የኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዴሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ                            የሰ//ቁጥር 221592

 ጠቅላይ ፍርድ ቤት ሰበር ሰሚ ችሎት                                ጥቅምት 06 ቀን 2016 /                                    

                                                         

                               ዳኞች፡- ብርሃኑ አመነው

                                       ረታ ቶሎሳ

                                       እንደሻው አዳነ   

                                       ቀነዓ ቂጣታ

                                       ኑረዲን ከድር

አመልካች፡-የኢትዩ ጫት የእርሻ እርባታ ኢንዱስትሪ ውጤቶች አምራቾች አክሲዩን ማህበር አልቀረቡም

ተጠሪ፡- አቶ ወንደሰን ዘለቀ አልቀረቡም

መዝገቡ የተቀጠረው ለምርመራ ሲሆን በዚሁ አግባብ ተመርምሮ የሚከተለው ፍርድ ተሰጥቷል፡፡

                                    ፍርድ

የሰበር አቤቱታው ሊቀርብ የቻለው አመልካች በቀን 15/06/2014 . ጽፎ ባቀረበው የሰበር አቤቱታ የፌዴራል ጠቅላይ /ቤት ይግባኝ ሰሚ ችሎት በይ... 207794 በቀን 18/04/2014. የፌ/ከፍ//ቤት በመ.. 15601 በቀን 13/07/2013. የሰጠውን ውሳኔ በከፊል አሻሽሎ መወሰኑ መሰረታዊ የህግ አተረጓጎም ሰህተት የተፈጸመበት ነው በማለቱ ሲሆን ተጠሪ በስር /ቤት ከሳሽ ሲሆኑ አመልካች ደግሞ 1 ተከሳሽ ነበር፡፡ ክርክሩ ውክልናን መሰረት ያደረገን የድካም ዋጋ ክፍያን የተመለከተ ነው፡፡

ተጠሪ በስር /ቤት በቀን 11/08/2011 ጽፈው ባቀረቡት አቤቱታ አመልካችን 1 ተከሳሽ እንዲሁም የድሬዳዋ ንግድ ዘርፍ ማህበራት ምክር ቤትን 2 ተከሳሽ አድርገው ከሰዋል፡፡ የአቤቱታቸው ይዘትም፦ በድሬዳዋ ከተማ ቀበሌ 04 በካርታ ቁጥር 2568 የተመዘገበው ባለ 4 ፎቅ ህንጻ የተወረሰበት አግባብ ትክክለኛ ባለመሆኑ ለአመልካችና 2 ተከሳሽ እንዲመለስ የተወሰነውን ውሳኔ እንደነሱ ሆኜ እንዳስፈጽምላቸው ሁለቱም ውክልና ሰጥተውኝ የማስፈጸሚያ ወጭውን በጋራ ሊችሉ ነገር ግን አመልካች የተሻለ አቅም ላይ በመሆኑ አመልካች ወጪውን ሸፍኖ ህንፃው ሲመለስ በሚቀርብ ማስረጃ ላይ በመመርኮዝ 2 ተከሳሽ ወጪውን የሚጋራ ለመሆኑ ተስማምተን፤ ጉዳዩን ለማስፈጸም ወደ አዲስ አበባ ስሄድ በቀን 600.00 ብር አበል እንዲከፈለኝ የሁለቱም የቦርድ አባላት ወስነው በዚሁ አግባብ ህንፃው እንዲመለስ በማድረግ ግዴታዬን ተወጥቼያለሁ፡፡ጉዳዩን ለማስፈፀም ከራሴ ያወጣሁትን ብር 1,410,000.00 እንዲተኩልኝ ስጠይቃቸው ህንፃው የተመለሰበትን ደብዳቤ ሳቀርብ እንደሚከፍሉኝና ለድካሜ ማካካሻ እንዲሆን የህንጻውን ዋጋ ግምት 5% እንደሚከፍሉኝ የአመልካች ፕሬዝዳንት 21/11/2007 ዓም ደብዳቤ የፃፉልኝና ማረጋገጫ የሰጡኝ ቢሆንም በተደጋጋሚ ብጠይቅም ሆነ ማስጠንቀቂያ ብሰጥም ሊከፍሉኝ ፈቃደኛ ባለመሆናቸው  ጉዳዩን ለማስፈጸም ከራሴ ያወጣሁትን ብር 1,410,000.00 (አንድ ሚልየን አራት መቶ አስር ሺህ ብር) መተማመኛ ከተሰጠኝ 25/11/2007. ጀምሮ ከሚታሰብ 9% ወለድ ጋር እንዲሁም ህንጻው 40 ሚሊየን ብር የሚያወጣ በመሆኑ የዚህን 5% ብር 2,000,000.00(ሁለት ሚልየን) እንዲከፍሉኝ ይወስንልኝ በማለት ዳኝነት ጠይቀዋል፡፡

