ፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት
FEDERAL SUPREME COURT
የሰበር መ/ቁ 223852
ጥቅምት 5 ቀን 2015 ዓ.ም
ዳኞች፡ ብርሃኑ አመነው
ረታ ቶሎሳ
እንዳሻዉ አዳነ
ቀነዓ ቂጣታ
ኑረዲን ከድር
አመልካች፡ አቶ ሞኤራ አዱኛ
ተጠሪዎች፡ 1ኛ/ አቶ ተሰማ አየለ
2ኛ/ ወ/ሮ ሊና ሰኢድ
3ኛ/ አቶ ወንድወሰን መንግስቱ
4ኛ/አቶ ባሻ በቀለ
5ኛ/ ፎሻን ሪል እስቴት አ.ማ
መዝገቡ ተመርምሮ የሚከተለው ፍርድ ተሰጥቷል፡፡
ፍርድ
መዝገቡ ለዚህ ችሎት የቀረበው የፌዴራል ከፍተኛ ፍ/ቤት በመ/ቁ 199251 በቀን 13/09/2013 ዓ.ም የሰጠውን ውሳኔ የፌዴራል ጠቅላይ ፍ/ቤት ይግባኝ ሰሚ ችሎት በመ/ቁ 208910 በቀን 30/06/2014 ዓ.ም አሻሽሎ በመወሰኑ ዉሳኔዉ መሰረታዊ የህግ ስህተት ተፈጽሞበታል በሚል አመልካች ባቀረበው አቤቱታ መነሻ ነው፡፡
የጉዳዩ አመጣጥ በአጭሩ ሲታይ በስር ፍ/ቤት ከሳሽ አመልካች ሲሆን ተጠሪዎች ተከሳሽ በመሆን ተከራክረዋል፡፡ አመልካች በቀን 08/03/2010 ዓ.ም ባቀረቡት ክስ 1ኛ ተጠሪ በራሱና በወኪል አድራጊ ባለቤቱ 2ኛ ተጠሪ ስም ህዳር 13 ቀን 2008 ዓ.ም በሰነዶች ማረጋገጫና ምዝገባ ጽ/ቤት የአመልካች ህጋዊ ተወካይ ከሆነው ከ4ኛ ተጠሪ ጋር በፈፀሙት የመኖሪያ ቤት ሽያጭ ውል ስምምነት መሰረት በቦሌ ክፍለ ከተማ ወረዳ 03 የቤት ቁጥር 2389/ለ የካርታ ቁጥር ቦሌ9/42/3/9/17764/20400/23602/02 የብሎክ ቁጥር 26 ፓርሴል ቁጥር 12 የቦታ ስፋት 500 ካ.ሜ የቦታው አገልግሎት ሚክስድ የሆነውን ቤት በብር12‚500‚000 (አስራ ሁለት ሚሊዮን አምስት መቶ ሺህ) ሸጠውልኝ ሙሉ ገንዘቡን ተቀብለው ቤቱንና የቤቱን ዋና ካርታ አስረክበውኛል፡፡ስመ ሀብቱን በስሜ ለማዞር የቀድሞውን ካርታ በአዲስ ካርታ ለመተካት 4ኛ ተጠሪ እንዲስፈጽምልኝ ዋናውን ካርታ ሰጥቼዋለሁ፡፡ተጠሪዎች ከቅን ልቦና ውጪ በህገወጥ መንገድ የንብረት መብቴን ለመጉዳት በማሰብ በይዞታዬ ስር የሚገኘውን ቤት ከ3ኛ ተጠሪ ጋር መጋቢት 23 ቀን 2007 ዓ.ም በብር 2‚000‚000 (ሁለት ሚሊዮን) እንደተሸጠ አድርገው ውል መዋዋላቸው 4ኛ ተጠሪ የአመልካች ህጋዊ ተወካይ ሆነው ለአመልካች ገዝተውት የነበረውን ቤት ከ3ኛ ተጠሪ በተሰጠው ውክልና ለ5ኛ ተጠሪ በብር 7‚500‚000 (ሰባት ሚሊዮን አምስት መቶ ሺህ) ሸጠዋል፡፡በ23/07/2007 ዓ.ም እና በ18/08/2009 ዓ.ም የተደረጉ ውሎች ፈራሽ ናቸው ተብሎ እንዲወሰን ይህ የሚታለፍ ከሆነ አመልካች በግዢ ውሉ መነሻ የከፈልኩትን ብር 12‚500‚000 (አስራ ሁለት ሚሊዮን አምስት መቶ ሺህ) እና ከጊዜ ሂደት ጋር ተያይዞ በሚመጣ የገበያ ዋጋ ለውጥ ምክንያት ተመሳሳይ ቤት ለመግዛት የሚስፈልገውን ተጨማሪ ወጪ ብር 5‚000‚000 (አምስት ሚሊዮን) በድምሩ 17‚500‚000 (አስራ ሰባት ሚሊዮን አምስት መቶ ሺህ) ተጠሪዎች በአንድነትና በነጠላ ክርክሩ ከሚያስከትለው ወጪና ኪሰራ ጋር እንዲከፍሉ ይወሰንልኝ በማለት ዳኝነት ጠይቀዋል፡፡
1ኛ ተጠሪ በቀን 25/12/2010 ዓ.ም ባቀረቡት መልስ ቤቱ አስቀድሞ በ23/07/2007 ዓ.ም በአዋዋይ ፊት በተደረገ ውል የተሸጠው ለ3ኛ ተጠሪ መሆኑን፤ አመልካች በተወካያቸው አማካኝነት በ18/08/2009 ዓ.ም በአዋዋይ ፊት በተደረገ ውል ቤቱን የገዙት ቤቱ አስቀድሞ ለ3ኛ ተከሳሽ የተሸጠ እና ውሉም ከቤቱ ማህደር ጋር የተያያዘ መሆኑን እያወቁ መሆኑን፤ የአመልካች ተወካይ ነበሩት 4ኛ ተጠሪ ይህንኑ ቤት የ3ኛ ተጠሪ ተወካይ በመሆኑ ለ5ኛ ተጠሪ በሽያጭ ያስተላለፉ መሆኑን፤ያስተላለፉትም ወደ 3ኛ ተጠሪ ስም ሳይዞር በ1ኛ ተጠሪ ስም እያለመሆኑን ፤በአመልካችና በ4ኛ ተጠሪ መካከል አሁንም የጠበቀ ግንኙነት መኖሩን፣አመልካች ቤቱን ለ5ኛ ተጠሪ ያስተላለፉ መሆኑን፣ በዚህም ምክንያት ሻጮች ዋቢ ሊሆኑ የሚችሉበት አግባብ አለመኖሩን፣ በ23/07/2007 ዓ.ም እና በ18/08/2009 ዓ.ም የተደረጉ ውሎች እንዲፈርሱ ሊወሰን የሚችልበት የህግ አግባብ አለመኖሩን፣1ኛ ተጠሪ ብር 5,000,000 (አምስት ሚሊዮን) ካሳ እንዲሁም ወጪና ኪሳራ የሚከፍሉበት አግባብ ስለሌለ ክሱ ውድቅ እንዲደረግ በማለት ተከራክረዋል፡፡
2ኛ ተጠሪ በጽሁፍ መልስ አላቀረቡም፡፡3ኛ ተጠሪ በቀን 04/10/2010 ዓ.ም ባቀረቡት መልስ አመልካች ቤቱን ገዝቸዋለሁ የሚሉት ከህዳር 13 ቀን 2008 ዓ.ም ከስምንት ወር በፊት 3ኛ ተጠሪ መጋቢት 23 ቀን 2007 ዓ.ም በሰነዶች ማረጋገጫና ምዝገባ ጽ/ቤት በመቅረብ ከ1ኛ እና 2ኛ ተጠሪዎች ጋር ሽያጭ ስምምነት በመፈፀም የገዛሁ መሆኑን፣ አመልካች ቤቱን በኃይል በመግባት የያዙት መሆኑን፣ በ3ኛ ተጠሪ ስም መጋቢት 20 ቀን 2009 ዓ.ም ካርታ ተሰርቶ ተሰጥቶኛል፣4ኛ ተጠሪ ቤቱን በአመልካች ስም ገዝቶ ከ3ኛ ተጠሪ በተሰጠው ውክልና መሰረት ለ5ኛ ተጠሪ የሸጠው መሆኑን፣3ኛ ተጠሪ የሽያጩን ገንዘብ ብር 7‚500‚000 (ሰባት ሚሊዮን አምስት መቶ ሺህ) ከ4ኛ ተጠሪ አለመቀበሉን፣ አመልካች 3ኛ ተጠሪ ከ1ኛ እና ከ2ኛ ተጠሪዎች ጋር ያደረግነው የቤት ሽያጭ ውል እንዲሁም 4ኛ ተጠሪ ከ5ኛ ተጠሪ ጋር ያደረጉት የቤት ሽያጭ ውል እንዲፈርስ በማስደረግ የሸጡትን ቤት በድጋሚ የቤቱ ባለቤት ለመሆን ወይም ለ5ኛ ተጠሪ በብር 7‚500‚000 (ሰባት ሚሊዮን አምስት መቶ ሺህ) ሸጠው የተቀበሉትን ገንዘብ ወይም ከ1ኛ እና 2ኛ ተጠሪዎች ቤቱን ሲገዙ የከፈሉትን ብር 12‚500‚000 (አስራ ሁለት ሚሊዮን አምስት መቶ ሺህ) ለመቀበል በማሰብ የተቀነባበረ ክስ በመሆኑ ክሱ ውድቅ ይደረግልኝ በማለት ተከራክረዋል፡፡
