የሰ/መ/ቁ.220961
ጥቅምት 6 ቀን 2016ዓ.ም
ዳኞች፡-
ብርሃኑ አመነዉ
ረታ ቶሎሳ
በእዉቀት በላይ
ቀነዓ ቂጣታ
ኑረዲን ከዲር
አመልካች፡- አቶ ሃዲስ መስፍን
ተጠሪዎች፡- 1ኛ. ወ/ሮ ጽጌ ወልዳይ
2ኛ. ሪም ሚካኤል ወልዳይ
3ኛ. ወሪ/ት መአዛ ሚካኤል ወልዳይ
4ኛ. ልዋም ሚካኤል ወልዳይ
5ኛ. ሜሮን ሚካኤል ወልዳይ
6ኛ. የአቶ ሞገስ ለማ ተተኪ ወራሽ ብሩክ ሞገስ
7ኛ. አስር አለቃ ሙስጠፋ አሊ
8ኛ. ወ/ሮ የሺ ውቤ
መዝገቡን ተመርምሮ ተከታዩ ፍርድ ሰጥተናል
ፍርድ
የሰበር አቤቱታው ሊቀርብ የቻለው አመልካች የካቲት 7/2013 ዓ.ም ጽፈው ባቀረቡት የሰበር አቤቱታ የፌዴራል የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት በመ/ቁ 74438 በ03/02/2012ዓ.ም የሠጠውን ብይን እና በቀን 12/08/2013 ዓ.ም የሰጠውን ውሳኔ የፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ይግባኝ ሰሚ ችሎት በመ.ቁ 275104 በ24/05/2014 ዓ.ም በመቀበል (ይግባኙን በመሰረዝ) በሰጠዉ ብይን መሰረታዊ የህግ አተረጓጎም ስህተት የተፈጸመበት በመሆኑ ይሄዉ ሊታረም ይገባል በማለታቸው ሲሆን ከ1ኛ እስከ 5ኛ የተዘረዘሩት ተጠሪዎች በስር ፍ/ቤት ከ1ኛ-5ኛ የመቃወም አመልካቾች የነበሩ ሲሆን አመልካችና ከ6ኛ እስከ 8ኛ የተዘረዘሩት ተጠሪዎች ደግሞ እንደቅደምተከተላቸዉ 1ኛ፣2ኛ፣3ኛ እና4ኛ የመቃወም ተጠሪዎች ነበሩ፡፡
በስር ፍ/ቤት ከ1ኛ እስከ 5ኛ የተዘረዘሩት ተጠሪዎች ህዳር 05/2012 ዓ.ም ባቀረቡት የመቃወም አቤቱታ በኮልፌ ቀራኒዩ ክ/ከተማ ወረዳ 05 ክልል ውስጥ የሚገኘው የቤት ቁጥሩ 1264 የሆነ መኖሪያ ቤት የ1ኛ እና ሌሎች መ/አመልካቾች ባል እና አዉራሽ የሆኑት አቶ ሚካኤል ወልዳይ ታህሳስ 06/1977 ዓ.ም በተጻፈ የቤት ሽያጭ ውል የ7ኛ ተጠሪ ወኪል ከነበሩት 6ኛ ተጠሪ አዉራሽ አቶ ሞገስ ለማ ታህሳስ 25/1973 ዓ.ም በተሰጣቸው ውክልና መሰረት ቤቱን ገዝተዉ እና ተረክበዉ ሲኖሩበት እንደነበረ፣ይህ በእንዲህ እንዳለ አቶ ሚካኤል በ1987ዓ.ም ለስራ ወደ ኤርትራ ሲሄዱ አመልካች ይሄንኑን ቤት እንዲጠብቁላቸዉ በአደራ ሰጥተዉ መሄዳቸዉን፣ከዚያም ለስራ በሄዱበት የኢትዮ-ኤርትራ ጦርነት ተጀምሮ በዚህ ምክንያት መመለስ ሳይችሉ ቀርተዉ እዚያዉ እየኖሩ እያሉ ባደረባቸው ህመም ምክንያት ጥር 15/1995ዓ.ም ከዚህ አለም በሞት መለየታቸዉን፣ከዚያም 1ኛ ተጠሪ ሚስትነታቸዉንና ሌሎቹ ደግሞ ወራሽነታቸዉን በማረጋገጥ አመልካች ይሄንኑን በ1987ዓ.ም በአደራ በተቀበለዉ መ/አመልካቾች ቤት ላይ ከ6ኛ -8ኛ ባሉት ተጠሪዎች ጋር ግዢና ሽያጭ ዉል ፈፅሜያለሁ በማለት ስምምነት መደረጉን እና ይህ ስምምነትም የመቃወሚያ አቤቱታዉ በቀረበበት መዝገብ ላይ በፍ/ቤቱ መፅደቁን ጠቅሰዉ ይህ ያላግባብ ተደርጎ በመዝገቡ እንዲፀድቅ የተደረዉ ስምምነት ፈርሶ 1ኛመ/ተጠሪ እንዲጠብቁ በአደራ የተሰጣቸዉን ቤት ለቀዉ ለመ/አመልካቾች እንዲያስረክቡ ከወጪና ኪሳራ ጋር ይወሰንላቸዉ ዘንድ ዳኝነት ጠይቀዋል፡፡
ፍ/ቤቱም የመቃዎም ተጠሪዎች መልስ እንዲሰጡ ባዘዘው መሰረት የአሁኑ አመልካች ህዳር 18/2012 ዓ.ም በተጻፈ መልስ፦ የ1ኛ መ/አመልካች ባል እና ሌሎች አባት የሆኑት አቶ ሚካዔል ወልዳይ ከሞቱ 15 አመት ያለፋቸው በመሆኑ የመ/አቤቱታቸዉ በይርጋ የታገደ በመሆኑ ውድቅ ይደረግልኝ በማለት የመጀመሪያ ደረጃ መቃዎሚያ ያቀረቡ ሲሆን በፍሬ ነገር አማራጭ መልሳቸውም ቤቱን በአደራ አለመቀበላቸዉን፣ ይልቁንም ቤቱን ያአሁን 7ኛ ተጠሪ ወኪል ከሆነው 6ኛ ተጠሪ አባት ህዳር 05/1987 ዓ.