡፡ ይህ በስር ፍርድ ቤት በነበረው ክርክር ባቀረብናቸው ምስክሮች ተረጋግጧል፡፡ በመሆኑም ይህንን የማስረጃ ጉዳይ መሰረት በማድረግ አመልካቾች ያቀረቡት የሰበር አቤቱታ መሠረታዊ የህግ ስህተት ጥያቄን የማያስነሳ በመሆኑ ውድቅ እንዲደረግልኝ፡፡ የአመልካቾች ጥያቄም ሆነ ክርክር የፍ/ብ/ሕ/ ቁ.2472(1) እና 2472(4) ድንጋጌን የሚፃረር በመሆኑ ውድቅ እንዲደረግልኝ በማለት ተከራክረዋል፡፡ አመልካቾች አቤቱታቸውን በማጠናከር የመልስ መልስ አቅርበዋል፡፡
ከስር ጀምሮ የጉዳዩ አመጣጥ እና የግራ ቀኝ ክርክር ይዘት አጠር አጠር ባለ መልኩ ሲታይ ከፍ ሲል የተመለከተዉን ሲመስል ይህ ችሎትም ለሰበር አቤቱታዉ ምክንያት የሆነዉ ዉሳኔ መሠረታዊ የህግ ስህተት የተፈጸመበት መሆን አለመሆኑን ከግራ ቀኝ ክርክር እና ለጉዳዩ አግባብነት ካላቸዉ ድንጋጌዎች ጋር በማገናዘብ መዝገቡን እንደሚከተለዉ መርምሮታል፡፡
እንደመረመረዉም የአመልካቾች የመጀመሪያዉ የቅሬታ ነጥብ 1ኛ ተጠሪ ከወ/ሮ የሺመቤት ጥላሁን ጋር ባደረጉት የብድር ዉል ግንኙነት መነሻነት በተደረገ ክርክር የፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት በመ/ቁጥር 179797 ላይ ለ1ኛ ተጠሪ የተወሰነዉ ብር 5,000,000.00 እንዲሁም በመ/ቁጥር 220657 ላይ የተሰጠዉ ብር 930,000.00 ዉስጥ አመልካቾች ድርሻ ያላቸዉ መሆኑን አረጋግጦ የወሰነ ቢሆንም ወለድ ለ1ኛ ተጠሪ እንድትከፍል ወስኖ እያለ የስር ፍርድ ቤት በሁለቱም መዝገቦች ላይ የተሰጠዉን ዋና ገንዘብ ብቻ አመልካቾች እንዲካፈሉ የሰጠዉ ዉሳኔ ተገቢ አይደለም የሚል ነዉ፡፡ የፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት በመ/ቁጥር 179797 ላይ በነበረዉ ክርክር መነሻነት የተወሰነዉ ብር 5,000,000.00 ከጥቅምት 02 ቀን 2009 ዓ.ም ጀምሮ ከሚታሰብ 9% ወለድ ጋር መሆኑ እንዲሁም በመ/ቁጥር 220657 ላይ የወሰነዉ ብር 930,000.00 የሚከፈለዉ ክሱ ከቀረበበት ጥቅምት 07 ቀን 2011ዓ.ም ጀምሮ ከሚታሰብ 9% ወለድ ጋር ስለመሆኑ የተረጋገጠ ከመሆኑም በላይ 1ኛ ተጠሪም ይህን ክደዉ አይከራከሩም፡፡ በሁለቱም መዛጋብት ላይ የተወሰነዉ ዋና ገንዘብ የሟች የአመልካቾች አባት ድርሻ ያለበት መሆኑ ተረጋግጦ ግማሽ ድርሻ 1ኛ ተጠሪ ለአመልካቾች እንዲከፍሉ ተወስኗል፡፡ በዚህ ሁኔታ አመልካቾች ዋና ገንዘቡ ላይ ድርሻ አላቸዉ ከተባለ ደግሞ ዋናዉ ገንዘብ የሚያስገኘዉ ፍሬ (ወለድ) አመልካቾች የማያገኙበት ህጋዊ ምክንያት የለም፡፡ በመሆኑም ጉዳዩን ከዚህ አንፃር ማየት ሲገባዉ በሁለቱም መዝገቦች ላይ የተወሰነዉን ገንዘብ አመልካቾች በዋናዉ ገንዘብ ላይ ብቻ ድርሻ እንዳላቸዉ በፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት የተሰጠ ዉሳኔ በርግጥም ሊታረም የሚገባዉ ሆኖ ተገኝቷል፡፡
የአመልካቾች ሁለተኛዉ የመከራከሪያ ነጥብ በሁለቱም መዛግብት ላይ ከተወሰነዉ የወጪና ኪሳራ ገንዘብ አመልካቾች ግማሹ ሳይወሰንላቸዉ መታለፉን የሚመለከት ነዉ፡፡ ከክርክሩ ሂደት መገንዘብ እንደሚቻለዉ በሁለቱም መዛግብት ላይ ክስ አቅርበዉ የተከራከሩት 1ኛ ተጠሪ ናቸዉ፡፡ ስለሆነም በክርክሩ ሂደት የወጣዉን ወጪ የሸፈኑት 1ኛ ተጠሪ ናቸዉ ተብሎ ይታመናል፡፡ ፍርድ ቤቱ ከወጪና ኪሳራ ጋር በተያያዘ የሰጠዉ ዉሳኔም አመልካች በክርክሩ ምክንያት ያወጡት ወጪ ሊተካላቸዉ እንደሚገባ በማመን ስለመሆኑ እሙን ነዉ፡፡ ስለሆነም በክርክሩ ምክንያት የወጣ ወጪና ኪሳራ የሚከፈለዉ በክርክር ምክንያት ወጪ ላወጡት 1ኛ ተጠሪ እንጂ የክርክሩ ተሳታፊ ላልነበሩት አመልካቾች የሚከፈልበት ምክንያት አይኖርም፡፡ ስለሆነም አመልካቾች ከዚህ ጋር በተያያዘ የሚያቀርቡት ክርክር ተቀባይነት ያለዉ አይደለም፡፡