አመልከችና 2 ተከሳሽ ተደርገው የተከሰሱትም መልሳቸውን ያቀረቡ ሲሆን አመልካች በቀን 15/11/2011. ጽፈው ባቀረቡት መልስ፡- በቀን 21/11/2007 . ተሠጠ የተባለው የክፍያ መተማመኛ ስልጣን ባለው አካል የተሰጠ ስላልሆነ የክፍያ ጥያቄው ተገቢነት የለውም፡፡ አመልካች 2 ተከሳሽ ማህበር ውስጥ ፕሬዘዳንት በመሆናቸው ህንጻውን ማስመለስ የስራ ሃላፊነታቸው ነው፡፡ ወደ አዲስ አበባ በሚሄዱበት ጊዜ ብር 600.00 አመልካች ለመክፍል በተሰማመው መሰረት በጠቅላላው ብር  510,802.00 (አምስት መቶ አስር ሺህ ስምንት መቶ ሁለት ብር) ለተጠሪ ተከፍሏል፡፡ ለትራንስፖርት አወጣሁት የሚለው  የብር 160,000.00 (አንድ መቶ ስልሳ ) ወጭም በዚህ ውሰጥ የሚካተት በመሆኑ በድጋሚ የቀረበ ነው፡፡ ከዚህ ውጭ የአመልካች ቦርድ ፕሬዘዳንት ጽፈውልኛል በማለት ያቀረበው ደብዳቤ በስራ አመራር ቦርዱ የማይታወቅ እና ያልጸደቀ በመሆኑ ጥያቄው የህግ መሰረት የለውም፡፡ ህንጻውን የማስመለስ ሂደቱ ደብዳቤ ከመጻጻፍ በቀር ይህን ያህል ወጭ የሚያስወጣ አይደለም፡፡ አመልካች የህግ ባለሙያ ያለው በመሆኑ ተጠሪ የህግ ባለሙያ በማማከር አወጣሁ የሚሉት ወጭ ከእውነታው የራቀ ማስረጃ ያልቀረበበት እንዲሁም የተጋነነ በመሆኑ ክሱ ውድቅ ይደረግልን ያሉ ሲሆን 2 ተከሳሽ ተደርጎ የተከሰሰውም ከአመልካች ጋር ተመሳሳይነት ያለው መልስ አቅርቧል፡፡

ከዚህ በኋላ /ቤቱ የቃል ክርክር በማድረግ ግራ ቀኙን ሲሰማ አቤቱታቸውን አጠናክረው አሰምተዋል፡፡ /ቤቱም ግራ ቀኙን የማጣሪያ ጥያቄዎች በመጠየቅ፤ ለተጠሪ ክፍያ ፈጽመዋል ከተባሉት ባንኮች ማስረጃ በማስቀረብ ግራ ቀኙ ካቀረቧቸው ክርክሮችና ሰነዶች በመነሳት ለጉዳዩ አግባብነት ያላቸውን ጭብጦች በመያዝ መርምሮ በሰጠው ውሳኔም አመልካችና 2 ተከሳሽ ለተጠሪ ህንጻውን ለማስመለስ አስፈላጊውን ሁሉ እንዲያደርግ አስፈላጊም ሲሆን ሶስተኛ ወገን ይዘው በመቅረብ ጉዳዩን እንዲያስፈጽሙ ውክልና የሰጧቸው መሆኑን፤ ተወካይ ለስራ ማስኬጃ ያወጡት ወጭ ካለ ይህንኑ ወጪ ወካይ ሊተካ እንደሚገባ የፍ///. 2221 የሚደነግግ መሆኑን እንዲሁም ተወካይ የስራውን የአፈፃጸም ሁኔታ እና የሂሳብ ሰነዶች በአግባቡ የመያዝ ግዴታ እንዳለበት የፍትሐ ብሄር ህግ ቁጥር 2208 2210 2211 እና 2213 ንባብ የሚያመለክቱ ቢሆንም ተጠሪ አወጣሁዋቸው ያሏቸውን ወጪዎች በተገቢው ማስረጃ አስደግፈው ያላቀረቡ መሆኑን እንዲሁም ተጠሪ 2 ተከሳሽ ድርጅት ፕሬዘዳንት በመሆኑ 2 ድርጅትን የንብረት ጥቅም የማስጠበቅ እና የማስመለስ ከህግ የመነጨ ግዴታ ያለባቸው ከመሆኑ ባሻገር ንብረቱን የማስመለስ ስራውን የሰራው በሙያ ስራው ባለመሆኑ በፍ///. 2220(2) መሰረት የድካም ዋጋ የመጠየቅ መብት የላቸውም በማለት የተጠሪን ክስ ውድቅ በማድረግ ወስኗል፡፡