4ኛ ተጠሪ በቀን 04/10/2010 ዓ.ም ባቀረቡት መልስ አመልካች ከ1ኛ እና 2ኛ ተጠሪዎች ጋር ህዳር 13 ቀን 2008 ዓ.ም ቤቱን ለመግዛት ስምምነት ካደረጉ በኋላ በ10/02/2010 ዓ.ም ከአመልካች በተሰጠኝ ውክልና መሰረት ቤቱን ገዝቼላቸዋለሁ፡፡አመልካችም በውሉ መሰረት ቤቱንና ቤቱን የሚመለከት ሰነዶችን ጭምር ሰነዶችና ማረጋገጫ ጽ/ቤት ቀርበው የተረከቡ በመሆኑ ግዴታዬን የተወጣሁ ስለሆነ የምከሰስበት የህግ አግባብ የለም፡፡ አመልካች ያቀረበብኝ ክስ ተቀባይነት የሌለውና ሀሰተኛ ክስ ነው፡፡ አመልካች እንደሚሉት ያስረከብኳቸውን ካርታ ነባሩን ወደ አዲስ አስቀይራለሁ ብዬ አልወሰድኩም፤3ኛ ተጠሪ ከ1ኛ ተጠሪ ጋር ባደረጉት ውል በግዢ ያገኙትን ካርታ በድጋሚ የምሰጥበት ምክንያት የለም፡፡ ከ3ኛ ተጠሪ ያገኘውን ውክልና ተጠቅሞ ካርታውን በ20/07/2009 ዓ.ም ወደ 3ኛ ተጠሪ ስም እንዲዞር አድርጓል የተባለው ሀሰት ነው፡፡3ኛ ተጠሪ ውክልና የሰጠኝ በ17/08/2009 ዓ.ም ሲሆን ካርታው ተሰርቶ ወደ 3ኛ ተጠሪ ስም የዞረው በ20/07/2009 ዓ.ም ውክልና ለኔ ከመስጠቱ አንድ ወር ቀደም ብሎ ነው፡፡ ከ3ኛ ተጠሪ በተሰጠኝ ውክልና መሰረት ቤቱን ለ5ኛ ተጠሪ በቀን 18/08/2009 ዓ.ም ሸጫለሁኝ፡፡ይህንን ማድረጌ በተሰጠኝ ውክልና ስልጣን መሰረት በመሆኑ የሚያስጠይቀኝ ባለመሆኑ ክሱ ውድቅ እንዲሆን በማለት ተከራክረዋል፡፡
5ኛ ተጠሪ በቀን 09/04/2010 ዓ.ም ባቀረበዉ መልስ አመልካች ከ1ኛ እና 2ኛ ተጠሪዎች ጋር በ13/03/2008 ዓ.ም ያደረጉት የሽያጭ ውል መሬት በአስተዳደር አካል ያልተመዘገበ በመሆኑ 3ኛ ወገን ላይ ውጤት የለውም፡፡5ኛ ተጠሪ ቤቱን የገዛሁት ህጋዊ ይዞታ ማረጋገጫ ካለው ከ3ኛ ተጠሪ ሲሆን ካርታ በስሜ አሰርቼ ወስጃለሁ፡፡አመልካች ከ1ኛ እና 2ኛ ተጠሪዎች ጋር ያደረጉት ውል በ5ኛ ተጠሪ ላይ መቃወሚ ሊሆን አይችልም፡፡1ኛ እና 2ኛ ተጠሪዎች ከ3ኛ ተጠሪ ጋር በ23/07/2007 ዓ.ም ያደረጉት ውል እንዲሁም 3ኛ እና 5ኛ ተጠሪዎች በ18/08/2009 ዓ.ም ያደረጉት ውል ይፍረስልኝ በማለት አመልካች ለመጠየቅ በቂና አሳማኝ ምክንያት የላቸውም፤የቅን ልቡና ባለመብት የሆንኩበትን ውል እንዲፈርስ መጠየቃቸው ተገቢነት የለውም፡፡አመልካች በውሉ መነሻ ቤቱን ተረክቤአለሁ ቢሉም በጉልበት ገብተው የያዙት እንጂ በውሉ መነሻ የተረከቡት አለመሆኑን፣አመልካች ደረሰብኝ ለሚሉት ጉዳት መጠየቅ የሚችሉት 1ኛ እና 2ኛ ተጠሪዎችን እንጂ እኔን አይደለም በማለት የተከራከሩ ሲሆን የተከሳሽ ከሳሽት ክስ በአመልካች ላይ ያቀረበ ሲሆን አጭር ይዘቱም በጉልበት የያዘዉን ቤት እንዲያስረክብ እንዲሁም ቤቱን በጉልበት ከያዘበት ከ08/12/2009 ዓ.ም ጀምሮ እስከሚያስረክብ ድረስ በወር ብር 20‚000 (ሃያ ሺህ) እየታሰበ ኪራዩን እንዲከፍል በማለት ጠይቀዋል፡፡
አመልካች የከሳሽ ተከሳሽነት ክስ ላይ በቀን 14/05/2010 ዓ.ም ባቀረቡት መልስ ቤቱ በ3ኛ ተጠሪ እጅ ገብቶ አያውቅም፤የተከሳሽ ከሳሽም ዘበኛ በማቆም ቤቱን ሲገለገሉ እንደነበረ ያቀረቡት ክስ ከእውነት የራቀ ነው፡፡በህገወጥ መንገድ የያዝኩት ሳይሆን በቀን 13/03/2008 ዓ.ም በተደረገ የሽያጭ ውል የያዝኩት ነው፡፡ቤቱ በወር ብር 20‚000 (ሃያ ሺህ) ይከራያል ተብሎ የቀረበው ዳኝነት ያልተከፈለበት በመሆኑና ማስረጃ ያልቀረበበት በመሆኑ ክሱ ውድቅ ሆኖ በነፃ ልሰናበት በማለት ተከራክረዋል፡፡
የፌዴራል ከፍተኛ ፍ/ቤት ግራ ቀኙን አከራክሮና መርምሮ ለክርክሩ መነሻ የሆኑት ሶስቱም ውሎች የተደረጉት በውልና ማስረጃ ጽ/ቤት በመሆኑ ተደረጉ የሚባለው በፍ/ብ/ሕ/ቁ 2015(ሀ) መሰረት በተመዘገበበት ቀን ወይም በፀደቀበት ቀን በመሆኑ ከዚህ አንፃር 3ኛ ተጠሪ ከ1ኛ እና 2ኛ ተጠሪዎች ጋር ባደረጉት የሽያጭ ውል ከአመልካች ቀድመው የገዙት በመሆኑ፣አመልካች ቤቱን የገዙት 3ኛ ተጠሪ ከገዙት በኋላ በመሆኑ የአመልካች የግዢ ውል በቤቱ ማህደር ውስጥ ባለመያያዙ እና ባለመመዝገቡ፣ የ3ኛ ተጠሪ የሽያጭ ውል ከመዝገቡ ጋር የተያያዘ በመሆኑ፣ 4ኛ ተጠሪ ካርታውን አስለውጠዋለሁ በማለት ከአመልካች ስለመቀበላቸው በማስረጃ ባለመረጋገጡ፣5ኛ ተጠሪ እዳና እገዳ የሌለበት ቤት መሆኑን በማረጋገጥ ከ3ኛ ተጠሪ በቅን ልቦና ገዢ በመሆናቸው እና በፍ/ብ/ህ/ቁ 1195(1) መሰረት የቤቱ ትክክለኛ ባለሀበት ሆኖ የሚገመት በመሆኑ፣ በ23/07/2007 ዓ.ም እና በ18/08/2009 ዓ.ም የተደረጉ ውሎች የሚፍርሱበት ህጋዊ ምክንያት ያልተገኘ በመሆኑ የአመልካች ክርክር ተቀባይነት የለውም፤1ኛ እና 2ኛ ተጠሪዎች ለ3ኛ ተጠሪ የሸጡትን ቤት በድጋሚ ለአመልካች የሸጡ በመሆኑ በሽያጭ ላይ ሽያጭ የፈፀሙ በመሆኑ በቀን 13/03/2008 ዓ.