የኢትዮጵያ ፌደራላዊ ዲሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ
የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት
ሰበር ሰሚ ችሎት
የሰ/መ/ቁ. 220980
ቀን ፡- ጥቅምት 05 ቀን 2016 ዓ/ም
ዳኞች፡- እትመት አሰፋ
ደጀኔ አያንሳ
ኑረዲን ከድር
ሀብታሙ እርቅይሁን
ብርሃኑ መንግስቱ
አመልካቾች ፡- 1. አቶ ጎይቶም ግደይ - ቀረቡ
2. አቶ ካሳሁን ማሞ - ጠበቃ አወቀ አበራ - ቀረቡ
3. አቶ ምናለ ኃይሌ - ቀረቡ
ተጠሪ ፡- ታግሮ ቢዝነስ ኃ/የተ/የግል ማህበር - አልቀረቡም
መዝገቡ ተመርምሮ ተከታዩ ፍርድ ተሠጠ፡፡
ፍርድ
የሰበር አቤቱታው የቀረበው የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ይግባኝ ሰሚ ችሎት የሠጠው ውሳኔ መሠረታዊ የሕግ ስህተት ተፈጽሞበታል በሚል ነው፡፡ የክርክሩን አመጣጥ ከስር ፍርድ ቤት የመዝገብ ግልባጭ እንደተረዳነው አመልካቾች በስር ፍርድ ቤት ከሥር 1ኛ ተከሳሽ ወ/ሮ ማዕበል ፍጽም ጋር ተከሳሾች፤ ተጠሪ ከሳሽ ሆነው ተከራክረዋል፡፡ ጉዳዩ የተጀመረው በፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ሲሆን ተጠሪ ታህሳስ 02 ቀን 2011 ዓ/ም በተጻፈ ክስ 154 ባለ ሶስት እግር ባጃጆችን ከስር 1ኛ ተከሳሽ ወ/ሮ ማዕበል ፍጹም ለመግዛት ተስማምተው ብር 9,086,004.11 ታህሳስ 17 ቀን 2006 ዓ/ም እና የካቲት 19 ቀን 2006 ዓ/ም ከፍሎ ቀሪ ክፍያ ብር 2772003.34 ደግሞ ባጃጆቹን ስረከብ ከፍያለሁ፡፡ ነገር ግን እንደ አንድ ችርቻሮ ሻጭ ባጃጆቹን ካስተላለፍኩ በኋላ 2 አመልካች በ1ኛ አመልካች በፌዴራል ከፍተኘ ፍርድ ቤት በመዝገብ ቁጥር 161609 ባቀረበው ክስ ምክንያት እነዚህን ባለ ሶስት እግር ተሽከርካሪዎች ወ/ሮ ማዕበል ፍጹም አሽሽቶ ተጠሪ እጅ አሉ በማለት ቢያሳግዳቸውም ፍርድ ቤቱ በመዝገብ ቁጥር 161609 ያገዳቸው ባጃጆች ተጠሪ ከፍሎ ባለቤትነት ያገኘባቸው እና ያቋቋመባቸው ናቸው፡፡ ተጠሪ ዕግዱ እንዲነሳ እስከ ፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ድረስ ብከራከርም ተቀባይነት አላገኘሁም፡፡ 1ኛ አመልካች የታገዱት ባጃጆች የወ/ሮ ማዕበል ፍጹም በማስመሰል በተለያዩ ባንኮች የሚገኙ የተጠሪን ገንዘብ አሳግዷል፡፡ 2ኛ እና 3ኛ አመልካቾች በተለያዩ ፍርድ ቤቶች ከወ/ሮ ማዕበል ፍጹም ጋር ባደረጓቸው ውሳኔዎች መነሻ በተጠሪ ገንዘብ እንዲፈጸም ከፍተኛ ፍርድ ቤት አፈጻጸም ችሎት በመዝገብ ቁጥር 16715 ትዕዛዝ ሰጥቷል፡፡ በመሆኑም በየትኛውም ፍርድ ቤት ዕግድ ከመሰጠቱ በፊት ለተጠቃሚዎች በሽያጭ ያስተላለፋቸው ባጃጆች ባለቤትነት እንዲወሰንለት፣ ተጠሪ ባለው ንግድ ፈቃድ ከወ/ሮ ማዕበል ፍጸም የገዛቸውን 154 ባለ ሶስት እግር ተሸከርካሪዎች በመሸጥ ያገኘው ገንዘብ የግል ገንዘቡ በመሆኑ ለፍርድ አፈጻጸም ዕዳ መክፈያ ሊውል አይገባም ተብሎ እንዲፈረድለት ዳኝነት ጠይቋል፡፡
1ኛ እና 2ኛ አመልካቾች አንድ ዓይነት ክሱ የክስ ምክንያት የሌለው በፍርድ ማያልቅ ነገር ነው፤ የባለቤትነት ማረጋገጫ ውሳኔ በፍርድ ቤት ውሳኔ የሚሰጥበት እንዳልሆነ ሰበር ሰሚ ችሎት በመዝገብ ቁጥር 31906 ተወስኗል፤ ክሱ ቀደም ብሎ እስከ ሰበር ሰሚ ችሎት ደርሶ ውሳኔ የተሰጠበት ስለሆነ ዳግም ክስ ሊቀርብ አይችልም የሚል ይዘት ያለው የመጀመሪያ ደረጃ መቃወሚያ አቅርበዋል፡፡ 3ኛ አመልካች ከሌሎቹ አመልካቾች ጋር ተጣምሬ ልከሰስ አይገባም፤ ጉዳዩ ቀድሞ በፍርድ ያለቀ ነው፤ ጉዳዩ በፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት በመዝገብ ቁጥር 166908፤ በፌዴራል መጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት በመዝገብ ቁጥር 2200512 እየታየ ስለሆነ በዚህ ፍርድ ቤት ሊታይ አይገባውም፤ ክሱ በ6 ወር ይርጋ ሊታገድ ይገባዋል የሚሉ ይዘት ያላቸውን የመጀመሪያ ደረጃ መቃወሚያዎች አቅርበዋል፡፡
የፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት በመዝገብ ቁጥር 227839 ላይ በአመልካቾች የቀረቡትን መቃወሚያዎች መርምሮ ጉዳዩ በፌዴራል መጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት በመዝገብ ቁጥር 220512 ተይዞ የነበረው ስለተዘጋ መቃወሚያው ተቀባይነት የለውም፤ ጉዳዩ በፍርድ ቤት ውሳኔ ያገኘ ነው የሚለውን በተመለከተ የቀረበው ክስ ይዘት እና አመልካቾች ተመሳሳይ እንደሆኑ፣ ክሱም እነዚህኑ ባጃጆች የተመለከተ እና ባለቤትነት እንዲወሰን እንደሆነ መዝገቦቹ ስለሚያዝገነዝቡ ክሱ ቀድሞ በፍርድ ያለቀ ነው በማለት መቃወሚያውን በመቀበል መልስ ሰጪዎች በክሱ ምክንያት የደረሰባቸውን ወጪ እና ኪሳራ የመጠየቅ መብታቸውን ጠብቆ መዝገቡን የዘጋ ሲሆን 3ኛ አመልካች ያቀረበውን የወጪ እና ኪሳራ ዝርዝር አስመልክቶ ተጠሪ ብር 88935.00 እንዲከፍለው ውሳኔ ሰጥቷል፡፡
ተጠሪ ይህንን ውሳኔ በመቃወም የይግባኝ አቤቱታውን የካቲት 08 ቀን 2013 ዓ/ም ለፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት አቅርቧል፡፡ ፍርድ ቤቱም መዝገቡን መርምሮ የሰበር ሰሚ ችሎት በሰበር መዝገብ ቁጥር 184585 በሰጠው ውሳኔ የሻረው ጉዳይ በስር ፍርድ ቤት እየታየ ባለበት እና ዕግድ ይነሳልኝ አቤቱታ የባለቤትነት ውሳኔ አይደለም በሚል እንደሆነ ከመዝገቡ ግልባጭ የምንረዳው ነው፡፡ የስር ፍርድ ቤት ጉዳዩ በድጋሚ የቀረበ ነው ያለው ቀደም ሲል ተጠሪ በፍ/ብ/ሥ/ሥ/ህ/ቁ 418 ያቀረበውን መቃወሚያ መሰረት አድርጎ ነው፡፡ በሌላ በኩል የሰበር ሰሚ ችሎት በሰበር መዝገብ ቁጥር 184585 የሰጠው ውሳኔም አሁን ክርክር እየተደረገበት ላለው መዝገብ ውሳኔ እንዳይሰጥበት የሚከለክል አይደለም፡፡ በመሆኑም የስር ፍርድ ቤት ጉዳይ በመታየት ላይ ነው በማለት መቃወሚያውን የተቀበለ ሲሆን በሌላ በኩል ደግሞ የሰበር ሰሚ ችሎትም ጉዳዩ በስር ፍርድ ቤት እየታየ ነው በማለት የፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት በመዝገድ ቁጥር 167153 እና የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ይግባኝ ሰሚ ችሎት በመዝገብ ቁጥር 166908 የሰጠውን ውሳኔ ሽሮታል፡፡ የስር ፍርድ ቤት ጉዳዩ በሌላ ፍርድ ቤት እየታየ ነው በሚል ምክንያት የይግባኝ ባይን ክስ ውድቅ ያደረገው ተገቢ ሆኖ አልተገኘም፡፡ ከክርክሩ ሂደት መገንዘብ የተቻለው በወ/ሮ ማዕበል ፍጹም እና አመልካቾች መካከል በነበረው የአፈጻጸም ክርክር ንብረትነታቸው የወ/ሮ ማዕበል ፍጹም ናቸው በሚል 154 ባለ 3 እግር ባጃጅ ተሽከርካሪዎች በተጠሪ እጅ ስለሚገኙ ለፍርድ ማስፈጸሚያነት እንዲውሉ በስር ፍርድ ቤት ታግደዋል፡፡ በየደረጃው ባሉት ፍርድ ቤቶች የተሰጠው ውሳኔም ተጠሪ በባጃጆቹ ላይ የቀዳሚ መብት የለውም በሚል ምክንያት አቤቱታው ውድቅ መደረጉን እንጂ ባጃጆቹ የወ/ሮ ማዕበል ፍጹም መሆናቸውን የሚያሳዩ እንዳልሆኑ ከውሳኔዎቹ ይዘት የምንገነዘበው ነው፡፡ ይግባኝ ባይ በባጃጆቹ ላይ የቅድሚያ መብት የለውም በሚል ቀደም ሲል በተሰጡት ውሳኔዎች የተደረሰበት ድምዳሜ ባጃጆቹ የወ/ሮ ማዕበል ፍጹም ናቸው በሚል እንደተወሰነ ሊተረጎም የሚገባው ስላልሆነ በማለት የስር ፍርድ ቤቱን ውሳኔ በመሻር የስር ፍርድ ቤቱ የተዘጋውን መዝገብ በማንቀሳቀስ በፍሬ ነገሩ ላይ ግራ ወገኖች የሚያቀርቡትን ክርክር እና ማስረጃ ከሰማ በኋላ ተገቢውን እንዲወስን መልሶ ልኮለታል፡፡