 በዚህ ውሳኔ ቅሬታ ያደረባቸው ተጠሪ ይግባኛቸውን ለፌዴራል ጠቅላይ /ቤት ይግባኝ ሰሚ ችሎት ያቀረቡ ሲሆን /ቤቱም የስር /ቤት ተጠሪ ያወጧቸው ወጭዎች በማስረጃ አልተረጋገጡም በማለት ክሱን ውድቅ ያደረገበትን አግባብ እና በማስረጃ ባይረጋገጥም በርትዕ ሊወሰን ይገባው የነበረ መሆን አለመሆኑን ለማጣራት ይግባኙ ያስቀርባል ካለ በኋላ የግራ ቀኙን የጽሁፍ ክርክር ከስር ፍርድ ቤት የግራ ቀኙ ክርክርና አግባብነት ካለው ህግ ጋር በማገናዘብ መርምሮ በሰጠው ውሳኔ አመልካች በተጠሪ ድካም የበለጸገ መሆኑ በክርክሩ የተረጋገጠ በመሆኑ በፍ/// 2102 መሰረት የስር /ቤት የድካም ዋጋውን በርትዕ መወሰን ሲገባው ክሱን ውድቅ ማድረጉ ተቀባይነት የሌለው ነው በማለት በመነሻነት አስቅምጦ በውክልና የተሰጡ ተግባራትን ከመፈጸም ጋር በተያያዘ የሚጠየቅ የድካም ዋጋ ከካሳ አይነቶች የሚመደብ መሆኑን፤ የሚካሰውም ለጉዳቱ ተመዛዛኝ የሆነ ካሳ እንዲከፈለው በማድረግ ስለመሆኑ የፍ/// 2090(1) የሚደነግግ መሆኑን ጠቅሶ ሆኖም ተመዛዛኝ የሆነው ካሳ ምን ያህል ነው የሚለውን በትክክል ለመወሰን ካልተቻለ ዳኛው በርትዕ ሊወስን እንደሚችል በፍ///. 2102(1) መመልከቱን በመጥቀስ አመልካች ለተጠሪ በርትዕ ብር 500,000.00 ሊከፍል ይገባል በማለት የስር /ቤቱን ውሳኔ በከፊል አሻሽሎ ወስኗል፡፡