ም የፈፀሙት ሽያጭ ሊፈርስና ቤቱ ለ5ኛ ተጠሪ ሊያስረክቡ ይገባል እንዲሁም አመልካች ከፈሉትን ገንዘብ ብር 12,500,000 (አስራ ሁለት ሚሊዮን አምስት መቶ ሺህ)1ኛ እና 2ኛ ተጠሪዎች ሊመልሱ ይገባል፣ አመልካች የጠየቁት የወቅታዊ የገበያ ማካካሻ ዳኝነት ብር 50000000 አምስት ሚሊዮን በማስረጃ ያልተደገፈ በመሆኑ እንዲሁም 5ኛ ተጠሪ ያቀረቡት የተከሳሽ ከሳሽነት ክስ ላይ የቤት ኪራይ የጠየቁትና አመልካች ያለዘግባብ በልጽገዋል ያሉት ተቀባይነት የለውም በማለት አመልካችና ተጠሪዎች ወጪያቸውን እንዲችሉ ሲል ወስኗል፡፡አመልካች በዚህ ውሳኔ ቅር በመሰኘት ይግባኝ ለፌዴራል ጠቅላይ ፍ/ቤት ይግባኝ ሰሚ ችሎት ያቀረቡ ሲሆን 5ኛ ተጠሪም መስቀለኛ ይግባኝ አቅርበው ፍ/ቤቱም ግራ ቀኙ ካከራከረ በኋላ ወጪና ኪሳራ ይቻቻሉ በሚል የስር ፍርድ ቤት የሰጠውን የውሳኔ ክፍል ብቻ በማሻሻል ወስኗል፡፡ አመልካች የሰበር አቤቱታ ያቀረቡት ይህን ዉሳኔ በመቃወም ለማስለወጥ ነዉ፡፡
የአመልካች የሰበር አቤቱታ ይዘት በአጭሩ፡- በሥር ፍ/ቤት ትዕዛዝ እንዲቀርቡ በአመልካች እና በ5ኛ ተጠሪ ተጠይቀው ከክፍለ ከተማ የቀረቡት የግል ማህደሮች /ኮፒው/ በድጋሚ ቀርቦ እንዲታይልኝ ለጠቅላይ ፍ/ቤት አመልክቼ መታለፉ የፍ/ብ/ሥ/ሥ/ህ/ቁ 145(1) እና የፌ/ጠ/ፍ/ቤት ሰበር ችሎት በመ/ቁ 99474 ቅጽ 21 ላይ የሰጠውን የህግ ትርጉም የሚፃረር በመሆኑ መሰረታዊ የህግ ስህተት ያለበት ነው፤ የከፍተኛው ፍ/ቤት ማህደሮቹን ተመልክቻለሁ በማለት በፍርዱ ላይ የተምታታ እና ትክክለኛ ያልሆኑትን ነገሮች መዝግቦ ኢ-ፍትሐዊ የሆነ ውሳኔ ሰጥተዋል፡፡ይግባኝ ሰሚው ፍ/ቤት ማህደሮቹን አስቀርቦ ሳይመለከት አንደኛ እና ሁለተኛ ነጥብ በማለት ባስቀመጠው ፍርድ ስር በቀጥታ ከማህደሮቹ ጋር ተያያዥነት ያላቸውን ፍሬ ነገሮች በራሱ ግምት እየወሰደ በስር ፍ/ቤት የተመዘገበውን ፍሬ ጉዳይ ሲፈልግ አሻሽሎ ሲፈልግ ትክክል እንደሆነ መዝግቦ ወስኗል፡፡ የከፍተኛው ፍ/ቤት ፍርድ ሐተታው ላይ የገለፃቸው ፍሬ ነገሮች በእጅጉ የተዛባ እና የአንዱን ተጠሪ ክርክር ለሌላኛው ተጠሪ በማድረግ ባልተገባ መንገድ በመተቸት የተሰጠ ፍርድ ነው፤የ1ኛ እና 3ኛ ተጠሪዎች ክርክር በበርካታ ጉዳዮች ላይ የሚጣረስ ከመሆኑም በላይ ብዙ ያልተመለሱና ሊመለሱ የማይችሉ ጥያቄዎችን ያስከተለ ቢሆንም የስር ፍ/ቤቶች በአግባቡ ሳያዩና ሳይመረምሩ ተገቢ ያልሆነ ፍርድ ሊሰጡ ችለዋል፤አመልካች ንብረቱን ስገዛው 3ኛ ተጠሪ አይታወቅም ነበረ፣ ካርታውም ሆነ ንብረቱ በ1ኛ ተጠሪ እጅ ነበር፣የሰነዶች ምዝገባና ማረጋገጫ ጽ/ቤት በ1ኛ ተጠሪ እጅ ያለውን ካርታ አይቶ ካረጋገጠ በኋላ ነው ውሉን ያፀደቀውና የመዘገበው፣ ቤቱን ከመግዛቴ በፊት ከማንኛውም ነገር ነፃ መሆኑን በ1ኛ ተጠሪ ስም ከሚገኘው ከማህደሩ አረጋግጬ ነው የገዛሁት፤ መጋቢት 23 ቀን 2007 ዓ.ም ተፈጽሟል የተባለው ውል በ1ኛ ተጠሪ ስም ከሚገኝ ፋይል ጋር አልተያያዘም፤አልተመዘገበም ፋይሉ ከፍተኛ ፍ/ቤት ቀርቦ ውሉ ከማህደሩ ጋር አለመያያዙንና አለመመዝገቡ ተረጋግጧል፤ይህ ከሆነ ደግሞ በፍ/ብ/ህ/ቁ 2878 እና በሰበር መ/ቁ 21448 ቅጽ 21 ላይ በሰጠው አስገዳጅ ትርጉም መሰረት በኔ ላይ መቃወሚያ በመሆን ሊቀርብብኝ አይገባም፡፡አመልካች ቤቱን ስገዛውም ሆነ ከገዛሁት በኋላ ወይም ወደ 3ኛ ተጠሪ ከዞረ በኋላ ቢሆን በ3ኛ ተጠሪ ስም የተደራጀ ማህደር የለም፤የስር ፍ/ቤት የቤቱን ማህደር ያጣራው ሕጋዊ ተወካዬ የነበሩት 4ኛ ተጠሪ እንደሆነ በማድረግ በማስረጃ ከተረጋገጠው ውጪ በፍርዱ ላይ አስቀምጦ ተገቢ ያልሆነ ድምዳሜ ላይ ሊደርስ ችሏል፤ መጋቢት 23 ቀን 2007 ዓ.ም የተደረገው ውል ከየትኛው ማህደር ጋር እንደተያያዘ የስር ፍ/ቤት ባይገልጽም ውሉ የተያያዘው አመልካች ሽያጭ ውል ከፈፀምኩ በኋላ በሂደት መሆኑን ግልጽነት በሌለውና እርስ በእርሱ በሚጣረስ መልኩ ማስቀመጡ ተገቢነት የለውም፤አመልካች በ13/03/2008 ዓ.ም የፈፀምኩት ግዢ ውል በቤቱ ማህደር ውስጥ የተያያዘና የተመዘገበ ቢሆንም የስር ፍ/ቤት እንዳልተያያዘ በማስመሰል መዝግቦታል፤5ኛ ተጠሪ የቅን ልቦና ገዢ ስለሆንኩ አመልካች ቤቱን በህገወጥ መንገድ ስለያዘ ይልቀቅልኝ በማለት የተከሳሽ ከሳሽት ክስ ያቀረበብኝ ክስ እኔ ከ1ዓመት ከ6 ወር በፊት አስቀድሜ የገዛሁትና የቅን ልቦና ህጋዊ ገዢ ስለሆንኩ ቤቱን እንዳስረክብ መወሰኑ መሰረታዊ የህግ ስህተት ነው፣አመልካች ቤቱን ሳስተዳር እንደነበር ለጠቅላይ ፍ/ቤት ያቀረብኩትን ክርክር ከካርታ ይዞታ እና ከስም ዝውውር ጋር አያይዞ ውድቅ ማድረጉ በማስረጃ ያልተረጋገጠውን ፍሬ ነገር መሰረት በማድረግ ህጋዊ መሰረት የሌለው ውሳኔ መስጠቱ ስህተት ነው፤ አመልካች በአማራጭ ባቀረብኩት ዳኝነት የጠየኩት የጉዳት ኪሳራ ብር 5000000 (አምስት ሚሊዮን) መታለፉ፣ 5ኛ ተጠሪ ወጪና ኪሳራ አቅርበው ማስወሰን እንዲችሉ የተወሰነበት አግባብ እንዲሁም 3ኛ እና 4ኛ ተጠሪዎች ለተጠየቀው ዳኝነት የጋራ ኃላፊነት የለባቸውም ተብሎ በነፃ መሰናበታቸው የቀረበውን ክርክር እና ማስረጃ መሰረት ያላደረገ ሕጋዊነት የሌለው ውሳኔ በመሆኑ ሊሻር ይገባዋል፣3ኛ ተጠሪ ካርታውንና ቤቱን ለሻጭ በመመለስ በድጋሚ እንዲሸጥ ያመቻቹና የተባበሩ መሆኑ እስከተረጋገጠ ድረስ ከሌሎቹ ጋር የጋራ ተጠያቂ መሆን ሲገባቸው በነፃ መሰናበታቸው መሰረታዊ የህግ ስህተት የተፈፀመበት በመሆኑ ሊታረም ይገባል የሚል ነው፡፡