ይሕ የሠበር አቤቱታ የቀረበው በዚህ ውሳኔ ነው፡፡ አመልካቾች በቀን 07/06/2014 ዓ/ም በጻፉት የሰበር አቤቱታ ቀደም ሲል በተወሰኑ የከፍተኛ ፍርድ ቤት መዝገብ ቁጥር 161609 በ24/06/2008 ዓ/ም፣ የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት በመዝገብ ቁጥር 125952 በ22/05/2009 ዓ/ም እና በፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ሰበር መዝገብ ቁጥር 138823 በ14/07/2010 ዓ/ም የተሰጠው ፍርድ በጉዳዩ የመጨረሻ ውሳኔ የተሰጠበት እና በፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት የቀረበው ክስ በድጋሚ የቀረበ ነው በማለት ሲሆን የከፍተኛው ፍርድ ቤት የወሰነው ፍርድ ቤት የወሰነው እነዚህን ውሳኔዎች መሰረት በማድረግ የመጨረሻ ውሳኔ ያገኘ ጉዳይ መሆኑን በማረጋገጥ ስለሆነ ግንኙነት የሌላቸውን መዝገቦች በማጣቀስ ሰበር ሰሚ ችሎቱ በመዝገብ ቁጥር 138823 የተሰጠውን ውሳኔ የተሻረ በሚመስል መልኩ የሰጠው ውሳኔ ተገቢ አይደለም፡፡ የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት በፍትሐ ብሔር ሥነ-ሥርዓት ህግ ቁጥር 418 መሰረት የሚቀርብ አቤቱታ ለአፈጻጸም እንዲውል ዕግድ በተላለፈበት ንብረት ላይ የቅድሚያ መብት ያለው መሆን ያለመሆን ላይ የተገደበ ከመሆኑ አንጻር ሲታይ ተጠሪ በባጃጆቹ ላይ የቅድሚያ መብት የለውም በሚል ቀደም ሲል በተሰጡት ውሳኔዎች የደረሰበት ድምዳሜ ባጃጆቹ የፍርድ ባለዕዳ ናቸው በሚል እንደተወሰነ ሊተረጎም የሚገባው አይደለም በማለት የሰጠው ሀተታ እና የደረሰበት ድምዳሜ መሰረታዊ የህግ ስህተት የተፈጸመበት ነው፡፡ ባጃጆቹን ተጠሪ አልገዛም፤ ገዛሁበት በማለት ያቀረበው ማስረጃ በፍርድ ተቀባይነት የለውም ተብሎ ባጃጆቹ የባለዕዳው መሆኑን ያረጋገጠ በመሆኑ የተፈረደውን ግልጽ ፍርድ እንዳልተፈረደ በማድረግ የተሰጠው ውሳኔ ህጋዊ ባለመሆኑ መዝገቦቹ ቀርበው ውሳኔው ታይቶ የጠቅላይ ፍርድ ቤት ፍርድ ተሰብሮ ታይቶ እንዲሻርልን እንጠይቃለን በማለት ዳኝነት ጠይቀዋል፡፡
የሰበር አጣሪ ችሎት ጉዳዩን ተመልክቶ ቀደም ሲል የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት በመዝገብ ቁጥር 125952 እንዲሁም ሰበር ሰሚው ችሎት በመዝገብ ቁጥር 138823 ተከራክረው በውሳኔ ያለቀ ሆኖ ሳለ የስር ፍርድ ቤት ድጋሚ የቀረበ ክስ አይደለም በማለት የወሰነበትን አግባብነት ለማጣራት ተጠሪዎች መልስ እንዲያቀርቡ አዟል፡፡
ተጠሪ ግንቦት 30 ቀን 2014 ዓ/ም በተጻፈ የመከላከያ መልስ ጉዳዩ በፍብ/ሥ/ሥ/ሕ/ቁ. 320(3) መሠረት ሰበር/ይግባኝ የሚቀርብበት የመጨረሻ ውሳኔ አይደለም፡፡ ተጠሪ ከወ/ሮ ማዕበል ፍጹም ጋር ውል አለው ወይም የለውም የሚለው ጭብጥ በፍሬ ነገር ክርክር በማስረጃ ተጣርቶ እና በህግ ላይ ተመስርቶ ውሳኔ የሚሰጥበት የፍሬ ነገር እና የህግ ክርክር እንጂ በፍ/ብ/ሥ/ሥ/ህ/ቁ 244 የሚሸፈን የመቃወሚያ ክርክር አይደለም፡፡ በተጠሪ እና በወ/ሮ ማዕበል ፍጹም መካካል በየደረጃው ባሉ ፍርድ ቤቶች በመዝገብ ቁጥር 161609፣ በመዝገብ ቁጥር 125952 እና በመዝገብ ቁጥር 138823 የሰጠው ውሳኔ ዕግድ እንዲነሳ በቀረበ አቤቱታ ላይ የተሰጠ እንጂ ንብረቱ የተጠሪ ነው ወይስ የወ/ሮ ማዕበል ፍጹም ነው የሚል ክርክር ተካሂዶ የተሰጠ ውሳኔ ስላልሆነ በዚህ ረገድ የቀረበውን መከራከሪያ አግባብነት የለውም፤ በየደረጃው ባሉ ፍርድ ቤቶች በመዝገብ ቁጥር 167153፣ 166908 እና 184585 የተደረገው የአፈጻጸም ክርክር ሲሆን ለተጠሪ በተሸጡ ባጃጆች ፍርዱ ሊፈጸም ይገባል ወይስ አይገባም የሚለውን ሰበር ሰሚ ችሎቱ በተጠሪ ገንዘብ ሊፈጸም አይገባም በመጀመሪያ በመዝገብ ቁጥር 227839 በከፍተኛ ፍርድ ቤት በመካሄድ ላይ ያለው ክርክር የመጨረሻ ውሳኔ ያግኝ በማለት ፍርድ ሰጥቷል፡፡ በመቀጠል ተጠሪ በመዝገብ ቁጥር 227839 የተሰጠው ውሳኔ ቅር ስላሰኘኝ በፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ አቤቱታ አቅርቤ ያሻርኩ ስለሆነ ሆነ እና የአመልካቾችን መቃወሚያ ውድቅ በማድረግ የበታች ፍርድ ቤት በፍሬ ነገር ላይ አከራክሮ ውሳኔ እንዲሰጥ በማለት ውሳኔ የሰጠ ስለሆነ የስር ፍርድ ቤት ውሳኔ የሚነቀፍበትም ሆነ መሰረታዊ የህግ ስህተት የተፈጸመበት አይደለም ተብሎ የተሰጠው ውሳኔ ሊጸናልን ይገባል እንዲባልልን በማለት ዳኝነት ጠይቀዋል፡፡ አመልካቾች ሰኔ 06 ቀን 2014 ዓ/ም የሰበር አቤቱታቸውን በማጠናከር የመልስ መልሳቸውን ሰጥተዋል፡፡
የክርክሩ ሂደት በአጭሩ ከላይ የተገለጸው ሲሆን እኛም ተጠሪ ያቀረበው ክስ አስቀድሞ በፍርድ ያለቀ ነው ወይስ አይደለም? የሚለውን ጭብጥ በመያዝ መዝገቡን መርምረናል፡፡
በመጀመሪያ ተጠሪ ጉዳዩ ላይ የመጨረሻ ፍርድ የለም፤ የሰበር አቤቱታ ሊቀርበበት አይገባም በማለት ያቀረቡትን ክርክር መርምረናል፡፡ በፍትሐ ብሔር ሥነ ሥርዓት ሕጉ ወይም በሌላ ሕግ ላይ በተለየ ሁኔታ ካልተደነገ በስተቀር በአንድ ጉዳይ ተከራካሪ የሆነ ሰዉ በሥነ ሥርዓት ሕጉ ስድስተኛ መጽሐፍ ስለይግባኝ አቀራረብ የተዘረጋዉን ሥነ ሥርዓት ተከትሎ በፍትሐ ብሔር ጉዳይ በተሰጠ የመጨረሻ ፍርድ ላይ ይግባኝ የማቅረብ መብት አለዉ፡፡ በዚሁ የሕጉ መጽሐፍ በቁጥር 320/3 ስር እንደ መጨረሻ ፍርድ የማይቆጠር እና በተናጠል ይግባኝ ሊባል የማይቻለዉ ጊዜያዊ አገልግሎት ባላቸዉ ጉዳዮች ላይ የተሰጡ ትእዛዛት ወይም ዉሳኔዎች(decision or order of any court on interlocutory matters) የትኞቹ እንደሆኑ በዝርዝር ተመልክቷል፡፡በዚህ መልኩ በዝርዝር ከተጠቀሱት ዉስጥ አንዱ በመጀመሪያ ደረጃ መቃወሚያነት የሚቀርብ መከራከሪያ ላይ ፍርድ ቤቱ የሚሰጠዉን ተገቢ መስሎ የታየዉን ዉሳኔ የሚመለከት ነዉ፡፡በእንዲህ አይነት ዉሳኔ ላይ ያለዉን ቅሬታ በተመለከተ ይግባኝ ማቅረብ የሚቻለዉ ለክርክሩ የመጨረሻ የፍርድ ዉሳኔ ከተሰጠ በኋላ በሥረ ነገሩ ላይ በተሰጠ የፍርድ ዉሳኔ ላይ ካለዉ ቅሬታ ጋር በማካተት ነዉ፡፡ ጊዜያዊ አገልግሎት ባላቸዉና ተያያዥ በሆኑ ዉሳኔዎች/ትእዛዛት ላይ በሥረ ነገሩ ላይ ዉሳኔ ሳይሰጥ ይግባኝ የሚቀርብ ከሆነ ይግባኝ ሰሚዉ ፍርድ ቤት እንዲህ አይነት ጊዜያዊ አገልግሎት ያላቸዉ ትእዛዛት/ዉሳኔዎች ተጠቃለዉ ቢቀርቡ ኖሮ በአንድ መዝገብ ይግባኙን አይቶ የተጠቃለለ(ወጥ) ዉሳኔ መስጠት እየቻለ በየጊዜያዊ ትእዛዛት/ዉሳኔዎች ላይ በተነጣጠለ መልኩ በበርካታ መዝገቦች ላይ የሚቀርበዉን ይግባኝ በየጊዜዉ እየመረመረ ዉሳኔ ለመስጠት እንዲገደድ ያደርጋል፡፡ይሕም ክርክሮች በአንድ በሥነ ሥርዓት ሕጉ በተዘረጋ በታወቀና ወጥነት ባለዉ ሂደት መቋጫ አንዲያገኙ (finality through recognized procedural due process of law) ሥነ ሥርዓት ሕጉ አልሞ የዘረጋዉ ሥነ ሥርዓት ተግባራዊ እንዳይሆን ያደርጋል ፡፡ በተጨማሪም ተከራካሪ ወገኖችን ከአላስፈላጊ የሰዉ ሀብት፣የጊዜና የወጪ ብክነት በማዳን ለክርክራቸዉ እልባት ለማስገኘት ብሎም የፍርድ ቤቶች የክርክር አመራር በአነስተኛና ምክንያታዊ በሆነ የሀብትና የጊዜ አጠቃቀም (judicial economy) ተከናዉኖ ክርክሮች