ፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት 

                                                                                                             FEDERAL SUPREME COURT                                                               

የሰበር / 226036

ጥቅምት 1 ቀን 2016 .

ዳኞች፡ ብርሃኑ አመነው

    ረታ ቶሎሳ

        እንዳሻዉ አዳነ

      ቀነዓ ቂጣታ

     ኑረዲን ከድር

       አመልካች፡- ታሱ ወዬሳ

       ተጠሪዎች፡- 1.የኢትዮጵያ መንገዶች አስተዳደር

                   2.ቻይና ሃይዌይ ድርጅት 

መዝገቡ ተመርምሮ የሚከተለው ፍርድ ተሰጥቷል፡፡

ፍርድ

መዝገቡ ለዚህ ችሎት የቀረበው የኦሮሚያ ጠቅላይ /ቤት በመ/ 348437 በቀን 06/11/2013 . የሰጠው ውሳኔ በመቃወም ይግባኝ የቀረበለት የፌዴራል ጠቅላይ /ቤት በመ/ 220518 በቀን 13/07/2014 . ይግባኙን በፍ///// 337 መሰረት በመሰረዙ ዉሳኔዉ የህግ ስህተት ተፈጽሞበታል በሚል አመልካች ባቀረቡት አቤቱታ መነሻ ነው፡፡ 

የጉዳዩ አመጣጥ በአጭሩ ሲታይ በስር /ቤት ከሳሽ አመልካች ሲሆኑ ተጠሪዎች ተከሳሽ በመሆን ተከራክረዋል፡፡አመልካች በቀን 07/08/2013. ባቀረቡት የክስ አቤቱታ ተጠሪዎች የመቀነጆ አይራ አስፓልት መንገድ ሲሰሩ በጉሊሶ ወረዳ ሞጋ ኮበራ ቀበሌ በሚባል ቦታ ላይ የሚገኝ ስፋቱ 0.06 ሄክታር የመስኖ መሬት ላይ ሐምሌ እና ነሐሴ 2011 . ጎርፍ ለቀው ስላበላሹብኝ 15 ዓመት ካሳ ብር 1,950,000 (አንድ ሚሊዮን ዘጠኝ መቶ ሃምሳ) በአንድነት እንዲከፍሉኝ እንዲወሰን በማለት ዳኝነት ጠይቀዋል፡፡

ተጠሪዎች በሰጡት መልስ የመንገድ ስራው የተጠናቀቀው 2006 . እስከ 2007 . ባለዉ ጊዜ ዉስጥ ስለሆነ ክሱ በፍ/// 2143(1) መሰረት በሁለት ዓመት ይርጋ ይታገዳል በማለት የመጀመሪያ ደረጃ መቃወሚያ በማቅረባቸዉ ጉዳዩ የቀረበለት የኦሮሚያ ክልል ጠቅላይ /ቤት ወደ ፍሬ ነገር ሳይገባ የቀረበውን የመጀመሪያ ደረጃ መቃወሚያ በመቀበል መንገዱ የተጠናቀቀው 2008. መሆኑን፤መንገድ ከመሰራቱ በፊት ዲች የሚሰራ በመሆኑ በፍ/// 2144(1) እና 2143(1) መሰረት የአመልካች አቤቱታ በይርጋ ይታገዳል በማለት ብይን ሰጥቷል፡፡አመልካች በዚህ ውሳኔ ቅር በመሰኘት ይግባኝ ለፌዴራል ጠቅላይ /ቤት ያቀረቡ ቢሆንም አያስቀርብም በማለት ይግባኙን በፍ///// 337 መሰረት ሰርዞታል፡፡አመልካች የሰበር አቤቱታ ያቀረቡት ይህን ዉሳኔ በመቃወም ለማስለወጥ ነዉ፡፡