የአመልካች አቤቱታ በሰበር አጣሪ ችሎት ተመርምሮ አመልካች በሥር ፍ/ቤት የ3ኛ ተጠሪ የሽያጭ ውል ከማህደር ጋር አልተያያዘም፣ ማህደሩ ቀርቦ ይታይልኝ እንዲሁም የሽያጭ ውሉ በሰነዶች ምዝገባና ማረጋገጫ ጽ/ቤት ስለመደረጉ እንዲጣላቸው በጠየቁበት ሁኔታ ሥር ከፍተኛ ፍ/ቤት የ3ኛ ተከሳሽ የሽያጭ ውል በአንድ በኩል ከማህደሩ ጋር ተያይዟል በሌላ በኩል ከማህደሩ ጋር አልተያያዘም እንደዚሁም ውሉ ከማህደሩ ጋር ዘግይቶ ተያይዟል በሚል በገለጸበት ሁኔታ ይግባኝ ሰሚው ፍ/ቤት ማህደሩን አስቀርቦ ማጣራት ሳያደርግ የወሰነበት አግባብ ከመሰረታዊ የክርክር አመራር ሥነ-ሥርዓት ማስረጃ ምዘና መርህ አኳያ መጣራት ያለበት መሆኑ ስለታመነ በአዋጅ ቁጥር 1234/2013 አንቀጽ 28/3 መሰረት መዝገቡ ለሰበር ሰሚ ችሎት ያስቀርባል ተብሎ ተጠሪዎች መልስ እንዲሰጡበት ታዟል፡፡
1ኛ ተጠሪ ባቀረቡት መልስ የቤት ሽያጭ ውሉ ከቤቱ ማህደር ጋር መያያዝና አለመያያዙ ውሉን ፈራሽ አያደርገውም፣የሽያጭ ውሉን በማስረጃነት ያቀረቡት አመልካች ሆነው ባሉበት ሁኔታ ስለሽያጭ ውሉ መከራከሪያ ሊያቀርቡ አይችሉም፣በ1ኛ እና 3ኛ ተጠሪዎች መካከል መጋቢት 23 ቀን 2007 ዓ.ም የተደረገው የሽያጭ ውል በሰነዶች ምዝገባና ማረጋገጫ ጽ/ቤት የተደረገ ሲሆን የሽያጭ ውሉም ከቤቱ ማህደር ጋር የተያያዘ በመሆኑ ወደ 3ኛ ተጠሪ የስም ዝውውር ተደርጎ ካርታ ተሰጥቶታል፤ይህም በስር ፍ/ቤት የቤቱ ማህደር ቀርቦ የተረጋገጠ በመሆኑ የሰበር አቤቱታው ውድቅ እንዲደረግ፤አመልካች ከ1ኛ ተጠሪ ጋር ምንም ዓይነት ግንኙነት አድርገን አናውቅም፤ለአንድም ቀን ተገናኝተን ስለ ቤቱ ሽያጭ እና ግዢ አውርተን አናውቅም፣የአመልካች ህጋዊ ወኪል ቤቱን ለመግዛት በመፈለጉ ለ3ኛ ተጠሪ የተሸጠ መሆኑን የሽያጭ ውሉን አሳይተናቸው እንዲሁም ክፍለ ከተማ በመሄድ ዝውውሩ ሊደረግ በሂደት ላይ መሆኑን ከቤቱ ማህደር አረጋግጠው ነገር ግን ወደ 3ኛ ተጠሪ ስም ዝውውር እስከሚደረግ ድረስ ከ1ኛ ተጠሪ ጋር የሽያጭ ውል ለጊዜው ለመዋዋል በመፈለጋቸው የሽያጭ ውል ተደርጓል፤የሽያጩን ውል ገንዘብ 4ኛ ተጠሪ ከራሳቸው ሂሳብ አካውንት ከፍለዋል፤የከፍተኛው ፍ/ቤት ማህደር አስቀርቦ ወስኖ እያለ ይግባኝ ሰሚው ጠቅላይ ፍ/ቤት ማህደር አስቀርቦ ውሳኔ አለመስጠቱ መሰረታዊ የህግ ስህተት አያስብልም፤አመልካችና 4ኛ ተጠሪ ወንድማማች በመሆናቸው 4ኛ ተጠሪ በውክልናቸው ቤቱን ከገዙ በኋላ መልሰው ለ5ኛ ተጠሪ ሸጠዋል፣አመልካች ክስ በማቅረብ ውሎቹን በማፍረስ ያለአግባብ ለመበልፀግ በማሰብ በቅንጅት የቀረበ ክስ በመሆኑ የሰበር አቤቱታው ውድቅ ይደረግልኝ በማለት ተከራክረዋል፡፡3ኛ ተጠሪ ባቀረቡት መልስ አመልካች ፌ/ጠ/ፍ/ቤት ሰበር በመ/ቁ 99474 የሰጠውን ውሳኔ በመጥቀስ ብቻ ያቀረቡት አቤቱታ ከዚህ ጉዳይ ጋር አግባብነት እና ተመሳሳነት የሌለው በመሆኑ የሰበር አቤቱታው አግባብነት የለውም፤ አመልካች ያቀረቧቸው የቅሬታ ነጥቦች የፍሬ ጉዳይ ክርክር መሰረት ያደረገ እንጂ በስር ፍ/ቤት በተሰጡ ውሳኔዎች ላይ መሰረታዊ የህግ ስህተት ያለባቸው መሆኑን የማያመላክት በመሆኑ በሰበር ሰሚ ችሎት የሚታይ አይደለም፤3ኛ ተጠሪ በ23/07/2007 ዓ.ም ውል ለማዋዋል ስልጣን ባለው በሰነዶች ምዝገባና ማረጋገጫ ጽ/ቤት በመቅረብ የሽያጭ ውል በመፈፀም ገዝቻለሁ ውሉም ከቤቱ ማህደር ጋር የተያያዘ በመሆኑ መጋቢት 20 ቀን 2009 ዓ.ም የስም ዝውውር ተደርጎ በስሜ ካርታ ከተሰጠኝ በኋላ ለአመልካች ህጋዊ ወኪል በሰጠኋቸው ውክልና መሰረት መጋቢት 23 ቀን 2009 ዓ.ም ለ5ኛ ተጠሪ የሸጡት በመሆኑ የአመልካች ክርክር ተገቢነት የለውም፤3ኛ ተጠሪ ቤቱን ስገዛው የስም ዝውውር ማድረግ ታግዶ የነበረ ቢሆንም የሽያጭ ውሉ ከቤቱ ማህደር ጋር የተያያዘ ሲሆን ካርታ መሰራት ሲጀምር የስም ዝውውር ተደርጎ ካርታ ተሰርቶ ተሰጥቶኛል ይህንንም የአመልካች ህጋዊ ወክል በክፍሉ መሬት አስተዳደር ቀርበው አጣርተው ቤቱን ገዝተዋል፡፡አመልካች ስለ ቤት ግዢም ሆነ የቤቱን ማህደር አንድም ቀን ሳይመለከቱ 1ኛ እና 3ኛ ተጠሪዎች መጋቢት 23 ቀን 2007 ዓ.ም ያደረጉት ውል ታማኝነት ለውም በማለት ያቀረቡት ክርክር በስር ፍ/ቤት ያላነሱትን ክርክር ማንሳታቸው ተገቢነት የሌለው በመሆኑ ሰበር አቤቱታቸው ውድቅ እንዲሆን በማለት ተከራክረዋል፡፡ 4ኛ ተጠሪ ባቀረቡት መልስ አመልካች ክስ አቀራረብ በተጠሪው ላይ ምንም ማስረጃ ባለመቅረቡ እና የቀረበው ክስ እውነትነት እንደሌለው አረጋግጦ ነው፣የአመልካች ክስ ተጀምሮ እስኪያልቅ ተመሳጥረው ተመሳጥረው የሚል ነው፤ከውክልና ጋር በተያያዘ አዲስ ቅሬታ በፍ/ብ/ሥ/ሥ/ህ/ቁ 259 መሰረት መቅረቡ ተቀባይነት የለውም፣4ኛ ተጠሪ በውክልናው መሰረት አልሰራህም ተብሎ የቀረበ ክስ የለም፤በሌላ በኩል ከ3ኛ ተጠሪ ውክልና በመቀበል ለ5ኛ ተጠሪ ሸጠ ተባለውን በተመለከተ ከ3ኛ ተጠሪ የተረከብኩት ካርታ ለአመልካች ከገዛሁት ቦታ የባለይዞታነት ስም እና ካርታ ጋር የማይገናኝ ነው፤እነዚህ ካርታዎች የተለያዩ የባለይዞታዎች ስም ሆነው አንድ መሆናቸውን የማውቅበት ምክንያት የለም፣ አውቅ እንደነበረም በስር ፍርድ ቤት ክርክር ያልተደረገ በመሆኑ ቅሬታው ውድቅ ተደርጎ ስር ፍ/ቤት ውሳኔ እንዲፀና በማለት ተከራክረዋል፡፡5ኛ ተጠሪ ባቀረቡት መልስ 5ኛ ተጠሪ ቤቱን የገዛሁት በህግ እውቅናና ማረጋገጫ በተሰጣቸው ውሎች አማካነት ከ3ኛ ተጠሪ ነው፤ 3ኛ ተጠሪ ከ1ኛ እና 2ኛ ተጠሪዎች መጋቢት 23 ቀን 2007 ዓ.