ወጥነት ያለዉን (consistent) እልባት እንዲያገኙ ለማድረግ ሕጉ ያሰበዉ ዓላማ እንዳይሳካ ያደርጋል፡፡ እንዲሁም ተከራካሪዎች ጊዜያዊ አገልግሎት ባላቸዉ ዉሳኔዎች/ትእዛዞች ላይ በየጊዜዉ በተናጠል ይግባኝ በማቅረብ የፍትሐ ብሔር ፍትህ አመራር ሂደቱን ባልተገባ መንገድ እንዳይጠቀሙ በሚያደርግ መልኩ ፍርድ ቤቶች ሂደቱን እንዲቆጣጠሩ (administration of civil justice by judiciary preventing misuse of procedure) ለማስቻል የተዘረጋዉ ሥነ ሥርዓት ገብራዊ እንዳይሆን ያደርጋል፡፡
በተያዘው ጉዳይ የሥር ከፍተኛ ፍርድ ቤት የመጀመሪያ ደረጃ መቃወሚያን በመቀበል የመጨረሻ ውሳኔ የሰጠ ሲሆን ጉዳዩን በይግባኝ የተመለከተው ፍርድ ቤት ደግሞ የመጀመሪያ ደረጃ መቃወሚያው ተቀባይነት የለውም በማለት ጉዳዩ በሥረ-ነገሩ እንዲወሰን ለሥር ከፍተኛ ፍርድ ቤት መልሷል፡፡ በፍብ/ሥ/ሥ/ሕ/ቁ. 320/3 ስለ መጀመሪያ ደረጃ መቃወሚያ የተመለከተው ጉዳዩን በመጀመሪያ ደረጃ ለያዘው ፍርድ ቤት እንጂ ለይግባኝ ሰሚ ፍርድ ቤት ተፈጻሚነት ያለው አይደለም፡፡ ይግባኝ ሰሚ ችሎት የሚሰጠው ውሳኔ ለይግባኝ ምክንያት የሆነው ጉዳይ ላይ በውሳኔ የሚቋጭና በራሱ የመጨረሻ የሆነ በመሆኑ ይግባኝ ሆነ ሰበር አቤቱታ ሊቀርበበት የሚችል ነው፡፡ ሰበር ችሎቱ በመዝገብ ቁጥር 119851 /በቅጽ 23 እንደታተመ/ የሰጠው ውሳኔም በመጀመሪያ ደረጃ መቃወሚያ ላይ በይግባኝ ሰሚ ችሎት የሚሰጥ ውሳኔ ራሱች ችሎ የሰበር አቤቱታ እንዳይቀርብበት የሚከለክል ሳይሆን በጊዜው ይግባኝ ካልቀረበበት ጉዳዩ ተጠቃሎ ሲቀርብ በሰበር ችሎቱ ሊታይ የሚችል መሆኑን ነው፡፡ በይግባኝ ሰሚ ችሎት በመጀመሪያ ደረጃ መቃወሚያ ላይ የተሰጠው ውሳኔ ይግባኝ/ሰበር አቤቱታ የማይቀርበበት ከሆነ በመቃወሚያ ሊቋጭ ይችል የነበረ ክርክር ወደሙግት ሂደት እንዲገባና ፍርድ ቤቱ ሆነ ተከራካሪዎች አላስፈላጊ ጊዜና ወጪ እንዲያባክኑ የሚያደርግ በመሆኑ የሥነ-ሥርዓት ሕጉን ዓላማ የሚያሳካ አይሆንም፡፡ ስለሆነም በይግባኝ ሰሚ ችሎት ውሳኔ ላይ የሰበር አቤቱታ መቅረቡ ሕጉን የተከተለ በመሆኑ በዚህ ረገድ ተጠሪ ያቀረበውን ክርክር አልተቀበልነውም፡፡
ወደዋናው ጉዳይ ስንመለስ ተጠሪ ታህሳስ 02 ቀን 2011 ዓ/ም በተጻፈ ክስ 154 ባለ ሶስት እግር ባጃጆችን ከስር 1ኛ ተከሳሽ ወ/ሮ ማዕበል ፍጹም ለመግዛት ተስማምተው ብር 9,086,004.11 ታህሳስ 17 ቀን 2006 ዓ/ም እና የካቲት 19 ቀን 2006 ዓ/ም ቅድመ ክፍያ ከፍሎ ቀሪ ክፍያ ብር 2,772,003.34 ደግሞ ባጃጆቹን ስረከብ ከፍያለሁ፡፡ ነገር ግን እንደ አንድ ችርቻሮ ሻጭ ባጃጆቹን ካስተላለፍኩ በኋላ 2ኛ አመልካች በሥር 1ኛ ተከሳሽ ላይ በፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት በመዝገብ ቁጥር 161609 ባቀረበው ክስ ምክንያት እነዚህን ባለ ሶስት እግር ተሽከርካሪዎች ወ/ሮ ማዕበል ፍጹም አሽሽቶ ተጠሪ እጅ አሉ በማለት ቢያሳግዳቸውም ፍርድ ቤቱ በመዝገብ ቁጥር 161609 ያገዳቸው ባጃጆች ተጠሪ ከፍሎ ባለቤትነት ያገኘባቸው እና ያቋቋመባቸው ናቸው፡፡ ተጠሪ ዕግዱ እንዲነሳ እስከ ፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ድረስ ብከራከርም ተቀባይነት አላገኘሁም፡፡ 1ኛ አመልካች የታገዱት ባጃጆች የወ/ሮ ማዕበል ፍጹም በማስመሰል በተለያዩ ባንኮች የሚገኙ የተጠሪን ገንዘብ አሳግዷል፡፡ 2ኛ እና 3ኛ አመልካቾች በተለያዩ ፍርድ ቤቶች ከወ/ሮ ማዕበል ፍጹም ጋር ባደረጓቸው ውሳኔዎች መነሻ በተጠሪ ገንዘብ እንዲፈጸም ከፍተኛ ፍርድ ቤት አፈጻጸም ችሎት በመዝገብ ቁጥር 16715 ትዕዛዝ ሰጥቷል፡፡ በመሆኑም በየትኛውም ፍርድ ቤት ዕግድ ከመሰጠቱ በፊት ለተጠቃሚዎች በሽያጭ ያስተላለፋቸው ባጃጆች ባለቤትነት እንዲወሰንለት፣ ተጠሪ ባለው ንግድ ፈቃድ ከወ/ሮ ማዕበል ፍጸም የገዛቸውን 154 ባለ ሶስት እግር ተሸከርካሪዎች በመሸጥ ያገኘው ገንዘብ የግል ገንዘቡ በመሆኑ ለፍርድ አፈጻጸም ዕዳ መክፈያ ሊውል አይገባም ተብሎ እንዲፈረድለት ዳኝነት ጠይቋል፡፡ በአመልካቾች በኩል ክሱ አስቀድሞ በተለያዩ መዝገቦች በፍርድ ያለቀ ነው በማለት የመጀመሪያ ደረጃ መቃወሚያ አቅርበዋል፡፡