በዚህ ውሳኔ ቅሬታ ያደረበት አመልካች በቀን 15/06/2014 . የተጻፈ የሰበር አቤቱታ ያቀረቡ ሲሆን የአቤቱታው ይዘትም በአጭሩ፦ አመልካች ተጠሪ ፕሬዘዳንት ከሆነበት ድርጅት ጋር በጋራ የህንጻው ባለቤት በመሆናችን ለብቻችን ከቅን ልቦና ውጭ በሆነ መንገድ ያገኘነው ብልጽግና የሌለ በመሆኑና ይግባኝ ሰሚ /ቤቱ ለውሳኔው መሰረት ያደረገው የፍ/// 2162 እና 2163 አነጋገርም ተገቢ ባልሆነ መንገድ የተገኘ ብልጽግናን የሚያመለክት በመሆኑ፤ ከዚህ ጋር በተገናኘም የፌ///ቤት በሰበር መዝገብ ቁጥር 59698(ቅጽ 11) 43381(ቅጽ 10) 90529(ቅጽ 18) እና 93104  የፍ/// 2162 2164 እና 2019 ላይ አስገዳጅነት ያለው ትርጉም የሰጠበት በመሆኑ፤ የድካም ዋጋ በርትዕ ሊከፈል የሚገባው ስራ አድርጎ ለያዘው እንደ ደላላ ወይም ጉዳይ አስፈጻሚ አይነት ሰው እንጂ የንብረቱ 50% ባለቤት የሆነ ሰው ለሚሰራው ስራ ባለመሆኑ ተጠሪ የራሱን ድርጅት ለማስመለስ በህግ የተጣለበትን ሃላፊነት ለመወጣት የሰራውን ተግባር ይግባኝ ሰሚ /ቤቱ የፍ/// 2220 እና 2162 በመተርጎም ውሳኔ የሰጠበት መንገድ ተገቢነት የሌለው ነው፡፡

 በይግባኝ ሰሚ /ቤቱ በርትዕ ሊወሰን ይገባል ካለ የርትዕ መጠኑን በተመለከተ መለኪያዎችን መሰረት በማድረግ አከራክሮ እንዲወስን ለስር /ቤት መመለስ ሲገባው ይህም በሰ//. 10825 ቅጽ 19 ትርጉም የተሰጠበት ሆኖ እያለ በራሱ መወሰኑ በአዋጅ ቁጥር 1234/2013 አንቀጽ 54 የተደነገገውን የይግባኝ መብታችንን ያጣበበ እና የካሳ መጠንን በርትዕ ለመወሰን መሟላት ያለባቸውን መለኪያዎችን ግምት ውስጥ ባላስገባ ሁኔታ እጅግ የተጋነነ ብር 500,000.00 (አምስት መቶ ሺህ) እንድንከፍል መወሰኑ መሰረታዊ የህግ አተረጓጎም ስህተት የተፈጸመበት በመሆኑ የፌ///ቤት ድሬዳዋ ምድብ ችሎት በመ.. 15601 በቀን 13/03/2013 የሠጠው ውሳኔ ጸንቶ የፌ///ቤት በይ...207794 በቀን 18/04/2014 . የሰጠው ውሳኔ እንዲሻርልን የሚል ነው፡፡

ከዚያም ጉዳዩ የቀረበለት የሰበር አጣሪ ተጠሪ 2 ተከሳሽ የንግድ ምክር ቤት አባልና ፕሬዘዳንት በመሆን የጋራቸው የሆነውን ንብረት (ህንጻ) ለማስመለስ በተሰጣቸው ውክልና ላከናወኑት ሥራ በተለያየ ጊዜ ክፍያ የተፈጸመላቸው ስለመሆኑ በተገለጸበት የድካም ዋጋ በርትዕ ብር 500,000.00 (አምስት መቶ ሺህ) እንዲከፈል የተወሰነበትን አግባብነት መጣራት ያለበት መሆኑ ስለታመነበት ጉዳዩ ለሰበር ችሎት ይቅረብ ተጠሪዎችም መጥሪያ ተልኮላቸው መልሳቸውን እንዲቀባበሉ በሰጠው ትእዛዝ መሰረት ተጠሪም መልሳቸውን አመልካችም የመልስ መልስ አቅርበዋል፡፡