ም በተደረገ ሽያጭ ውል በብር 23,000 ገዝተዉና ተረክበዉ ሲገለገሉበት መቆየታቸዉን፣በማስከተልም ውክልና ሰጪና የቤቱ ባለበት የሆኑት 7ኛ ተጠሪ ከባለቤታቸው 8ኛ ተጠሪ ጋር በመሆን ሽያጩን ያፀደቁላቸዉ መሆኑን፣እኚህ ሻጮች የቤቱ ህጋዊ ባለንብረቶች መሆናቸውን በማረጋገጥ በቅን ልቦና መግዛታቸዉን፣ይሁንና ሽያጩን መሰረት በማድረግ የቤቱን ስመ-ሀብት ለማዞር ባለመቻሉ ምክንያት ክስ ቀርቦ ከዚያም ጉዳዩ በእርቅ መቋጨቱን፣ይህ እንደተጠበቀ ሆኖ በሌላ በኩል ከአቶ ሚካኤል ጋር ተደረገ የተባለው ቤቱ ሽያጭ ውል ቀብድ እንጂ የተሟላ የሽያጭ ውል አለመሆኑንና የመሳሰሉትን በማንሳት የመ/አመልካቾች ዳኝነት ጥያቄ ውድቅ ሊደረግ ይገባል በማለት ተከራክረዋል፡፡6ኛ ተጠሪ በበኩሉ ህዳር 16/2012 ዓ.ም በተጻፈ መልስ ክሱ በይርጋ የሚታገድ መሆኑንና ስምምነቱ ላይ ተሳታፊ ባለመሆናቸውና ከዚህ አንፃረር ክሱ የማይመለከታቸው መሆኑን በመጀመሪያ ደረጃ መቃወሚያነት አቅርበዉ በፍሬ ነገር ረገድ ከአውራሽ የተላለፈልኝ መብት ስለሌለ ከ6ኛ ተጠሪ የሚጠየቅ ዳኝነትም ምን እንደሆነ ግልጽ ባለመሆኑ የቀረበው አቤቱታ ውድቅ ይደረግልኝ የሚል መልስ ሠጥተዋል፡፡
7ኛ እና 8ኛ ተጠሪዎች በበኩላቸዉ በጋራ ህዳር 18/2012ዓ.ም ጽፈው ባቀረቡት መልስ 8ኛ ተጠሪ ከሽያጭ ውሉ ጋር ምንም አይነት ግንኙነት እንደሌላቸዉ ጠቅሰዉ በሌላ በኩል ያአሁን 2ኛ-5ኛ የተዘረዘሩት ተጠሪዎችም የመ/አቤቱታዉን ለማቅረብ መብትና ጥቅም የሌላቸዉ መሆኑን መቃወሚያ በማስቀደም ፍሬ ነገሩን በሚመለከትም 7ኛ ተጠሪ ለ6ኛ ተጠሪ ሰጡ የተባለዉ ውክልና የ8ኛ ተጠሪ ፈቃድ የሚያሥፈልገውና ቤቱን ለማስተላለፍ የማያስችል ውክልና በመሆኑ የቀረበው ቤቱን እንረከብ ዳኝነት ጥያቄ ተቀባይነት የሌለዉ መሆኑንና ከዚህ በፊት ከ1ኛ መ/ተጠሪ ጋር ያደረጉት ስምምነትም እንዲሁ የህግ ባለሙያ ሳያማክሩ ማድረጋቸዉን ጠቅሰዉ ዉሉ መሰረዙን እንደሚደግፉና እንዲሁም 8ኛ ተጠሪም በበኩላቸዉ ውክልና ያልሰጠሁ በመሆኑ ሸያጩ አይመለከተኝም፤በመሆኑም አቤቱታው ውድቅ ይደረግልኝ በማለት መልስ አቅርበዋል፡፡
ፍ/ቤቱም ግራ ቀኙን አከራክሮ መቃዎሚያዎቹን በብይን ውድቅ አድርጎ በማለፍ ምስክሮችን ከሰማ በኋላ የአሁን 2ኛ-5ኛ የተዘረዘሩት ተጠሪዎች አውራሽ የሆኑት አቶ ሚካኤል ወልዳይ የ7ኛ ተጠሪ ወኪል ከሆኑት 6ኛ ተጠሪ ታህሳስ 06/1977ዓ.ም በተጻፈ ውል ቤቱን የገዙ ስለመሆኑና ውሉ ሲጸድቅ ቀሪ ክፍያ ለመክፈል የተስማመሙ ስለመሆኑ ይሄ ው የውል ሰነድ ያሳያል፤በሌላ በኩል አመልካችም ይህንኑን ቤት የ7ኛ ተጠሪ ወኪል ከሆኑት 6ኛ ተጠሪ ጋር ህዳር 05/1987ዓ.ም በተደረገ ውል ስለመግዛታቸው የሚያሳይ ማስረጃ አቅርበዋል፡፡ይሁንና ሁለቱም ውሎች በውል አዋዋይ ፊት ያልተደረጉ ሲሆን በሁለቱም ውሎች ውል ሰጪ የነበሩት የ7ኛ ተጠሪ ወኪል የሆኑት 6ኛ ተጠሪ አዉራሽ ይህን ቤትና ይዞታ ቀድሞ ለ3ኛ ወገን በተላለፈበት እና በሌላቸው መብት ለአመልካች ለማስተላለፍ ያደረጉት ስምምነት መሆኑን ከማስረጃዎች ለመረዳት የተቻለ በመሆኑና አንድ ውል የሚደረገው ደግሞ በሚቻልና ህጋዊ ጉዳይ በመሆኑ ይህ የ7ኛ ተጠሪ ወኪል የነበሩት ግለሰብ ከ2ኛ እስከ 5ኛ ለተዘረዘሩት ተጠሪዎች አውራሽ ቤቱን ካስተላለፉ በኋላ ለአመልካች በድጋሚ ማስተላለፋቸው ህጋዊ ተግባር አይደለም፤ከቀረቡት ምስክሮች መረዳት እንደተቻለው አመልካች ያቀረቡት የቅን ልቦና ገዥነት ክርክር የማስረጃ መሰረት ያለዉ አይደለም፤እንዲሁም 7ኛ እና 8ኛ ተጠሪዎች ውሉ ስላለመደረጉ ያቀረቡት ክርክር ሳይኖር የውል ምዝገባን መሰረት በማድረግ ያቀረቡት ክርክርም የፌ/ጠ/ፍ/ቤት ሰበር ሰሚ ችሎት በሰበር መ.ቁ 36887 በሰጠው አስገዳጅ ውሳኔ መሰረት ተቀባይነት የለውም፡፡8ኛ ተጠሪ ውሉ እንዲደረግ ፈቃድ አልሰጠሁም በማለት ቢከራከሩም በህጉ በተቀመጠው ጊዜ ውስጥ ውሉን ለማስፈረስ ያቀረቡት ዳኝነት ባለመኖሩ ፍ/ቤቱ ይሄንኑንም አልተቀበለውም በማለት በአመልካች እና 7ኛ እና 8ኛ ተጠሪዎች መካከል ጥቅምት 16/2010 ዓ.ም የተደረገው ስምምነትና ፍ/ቤቱ ይሄንኑን ስምምነት በማፅደቅ ረገድ በ27/2/2010ዓ.ም የሰጠው ውሳኔ በፍ/ብ/ስ/ስ/ህ/ቁ.360(2) መሰረት እንዲሰረዝና እንዲሁም አመልካች የመ/አቤቱታ የቀረበበትን ቤት ከ1ኛ- 5ኛ ላሉት ተጠሪዎች ያስረክቡ ሲል ወስኗል፡፡