በፍብ/ሥ/ሥ/ሕ/ቁ. 5(1) መሠረት በሕግ ሥልጣን የተሠጠው ማናቸውም ፍርድ ቤት ክርክሩን ተቀብሎ የመጨረሻ ፍርድ ከሠጠ በኋላ ቀድሞ በፍርድ የተወሰነው ክርክር ሥረ-ነገርና የተያዘው ጭብጥ አንድ ዓይነት ከሆነ፤ በክርክሩ ላይ የነበሩት ወይም ከተከራካሪዎቹ መብት ያገኙ ሦስተኛ ወገኖች በዚያው ነገር ሁለተኛ ክስ ማቅረብ አይችሉም፡፡ በድንጋጌው መሠረት ጉዳዩ አስቀድሞ በፍርድ አልቋል ለማለት የተዘረዘሩት አራት መስፈርቶች በአንድነት መሟላት አለባቸው፡፡ የመጀመሪያው መስፈርት ጉዳዩን የተመለከተው በሕግ ሥልጣን የተሠጠው ማናቸውም ፍርድ ቤት መሆኑ ነው፡፡ በሕግ ሥልጣን የተሰጠው የሚለው ትርጉም የሚያስፈልገው መስፈርት ነው፡፡ በፍርድ ቤት የሥረ-ነገር ሥልጣን ሳይኖረው የተሠጠ ውሳኔ በፍብ/ሥ/ሥ/ሕ/ቁ. 212 እንደተመለከተው በይግባኝ እስካልተለወጠ ድረስ የጸና በመሆኑ ጉዳዩን አስቀድሞ ፍርድ እንደተሠጠበት የሚያስቆጥር ነው፡፡ ስለሆነም በሕግ ሥልጣን የተሠጠው የሚለው የሥረ-ነገርና አካባቢያዊ ሥልጣንን የሚመለከት ሳይሆን አስቀድሞ ጉዳዩ የታዬው በሕግ ዳኝነት ለመስጠት ሥልጣን ያለው ፍርድ ቤት ወይም ዳኝነት ነክ አካል መሆኑን ለማመላከት ነው፡፡ ይህም በፍርድ ቤት ሥልጣን ሳይኖረው ፍርድ መስጠት እንደ አስገዳጅ ውሳኔ የሚቆጠርና የሚፈጸም መሆኑን የሚያሳይ እና በኢትዮጵያ እንዳልተሰጠ የሚቆጠር ፍርድ (void judgment) እንደሌለ ያስረዳል፡፡ ዳኝነት ለመስጠት በሕግ ሥልጣን ያልተሠጣቸው አካላት ጉዳዩ ላይ አስቀድመው በአስተዳደር ማየታቸው ሆነ ውሳኔ መስጠታቸው ጉዳዩን በፍርድ እንዳለቀ የማያስቆጥር እና ክርክር ከማድረግ የሚከለክል አይሆንም፡፡ ይህም በኢፌዲሪ ሕገ-መንግሥት አንቀጽ 37 እና አንቀጽ 79(1) እንደተመለከተው የመዳኘት ሥልጣን የፍርድ ቤቶች እና የዳኝነት ነክ አካል ብቻ መሆኑን የሚያሳይ እና በኢፌዲሪ ሕገ-መንግሥት አንቀጽ 50(2) የመንግሥት አካላትን የሥልጣን ክፍፍል መርህን (principle of separation of powers) የተከተለ መሆኑን የሚያረጋግጥ ነው፡፡
ሁለተኛው መስፈርት አስቀድሞ በፍርድ ቤት የተሠጠው የመጨረሻ ፍርድ መሆን አለበት የሚለው ነው፡፡ ፍርድ ቤቱ ክርክሩን አይቶ ጉዳዩ ላይ የመጨረሻ እልባት ወይም ውጤት የሠጠበት መሆን እንዳለበት የሚያስረዳ መስፈርት ነው፡፡ ጉዳዩ በመጀመሪያ ሆነ በይግባኝ በመሠማት ላይ እያለ በፍብ/ሥ/ሥ/ሕ/ቁ. 69(2)፣ አንቀጽ 70(መ) እና አንቀጽ 73 በተመለከተው አግባብ መዝገቡ ከተዘጋም፤ በፍብ/ሥ/ሥ/ሕ/ቁ. 74(1) እንደተመለከተው በተቋረጠው ጉዳይ አዲስ ክስ ማቅረብ መከልከሉ ጉዳዩ በፍርድ አልቋል የሚለውን መርህ የሚከተል ነው፡፡ በሌላ በኩል በፍብ/ሥ/ሥ/ሕ/ቁ. 231(1) የተመለከተው በክስ አቤቱታው የተገለጸው የማያስከስስ መሆን ወይም የሥረ-ነገር ሥልጣን አለመኖር ምክንያት ተደርጎ ክሱ መቋረጡ በጉዳዩ ላይ የመጨረሻ ፍርድ ያልተሠጠበት ስለሆነ በፍርድ እንዳለቀ የሚያስቆጥር አይሆንም፡፡ የክስ ምክንያት ከሕግ ወይም ከውል የመነጨ ግዴታ መኖሩን፣ የተጠየቀው ዳኝነት በፍርድ ቤት የሚዳኝ መሆን አለመሆኑን እና በክሱ ዝርዝር ውስጥ የተመለከቱት ጉዳዮች ቢረጋገጡ የተጠየቀውን ዳኝነት ለከሳሽ ለመወሰን ህግ የሚፈቅድ መሆን አለመሆኑን መመርመርን የሚጠይቅ ነው፡፡ ይህም የክስ ምክንያት የሌለው ጉዳይ የሚለው በዋነኛነት ዳኝነቱን ለመጠየቅ ከህግ የመነጨ ግንኙነት እያለው ግን በፍርድ ቤት ሊዳኙ የማይችሉ ጉዳችን (non-justiciable matters) የጉዳዩ ባሕሪ በፍርድ ቤት ሥልጣን ሥር ሊወድቁ የማይችሉ፣ አከራክሮ ሊፈጸም የሚችል ውሳኔ ሊሰጥባቸው የማይችሉ በመሆናቸውና ከሳሽ ወገን ክሱን ሲያቀርብ የጠቀሰው ወይም የገለጸው የክሱ መሰረት የሆነው ምክንያት በህግ የክስ መሰረት ሊሆን የማይችል ከሆነ የማያስከስስ ነው ተብሎ ክሱ ውደቅ የሚደረግበት ሥርዓት ነው፡፡ ጉዳዩም በሥረ-ነገሩ ታይቶ ውሳኔ ያላረፈበት በመሆኑ እንደ መጨረሻ ፍርድ የሚቆጠር አይደለም፡፡ የሥረ-ነገር ሥልጣን ባለመኖር ክሱ ውድቅ መደረጉም ሥልጣን ባለው ሌላ የዳኝነት አካል ጉዳዩ ቀርቦ ሊወሰን የሚችል በመሆኑና በሥረ-ነገሩ ጉዳዩ ላይ ውሳኔ ያልተሠጠበት በመሆኑ በፍርድ እንዳለቀ ጉዳይ ተቆጥሮ መቃወሚያ ሊቀርብበት የሚችል አይደለም፡፡ ስለሆነም የመጨረሻ ፍርድ የሚለው በሥረ-ነገሩ መታየትን መሠረት ያደረገ ቅድመ ሁኔታ መኖር እንዳለበት የሚያስገነዝብ ነው፡፡
ሦስተኛው መስፈርት አስቀድሞ ፍርድ ያረፈበት ጉዳይ ሥረ-ነገሩና ጭብጡ አሁን ከተያዘው ጉዳይ ጋር አንድ ዓይነት መሆን አለበት የሚለው ነው፡፡ የክርክሩ መነሻ ጉዳይ አንድ መሆኑ ብቻ ሳይሆን ፍርድ ቤቱ በጭብጥነት የመረመረው ጉዳይ አሁን በተያዘው ክርክርም በጭብጥነት ተይዞ የሚመረመር ከሆነ ውጠቴ አስቀድሞ ፍርድ ያረፈበት ይሆናል፡፡ ሥረ-ነገሩ ተመሳሳይ ሆኖ ነገር ግን የሚያዘው ወይም የተያዘው ጭብጥ የተለያዬ ከሆነ በተያዘው ጭብጥ ላይ የቀደመ ፍርድ ባለመኖሩ ጉዳዩ በፍርድ እንዳለቀ ሳይቆጠር ክርክሩ ቀጥሎ ፍርድ ሊያርፍበት የሚችል ጉዳይ ነው፡፡ በሕጉ ላይ የተቀመጠው አራተኛው መስፈርት የተከራካሪዎች ወይም ከተከራካሪዎች መብት ያገኙ ሦስተኛ ወገኖች ተመሳሳይ መሆን እና በእነርሱ መካከል ያለ ክርክር መሆኑ ነው፡፡ የዚህ መስፈርት መነሻ ፍርድ የአስገዳጅነት ሀይል ሆነ ውጤት የሚኖረው በተከራካሪዎች መካከል ብቻ ነው የሚል ነው፡፡ ከተከራካሪዎች ውጭ ፍርዱን በመያዝ መብት ማቋቋም ሆነ ማስፈጸም አይቻልም፡፡ ፍርድ ቤት ጉዳዩን የሚመረምረው ሆነ ፍርድ የሚሠጠው ከተከራካሪዎች መካከል የተሻለ መብት ያለው ማን ነው ከሚለው ነጥብ አኳያ ብቻ ነው፡፡ በጉዳዩ ላይ ያላቸው መብት በፍርድ ቤቱ ሳይመረመር እና የመደመጥ ሆነ የመከላከል መብታቸው ሳይከበር ተከራካሪ ያልሆኑ ወገኖች ላይ ፍርዱ አስገዳጅነት አለው ሊባል አይችልም፡፡ የተከራካሪዎች ተመሳሳይነት የሚለው ከተከራካሪዎች በሕግ ሆነ በውል መብት የተላለፈላቸውን ሦስተኛ ወገኖች የመብታቸው ምንጭ የቀድሞው ክርክር ላይ ተከራካሪ በሆኑት ወገኖች ልክ በመሆኑ በእነዚህ ወገኖች ላይም ጉዳዩ አስቀድሞ በፍርድ እንዳለቀ የሚያስቆጥር ስለመሆኑ በሰበር መዝገብ ቁጥር 182458 እና ሌሎች በርካታ መዝገቦች ላይ ትርጉም የተሰጠበት ነው፡፡
በሕጉ የተመለከተውን መስፈርት ከተመለከትን ወደያዝነው ጉዳይ ስንመለስ አመልካቾች ጉዳዩ አስቀድሞ በፍርድ አልቋል በማለት ለሚያቀርቡት ክርክር የመጀመሪያው ቀደም ሲል በፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት መዝገብ ቁጥር 161609፣ በፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ይግባኝ ሰሚ ችሎት በመዝገብ ቁጥር 125952 እና በሰበር ሰሚ ችሎት በመዝገብ ቁጥር 138823 ላይ የመጨረሻ ውሳኔ ተስጥቶበታል የሚል ነው፡፡ በእነዚህ መዝገቦች ጉዳዩ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ሲጀምር ሥረ-ነገሩ 1ኛ አመልካች