የአመልካች የሰበር አቤቱታ ይዘት በአጭሩ ሲታይ በይዞታዬ ላይ ጉዳት የደረሰው 2011 . ሆኖ ክስ የቀረበው ደግሞ 07/08/2013 . ስለሆነ ሁለት ዓመት አልሞላውም፤ የስር /ቤት ለብይኑ መነሻ ያደረገው መንገድ ከመሰራቱ በፊት ዲች ይሰራል ቢልም መንገድ ከተሰራ በኋላ ዲች የተሰራ መሆኑን ነገር ግን ተጠሪዎች ያሉትን ተቀብሎ መወሰኑ ስህተት ነው፤የቀረበውን ክስ በምስክር ሳይጣራ ብይን መስጠቱ እንዲሁም ጠቅላይ /ቤቱ ሳይመረምር ውድቅ ማድረጉ ስህተት ነዉ በማለት በሰበር እንዲታረም ሲሉ አመልክተዋል፡፡

የአመልካች አቤቱታ በሰበር አጣሪ ችሎት ተመርምሮ አመልካች በመሬቱ ላይ በተሰራው መንገድ እና ዲች ምክንያት ጉዳት የደረሰው በሐምሌ እና ነሐሴ 2011 . ነው ካለ መንገዱ 2008 . ቢጠናቀቅ 2 ዓመት ይርጋው ጉዳት ከደረሰበት ጊዜ ጀምሮ ሊታሰብ አይገባም ወይ? የሚለው የህግ ስህተት መሆን አለመሆኑን ለመመርመር ሲባል መዝገቡ ለሰበር ሰሚ ችሎት ያስቀርባል ተብሎ ተጠሪዎች መልስ እንዲሰጡበት ታዟል፡፡

1 ተጠሪ ባቀረበዉ መልስ የመቀነጆ አይራ መንገድ ግንባታ የተጀመረው 2004 . ጀምሮ ሲሆን የውሃ መውረጃ ዲች ተገንብቶ የተጠናቀቀው 2005–2006 . መሆኑን፤በዚህ ዲች ምክንያት በአመልካች ይዞታ ላይ ጉዳት ቢደርስ መድረስ የሚጀምረው 2006. ክረምት ሲሆን አመልካች ክስ ያቀረበው 2011.ም፤ መሆኑን፤ጉዳት መድረስ ከጀመረበት ጊዜ ጀምሮ አመልካች ጉዳቱን ማሳወቅ የነበረበት ይዞታው ሙሉ በሙሉ በደረሰው ጉዳት ከወደመ በኋላ ሳይሆን ጉዳት መድረስ ከጀመረበት ጊዜ አንስቶ ባለው 2 ዓመት ውስጥ ያላሳወቀ በመሆኑ የስር /ቤት የፈፀመው የህግ ስህተት የለም በማለት ተከራክራል፡፡2 ተጠሪ የፍርድ ቤቱ መጥሪያ ደርሶት መልስ ባለመቅረቡ መከራከር እንዳልፈለገ ተቆጥሮ መብቱ ታልፏል፡፡1 ተጠሪ ባቀረበዉ መልስ ላይ አመልካች ባቀረቡት የመልስ መልስ ጊዜዉ የሚታሰበዉ መንገዱ ተሰርቶ ከተጠናቀቀበት ሳይሆን ጉዳት ከደረሰበት ጊዜ ጀምሮ እስከ 2 ዓመት ክስ መቅረብ እንዳለበት የፌዴራል ጠቅላይ /ቤት ሰበር በመ/ 34544 እና 16062 ትርጉም ሰጥተውበታል በማለት የሰበር አቤቱታቸውን አጠናክረው ተከራክረዋል፡፡