አመልካችም በዚህ ውሳኔ ቅር በመሰኘት ለፌ/ከፍ/ተኛ ፍ/ቤት የይግባኝ አቤቱታ ያቀረቡ ቢሆንም አቤቱታው ተቀባይነት ባለማግኘት ተሰርዟል፡፡
አመልካችም ውሳኔዉ መሰረታዊ የህግ አተረጓጎም ስህተት የተፈጸመበት በመሆኑ ሊታረም ይገባል በማለት የካቲት 07/2014 ዓ.ም የተጻፈ የሰበር አቤቱታ ለዚህ ሰበር ችሎት ያቀረቡ ሲሆን ይዘቱም፦ ወራሽ የሆነ ወገን ወራሽ ባልሆነ ወገን ላይ የውርስ ሃብት እንዲለቀቅ ክስ የማቅረብ መብቱ በ10 አመት ይታገዳል በማለት ያቀረብኩትን መቃወሚያ የስር ፍ/ቤት ክሱ የመፋለም ክስ ስለመሆኑ የሚያሳይ ነገር ሳይኖር የመፋለም ክስ ነው በማለትና እንዲሁም የስር መ/አመልካቾቹ በወቅቱ በጦርነት ምክንያት ወደ ኢትዮጵያ መግባት አልቻሉም በሚል በደፈናዉ ማለፉ ያላግባብ ነዉ፤በተጨማሪም 1ኛ ተጠሪ የአቶ ሚካኤል ወልዳይ ሚስት ነኝ ከማለት በዘለለ ቤቱ የጋራ ንብረት ስለመሆኑ የቀረበ ማስረጃ ሳይኖር ይህ ሁሉ ታልፎ የተሰጠዉ ዉሳኔ ያላግባብ መሆኑን፤ የስር 1ኛ መ/አመልካች ባል እና ሌሎች አውራሽ የሆኑት አቶ ሚካኤል ወልዳይ የ7ኛ ተጠሪ ወኪል ከሆኑት ከ6ኛ ተጠሪ ታህሳስ 06/1977ዓ.ም ያደረጉት ሽያጭ ውል ህጋዊ ውጤት የሚኖረው ለማዘጋጃ ቤት ቀርቦ ሲጸድቅ ስለመሆኑ የዉሉ ሰነድ በግልፅ የሚያሳይ ሲሆን ሆኖም ግን በዚህ መሰረት ዉሉ ለሚመለከተዉ አካል ቀርቦ ያልጸደቀ ረቂቅ ውል በመሆኑ በሰበር መ/ቁ 99124 በተሰጠው ትርጉም መሰረት የአስገዳጅነት ውጤት የሌለዉ ሆኖ እያለና እንዲሁም ከዚህ በተጨማሪነትም ዉሉ በፌ/ጠቅላይ ፍ/ቤት ሰበር ሰሚ ችሎት መ/ቁ 123761 በተሰጠ ትርጉምና በፍ/ብ/ህ/ቁ.2878 መሰረትም የማይንቀሳቀስ ንብረት ሽያጭ ውል ካልተመዘገበ እጁ ባስገባ 3ኛ ወገን ላይ መቃዎሚያ ሊሆን እንደማይችል ተደንግጎ እያለ አመልካች በውል ገዝቼና ተረክቤ ሲገልገልበት የቆየሁትን ቤት የስር ፍ/ቤት ያልተመዘገበ የሽያጭ ውል መሰረት በማድረግ እንድለቅ መወሰኑ ያላግባብ ነዉ፤ ክስ የቀረበበትን ቤት አመልካች ከአቶ ሚካኤል በአደራ የተረከብኩ ስለመሆኔ በጽሁፍም ሆነ በምስክሮች በእርግጠኝነት ሳይስረዱና እንዲሁም በፍ/ብ/ህ/ቁ.1723 መሰረት በማይንቀሳቀስ ንብረት ላይ የሚደረጉ ውሎች በጽሁፍ መሆን እንዳለባቸው ከተደነገገዉ ውጭ በጽሁፍ የተደረገ የአደራ ውል ሳይኖር የስር ፍ/ቤት ቤቱ በአደራ የተያዘ ነው በማለት መወሰኑ፤እንዲሁም ቤቱን የ7ኛ ተጠሪ ወኪል ከሆነው 6ኛ ተጠሪ ስገዛ የቤቱ ስመ-ሀብት የቤቱ ባለቤቶች በሆኑት 7ኛ እና 8ኛ ተጠሪዎች ስም እንጂ በአቶ ሚካኤል ወልዳይ ስም አለመመዝገቡንና ካርታና የተሟላ ሰነድ ያለው መሆኑን አረጋግጩ በቅን ልቦና የገዛሁት ሲሆን ከአቶ ሚካኤል ጋር ተደረገ የተባለው ውልም በጅምር የቀረ፣ያልተመዘገበና ያልጸደቀ በመሆኑ አመልካች በምገዛበት ወቅትም ቤቱ የ7ኛ ተጠሪ መሆኑን እንጂ የአቶ ሚካኤል ባለመሆኑ ፍ/ቤቱ በሌለ መብት የተሸጠ ነው በማለት መወሰኑ፤እንዲሁም የስር መ/አመልካቾች ኤርትራውያን ከመሆናቸው አኳያ በዚህ አገር የማይንቀሳቀስ ንብረት ባለሃብት መሆን እንደማይችሉ በፍ/ብ/ህ/ቁ 390 ስር ተደንግጎ ባለበትና ከአገር ስለወጡ ኤርትራውያን ንብረት አስተዳደር እና አመላለስ በተመለከተ የወጣው መመሪያም ቤቱን የሚጠብቀው ግለሰብ ቤቱን ሽጦ ገንዘቡን በባንክ እንዲያስቀምጥ የሚደነግግ በመሆኑና ከጠየቁም የሽያጭ ገንዘቡ ብቻ ሆኖ ባለበት ሁኔታ በውል ገዝቼ ከ20 አመት በላይ በእጄ የቆየዉን ንብረት ከ1ኛ-5ኛ ለተዘረዘሩት ተጠሪዎች እንዳስረክብ መወሰኑ ያላግባብ ነዉ፤ በውጭ አገር የተሰጠ የሚስትነትና የወራሽነት ማስረጃም ለፍ/ቤት ከመቅረቡ በፊት አግባብ ላለው አካል ቀርቦ ትክክለኛነቱ ባልተረጋገጠበት ሁኔታ የስር