ተጠሪ በቀን 8/9/2014. ጽፈው ባቀረቡት መልስ፦ ከዚህ ቀደም ተጠሪ በዚሁ ጉዳይ በሰ... 220559 የሰበር ቅሬታ አቤቱታ አቀርቤ የተፈጸመ መሰረታዊ የህግ አተረጓጉም ስህተት የለም ከተባለ በኋላ አሁን በአመልካች የቀረበው ተመሳሳይ አቤቱታ ያስቀርባል መባሉ የዜጎችን በእኩልነት ፍትህ የማግኘት መብት የሚጥስና በሰ... 52546 ላይ የተሰጠውን ትርጉም የሚጥስ በመሆኑ አቤቱታው ተቀባይነት ሊኖረው አይገባም የሚል መቃወሚያ በማስቀደም አመልካች ያቀረበው ማመልከቻ የፍሬ ነገር ክርክር እንጂ የህግ ስህተትን ያመላከተ ባለመሆኑ ተቀባይነት የለውም፡፡ በርትዕ መወሰንን የትኛውም /ቤት ሊወስነው የሚችል በመሆኑ አመልካች የይግባኝ መብቴን አጣቦብኛል የሚለውን ማስረዳት ያልቻለ በመሆኑ ተቀባይነት የለውም፡፡ ተጠሪ በስራ ላይ እያለሁ 2 አመታት ስራ ከለቀቅሁ በኋላ 3 አመት በአጠቃላይ 5 አመታት ከድሬዳዋ አዲስ አበባ በመመላለስ በግል የምሰራውን የኮንስትራክሽን ስራ በማቋረጥ ሙሉ ጊዜየን ለዚሁ ስራ በማዋል ጊዜና ጉልበቴን አውጥቼ ህንጻውን ያስመለስኩ በመሆኑ የተወሰነው ብር 500,000 (አምስት መቶ ሺህ) ተጋኗል ሊባል አይችልም፡፡

 በስር /ቤት የቦርዱ ሰብሳቢና ስራ አስኪያጅ የነበሩት ግለሰብ  ለተጠሪ የድካም ዋጋ  በአጠቃላይ ብር 3,410,000.00 (ሶስት ሚልየን አራት መቶ አስር ሺህ ብር ) እንዲከፈለኝ በቁጥር አሰ///01/6354 በቀን 21/11/2007 . የተጻፈ መተማመኛ ሰነድ በማስረጃነት በስር /ቤቶች ያቀረብኩ ቢሆንም አመልካችም ሆነ 2 ተከሳሽ ተቃራኒ ማስረጃ ባላቀረቡበት ሁኔታ /ቤተ በራሱ ስልጣን ተችቶ ውድቅ ማድረጉ ተገቢነት የለውም፡፡ በቀን 21/11/2007. ከተሰጠኝ መተማመኛ በፊትና በኋላ በውክልና ለምሰራው ስራ በተለያዩ ባንኮች ክፍያ እንደተፈጸመልኝ የሚያስረዳው ማስረጃ በውከልና ከምሰራው የህንጻ ማስመለስ ስራ ጋር የተገናኘ አለመሆኑን በስር /ቤት አስረድቻለው፡፡ የተገናኘ ቢሆን ኖሮ ከላይ በጠቀስኩት ቀን የተሰጠኝ መተማመኛ ላይ እነዚህ ክፍያዎች ተቀናሽ እንደሚደረጉ ይገለጽ ነበረ፡፡ ይህም በስር /ቤት በተለያየ ጊዜ ክፍያ ተፈጽሞላቸዋል በሚል የተሰጠው ውሳኔ መሰረታዊ የህግ አተረጓጎም ስህተት የተፈጸመበት እንደሆነ የሚያረጋግጥ በመሆኑ የስር /ቤት ውሳኔ ተሻሽሎ እንዲወሰንልኝ ወይም የፌ///ቤት  በይ.. 207794 በቀን 18/04/2014 . የሰጠው ውሳኔ እንዲጸናልኝ ዳኝነት እጠይቃለው የሚል ይዘት ያለው ነው፡፡

አመልካችም በቀን 17/09/2014 . የተጻፈ የመልስ መልስ ያቀረበ ሲሆን ይዘቱም በአጭሩ፦ የሰበር አቤቱታ ያስቀርባል ሊባል የሚችልበት ምክንያት እንደየአቤቱታው የሚለያይ በመሆኑ የተጠሪ የሰበር አቤቱታ አያስቀርብም በማባሉ የተፈጸመ የህግ ጥሰት የለም፡፡ በስር /ቤት ተጠሪ ውልን መሰረት ያደረገ ክስ አቅርበው እያለ /ቤቶች የፍ///. 2162 እና 2163 በመተርጎም አላግባብ መበልጸግ በሚል ውሳኔ መስጠታቸው ባልቀረበ ዳኝነት ላይ የተሰጠ ውሳኔ ነው የሚልና በአቤቱታቸው ያቀረቡትን ክርክር የሚያጠናክር ነው፡፡                      