የጉዳዩ አመጣጥ እና የግራቀኙ ክርክር ባጭሩ ከላይ የተገለጸ ሲሆን እኛም አቤቱታዉ ለሰበር ችሎት እንዲቀርብ የተደረገበትን ጭብጥ መሰረት በማድረግ አግባብነት ከላዉ ህግ ጋር በማገናዘብ መርምረናል፡፡እንደመረመርነዉ የዚህ ችሎት ምላሽ የሚያስፈልገዉ ጭብጥ የአመልካቹ ክስ በሁለት ዓመት ይርጋ ጊዜ ታግዷል ተብሎ የተሰጠዉ ብይን ላይ የተፈጸመ የህግ ስህተት መኖር አለመኖሩን በሚመለከት ነዉ፡፡ይርጋ ደንብ መብት ለማስከበር የሚቀርብ ክስ /limitation of action/ ቀሪ የማድረግ ዉጤት ያለዉ የህግ ጽንሰ ሃሳብ ነዉ፡፡የይርጋ ደንብ /period of limitation/ ዓይነተኛ ዓላማ አንድ ግዴታ እንዲፈጸምለት የሚጠይቅ ባለመብት በህጉ በተገለጸ የጊዜ ገደብ ዉስጥ በመብቱ ባለመስራቱ የመብት ጥያቄዉ በጊዜ ማለፍ ምክንያት ቀሪ የሚሆንበት በሌላ በኩል ግዴታ ያለበትን ወገን ግዴታዉን እንዲፈጽም ከሚቀርብበት ክስ ነጻ የማድረግ ዉጤት ያለዉ ነዉ፡፡የይርጋ ጊዜ እርዝማኔ እንደጉዳዩ ዓይነትና ባሕርይ የሚለያይ ስለመሆኑ የይርጋ ደንብ የሚመለከቱ ድንጋጌዎች ያስገነዝባሉ፡፡ስለዚህም ተፈጻሚነት ያለዉ ይርጋ ጊዜ ለመለየት የሚቻለዉ የተጠየቀዉ ዳኝነት ዓይነት ወይም የክስ ምክንያት እና በመብቱ መስራት የሚቻልበትን ጊዜ በሚመለከት ለጉዳዩ ተፈጻሚነት ያለዉን ህግ መሰረት በማድረግ መሆን አለበት፡፡