ሦስተኛዉ የአመልካቾች ክርክር 2ኛ ተጠሪ ለ1ኛ ተጠሪ አበድረዋል የተባለዉን ብር 1,600,000.00 የሚመለከት ነዉ፡፡ በዚህ ረገድ አመልካቾች አጥብቀዉ የሚከራከሩት 2ኛ ተጠሪ የባለቤቱ እህት የሆኑትን 1ኛ ተጠሪን ለማገዝ የብድር ዉል በሐሰት አዘጋጅቶ ያቀረበ እንጂ በ1ኛ እና በ2ኛ ተጠሪ መካከል የተደረገ የብድር ዉል የለም፤ 1ኛ ተጠሪ ተበድረዋል የሚባል ከሆነም ብር 1,100,000.00 ከፍለዋል በማለት ሲሆን፣ ተጠሪዎች በበኩላቸዉ የብድር ዉሉ መኖሩን የሚያሳይ ዉል መቅረቡንና 1ኛ ተጠሪ የብድር ገንዘቡን ለ2ኛ ተጠሪ የመለሱ መሆኑን የሚያሳይ ማስረጃ ያልቀረበ መሆኑን ጠቅሰዉ የሚከራከሩ መሆኑን መዝገቡ ያሳያል፡፡ 1ኛ ተጠሪ ሁለት በተለያዩ ቀናት ከ2ኛ ተጠሪ ገንዘብ የተበደሩ መሆኑን የሚያሳይ በጽሑፍ የተደረገ ዉል አቅርበዋል፤ በተጨማሪም የሰዉ ምስክሮችም ቀርበዉ የምስክርነት ቃላቸዉን የሰጡ ሲሆን፣ አመልካቾች የሰዉ ምስክሮች የለንም በማለታቸዉ የሰዉ ምስክሮችን ያላሰሙ ስለመሆኑ የስር ፍርድ ቤት መዝገብ ያሳያል፡፡ የፌዴራል የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት ሟች የአመልካቾች አባት እና 1ኛ ተጠሪ በጋብቻ ዉስጥ እያሉ 1ኛ ተጠሪ በሁለት የተለያዩ ቀናት በድምሩ ብር 1,600,000.00 ከ2ኛ ተጠሪ መበደራቸዉ እና ብድሩም ለትዳር ጥቅም የዋለ ስለመሆኑ በማስረጃ ተረጋግጧል በሚል ድምዳሜ ላይ የደረሰዉም እነዚህኑ ማስረጃዎች መርምሮ እና መዝኖ ሲሆን፣ የፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤትም ይህን የፍሬ ነገር ድምዳሜ ተቀብሎ አጽድቆታል፡፡ ከዚህም አልፎ 1ኛ ተጠሪ ከብድሩ ገንዘብ ብር 1,100,000.00 ለ2ኛ ተጠሪ መክፈሉን የሚሳያይ ማስረጃ አቅርበናል በማለት የሚከራከሩ ቢሆንም፣ በዚህ ረገድ በማስረጃነት የቀረበዉ የባንክ ደረሰኝ የብድር ዉሉ ከመደረጉ በፊት 1ኛ ተጠሪ ለ2ኛ ተጠሪ ገንዘብ መላካቸዉን የሚያሳይ በመሆኑ ገንዘቡ የተላከዉ ይህን የብድር ገንዘብ ለመክፈል ስለመሆኑ አያስረዳም በሚል ድምዳሜ መድረሱን የዉሳኔዉ ይዘት ያሳያል፡፡ የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ስልጣን መሠረታዊ የህግ ስህተት የተፈጸመባቸዉን ዉሳኔዎች በማረም ላይ የተገደበ ስለመሆኑ የኢፌዲሪ ህገ መንግስት አንቀጽ 80 (3-ሀ) እንዲሁም የፌዴራል ፍርድ ቤቶች አዋጅ ቁጥር 1234/2013 አንቀጽ 4 እና 10 ላይ ከተመለከቱት ድንጋጌዎች መገንዘብ የሚቻል ነዉ፡፡ በመሆኑም የስር ከፍተኛ ፍርድ ቤት ከላይ በተመለከተዉ መልኩ ማስረጃን መዝኖ የደረሰበትን የፍሬ ነገር ድምዳሜ ይህ ችሎት በድጋሚ ሊመረምር የሚችልበት ህጋዊ ምክንያት የለም፡፡ ስለሆነም የብድር ገንዘቡን አስመልክቶ አመልካቾች የሚያቀርቡት ክርክርም ተቀባይነት ያለዉ ሆኖ አልተገኘም፡፡
በዚህ ሁሉ ምክንያት ተከታዩ ዉሳኔ ተሰጥቷል፡፡
ዉሳኔ
መዝገቡ ተዘግቷል፤ ወደ መዝገብ ቤት ይመለስ፡፡
የማይነበብ የአምስት ዳኞች ፊርማ አለበት፡፡
ፋ/ዘ