ፍ/ቤት ይሄንኑን ጭምር በቀጥታ ተቀብሎና መሰረት አድርጎ መወሰኑ ያላግባብ መሆኑንና እንዲሁም በስር ፍ/ቤት በፍ/ብ/ስ/ስ/ህ/ቁ.358 መሰረት የቀረበዉ መቃዎሚያም በቃለ መሃላ የተደገፈ ባልሆነበትና እንዲሁም እነዚህ ከ1ኛ-5ኛ የተዘረዘሩት ተጠሪዎች ቤቱን በተመለከተ በየጊዜዉ በዚህ መዝገብና ሌላ መዝገብ የሚያቀርቡት ክርክር እርስ በርስ የሚቃረን በመሆኑ ሀሰተኛ ነዉ በማለት ያቀረብኩትን ክርክር የስር ፍ/ቤት ምንም ሳይል አልፎ የሰጠው ብይን እና ውሳኔ መሰረታዊ የህግ ስህተት የተፈጸመበት በመሆኑ ተሸሮ ቀደም ሲል ፍ/ቤቱ በመ/ቁ.74438 በቀን 27/02/2010 ዓ.ም ስምምነታችን በማጽናት የሰጠው ትእዛዝ እንዲጸናልኝ የሚል ነው፡፡
የሰበር አጣሪ ችሎቱም አቤቱታዉን መርምሮ በአመልካች የቀረበው የይርጋ መቃዎሚያ ውድቅ ተደርጎና ታልፎ የ1ኛ ተጠሪ ባለቤትና ከ2ኛ-5ኛ ያሉት ተጠሪዎች አባት የክርክሩ መነሻ የሆነውን ቤት ስለመግዛታቸው ያቀረቡት ህጋዊ ውል ስለመኖሩ ባልተገለጸበት ሁኔታ ይህ በአመልካች እና በ7ኛ እና 8ኛ ተጠሪዎች መካካል የተደረገውን ስምምነት በማፅደቅ የተሰጠውን ውሳኔ በፍ/ብ/ሥ/ሥ/ህ/ቁ.360(2) መሰረት እንዲሰረዝ የተወሰነበትን አግባብነትና ተያያዥ ነጥቦችን ለማጣራት ሲባል ጉዳዩ ለሰበር ችሎት እንዲቀርብ መደረጉን ተከትሎ 7ኛ እና 8ኛ ተጠሪ በጋራ በመሆን በ05/08/2014 ዓ.ም የተጻፈ መልስ ያቀረቡ ሲሆን ይዘቱም፦ከ1ኛ-5ኛ የተዘረዘሩት ተጠሪዎች ክርክር የቀረበበት ቤት የአውራሻቸው ስለመሆኑ ውርስ ተጣርቶ ባልተረጋጋጠበት፣ዉል ነዉ በማለት ያቀረቡት ሰነድም የቀብድ ውል መሆኑን እንጂ የቤት ሽያጭ ዉልን የሚያቋቁም ባልሆነበት እና ውል ለማዋዋል ስልጣን ባለው አካል ፊት ባልተደረገበትና ባልተመዘገበበት፣ቤቱም ለአመልካች በአደራ ስለመሰጠቱ በስሚ ስሚ ምስክርነት ቃል እንጂ ለጉዳዩ አግባብነት ባለዉ ህግ መሰረት ተቀባይነት ባለዉ ማስረጃ ባልተረጋገጠበት፣ቤቱን አስመልክቶ በ05/03/1987ዓ.ም ከአመልካች ጋር የተደረገው የሽያጭ ውል በ06/04/1977ዓ.ም ከ1ኛ-5ኛ ተጠሪዎች አዉራሽ ጋር ከተደረገው ቀብድ ውል ጋር ሲነፃፀር ይህ ከአመልካች ጋር በ1987ዓ.ም የተደረገው ውል በፍ/ቤት የጸደቀ ከመሆኑ አኳያ ሲታይ የተሸለ እና ህጋዊ ዉጤት ያለዉ መሆኑን፣ከዚህ በተጨማሪነትም ይህ በ6/04/1977ዓ.ም ተደረገ የተለዉ ሽያጭ ዉል የ8ኛ ተጠሪ ፈቃድና ተሳትፎ የሌለበት በመሆኑ ከዚህ አኳያም ተቀባይነት የሌለዉ መሆኑን፣የማይንቀሳቀስ ንብረትን በተመለከተ ተገቢዉ ማስረጃ ሳይቀርብና እንዲሁም በጉዳዩ መብትና ጥቅም ሳይኖራቸዉ ያቀረቡትን የመቃወሚያ አቤቱታ የስር ፍ/ቤቱ ተቀብሎ ስምምነቱን በመሰረዝ የሰጠው ውሳኔ መሰረታዊ የህግ አተረጓጎም ስህተት የተፈጸመበት በመሆኑ ሊሻር ይገባል የሚል ሲሆን 4ኛ ተጠሪም በበኩሉ ሚያዚያ 26/2014ዓ.ም የተጻፈ መልስ ያቀረቡ ሲሆን ይዘቱም፦ የ4ኛ ተጠሪ አውራሽ በ1987 ዓ.ም ወደ ኤርትራ ከሄዱ በኋላ የመንግስት ክልከላ በመኖሩ ወደ ኢትዮጵያ ለመመለስና ውሉን ለማስፈጸም አለመቻሉን፣ይህም በፍ/ብ/ህ/ቁ.1793 (ለ) የተመለከተውን ከአቅም በላይ የሆነ ሃይል የሚያቋቁም ከመሆኑም በላይ የቀረበዉ ዳኝነት ጥያቄም የመፋለም ክስ በመሆኑና እንዲሁም የሚኒስትሮች ምክር ቤት በኢትዩ ኤርትራ ከሃገር የወጡ ገለሰቦችን ንብረት በሚመለከት ያወጣው መመሪያ ከይርጋ ጥያቄ ጋር የሚገናኝ ባለመሆኑ ክሱ በይርጋ ቀሪ ሊደረግ አይችልም በማለት የስር ፍ/ቤት የሰጠው ብይን ስህተት የሌለበት መሆኑን፣የ4ኛ ተጠሪ አባት 7ኛ ተጠሪ በማህበር ተደርጅቶ ያገኘውን ቤት በወኪሉ በ6ኛ ተጠሪ አውራሽ አቶ ሞገስ ለማ አማካኝት በ1977ዓ.