በተያዘዉ ጉዳይ የአመልካቹ የዳኝነት ጥያቄ ለመንገድ ግንባታ የተሰራ ዲሽ ባስከተለዉ ጎርፍ የእርሻ ማሳ (መሬት) ላይ ለደረሰ ጉዳት ተጠሪዎች ሃላፊ እንዲባሉ እና ካሳ እንዲከፍሉ የሚል ሲሆን ተጠሪዎች በበኩላቸዉ የመንገዱ ስራ ከተጠናቀቀ ሁለት ዓመት ካለፈ በኋላ የቀረበ ክስ ነዉ በማለት ክሱ በይርጋ ቀሪ ነዉ የሚል ክርክር ማቅረባቸዉን መዝገቡ ያሣያል፡፡የስር ፍርድ ቤት ክሱ በሁለት በይርጋ ቀሪ ነዉ ሲል የወሰነዉ የፍ//ህግ አንቀጽ 2143(1) ምርኩዝ በማድረግ ነዉ፡፡ክርክሩ እንደሚያሣየን ክሱ ከዉል ዉጭ የፍ// ሃላፊነት መሰረት ያደረገ እንደመሆኑ ለጉዳዩ አግባብነት ያለዉ ይርጋ ጊዜ በፍ//ህጉ አንቀጽ 2143(1) ድንጋጌ ስር የተመለከተዉ ሁለት አመት የጊዜ ገደብ መሆኑ አከራካሪ አይደለም፡፡ይሁንና ሁለት ዓመት ይርጋ ጊዜ መቆጠር የሚመጀረዉ ከመቼ ጀምሮ ነዉ የሚለዉ በአግባቡ መመርመር አለበት፡፡ምክንያቱም አመልካቹ ጉዳት ደርሰብኝ የሚለዉ 2011. ሐምሌ እና ነሀሴ ወር በነበረዉ ጎርፍ ነዉ በማለት ሲሆን ተጠሪዎች በበኩላቸዉ መንገዱም ሆነ ዲሽ ተሰርቶ የተጠነቀቀዉ 2008. መሆኑን ጠቅሰዉ ጉዳት ካለም 2008. ጀምሮ ነዉ የሚል መከራከሪያ አቅርበዋል፡፡ከክርክሩ መገንዘብ እንደሚቻለዉ በመንገዱም ሆነ በዲሽ ስራ ምክንያት ከአመልካች ይዞታ ላይ የተወሰደ ወይም የተቀሰነ መሬት ስለመኖሩ የቀረበ ክርክር የለም፡፡ይልቁንም ለክሱ ምክንያት የሆነዉ መንገዱ ሲሰራ ለጎርፍ ማስወገጃ ተብሎ ከተሰራ ዲሽ ላይ የሚፈስ ዉሃ (ጎርፍ) የአመልካቹ እርሻ ማሳ (መሬት) ላይ ገብቶ ጉዳት አድርሷል የሚል መሆኑን የክሱ ፍሬነገር ያሳያል፡፡የፍ//ህጉ አንቀጽ 2143(1) ድንጋጌ ይዘት በግልጽ እንደሚያሳዉ ተበዳዩ ክስ ማቅረብ የሚችለዉ ካሳ የሚጠይቅበነት  ጉዳት ከደረሰበት ጊዜ ጀምሮ እስክ ሁለት ዓመት ድረስ ነዉ፡፡ይህ ከሆነ ደግሞ በዚህ ምክንያት ክስ ለማቅረብ የሚችለዉ ጉዳት ከደረሰበት ጊዜ ጀምሮ እንጂ መንገዱ ወይም ዲሹ ከተሰራበት ጊዜ ጀምሮ ነዉ የሚያሠኝ ምክንያት የለም፡፡አመልካቹ ጉዳት ደረሰብኝ የሚለዉ ሐምሌ እና ነሐሴ ወር 2011 ነዉ የሚል ሲሆን ተጠሪዎች ይህንን ፍሬነገር በመካድ ተከራክረዋል፡፡በመሆኑም ክሱ በይርጋ ቀሪ ነዉ ወይስ አይደለም የሚለዉን ለመወሰን ፍርድ ቤቱ በጭብጥነት ይዞ መመርመር የሚገባዉ ለክሱ ምክንያት የሆነዉ ጉዳት የደረሰዉ መቼ እና በምን ምክንያት እንዲሁም ሁኔታ ነዉ የሚለዉ እና ተያያዥ የፍሬነገር ክርክር ላይ መሆን አለበት፡፡ይህንን የፍሬነገር ክርክር በግራቀኙ በኩል በተቆጠረ ማስረጃ ነጥሮ የሚወሰን መሆኑ ልብ ይለዋል፡፡

ስለሆነም አመልካቹ በክሱ የጠቀሰዉን ፍሬነገር የማስረዳት ሽክም እንዲሁም በተጠሪዎች በኩል በፍሬነገር ረገድ የሚቀርብ ክርክር እና ዉጤቱ በክርክሩ ሂደት የሚወሰን መሆኑ  እንደተጠበቀ ሆኖ አመልካቹ ጉዳት ደርሰብኝ የሚለዉ ሀምሌ እና ነሀሴ ወር 2011. ሆኖ ክሱን ያቀረበዉ 2013. እንደመሆኑ ይህም ከፍ//ህግ ቁጥር 2143(1) ድንጋጌ ጋር ተገናዝቦ ሲታይ ክስ የማቅረብ መብቱ ሁለት ዓመት ይርጋ ጊዜ አልፎበታል የሚል ድምዳሜ ላይ ለመድረስ የሚያስችል አይደለም፡፡ስለሆነም የስር ፍርድ ቤቶች ሁለት ዓመት ይርጋ ጊዜ መንገዱም ሆነ ዲሹ ተሰርቶ ከተጠናቀቀበት (2008.) ጀምሮ በማስላት ክሱ ከሁለት ዓመት በኋላ የቀረበ ነዉ በሚል በይርጋ ቀሪ ነዉ የሚል ድምዳሜ ላይ መድረሳቸዉ አመልካቹ በክሱ የጠቀሰዉን የክስ ምክንያትና ፍሬነገሩን ያላገናዘበ እንዲሁም ለይርጋ ጊዜ አቆጣጠርም መነሻ ጉዳት የደረሰበትን ጊዜ ለመለየት በማስረጃ ሳያጣሩ መወሰናቸዉ የክርክር አመራር ስህተት የተፈጸመበት መሆኑን ያሣያል፡፡ፍርድ ቤቱ ተገቢዉ ጭብጥ ሳይያዝ እና በማስረጃ ሳያጣራ የሚሰጠዉ ዉሳኔ የክርክር አመራር ጉድለት ስለመሆኑ እና መሰረታዊ የህግ ስህተት ሆኖ በሰበር ችሎት ሊታረም የሚገባ መሆኑን በሰበር ችሎቱ በተለያዩ መዝገቦች ገዥ ዉሳኔ ሰጥቶበታል፡፡ሰበር  // 47252 37105 29861 47551 49660 እና ሌሎች ተመሳሳይ ጉዳዮች ላይ የሰጠዉ ዉሳኔ ይህንኑ ይመለከታል፡፡ሰበር ችሎቱ የሰጠዉ ገዥ ዉሳኔ በተመሳሳይ ጉዳዮች ላይ ተፈጻሚነት እንዳለዉ በአዋጅ ቁጥር 1234/2011 አንቀጽ 26(3) ላይ ተደንግጓል፡፡