ም ያደረገው የመኖሪያ ቤት ሽያጭ በቁጥር ቅ9/1066/2ለ/07 በቀን 23/07/2007 በኢፌዲሪ ፍትህ ሚኒስቴር የሰነዶች ማረጋገጫና ዝገባ ኤጀንሲ የተመዘገበና የተረጋገጠ ህጋዊ ውል ሲሆን አመልካችም በስር ፍ/ቤት ክስ ሲመሰርቱ በማስረጃነት አያይዘውታል፤በውሉ መሰረት የቦሌ ክፍለ ከተማ የመሬት ይዞታ እና መረጃ ኤጀንሲ በቁጥር AA000060303635 የሆነ ህጋዊ ካርታ ለ3ኛ ተጠሪ ሰጥቷል፡፡ይህም በስር ፍ/ቤት በተገቢው መልኩ ማህደሩ ቀርቦ ተረጋግጧል፣አመልካችም ካርታው በህገ ወጥ ውል ነው የተሰጠው በማለት ክስ አልመሰረቱም፤አመልካች በከፍተኛ ፍ/ቤት ፍርድ የቃላት ግድፈት በመጠቀም ውላቸው በግልጽ ያልተመዘገበ መሆኑ ተረጋግጦ እያለ ያልተገባ መብት ለማግኘት በማስረጃ የተረጋገጠውን እንዲመረመር ያላግባብ ያቀረቡት የቅሬታ ነጥብ መሆኑን ፍ/ቤቱ እንዲያይልን፤በስር ፍ/ቤት በተሰጠው ትዕዛዝ መሰረት የቤቱ ማህደር ከቦሌ ክፍለ ከተማ ይዞታ አስተዳደር የሽግግር ጊዜ ፕሮጀክት ጽ/ቤት እና በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የመሬት ይዞታ ምዝገባ እና መረጃ ኤጀንሲ የቦሌ ክፍለ ከተማ ቅርንጫፍ ጽ/ቤት የቀረበ ሲሆን ከቦሌ ክፍለ ከተማ ይዞታ አስተዳደር የሽግግር ጊዜ ፕሮጀክት ጽ/ቤት የተገኘው ማህደር የሚያመለክተው በፊት የነበሩቱን ባለይዞታዎች እና 1ኛ ተጠሪ ታሪክ ነው የሚያሳየው፣ተቋሙ በዲጂታል ካርታ በመቀየር ወደ አዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የመሬት ይዞታ ምዝገባ እና መረጃ ኤጀንሲ የቦሌ ክፍለ ከተማ ቅርንጫፍ ጽ/ቤት በማስተላለፉ ከመነሻ የነበሩትንና ከ3ኛ ተጠሪ ጀምሮ ዲጂታል ካርታ በመጠቀም እና ቤቱን በተመለከተ መረጃ ተደራጅቷል፤አመልካች የተዋዋሉት ውል በማህደሮቹ ውስጥ አልተያያዘም የ3ኛ ተጠሪ ውል ማህደር ውስጥ ተያይዞ እና ተመዝግቦ በውሉ መነሻ ካርታ ተሰጥቶ የቤቱ ባለቤት ሆኖ ሳለ አልተያያዘም በማለት ካርታ ያለውን ግለሰብ የለውም በሚል ያልተገባ ክርክር መቅረቡ ተገቢነት የለውም፤ 5ኛ ተጠሪ ቤቱን ገዝቼ በመሀንዲስ በማስለካት ሊዝ ውል በመዋዋል ካርታ ለማሰራት በቀጠሮ ላይ እያለሁ አመልካች ቤቱን ከገዛሁ 5 ወር በኋላ ነሐሴ 08 ቀን 2009 ዓ.ም ከሌሊቱ 7፡00 ሰዓት ጥበቃዎችን በማባረር የፍ/ቤት እግድን በመጠቀም በኃይል ይዘውታል እንጂ በህጋዊ መንገድ አልያዙም፤ 5ኛ ተጠሪ 1ኛ ተጠሪንም ሆነ አመልካችን ያወቃቸው በፍ/ቤት ክስ ከተመሰረተ በኋላ ነው ፍጹም ቅን ልቦናን መሰረት ባደረገ መልኩ ከ3ኛ ተጠሪ ጋር ውል በመዋዋል ነው የገዛሁት፤አመልካች በስር ፍ/ቤት ተጨማሪ ማስረጃ እንዲቀርብላቸው ጠይቀው አስተያየት ሰጥተንበት አመልካች ለማቅረብ የጠየቁት ማስረጃ የፍ/ብ/ሥ/ሥ/ህ/ቁ 137 ድንጋጌ መሰረት የሚያሟላ ባለመሆኑ ፍ/ቤቱ ሳይቀበለው ቀርቷል ይህም ስነ ስርዓታዊ ነው፤አመልች በአማራጭ ያቀረቡት ዳኝነት የውል ግንኙነት የሌለውን 5ኛ ተጠሪን የሚመለከት ባለመሆኑ የስር ፍ/ቤት ውሳኔ እንዲፀና በማለት ተከራክረዋል፡፡ተጠሪዎች ላቀረቡት መልስ አመልካቹ የመልስ መልስ በመስጠት የሰበር አቤቱታቸውን ያጠናከሩ ሲሆን 4ኛ ተጠሪ ከአመልካች በተሰጠው ህጋዊ ውክልና መሰረት በብር 12‚500‚000 (አስራ ሁለት ሚሊዮን አምስት መቶ ሺህ) ከ1ኛ እና 2ኛ ተጠሪዎች በስሜ የገዛልኝና በይዞታዬ ስር መሆኑን እያወቀ በ3ኛ ተጠሪ ስም ካርታ እንዲሰራ ሁኔታ ማመቻቸቱና በ3ኛ ተጠሪ ስም ሽያጭ ማከናወኑ የተመሳጠረ መሆኑን የሚያሳይ በመሆኑ የአመልካችን መብትና ጥቅም የሚፃረር ተግባር ነው በማለት ተከራክረዋል፡፡
የጉዳዩ አመጣጥ እና ክርክሩ በአጭሩ ከላይ የተገለጸዉን የሚመስል ሲሆን እኛም አቤቱታ የቀረበበት ዉሳኔ ከግራቀኙ ክርክር እና በሰበር አጣሪ ችሎት የተያዘዉን ጭብጥ መሰረት በማድረግ አግባብነት ካላቸዉ የሕግ ድንጋጌዎች ጋር በማገናዘብ መዝገቡን መርምረናል፡፡ እንደመረመርነዉ ለክርክሩ ምክንያት የሆነዉ በአንድ ቤት ላይ በተለያየ ጊዜ የተደረገ ሽያጭ ዉል ነዉ፡፡ግራ ቀኙ የሚከራከሩበት ቤት ቦሌ ክ/ከተማ በቦሌ ክፍለ ከተማ ወረዳ 03 የቤት ቁጥር 2389/ለ የካርታ ቁጥር ቦሌ9/42/3/9/17764/20400/23602/02 የብሎክ ቁጥር 26 ፓርሴል ቁጥር 12 የቦታ ስፋት 500 ካ.ሜ ሲሆን ለክርክር ምክንያት የሆነዉ በዚህ ቤት ላይ በቀን 23/07/2007ዓ.ም፣13/03/2008ዓ.ም እና 18/08/2009ዓ.ም የተደረገ የሽያጭ ዉል መኖሩን ክርክሩ ያሣያል፡፡