ም በተደረገ ውል የገዛው ሲሆን መብራትም የገባው በ4ኛ ተጠሪ አባት ስም በመሆኑና ይህም ሊፈቀድ የቻለው ሟች አባቴ በወቅቱ የሽያጭ ውሉን በማያያዝ ሰኔ 25/1978 ለማዘጋጃ ቤት ይኸው አካራካሪ ቤት የሚጸድቅ የማህበር ቤት ሽያጭ የተደረገበት ስለመሆኑ ፎርም ተሞልቶ የተቀመጠ መሆኑን፣ እንዲሁም የማህበር ቤትን አስመልክቶ የፍ/ብ/ህ/ቁ 1723 ድንጋጌ ተፈጻሚነት የሌለው ስለመሆኑ የፌ/ጠ/ፍ/ቤት ሰበር ሰሚ ችሎት በሰ/መ/ቁ 36294 ትርጉም የሰጠበት በመሆኑና እንዲሁም አመልካች በዚሁ ቤት ላይ በድጋሚ አደረግኩት የሚሉት ሽያጭ ውልም የተመዘገበ ባልሆነበት ሁኔታ በኃላ ላይ ከ7ኛ እና 8ኛ ተጠሪዎች ጋር ያደረጉት ሰምምነት ቀድሞዉንም በፍ/ቤት መጽደቁ መፅደቅ በሌለበት እና አላግባብ በመሆኑ ይህ በፍ/ቤቱ ራሱ የመቃወሚያ አቤቱታዉን መሰረት በማድረግ መታረሙ ተገቢነት ያለዉ መሆኑን፣አመልካች ቤቱን እንዲጠብቁ በአደራ የተሰጣቸው መሆኑን በስር ፍ/ቤት አቅርበን ባሰማናቸዉ ምስክሮች ያስረዳን ሲሆን አመልካች ግን ይህንን የሚያስተባብል ተቃራኒ ማስረጃ አላማቅረቡን፣የቤቱን ካርታ መያዝ የማይንቀሳቀስ ንብረት ባለሃብትነት ለማረጋገጥ ብቸኛ እና የማይተበል ማስረጃ አለመሆኑን፣ያቀረብናቸዉ ማስረጃዎችም በኢትጵያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በኩል ተረጋግጠዉ የቀረቡ መሆናቸዉን በስር ፍ/ቤት መረጋገጡንና የመሳሰሉትን በመዘረዘር ቀረበዉ ሰበር አቤቱታ ውድቅ ተደርጎ የስር ፍ/ቤቱ ውሳኔ እንዲጸና ዳኝነት የተጠየቀበት መሆኑን የሚያሳይ ነው፡፡እንዲሁም 1ኛ እና 3ኛ ተጠሪዎች በበኩላቸዉ በጋራ በመሆን መጋቢት 05/2014ዓ.ም የተጻፈ 4ኛ ተጠሪ ካቀረቡት ጋር ተመሳሳይነት ያለው መልስ አቅርበዋል፡፡
በሌላ በኩል 2ኛ እና 5ኛ ተጠሪዎች በበኩላቸዉ መልሳቸዉን ለማቅረብ እንዲችሉ ተለዋጭ ቀጠሮ ከተሰጣቸው በኋላም መልሳቸዉን ሳያቀርቡ በመቅረታቸዉ እንዲሁም 6ኛ ተጠሪም በጋዜጣ ጥሪ ቢደረግላቸውም ቀርበዉ መልስ ባለመስጠታቸዉ መልስ የማቅረብ መብታቸው መታለፉን የክርክሩ መዝገብ የሚየስረዳ ሲሆን አመልካችም በበኩላቸዉ ሚያዚያ 26/2014 ዓ.ም 7ኛ እና 8ኛ ተጠሪ ላቀረቡት መልስ፤ ግንቦት 12/2014 ዓ.ም 4ኛ ተጠሪ ላቀረቡት መልስ እንዲሁም መጋቢት 26/2014 ዓ.ም 1ኛ እና 3ኛ ተጠሪ ላቀረቡት መልስ የመልስ መልሳቸዉን በማቅረብ አቤቱታቸውን በማጠናከር ተከራክረዋል፡፡
አጠቃላይ የጉዳዩ አመጣጥና ግራ ቀኙ ክርክር ይዘት ከፍ ሲል የተገለፀውን የሚመስል ሲሆን ይህ ችሎትም ለዚህ ሰበር አቤቱታ ምክንያት የሆነውን የስር ፍ/ቤቱ ብይንና ውሳኔ አግባብነት አቤቱታው አስቀድሞ በሰበር ኣጣሪ ችሎቱ ከተያዘው ጭብጥ፣ ከግራ ቀኙ ክርክርና እንዲሁም ለጉዳዩ አግባብነት ካላቸው ህጉ ድንገጌዎች ጋር በማገናዘብ ጉዳዩን በሚከተለው መልኩ መርምረናል ፡፡
በዚሁ መሰረት እንደመረመርነውም የአመልካች የሰበር አቤቱታ ይዘት በጥቅሉ ሲታይ በሁለት ነጥቦች ዙሪያ ሲሆን ይሄውም አመልካች ከይርጋ አኳያ በስር ፍ/ቤት ባሁን 1ኛ-5ኛ ተጠሪዎች በቀረበው ዳኝነት ጥያቄ ላይ ያነሳውን የመጀመሪያ መቃወሚያ በተመለከተ በስር ፍ/ቤት በተሰጠዉ ብይን ላይ ያተኮረ ሲሆን ሌላኛው እና ዋነኛው ደግሞ በፍሬ-ጉዳይ ክርክሩ ላይ የስር ፍ/ቤቱ አመልካች ገዛው ከሚለው ጊዜ በፊት የቤቱ ባለቤትነት መብት በሽያጭ ወደ 1ኛ-5ኛ ተጠሪዎች አውራሽ ወደ ሆኑት አቶ ሚካኤል ወልዳይ ተላልፏል ወደሚል ድምደሜ ደርሶና ይሄንኑን ድምዳሜ መሰረት በማድረግ በጉዳዩ ላይ የሰጠውን ውሳኔ አግባብነት ላይ ያተኮረ ከመሆኑ አኳያ ሁለቱንም ነጥቦች ለያይተን እንደሚከተለዉ አንድ በአንድ መመልከት እንሞክራለን ፡፡
በመጀመሪያ የይርጋ መቃወሚያን በሚመለከት የቀረበውን የሰበር ቅሬታ በተመለከተ
ከስር ፍ/ቤት ብይንና ውሳኔ ግልባጩ በግልፅ መገንዘብ እንደሚቻለው ባአሁን 1ኛ-5ኛ ተጠሪዎች ስር ፍ/ቤት የቀረበው መቃወሚያ አቤቱታ በዋናነት መሰረት ያደረገው በቤቱ ላይ ውል ለማድረግ መብት ሳኖራቸው በአንድ በኩል ባሁን አመልካች በሌላ በኩል ደግሞ 7ኛ እና 8ኛ ተጠሪዎች መካከል ተደርጎና ለፍ/ቤቱ ጭምር ቀርቦ የፀደቀው ስምምነት ለአሁን አመልካች በአደራ እንዲጠብቅ በተሰጠ እና ንብረትነቱ የራሳቸው ባልሆነ ቤት ላይ በመሆኑ ፍ/ቤቱ ከዚህ ቀደም ስምምነቱን በማፅደቅ ረገድ በዚህ መዝገብ የሰጠው ውሳኔ በፍ/ብ/ስ/ስ/ህ/ቁ. 360(2) መሰረት ተሰርዞ አመልካች በአደራ ሊጠብቅ ከ1ኛ-5ኛ ተጠሪዎች ባለቤት እና አዉራሽ የተቀበለውን ቤት ለቆ እንዲያስረክብ ይወሰንልን የሚል በመሆኑና ይህም ከመቃወሚያ አቤቱታው ይዘት በግልፅ መገንዘብ እንደሚቻለው አመልካች ጠቅሶ እንደሚከራከረው ጉዳዩ የውል ይፈፀምልኝ ወይም እጃቸው ያልገባ ውርስ ሀብትን ለማስገባት የቀረበ ዳኝነት ጥያቄን የሚመለከት ሳይሆን ይልቁንም በንብረት ህጉ እና በተለይ ደግሞ ፍ/ብ/ህ/ቁ.1206 ድንጋጌና ተከታይ መሰረት የቤት ይገባኛል ወይም የመፋለም መብትን መሰረት በማድረግ የቀረበ ዳኝነት መሆኑን የሚየስገነዝብ ነው፡፡
እንዲህ ከሆነ ደግሞ በእርግጥም 1ኛ-5ኛ ተጠሪዎች የቤቱ ባለሀብት መሆን ያለመሆናቸው ጉዳይ፣ ጉዳዩ በፍሬ-ነገር ደረጃ በሚደረግ ክርክር እና በዚህ ደረጃ በሚያዘው ጭብጥ መሰረት በማድረግ ተጣርቶ እና ተመርምሮ ተገቢው ውሳኔ የሚሰጥበት መሆኑ እንደተጠበቀ ሆኖ በሌላ በኩል ግን ከላይ እንደተገለፀዉ በመቃወሚያ አቤቱታዉ ላይ የተገለፀው ፍሬ-ነገር የማይንቀሳቀስ ንብረትን (ቤትን) በሚመለከት የቀረበ የመፋለም ዳኝነት ጥያቄን የሚመለከት መሆኑን የሚያሳይ በመሆኑና ይህ ዓይነቱ ዳኝነት ጥያቄ ደግሞ በፌ/ጠቅላይ ፍ/ቤት ሰበር ችሎት ሰ/መ/ቁ.43600 በተሰጠ ትርጉም መሰረት በይርጋ የማይታገድ በመሆኑ አመልካች ይሄንን ጉዳይ በተመለከተ በመጀመሪያ መቃወሚያነት ያቀረባቸው የውል አፈፃፀም ክስን እና ውርስ ጉዳይን የሚመለከቱ ይርጋ ደንቦች ለጉዳዩ አግባብነት ስለማይኖራቸው የስር ፍ/ቤቱ ይሄንኑን በዚህ ረገድ በአመልካች የቀረበውን የይርጋ መቃወሚያ ከወዲሁ ወደ ፍሬ-ነገር ክርክሩ ከመግባቱ በፊት አስቀድሞ በብይን ውድቅ አድርጎ ማለፉ የስነ-ስርዓት ህጉን የተከተለ እና የቀረበዉ ዳኝነት ጥያቄን መሰረት ያደረገከ ሚባል በስተቀር (በተለይ በቀረበዉ መጀመሪያ ደረጃ መቃወሚያ ላይ በዚህ ደረጃ ብይን ሰጥቶ ከማለፍ አኳያ) ብይኑ የሚነቀፍና መሰረታዊ የህግ ስህተት የተፈፀመበት ሆኖ ባለመገኘቱ አመልካች በዚህ ረገድ ያቀረበውን ሰበር ቅሬታ ነጥብ በዚህ ምክንያት ባለመቀበል አልፈነዋል፡፡
ፍሬ-ጉዳዩን በሚመለከት በስር ፍ/ቤቶች የተሰጠውን ውሳኔ አግባብነት በተመለከተ
ከፍ ሲል እንደተጠቀሰው የክሱ አቤቱታ ሙሉ ይዘት ከጅምሩ ሲታይ ይህ በስር ፍ/ቤት በ1ኛ-5ኛ ተጠሪዎች የቀረበው ዳኝነት ጥያቄ የቤት ባለቤትነት መብትን ወይም የመፋለም ክስን መሰረት ያደረገ ሲሆን ይህ ለመቀወሚያ አቤቱታቸው መነሻ የሆነው የቤቱ ባለቤትነት መብታቸውም የመነጨው እንዲሁ ከውል መሆኑን በተጠቀሰዉ መቃወሚያ አቤቱታቸው፣ዳኝነት ጥያቄያቸው እና ክርክራቸዉ ይሄንኑን ጠቅሰው መከራከራቸውን የስር ፍ/ቤቱ ውሳኔ ግልባጭ ያስረዳል፡፡
ይህም ለክርክሩ ምክንያት የሆነውን ቤት የ1ኛ ተጠሪ ባለቤትና 2ኛ-5ኛ ተጠሪዎች አውራሽ የሆኑት አቶ ሚካኤል ወልዳይ በ06/04/1977ዓ.ም በተደረገ ሽያጭ ውል ገዝተውና ተረክበው እስከ 1987ዓ.ም ድረስ ሲገለገሉበት መቆየታቸውን፤ይሄንኑን ተጠቃሹን ቤት ሽያጭ ውል ስምምነት መሰረት በማድረግም የቤቱን ኤሌክትሪክ ማደል ዉል ጭምር በአውራሻቸው ስም በ29/08/1977ዓ.ም መደረጉንና እንዲሁም የቤቱ ስመ-ሀብት ዝውውርም እንዲደረግላቸው አውራሻቸው ሰኔ 25ቀን1978ዓ.ም በተሞላ ፎርም መጠየቃቸውንና በኃላም እኚሁ አውራሻቸው ለስራ ኤርትራ በ1987ዓ.ም ሲሄዱ ቤቱን እንዲጠብቁና እንዲያስተዳድሩ ለአመልካች በአደራ ሰጥተዉ መሄዳቸዉንና ይህም የቤቱ ባለቤትነት መብት አመልካች ቤቱን ገዝቻለዉ ከሚለዉ 1987ዓ.ም አስቀድሞ ከፍ ሲል በተጠቀሰዉ አግባብ የተላለፈላቸዉ መሆኑን በመዘርዘር ዳኝነቱን ማቅረባቸዉ እና መከራከራቸውን የስር ፍ/ቤቱ ዉሳኔ ግልባጭና አጠቃላይ የክርክሩ ሂደት ያሳያል፡፡