ከዚህ አኳያ ሲታይ በዚህም ጉዳይ የስር ፍርድ ቤት ተገቢዉን ጭብጥ ይዞ ሳያጣራ ክሱ በይርጋ ታግዷል በማለት የደረሰበት ድምዳሜ የክርክር አመራር ጉድለት የተፈጸመበት ነዉ፡፡ይግባኝ ሰሚ ችሎትም ይህንኑ ሳያርም ማለፉ ስህተት ነዉ፡፡ስለሆነም ክርክሩ የተመራበት አግባብ የክሱን ፍሬነገር መሰረት አድርጎ ተገቢዉ ጭብጥ ተይዞ ሳይጣራ በመሆኑ እና ሰበር ችሎቱ የሰጠዉ አስገዳጅ የህግ ትርጉም የሚቃረን ስለሆነ በፌዴራል ፍርድ ቤቶች አዋጅ ቁጥር 1234/2011 አንቀጽ 2(4/) እና 10(1/) መሰረት መሰረታዊ የህግ ስህተት የተፈጸመበት ሆኖ አግኝተናል፡፡በዚሁ አግባብ ተከታዩን ዉሳኔ ሰጥተናል፡፡

ዉሳኔ

1/የኦሮሚያ ጠቅላይ ፍርድ ቤት በመ/ 348437 ላይ በቀን 06/11/2013 . የሰጠውን ብይን በማጽነት የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ይግባኝ ሰሚ ችሎት በመ//220518 ላይ በቀን 13/07/2014. የሰጠዉ ትእዛዝ በፍ///// 348(1) መሠረት ተሸሯል፡፡

2/የኦሮሚያ ክልል ጠቅላይ /ቤት የዘጋዉን መዝገብ በማንቀሳቀስ ክሱ በይርጋ የሚታገድ ነዉ ወይስ አይደለም የሚለዉን?ለመለየት ለክሱ ምክንያት የሆነዉ ጉዳት የደረሰዉ መቼ እና በምን ምክንያት እንዲሁም ሁኔታ ነዉ የሚለዉን በግራቀኙ ማስረጃ አጣርቶ ክሱ በይርጋ የሚታገድ አይደለም ከተባለ ደግሞ በፍሬነገሩ ገብቶ ተገቢዉን ዉሳኔ እንዲሰጥበት በፍ////ህግ ቁጥር 343(1) መሰረት መልሰንለታል፡፡ይጻፍ 

4/የሰበር ክርክሩ ያስከተለዉን ወጪና ኪሳራ ግራ ቀኙ የየራሳቸዉን ይቻሉ፡፡ 

         መዝገቡ ዉሳኔ ያገኘ ስለሆነ ተዘግቷል፡፡ ይመለስ፡፡

 

 

የማይነበብ የአምስት ዳኞች ፊርማ አለበት፡፡

/