ባቀረቡት የክስ መነሻ ከሥር 1ኛ ተከሳሽ እና ሌላ ግለሰብ ጋር ያደረጉት ክርክርን የሚመለከት እንጂ ተጠሪ በመጀመሪያ በሥረ-ነገሩ ተከራካሪ አልነበረም፡፡ አመልካች ወደ ክርክሩ የገባው በፍብ/ሥ/ሥ/ሕ/ቁ. 151 መሠረት አሁን ክርክር ካስነሱ ባጃጆች ላይ የተሰጠው እግድ፤ ንብረቶች የተከሳሾች ሳይሆኑ የ3ኛ ወገን የሆነው የተጠሪ ንብረት ናቸው በማለት በፍብ/ሥ/ሥ/ሕ/ቁ. 153 መሠረት እግዱ እንዲነሳለት ባቀረበው ማመልከቻ መሠረት የተደረገ እግድ ይነሳ አይነሳ ክርክር ነው፤ በክርክሩም የተሰጠው ውሳኔ የተሰጠው እግድ አይነሳም/የእግድ ትዕዛዙ ጸንቶ ሊቀጥል ይገባል የሚል ነው፡፡ በፍብ/ሥ/ሥ/ሕ/ቁ. 151-153 የሚደረጉ ክርክሮች እግድ በሰጠው ሰውና እግዱ እንዲነሳለት በሚጠየቅ 3ኛ ወገን በኩል የሚደረግ ከዋናው ሥረ-ነገር ክርክር የተለየ ንዑስ ክርክር ሲሆን ውጤቱም የተሰጠው የእግድ ትዕዛዝ ሊነሳ የሚችል መሆን አለመሆኑ ላይ ብቻ የተመሰረተ እንጂ በግራቀኙ መካከል እግድ በተሰጠበት ንብረት ላይ የመፋለም ሆነ የባለቤትነት መብት ለመወሰን የሚደረግ ክርክር አይደለም፤ ውሳኔውም ንብረቱ ላይ ማን ባለቤት ነው የሚለውን የመጨረሻ ፍርድ የሚሰጥ አይደለም፡፡ ንብረቱ ላይ ዳኝነት ተጠይቆበት አቤቱታ አቅራቢው ተከሳሽ ሆኖ ክርክር ባልተደረገበት ሁኔታ ንብረቱ የአቤቱታው አቅራቢው መሆን አለመሆኑ ላይ በሥረ-ነገሩ ታይቶ የመጨረሻ ፍርድ ተሰጥቶበታል የሚያስብል ባለመሆኑ ቀደም ሲል የእግድ ይነሳልኝ አቤቱታ ቀርቦ የተደረጉ ክርክሮች ሆነ እግዱ ሊነሳ አይገባም በሚል የተሰጡ ውሳኔዎች በፍብ/ሥ/ሥ/ሕ/ቁ. 5/1/ የተመለከተው ቀደም ሲል በሥረ-ነገሩ ዳኝነት ተጠይቆበት የመጨረሻ ፍርድ የተሰጠበት የሚለውን የሕጉን መስፈርት የማያሟላ በመሆኑ ተጠሪ ያቀረበው የንብረት መብት ይከብርልኝ ክስ አስቀድሞ በፍርድ ያለቀ አይደለም ብለናል፡፡
አመልካቾች ከተጠሪ ጋር ክርክር አድርገን አስቀድሞ ፍርድ ያረፈበት ነው በሚል በሁለተኛ ደረጃ የሚከራከሩት በፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት በመዝገብ ቁጥር 167153 እና በፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ይግባኝ ሰሚ ችሎት በመዝገብ ቁጥር 166908 የተሰጡ ውሳኔዎችን መሠረት ያደረገ ሲሆን ተጠሪ በአፈጻጸም መዝገብ እግድ እንዲነሳና አሁን ክርክር ያስነሱት ባጃጆች ሽያጭ ሆኖ በባንክ በተቀመጠ ገንዘብ ላይ አፈጻጸሙ እንዳይቀጥል ትዕዛዝ እንዲሰጥለት ባቀረበው ጥያቄ መሠረት የተደረገ ክርክር ነው፡፡ በእነዚህ መዝቦች የተሰጠው ውሳኔ በይግባኝ ሰሚ ችሎቱ እንደተጠቀሰው በሰበር መዝገብ ቁጥር 184585 ላይ ውሳኔው የተሻረ በመሆኑ ጉዳዩ አስቀድሞ በፍርድ ያለቀ ነው በሚል ክርክር ሊቀርብበት የሚችል አይደለም፡፡ ስለሆነም ተጠሪ ያቀረበው ክስ አስቀድሞ በፍርድ ያለቀ ባለመሆኑ የሥር ከፍተኛ ፍርድ ቤት በሥረ-ነገሩ አከራክሮ ውሳኔ እንዲሰጥበት የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ይግባኝ ሰሚ ችሎት የሰጠው ውሳኔ መሠረታዊ የሕግ ስህተት የተፈጸመበት ሆኖ አላገኘነውም፡፡
ውሳኔ
1. የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ይግባኝ ሰሚ ችሎት በመዝገብ ቁጥር 202459 ታህሳስ 20 ቀን 2014 ዓ/ም የሰጠው ውሳኔ በሰበር ሥነ-ሥርዓት መመሪያ ቁጥር 17/2015 አንቀጽ 9(1)(ሀ) መሰረት ፀንቷል፡፡
2. በዚህ ችሎት ለወጣ ወጭና ኪሣራ ግራቀኙ የየራሳቸውን ይቻሉ ብለናል፡፡
ትዕዛዝ
የውሳኔው ግልባጭ ለስር ፍርድ ቤቶች ይተላለፍ፡፡
መዝገቡ ተዘግቷል ወደ መዝገብ ቤት ይመለስ፡፡
መ/ዐ የማይነበብ የአምስት ዳኞች ፊርማ አለበት