በመሰረቱ የማይንቀሳቀስ ንብረት ባለቤትነት ወይም በአንድ በማይንቀሳቀስ ንብረት ላይ የአላባ ጥቅም /መብት/ የመያዣ ወይም ሌላ የአልግሎት መብት ለማቋቋም ወይም ለማስተላለፍ የሚደረጉ ውሎች ሁሉ በፅሁፍ እና በሚገባ አኳኃን በፍ/ቤት መዝገብ ወይም ውል ለማዋዋል ስልጣን በህግ በተሰጠው አካል ፊት መሆን እንዳለባቸዉ አስገዳጅነት ባለው መልኩ በህግ አዉጪዉ በፍ/ብ/ስ/ስ/ህ/ቁ.1723(1)ስር ከመደንገጉም በላይ የአንድ የማይንቀሳቀስ ንብረት ባለሀብትነትን (ባለርስትነትን) በዉል ለማስተላለፍ ውሉን በተጠቃሹ የማይንቀሳቀስ ንብረት መዝገብ ማስመዝገብና ማስቀመጥ እንዲሁ አስፈላጊ መሆኑን ከፍ/ብ/ህ/ቁ.1185 ድንጋጌ ይዘት የምንገነዘበው ጉዳይ ነው፡፡ይህ ብቻ ሳይሆን ከዚህ በተጨማሪነትም አንድ የማይንቀሳቀስ ንብረት ሽያጭ ውል በማይንቀሳቀሰው ንብረት መዘገብ ካልተፃፈ በስተቀር በ3ኛ ወገኖች ላይ መቃወሚያ ሊሆን እንደማይችል በፍ/ብ/ህ/ቁ .2878 ስር በግልፅ ተደንግጎ እናገኛለን ፡፡
እንግዲህ የተያዘዉን ጉዳይም ከዚህ አኳያ ስንመለከት ይህ ክርክር የቀረበበት ቤት ባለሀብትነት መብቱ አስቀድሞ በ06/04/1977ዓ.ም በተደረገ ሽያጭ ውል መነሻነት ወደ 1ኛ -5ኛ ተጠሪዎች አውራሽ ተላልፏል ለማለት ይቻላል? ወይስ አይቻልም? ተጠሪዎችም ሆኑ አውራሻቸዉ መብቱ በሸያጭ ዉሉ መሰረት አሰቀድሞ የተላለፈላቸዉ መሆኑንና የቤቱ ባለሀብት የሚያሰኛቸዉን ህጋዊ መስፈርቶች ሁሉ አሟልተዉ መገኘታቸዉን ስር ፍ/ቤት ባቀረቡት ክርክር እና ማስረጃ ይሄንኑ አስረድተዋል ወይ ? የሚሉ እና ተያያዥ ነጥቦችን ከፍ ሲል ከተጠቀሱት ህጉ ድንጋጌዎች ጋር በማገናዘብ ጉዳዩ ሲመረመር የቤቱ ባለቤትነት መብት በፍ/ብ/ህ/ቁ.1185 ስር በተመለከተዉ አግባብ ከሻጭ ገዢ ወደተባለዉ ሰዉ በውል መተላለፉን በስር መቃወሚያ አመልካቾቹ በቀረበው ክርክር እና ማስረጃ በፍሬ-ነገር ደረጃ መረጋገጡን የስር ፍ/ቤቱ ዉሳኔ ግልባጭ አያመለክትም፡፡ይህ በስር መ/አመልካች አውራሽና 7ኛ ተጠሪ ወኪል በተባለው 6ኛ ተጠሪ አውራሽ መካከል አስቀድሞ በ06/04/1977 ዓ.ም ተደረገ የተባለው ቤቱ ሽያጭ ዉልም በህጉ አግባብ ውልን ለማዋዋል ስልጣን በተሰጠው አካል ፊት የተደረገና የተመዘገበ ነዉ በሚል የቀረበ ክርክርም ሆነ ማስረጃ ስለመኖሩም የክርክሩ ሂደት አያሳይም፡፡ይልቁንም ከግራ ቀኙ ክርክር እና ስር ፍ/ቤቱ ዉሳኔ ግልባጭ ይዘት መገንዘብ የተቻለዉ ዉሉ በአዋዋይ ፊት ተረጋግጦ አለመደረጉንና አለመመዝገቡን ሲሆን ቤቱ የማህበር ቤት ስለሆነ በዚህ አግባብ መደረግ እና መመዝገብ የሚያስፈልገዉ አይደለም በሚል በዚህ ሰበር ደረጃ የቀረበዉ መከራካሪያም ስር ፍ/ቤት ያልቀረበ እና ክርክር ያልተደረገበት ከመሆኑ አኳያ በፍ/ብ/ስ/ስ/ህ/ቁ.329 መሰረት ተቀባይነት ያለዉ አይደለም፡፡እንዲሁም ይህ ችሎት የስር ክርክሩን መዝገብ ጭምር በትዕዛዝ አስቀርቦ የሽያጭ ዉሉን ሰነድ ይዘት እንደተመለከተዉም ዉሉ ለማዘጋጃ ቤት ቀርቦ መፅደቅ እንዳለበት የሚያመላክት ሲሆን በዚህ መሰረት ለማዘጋጃ ቤቱ አሊያም ስልጣን ላለዉ አካል ቀርቦ ታይቶ እና ተረጋግጦ መፅደቁን የሚያሳይ ነገር የለም፡፡
እንዲህ ከሆነ ደግሞ በተለይ 8ኛ ተጠሪ የቤቱ ጋራ ባለሀብት መሆኗ(የነበረች መሆኑ) ባለከራከረበትና ይሄዉም በማስረጃ ጭምር በተረጋገጠበት ሁኔታ ቤቱን በውክልና ሽጧል ለተባለዉ ግለሰብ የሰጠችው ውክልና ስልጣን ሳይኖርና እንዲሁም የዉሉን መደረግም እንደማታቅ ክዳ በተከራከረችበት ሁኔታ የዉሉን መደረግ እና መኖር 8ኛ ተጠሪን ጨምሮ በሁሉም የስር መቃወሚያ ተጠሪዎች በሙሉ እንደታመነ የስር ፍ/ቤቱ ከድምዳሜ ደርሶ የሰጠዉ ዉሳኔ ከፍ ሲል የተጠቀሰዉን የፍ/ብ/ህ/ቁ.1723 ድንጋጌ ይዘትና ዓላማ እንዲሁም ይሄንኑን ድንጋጌ በተመለከተ በፌ/ጠቅላይ ፍ/ቤት ሰበር ችሎት በሰ/መ/ቁ.21448፣36887 እና 99124 የተሰጡ አሰገዳጅ ዉሳኔዎችን ያላገናዘበ በመሆኑ የሚነቀፍ እና መሰረታዊ የሆ የህግ ስህተት የተፈፀመበት ነዉ፡፡