 ከዚህ በላይ አጠር ባለመልኩ የተገለጸዉ የግራ ቀኙን ክርክርና በስር ፍርድ ቤቶች የተሰጡ ዉሳኔዎች ይዘት የሚመለከት ሲሆን እኛም የሰበር አጣሪ ችሎት የያዘዉን ማስቀረቢያ ጭብጥ መሰረት በማድረግ  በውሳኔው ላይ በዚህ ችሎት ደረጃ ሊታረም የሚችል የተፈጸመ መሰረታዊ የሕግ ስህተት መኖር አለመኖሩን አግባብነት ካለዉ ሕግ ጋር በማገናዘብ እንደሚከተለዉ መርምረናል፡፡በመሰረቱ ግዴታ በተጠቃለለ መልኩ ከህግ፤ከውል፤ከማህበራዊ ህይወት፤ከሀይማኖታዊ እሴቶች እና ከመሳሳሉት የሚመነጭ ቢሆንም ከበስተጀርባው የህግ ዋስትና ያለው ፍትሐ ብሄራዊ ግዴታ የሚመነጨው ከህግና ከውል ነው፡፡በዚህ አግባብም ግዴታ አንድ ሰው ከሌላው ሰው ጋር በሚኖረው ግንኙነት አንድን ነገር ለማድረግ ወይም ከማድረግ ለመቆጠብ በህግ ወይም በውል የሚገደድበትን ስርዓት የሚወክል ሆኖ እናገኘዋለን፡፡የግዴታው መነሻ ውል ከሆነ ባለዕዳው ውሉን እንዲፈፅም የሚገደድ ሲሆን በህግ የተቀመጠ የተለየ አይነት ግዴታ ከሆነም ባለዕዳው በህጉ መሰረት ማድረግ ያለበትን ተግባር እንዲያደርግ ይገደዳል፡፡

አሁን በያዝነው ጉዳይ ተጠሪ የአመልካችና የስር 2 ተከሳሽ የጋራ ወኪል በመሆን ህንፃውን እንዲያስመልሱ ለዚህ እንዲረዳም መንግስታዊ ከሆኑና ካልሆኑ ተቋማት ጋር እንዲደራደሩና 3 ወገን ይዘው እንዲከራከሩ አስፈላጊ የሆኑ ሰነዶች ላይ ፈርመው እንዲሰጡ በአጠቃላይ ለሂደቱ አስፈላጊ የሆኑ ተግባራትን እንዲፈፅሙ የጋራ ወኪል ሆነው መሾማቸውን፤ይህንን ስራ ሲሰሩም የውሎ አበል በቀን ብር 600.00 እና የትራንስፖርት ወጪ ለጊዜው በአመልካች እንዲከፈላቸው ሆኖ ህንፃው በሚመለስበት ጊዜ በሚቀርበው ማስረጃ መሰረት የስር 2 ተከሳሽ ድርሻውን ለመጋራት የተስማማ መሆኑን ማስረጃን የመስማት፤የመመርመርና የመመዘን ስልጣን ያላቸው የስር ፍርድ ቤቶች ለጉዳዩ አግባብነት ያለውን ቃለ ጉባዔ በመመልከት ማረጋጣቸውን በውሳኔያቸው አመልክተዋል፡፡ይህም ውክልናን መሰረት ባደረገው ግንኙነት አመልካች (የስር 2 ተከሳሽን ጨምሮ) ለተጠሪ ለመክፈል የተስማማው የውሎ አበል በቀን ብር 600.00 ሂሳብና  የትራንስፖርት ወጪ በሚቀርበው ማስረጃ መሰረት መሆኑን ከአጠቃላይ የግራ ቀኙ ክርክር የምንረዳው ነው፡፡

ይህንን በተመለከተም አመልካች ለተጠሪ በድምሩ ብር 409,267.00 (አራት መቶ ዘጠኝ ሺህ ሁለት መቶ ስልሳ ሰባት ብር) ለትራንስፖርት ወጪና ለውሎ አበል መክፈላቸው ማስረጃን የመስማት፤የመመርመርና የመመዘን ስልጣን ባላቸው የስር ፍርድ ቤቶች በዋነኝነትም የፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ተረጋግጦ በይግባኝ ሰሚው ፍርድ ቤት ያልተለወጠ ፀንቶ ያለ ነጥብ ነው፡፡ይህም አመልካች በውል ግዴታ የገባበትን ክፍያ በአግባቡ መፈፀሙን ከዚህ በተጨማሪም በፍ///.2221 የተመለከተውን የህግ ግዴታውን መወጣቱ በስር ፍርድ ቤቶች መረጋገጡን ያሳያል፡፡