የማይንቀሳቀስ ንብረት ካለዉ ከፍተኛ ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታ የተነሳ ህጉ ልዩ ጥበቃ ያደረገ መሆኑን መገንዘብ ተገቢ ነዉ፡፡የማይንቀሳቀስ ንብረት ጋር ተያይዞ የሚከናወኑ መብት ማቋቋም ወይም ማስተላለፍ የሚመለከቱ ህጋዊያን ተግባራት ሁሉ በጽሁፍና በሚገባ አኳኋን በፍርድ ቤት መዝገብ ወይም ዉል ለማዋዋል ስልጣን በተሰጠዉ አካል ፊት መደረግ አለበት የሚለዉ የህግ አሰገዳጅ ድንጋጌ ይህንኑ የሚያሳይ ነዉ፡፡የፍ/ብ/ህግ ቁጥር 1723/1/ይመለከታል፡፡ከዚህም ባሻገር የማይንቀሳቀስ ንብረት በሚገኝበት አስተዳደር ክፍል መዝገብ ዉስጥ ተመዝግቦ እንዲገኝ ህጉ ግድ ይላል፡፡የፍ/ብ ህግ ቁ/1567 እና 1570፣1645 እና 2878 ይመለከታል፡፡የዚህም ምዝገባ አስፈላጊነት በማናቸዉም ሁኔታ በንብረቱ ላይ ለተቋቀቋመ መብት ዋስትና ማረጋገጥ ብሎም መብት ለማስተላለፍ ወይም ለማቋቋም የሚሹ ሶስተኛ ወገኖች ይህንኑ አዉቀዉ ለመዋዋል እንዲችሉ ለማድረግ እንደሆነ እሙን ነዉ፡፡፡የማይንቀሳቀስ ንብረት ሽያጭ ውል በአዋዋይ አካል ወይም በፍርድ ቤት ፊት እንዲደረግ የማድረጉ አስፈሊጊነት በተዋዋይ ወገኖቹ መካከል የፀና ውል መኖሩን ለማረጋገጥ ሲሆን በፍ/ብ/ሕ/ቁ. 2878 የተመለከተው የማይንቀሳቀስ ንብረት ምዝገባ ዓላማ ውሉ በሦስተኛ ወገኖች ላይ ውጤት እንዲኖረዉ ለማድረግ ሲባል ነው፡፡በሌላ አገላለጽ የማይቀሳቀስ ንብረት ሽያጭ ዉል በንብረት ምዘገባ ጽ/ቤት እንዲመዘገብ የሚደረግበት ዋነኛዉ ምክንያት ሶስተኛ ወገኖች ይህንኑ አዉቀዉ ተገቢዉን ጥንቃቄ እንዲያደርጉ ለማስቻል ነዉ፡፡በመሆኑም በፍ/ብ/ህግ ቁጥር 1195 ላይ እንደተደነገገዉ አንድ የማይንቀሳቀስ ንብረት ስመ ሀብት በስሙ የተመዘገበ ሰዉ የዚሁ ንብረት ባለሀብት እንደሆነ የህግ ግምት ይወሰዳል፡፡ንብረቱ በስሙ የተመዘገበ ሰዉ ይህንኑ ንብረት የመሸጥ ወይም በሌላ አግባብ የማስተላለፍ ሙሉ መብት ያለዉ ስለመሆኑ የፍ/ብ/ህግ ቁጥር 1205 ድንጋጌ ይዘት ያሥገነዝባል፡፡ የማይንቃሳቀስ ንብረት ገዥም ስመ ንብረቱ በሻጭ የተመዘገበና ከእዳና እገዳ ነጻ መሆኑን ከሚመለከተዉ አስተዳደር አካል በማረጋገጥ የተዋዋለ እንደሆነ አንድ ጠንቃቃ ሰዉ ማድረግ የሚጠበቅበት ጥንቃቄ እንዳደረገ ግምት ተወስዶ ሕጉ ጥበቃ ያደርግለታል፡፡የፍ/ብ/ህግ ቁጥር 1553 እስከ 1646፤2878 እና 3052 ድንጋጌዎች የማይንቀሰቃስ ንብረት ምዝገባ አስፈላጊነትም የንብረት መብት ጥበቃ ለማረጋገጥ፣የግብይት ዋስትና እና የ3ኛ ወገኖችን መብት ለማስከበር እንደሆነ የሚያሥገነዝቡ ናቸዉ፡፡ስለዚህም የማይንቃሳቀስ ንብረት ላይ በዉል መብት ለማቋቋም የፈለገ ሰዉ እንደ አንድ ጠንቃቃ ገዥ ይህንኑ ስርዓት ተከትሎ ማለትም ስመ ንብረቱ በሻጭ ስም የተመዘገበና ንብረቱ ከእዳና እገዳ ነጻ መሆኑን የማረጋገጥ ሃላፊነት አለበት፡፡በዚህ ረገድ ተገቢ ጥንቃቄ ማድረጉ ከተረጋገጠ ዉሉ የሚፈርስበት ህጋዊ ምክንያት አይኖርም፡፡የፍ/ብ/ህግ ቁጥር 2881 ይመለከታል፡፡
በተያዘዉ ጉዳይ የአመልካቹ ክስ ይዘት እንደሚያሳየዉ ቤቱን ከእዳና እገዳ ነጻ መሆኑን በማረጋገጥ ወኪሉ በሆነዉ 4ኛ ተጠሪ አማካይነት በቀን 13/03/2008ዓ.ም በተደረገ የሽያጭ ዉል ገንዘቡን ከፍሎ ቤቱንና ስነዱን ተረክቦ እያለ ቤቱ አስቀድሞ በቀን 23/07/2007ዓ.ም ለ3ኛ ተጠሪ እንደተሸጠ ተደርጎ ለ5ኛ ተጠሪ በቀን 18/08/2009ዓ.ም በሽያጭ መተላለፉ የአመልካቹን ጥቅም ለመጉዳት በመመሳጠር የተደረገ ነዉ በሚል ሁለቱ ዉሎቹ እንዲፈርሱ ዳኝነት የጠየቀ ሲሆን የ1ኛ ተጠሪ ዋነኛ መከራከሪያ ቤቱ ለ3ኛ ተጠሪ የተሸጠ መሆኑን አመልካቹ እያወቀ ነዉ የገዛዉ የሚል እንጂ ሽያጭ ዉሉን በመካድ ያቀረበዉ ክርክር የለም፡፡ከዚህ አኳያ በአመልካች እና በ1ኛ ተጠሪ መካከል በቀን 13/03/2008ዓ.ም የተደረገዉ ዉል በተዋዋይ ወገኖች የታመነ ከመሆኑም በተጨማሪ ዉሉ በዉል አረጋጋጭ አካል ፊት የተደረገ መሆኑ በስር ፍርድ ቤትም የተረጋገጠ ጉዳይ ነዉ፡፡ስለዚህም በተዋዋይ ወገኖች መካከል የጸና ዉል ስለመኖሩ አከራካሪ አይደለም፡፡
ይሁንና ይህ ዉል ከሶስተኛ ወገን መብት አንጻር የሚኖረዉን ህጋዊ ዉጤት ለመወሰን 3ኛ ተጠሪ ያደረገዉ ዉል መኖሩን አመልካቹ የሚያዉቅበት ሁኔታ ነበር ወይስ አልነበረም የሚለዉ መመርመር አስፈላጊ ነዉ፡፡አመልካቹ ዉሉን ያደረገዉ ለ3ኛ ተጠሪ መሸጡን እያወቀ ነዉ በሚል ክርክር ያነሳዉ 1ኛ ተጠሪ እንደመሆኑ ይህንኑ ማስረዳት ይጠበቅበታል፡፡በሌላም በኩል 3ኛ ተጠሪ ያደረገዉ ዉል ከማህደር ጋር ተያይዟል የሚል ክርክር መቅረቡን እና ይህ ደግሞ በአመልካቹ መካዱን ተከትሎ በማስረጃ መጣራት ያለበት ጉዳይ ነዉ፡፡በዚህ ረገድ የፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ዉሳኔ ይዘት ሲታይ በአንድ በኩል ዉሉ ከማህደሩ ጋር ተያይዟል በሚል በሌላ በኩል ደግሞ ዉሉ ከማህደሩ ጋር አልተያያዘም፤ተያይዟል ቢባል አንኳን ዘግይቶ ነዉ የተያያዘዉ የሚሉ መንደርደሪያዎች የያዘ መሆኑን፤ይህንኑ እንዲያጣራ ይግባኝ የቀረበለት ይግባኝ ሰሚ ፍርድ ቤትም ስህተት መኖሩን ገልጾ ነገር ግን የአመልካቹም ዉል ከማህደር ጋር መያያዙ ስላልተረጋገጠ የሚያስከትለዉ ለዉጥ የለም በሚል ዉድቅ ማድረጉን ዉሳኔዉ ያሣያል፡፡ከላይ እንደተገለጸዉ የማይቀንቀሰቀቀስ ንብረት ሽያጭ ዉል ሶስተኛ ወገን ላይ መቃወሚያ ሊሆን የሚችለዉ ዉሉ በሚመለከተዉ አስተዳደር አካል መመዝገቡ ሲረጋገጥ ነዉ፡፡የፍ/ብ/ህግ ቁጥር 2878 ይመለከቷል፡፡በዚህም ጉዳይ ቤቱን ቀድሞ ገዝቷል የተባለዉ 3ኛ ተጠሪ ከአመልካቹ የተሻለ መብት የሚኖረዉ አስቀድሞ 3ኛ ተጠሪ በዉል መብት ያቋቋመበት መሆኑን አመልካቹ እያወቀ ዉል ያደረገዉ እንደሆነ ነዉ፡፡በዚህ ረገድ በአመልካች እና 3ኛ ተጠሪ መካከል ሌላ ስምምነት መኖሩ ካልተረጋገጠ በስተቀር አመልካቹ እያወቀ ነዉ የተዋዋለዉ ሊባል የሚችለዉ ዉሉ ከማህደሩ ጋር የተያያዘ መሆኑ በአግባቡ ሲረጋገጥ ነዉ፡፡በሌላ በኩል እንደአንድ ጠንቃቃ ገዥ ተገቢዉን ትጋት አድርጎ ማህደሩን ሳያጣራ ቢዋዋል ሃላፊነቱን የሚወሰደዉ ራሱ ነዉ፡፡አመልካቹ አጥብቆ የሚከራከረዉም ቤቱን 3ኛ ተጠሪ ቀድሞ ስለመግዛቱ የሚያሳይ ነገር እንደሌለ እና ዉሉም በ1ኛ ተጠሪ ስም በሚታወቀዉ ማህደር ዉስጥ አለመኖሩን እና የስር ፍርድ ቤት ለዉሳኔ መሰረት ያደረገዉ ማህደር ስመ ሀብቱ ወደ 5ኛ ተጠሪ ከተዛወረ በኋላ የተደራጀዉን ማህደር በመመልከት ስለመሆኑ እና ይግባኝ ሰሚ ፍርድ ቤት ጉዳዩ እንዲያጣራ የቀረበለትን ይግባኝ ዉድቅ ማድረጉን በመቃወም ነዉ፡፡
ሰበር አጣሪ ችሎት ማስቀረቢያ ጭብጥም ይህንኑ መሰረት ያደረገ ስለመሆኑ ከላይ ተመልክተናል፡፡ከዚህ ጋር በተያያዘም ቀድሞ በ1ኛ ተጠሪ ስም ያለዉ ማህደር ቀርቦ እንዲጣራ መጠየቁን መዝገቡ ያሣያል፡፡በእርግጥ የፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ማህደር አስቀርቦ ማየቱን በፍርዱ ላይ የገለጸ ቢሆንም ዉሉ ከየትኛዉ ማህደር ጋር እንደተያያዘ እና መቼ እንደተያያዘ በግልጽ የሚያሣይ ካለመሆኑም በተጨማሪ ከማህደር ጋር ስለመያያዙ የተምታታ መንደርደሪያ ማስፈሩ ሲታይ ቤቱን አመልካች በገዛበት ጊዜ በ1ኛ ተጠሪ ስም ካለዉ ማህደር ጋር ዉሉ መያያዙ በማያጠራጥር ሁኔታ የተረጋገጠ ፍሬነገር ነዉ ለማለት የሚያስችል አይደለም፡፡ስለሆነም ከ3ኛ ተጠሪ ጋር የተደረገዉ የሽያጭ ዉል ከማህደር ጋር ተያይዟል የሚለዉ የስር ፍርድ ቤት ድምዳሜ በቀረበዉ ክርክር አግባብ የተጣራ ባለመሆኑ ተቀባይነት የለዉም፡፡በመሆኑም ጉዳዩ ይህንን ያህል አከራካሪና አጠራጣሪ ከሆነ ደግሞ አንጻራዊ እዉነትን ለማፈላለግ እና ለትክክለኛ ፍትህ አሰጣጥ ሲባል የተባሉትን ማህደሮች አስቀርቦ መመርመር የፍርድ ቤቱ ሃላፊነት ነዉ፡፡ተገቢዉ ጭብጥ ሳይያዝ እና በማስረጃ ሳይጣራ የሚሰጥ ዉሳኔ የክርክር አመራር ጉድለት ስለመሆኑና መሰረታዊ የህግ ስህተት ሆኖ በሰበር ችሎት ሊታረም የሚገባ መሆኑን በሰበር ችሎቱ በተለያዩ መዝገቦች ገዥ ዉሳኔ ሰጥቶበታል፡፡ሰበርመ/ቁ/47252፣ 37105፣ 29861፣47551፣49660 እና ሌሎች ተመሳሳይ ጉዳዮች ላይ የሰጠዉ ዉሳኔ ይህንኑ ይመለከታል፡፡ሰበር ችሎቱ የሰጠዉ ገዥ ዉሳኔ በተመሳሳይ ጉዳዮች ላይ ተፈጻሚነት እንዳለዉ አዋጅ ቁጥር 1234/2011 አንቀጽ 26(3) ላይ ተደንግጓል፡፡ሰበር ችሎቱ ስለማስረጃ አቀራረብ በተለያዩ መዝገቦች የሰጠዉ አስገዳጅ የህግ ትርጉም ይህንኑ የሚያጠናክር ነዉ፡፡አመልካቹ አጥብቆ የሚከራከረዉ የቤቱ ማህደር የተለያየ ሁኔታና ስም የተደራጀ መሆኑን በመጥቀስ እንደመሆኑ ሁለቱም ማህደር አስቀርቦ ማጣራት ተገቢ ነዉ፡፡ከዚህ ጋር ተያይዞ መታየት ያለበት ሌላዉ አከራካሪ ጉዳይ በአንድ ንብረት ላይ በተለያዩ ሰዎች የተደረገዉ የሽያጭ ዉል በዉል አዋዋይ መ/ቤት እንዴት ሊረጋገጥ ቻለ የሚለዉ ነዉ፡፡በተዋዋይ ወገኖች መካከል የተለየ ስምምነት መኖሩ ካልተረጋገጠ በስተቀር በአንድ ሰዉ ስም ባለ ቤት ላይ ተደራራቢ ዉል በተለያዩ ሰዎች ሲደረግ የሚችልበት ሁኔታ መኖር አለመኖሩ እና ዉጤቱን በሚመለከት ዉል አረጋገጭ ክፍል ያለዉ አሰራር እና ህጉን በማገናዘብ እልበት ሊሰጠዉ ይገባል፡፡በዚህም ጉዳይ የክርክር የተነሳበት ቤት በ1ኛ ተጠሪ ስም ሆኖ እያለ 3ኛ ተጠሪ እና አመልካች በተለያየ ጊዜ ያደረጉት ዉል በሰነድ አረጋገጭ ከፍል የተመዘገበበት ሁኔታ መጣራት ያለበት ጉዳይ ነዉ፡፡
ሁለተኛዉ የአመልካቹ የዳኝነት ጥያቄ ከ5ኛ ተጠሪ ጋር የተደረገዉ ዉል በተመሳሳይ ምክንያት እንዲፈርስ የሚል ነዉ፡፡5ኛ ተጠሪ ቤቱን የገዛዉ ከ3ኛ ተጠሪ እንደመሆኑ የ5ኛ ተጠሪ መብት ምንጩ 3ኛ ተጠሪ መሆኑ በክርክሩ ሂደት የተረጋገጠ ከመሆኑ አኳያ በ5ኛ ተጠሪ በኩል የተደረገዉ ዉል የሚኖረዉ ህጋዊ ዉጤት በአመልካቹ እና በ3ኛ ተጠሪ መካከል ያለዉን ክርክር ዉጤት የሚከተል መሆኑን ክርክሩ ያሣያል፡፡በመሆኑም 5ኛ ተጠሪ ዉል አስመልከቶ ከላይ በተገለጸዉ አግባብ ተጣርቶ የሚገኘዉን ዉጤት መሰረት በማድረግ የሚወሰን ነዉ ብለናል፡፡ከዚህም በተጨማሪ 5ኛ ተጠሪ ቤቱን ለመረከብ ያቀረበዉ ዳኝነት ይህንኑ ተከትሎ እልባት የሚያገኝ መሆኑ ግንዘቤ ተወስዷል፡፡
ሌላዉ የአመልካቹ መከራከሪያ ነጥብ 4ኛ ተጠሪ በአመልካቹ የተሰጠዉን ዉክልና ስልጣን ተጠቅሞ ከ1ኛ ተጠሪ ጋር ተዋዉሎ ስመሀብት ለማዛወር በሚል የቤቱን ሰነድ ከአመልካች ወስዶ አዲስ ማህደር በማደራጀት አዲስ ካርታ ከወሰደ በኋላ ከ3ኛ ተጠሪ ዉክልና ወስዶ ቤቱን ለ5ኛ ተጠሪ መሸጡ የአመልካቹን ጥቅም ለመጉዳት በመመሳጠር የተደረገ ዉል ነዉ የሚል ሲሆን በሁለቱም ወገን ማለትም በአመልካቹ እና በ3ኛ ተጠሪ ለ4ኛ ተጠሪ ዉክልና የተሰጠ መሆኑ አላከራከረም፡፡ከዚህ ጋር በተያያዘ የ4ኛ ተጠሪ ክርክር ሲታይ ከ3ኛ ተጠሪ ውክልና በመቀበል ለ5ኛ ተጠሪ ሸጠ ተባለውን በተመለከተ ከ3ኛ ተጠሪ የተረከብኩት ካርታ ለአመልካች ከገዛሁት ቦታ የባለይዞታነት ስም እና ካርታ ጋር የማይገናኝ ነው የሚል በመሆኑ ዉክልናዉ በአንድ ቤትና ይዞታ ላይ ነዉ ወይስ አይደለም አንድ ነዉ ከተባለ የጥቅም ግጭት ወይም መመሳጠር ሁኔታ መኖር አለመኖሩን ማረጋገጥ የ4ኛ ተጠሪን ሃላፊነትም ሆነ ዉጤቱን ለመወሰን ጠቃሚ ፍሬነገር ነዉ፡፡ስለዚህም 4ኛ ተጠሪ በሁለት ወገን ዉክልና የሰራበት አግባብ እና ያስከተለዉ ጉዳት እና ሃላፊነት ምንድነዉ ሚለዉን መመርመር ነበረበት፡፡