ይህ ብቻ ሳይሆን ጉዳዩ ከፍ/ብ/ህ/ቁ.2878 ድንጋጌ አኳያም ሲታይ የዉሉ ተዋዋይ ባልሆነውና ይልቁንም ለዉሉ 3ኛ ወገን በሆነው አመልካች (ቤቱን በሌላ ሽያጭ ዉል ገዝቼና ተረክቤ እተገለገልኩበት እገኛለሁ በሚል እየተከራከረ ባለዉ ወገን) ላይ መቃወሚያ መሆን ይችል ዘንድ ይህ በ6/4/1977ዓ.ም በቤቱ ላይ ተደረገ የተባለዉ ሽያጭ ዉል በቤቱ ማህደር መዝገብ መመዝገብ እንዳለበት በህጉ የተደነገገ ሲሆን በተያዘው ጉዳይ ግን ውሉ በዚህ አግባብ ጭምር በቤቱ ማህደር ውስጥ መግባቱና መመዝገቡን ከ1ኛ-5ኛ ተጠሪዎች በኩል የቀረበ ክርክርም ሆነ ማስረጃ መኖሩን የክርክሩ ሂደት የማያሳይ ሲሆን ውሉ በዚህ አኳኃን ካልተመዘገበ ደግሞ ለውሉ 3ኛ ወገን በሆነው አመልካች ላይ መቃወሚያ ሊሆን ስለማይችል የስር መቃወሚያ አመልካቾች ዳኝነት ጥያቄ እና ክርክር ከዚህ አኳያም ሲታይ ተቀባይነት የሌለዉ በመሆኑ የቤቱ ባለቤትነት መብት ከፍ ሲል በተጠቀሱት ምክንያቶች ሁሉ ወደ 1ኛ-5ኛ ተጠሪዎች አዉራሽም ሆነ ወደ ራሳቸዉ ተላልፏል ለማለት የሚያስችል ሆኖ አላገኘንም፡፡
እንዲሁም የቤቱ አሌክትሪክ ውል በአውራሻቸው ስም መደረጉ፣ የቤቱ ስመ-ሀብት ዝውውር መጠየቂያ ቅፅ ወይም ፎርም መሞላቱ ብቻዉንና እንዲሁም ቤቱን ሲገለገሉበት መቆየታቸውም ሆነ ቤቱን ለአመልካች በአደራ ሰጥተናል በማለት መከራከራቸውና ይሄንኑንም በሰው ምስክሮች ማስነገራቸው የቤቱ ባለሀብነትነት መብት በህጉ መሰረት ከሻጭ ወደ አውራሻቸው መተላለፉን ሊያስረዳ የሚችል ለጉዳዩ አግባብነት እና ተገቢነት ያለዉ አስረጂ አይደለም፡፡
በመጨረሻም የስር መ/አመልካቾች ከዚህ ቀደም በሌላ መዝገብ ይሄንኑን ቤት በተመለከተ በአመልካች ላይ ባቀረቡት ክሳቸው ያሁን አመልካች ቤቱን በእጀ መናኛ እንደያዘባቸው ጠቅሰው አሁን ደግሞ በዚህ በተያዘዉ መዝገብ ቤቱን እንዲጠብቅልን በአደራ ሰጥተነው (የማይንቀሳቀስ ንብረት/ቤትን አስመልክቶ ለተደረገ አደራ ዉል በፍትሐብሔር ህጋችን አንቀፅ አንቀፅ 2771 እና ተከታይ ድንጋጌዎች መሰረት የህግ ጥበቃ ተደርጎለታልወይ? የሚለዉ ጥያቄ እንደተጠበቀ ሆኖ)ነበር በሚል ያቀረቡት ክርክራቸው እርስ በእርሱ የሚጋጭ እና የሚጣረስ ነዉ በሚል ያሁን አመልካች ከስር ጀምሮ ክርክር ያቀረበ ሲሆን በአንፃሩ ደግሞ 1ኛ-5ኛ ተጠሪዎች ይሄንኑን በዚህ ረገድ በአመልከች የቀረበዉን መከራከሪያ በግልፅ በመካድ ያቀረቡት ማስተባበያ ክርክር ስለመኖሩ መዝገቡ ስለሚያሳይና ይህም ዳኝነት ጥያቄያቸውን እና ክርክርራቸውን እውነታ ጥያቄ ውሥጥ የሚያስገባ ሆኖ አግኝተነዋል፡፡በመሆኑ የስር ፍ/ቤቶች ውሳኔ ከዚህ በላይ በተገፁት ምክንያቶች ሁሉ የሚነቀፍ እና መሰረታዊ የህግ ስህተት የተፈፀመበት ሆኖ በመገኘቱ ተከታዩ ተወስኗል፡፡
ዉሳኔ
1.የስር ፍ/መጀመሪያ ደረጃ ፍ/ቤት በኮ/መ/ቁ.74438 በ12/8/2013ዓ.ም የሰጠዉ ፍርድም ሆነ ይሄንኑን ፍርድ በመቀበል እና የቀረበለትን ይግባኝ ቅሬታ በመሰረዝ የስር ፌ/ከፍተኛ ፍ/ቤት ይግባኝ ሰሚ ችሎት በኮ/መ/ቁ.275104 በ24/5/2014ዓ.ም የሰጠዉ ብይን በፍ/ብ/ስ/ስ/ህ/ቁ.348 መሰረት ተሸረዋል፡፡
2.አመልካች ለክርክሩ ምክንያት የሆነዉን ቤት ለቆ ለ1ኛ-5ኛ ተጠሪዎች ሊያስረክብ አይገባም በሚል ተወስኗል፡፡
3.ይህ ሰበር ችሎት ክርክር ያስከተለዉን ውጪና ኪሳራ ግራ ቀኑ የየራሳቸዉን ይቻሉ ብለናል፡፡
4.ከስር ፍ/ቤት የመጣዉ ዋና ክርክሩ መዝገብ በመጣበት አግባብ ይመለስ ብለናል፡፡
5.በዚህ መዝገብ የካቲት 8 ቀን 2014ዓ.ም ተሰጥቶ የነበረዉ እግድ ተነስቷል፣ይፃፍ፡፡
ጉዳዩ እልባት አግኝቶ መዝገቡ በዉሳኔ የተዘጋ ስለሆነ ወደ መ/ቤት መለስ፡፡
የማይነበብ የአምስት ዳኞች ፊርማ አለበት፡፡
ፋ/ዘ