አመልካች በውል ግዴታ ከገባበት ክፍያ በተጨማሪ ሌሎች ክፍያዎችን ከህግ በመነጨ ግዴታ ለወኪሉ ተጠሪ ሊከፍለው የሚገደደው የስራውን ተግባር በውክልና የፈፀመው በሞያ ስራው ውስጥ በተመለከተ በግል ስራው ሆኖ እንደ ልማዳዊ ህግ የድካም ዋጋ ማግኘት የሚገባው መሆኑን ተጠሪ ሲያስረዳ መሆኑን የፍ///.2220(1) የሚያመለክት ቢሆንም ተጠሪ በዚህ አግባብ ውክልና ተቀብሎ ጉዳዮችን በማስፈፀም ሙያዊ ክፍያዎችን የሚቀበሉ ባለሙያ መሆናቸውን እንዲሁም በዚህ መልኩ ለተሰራ ስራ በልማድ ክፍያ የሚፈፀም መሆኑን ማስረዳታቸውን የስር ፍርድ ቤት መዝገብ አያሳይም፡፡ከዚህ ይልቅ ተጠሪ በኮንስትራክሽን ዘርፍ የተሰማሩ የራሳቸውን ስራ የሚሰሩ ባለሙያ መሆናቸው በግራ ቀኙ ክርክር ያልቀረበበት ነጥብ መሆኑ አመልካች ለተጠሪ በፍ///.2220(1) መሰረት የድካም ዋጋ የመክፈል ግዴታ ያልተጣለበት መሆኑን ያሳያል፡፡ይህ ከሆነ ደግሞ ይግባኝ ሰሚው ፍርድ ተጠሪ የድካም ዋጋ እንዲከፈላቸው ያቀረቡትን የዳኝነት ጥያቄ ውድቅ በማድረግ የስር ፍርድ ቤትን ውሳኔ ሊያፀና ሲገባ አመልካች የውል ግዴታ ገብቶ አልፈፅምም ያለው ግዴታ ሳይኖር በውል አለመፈፀም ምክንያት ለደረሰ ጉዳት ኪሳራ ሊከፍል ይገባል በማለት ለጉዳዩ አግባብነት ያላቸው ድንጋጌዎች ከላይ የተመለከቱት ግልፅ ድንጋጌዎች ሆነው እያለ አግባብነት የሌላቸውን ድንጋጌዎች በመጥቀስ አመልካች ለተጠሪ በርትዕ ብር 500,000.00 ሊከፍል ይገባል በማለት መወሰኑ መሰረታዊ የህግ ስህተት የተፈፀመበት ሆኖ ስላገኘነው ተከታዩን ወስነናል፡፡

                                           ውሳኔ

  1.  የፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ይግባኝ ሰሚ ችሎት በመ/.207794 በቀን 18/04/2014 . በዋለው ችሎት አመልካች ለተጠሪ ብር 500,000.00 ሊከፍል ይገባል በማለት የሰጠው የውሳኔ ክፍል በፍ////.348(1) መሰረት ተሸሯል፡፡አመልካች ለተጠሪ የድካም ዋጋ የመክፈል የህግም ሆነ የውል ግዴታ የለበትም ብለናል፡፡
  2. የፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ድሬዳዋ ምድብ ችሎት በመ/.15601 በቀን 13/07/2013 . በዋለው ችሎት የሰጠው ፍርድ ከውጤት አንፃር ጸንቷል፡፡
  3. ግራ ቀኙ በሰበር ክርክሩ ምክንያት ያወጡትን ወጪና ኪሳራ ይቻቻሉ፡፡

ጉዳዩ ውሳኔ ስላገኘ መዝገቡ ተዘግቷል፡፡ይመለስ፡፡

የማይነበብ የአምስት ዳኞች ፊርማ አለበት፡፡

/