በመጨረሻም ክርክር የተነሳበትን ቤት 1ኛ ተጠሪ አስቀድሞ ለ3ኛ ተጠሪ መሸጡ አመልካቹ እንደሚያዉቅ በማያጠራጥር ሁኔታ ቢረጋገጥ እና ዉሉ አይፈርስም ቢባል 1ኛ ተጠሪ በአንድ ቤት ላይ ከሁለት ወገን ጋር ዉል ማድረጋቸዉ ያስከተለዉ ጉዳትና ሃላፊነት ይመለከታል፡፡ከዚህ ጋር በተያያዘ የአመልካቹ የሰበር አቤቱታ እንደሚያሣዉ ዉሉ ሊፈጸም የማይቻል ከሆነ 1ኛ ተጠሪ የወሰደዉን ገንዘብ ብቻ ሳይሆን ዉሉ በመፍረሱ ያስከተለዉን ኪሳራ ጭምር 3ኛ ተጠሪ እንዲከፍሉ የቀረበዉ ጥያቄ በስር ፍርድ ቤት ዉድቅ መደረጉ እንዲታረም የሚል ነዉ፡፡በህግ አግባብ የተደረገ ዉል ህግ ሆኖ ተዋዋይ ወገኖችን የሚያስገድድ ስለመሆኑ እና እንደዉሉ ያልተፈጸመለት ወገን እንደዉሉ እንዲፈጸምለት ወይም ዉሉ ካልተፈጸመ ደግሞ እንደዉሉ ባለመፈጸሙ ለደረሰበት ጉዳት ኪሳራ የመጠየቅ መብት እንዳለዉ ህጉ ያስገነዝባል፡፡የፍ/ብ/ህግ ቁጥር 1731(1) እና ይመለከታል፡፡በተያዘዉ ጉዳይ በቀን 13/03/2008ዓ.ም በተደረገዉ ዉል መሰረት 1ኛ ተጠሪ የሽያጩን ገንዘብ ከአመልካቹ መቀበሉ የተካደ አይደለም፡፡የአመልካቹ የዳኝነት ጥያቄ ዉሉ የማይፈጸም ከሆነ ዋና ገንዘብ ብቻ ሳይሆን ኪሳራ ብር 5,000,000ጭምር መሆን አለበት የሚል ነዉ፡፡ ዉሉ ሊፈጸም አይችልም ከተባለ ለአመልካቹ የሚመለሰዉ ገንዘብ ዉሉ በተደረገበት ጊዜ የወሰደዉን ገንዘብ ብቻ ነዉ ወይስ ኪሳራ ጭምር መሆን አለበት የሚለዉ በጭብጥነት ተይዞ መመርመሩን መዝገቡ ያሣያል፡፡ይሁንና የስር ፍርድ ቤት ማስረጃ አልቀረበም በሚል የአመልካቹን ዳኝነት ዉድቅ ማድረጉን ዉሳኔዉ ያሣያል፡፡የአመልካቹ መከራከሪያ ነጥብ ዉሉ በተደረገበት ጊዜ (13/03/2008ዓ.ም) እና ዉሉ ፈርሶ ወደ ነበሩበት እንዲመለሱ የተወሰነበት ጊዜ (30/06/2014ዓ.ም) መካከል ካለዉ ጊዜ ጋር በማያያዝ የገንዘብ የመግዛት አቅም ከፍተኛ ልዩነት ያለዉ በመሆኑ ተመሳሳይ ቤት ለመግዛት የሚያስፈልገዉን ገንዘብ ከግምት በማስገባት ኪሳራ መጠየቁን ክርክሩ ያሣያል፡፡በሌላ በኩል አመልካቹ ዉሉን መሰረት አድርጎ ቤቱን መረከቡን ያመነ ስለሆነ በቤቱ ሲገለገል እንደነበር ግምት ይወሰዳል፡፡በመሆነም ኪሳራ ጥያቄዉን አግባብነት የሚያስረዳ ማስረጃ የማቅረብ ግዴታ የአመልካቹ በመሆኑ እና ማስረጃ አቅርቦ የታለፈበት ስለመሆኑ መዝገቡ ስለማያሳይ በዚህ ረገድ የሥር ፍርድ ቤት ዉሳኔ የሚነቀፍበት ምክንያት አላገኘንም፡፡
ሲጠቃለል ክርክር የተነሳበት ቤት ላይ የተደረጉት ዉሎች ህጋዊ ዉጤት በመወሰን ረገድ ዉሎቹ በሚመለከተዉ አስተዳደር አካል የተመዘገቡ መሆን አለመሆኑን በማጣራት ረገድ ፍርድ ቤቶቹ ክርክሩን የመሩበት አግባብ ከላይ በዝርዝር በተገለጹት ምክንያቶች ጉድለት ያለበት በመሆኑን መሰረታዊ የክርክር አመራር ስህተት በሰበር ሊታረም የሚገባ ስለመሆኑ ሰበር ችሎቱ ገዥ ዉሳኔ የሰጠባቸዉ በመሆኑ የስር ፍርድ ቤቶች ዉሳኔ በአዋጅ ቁጥር 1234/2013 አንቀጽ 2(4)ሐ/ሸ እና 10(1/ለ) መሰረት በማረም ተከታዩን ዉሳኔ ሰጥተናል፡፡
ዉሳኔ
1ኛ/የፌዴራል ከፍተኛ ፍ/ቤት በመ/ቁ 199251 በቀን 13/09/2013 ዓ.ም የሰጠውን ውሳኔ በማሻሻል የፌዴራል ጠቅላይ ፍ/ቤት በመ/ቁ 208910 በቀን 30/06/2014 ዓ.ም የሰጠዉ ፍርድ በፍ/ብ/ሥ/ሥ/ሕ/ቁ 348(1) መሠረት ተሻሽሏል፡፡
2ኛ/አመልካቹ ከጠየቀዉ ዳኝነት ዉስጥ ኪሳራ በማስረጃ አላስረዳም የተባለዉ ዉሳኔ ክፍል ብቻ ባለበት ጸንቷል፡፡ሌላዉ ስር ፍርድ ቤት ዉሳኔ ክፍል ተሸሯል፡፡
3ኛ/የፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ቤት የዘጋዉን መዝገብ በማንቀሳቀስ፤
ሀ/ በ3ኛ ተጠሪም ሆነ በአመልካቹ በኩል የተደረገዉ ዉል ከየትኛዉ ማህደር ጋር እንደተያያዘ እና መቼ እንደተያያዘ ወይም ከዚህ ዉጪ አስቀድሞ ዉል መደረጉን አመልካቹ የሚያዉቅበት ሁኔታ መኖር አለመኖሩን እና ህጋዊ ዉጤቱን
ለ/ክርክር የተነሳበት ቤት በ1ኛ ተጠሪ ስም ሆኖ እያለ 3ኛ ተጠሪ እና አመልካች በተለያየ ጊዜ ያደረጉት ዉል በሰነድ አረጋገጭ ከፍል የተመዘገበበት ሁኔታ እና ህጋዊ ዉጤቱን ሐ/ 4ኛ ተጠሪ ከአመልካች እና ከ3ኛ ተጠሪ ያገኘዉ ዉክልና ስልጣን በአንድ ቤትና ይዞታ ላይ ነዉ ወይስ አይደለም አንድ ነዉ ከተባለ የጥቅም ግጭት ወይም መመሳጠር ሁኔታ መኖር አለመኖሩን እና 4ኛ ተጠሪ በሁለት ወገን ዉክልና የሰራበት አግባብ እና አመልካቹ ላይ ያስከተለዉ ጉዳት መኖር አለመኖሩን እና ሃላፊነት ምንድነዉ የሚለዉን አጣርቶ እንዲሁም
መ/ የ5ኛ ተጠሪን መብት አስመልከቶ ከላይ በተገለጸዉ አግባብ ተጣርቶ የሚገኘዉን ዉጤት መሰረት በማድረግ ህጋዊ ዉጤት እንዲወሰን በማለት በፍ/ብ/ስ/ስ/ህግ ቁጥር 343(1) መሰረት መልሰንለታል፡፡ይጻፍ
4ኛ/በዚህ መዝገብ ላይ በቀን 01/082015ዓ.ም የተሰጠዉ የእግድ ትእዛዝ ተነስቷል፡፡
5ኛ/የሰበር ክርክሩ ያስከተለዉን ወጪና ኪሳራ ግራ ቀኙ የየራሳቸዉን ይቻሉ፡፡
መዝገቡ ዉሳኔ ያገኘ ስለሆነ ተዘግቷል፡፡ ይመለስ፡፡
የማይነበብ የአምስት ዳኞች ፊርማ አለበት
መ/ዐ